ትምህርቱ፤ ትግሉና ከፍተኛዉ መስዋዕትነት ለዲሞክራሲና ለእድገት ነበር

ከበቀለ ገሠሠ (ዶ/r) – መንደርደሪያ – ከተገንጣይ ቡድኖች በስተቀር በ50ዎቹና 60ዎቹ የተጀመሩት እልህ አስጨራሽ ትግሎች ታላቅ አገራዊ ራዕይ ነበራቸዉ። እነዚህም በዉድ አገራችን የዲሞክራሲን ሥርዓት ለመገንባት፤ እኩልነት ለማስፈንና ዘለቄታ ያለዉን ዕድገት ለማምጣት ነበር። ይህ ግብ ባለመሳካቱ ምክንያት አንዳንድ ሰዎች የየግላቸዉን ፍላጎት ለማሳካት የተዛባ ትንታኔ ለማቅረብ ይሞክራሉ። በዚህም ላይ ወደኋላ እየተመለከቱ እንዲህ ቢሆን፤ እንዲያ ቢሆን ይሻል ነበር ብሎ መፍረድ ይቀላል። ዋናዉ ነገር ግን በወቅቱ መደረግ የሚገባዉን መልካም ነገር መሞከሩ ላይ ነዉ። በእርግጠኝነት ለመናገር የሚቻለዉ ግን በህዝብ ጎን የተሰለፉት ወጣቶችና መሪዎች ወቅቱ የፈቀደዉ ከፍተኛ ንቃተ ኅሊና የነበራቸዉ፤ ለህዝብ እኩልነትና ለአገር ዕድገት ከፍተኛ ራዕይ የነበራቸዉና ለዚህም የተቀደሰ ዓላማ ከፍተኛ የሕይወት መስዋዕትነት ለመክፈል ቆርጠዉ የተነሱና የከፈሉ ብሩህ ዜጎች መሆናቸዉን ነዉ። የጎሳ አባዜ ያልተጠናወታቸዉ፤ ሃይማኖት ያልከፋፈላቸዉና ዕድሜ ያልገደባቸዉ ንፁሓን ዜጎች ነበሩ። ምንም እንኳን በወቅቱ ብዙ ተሞክሮዎች ባይኖሩም የተደረጉት ሙከራዎችና የተከፈለዉ መስዋዕትነት ለአንድነት፤ ለእኩልነትና ለአገር ግንባታ ነበር። ‘ድር ቢያብር አንበሳ ያስር’ ይላል ያገራችን ሰዉ። ቀላል አባባል አይደለም። በትብብር ነበር አገራችን ነፃነቷን ጠብቃ የቆየችዉ። እንደዚያ ባይሆን ኖሮ በተለያዩ ወቅቶች አንጃብበዉ የመጡብን የተለያዩ የዉጪ ጠላቶች በቀላሉ ድምጥማጣችንና ታሪካችንን ለማጥፋት በቻሉ ነበር። ግን አልቻሉም፤ ለፈጣሪያችን ታላቅ ምስጋና ይግባዉና።በግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት ብዙ ግንባታዎች ታይተዋል። ነገር ግን የወቅቱ ዋና ጥያቄዎች የሆኑት የመሬት ሥሪትና የዲሞክራሲ ጉዳዮች አልተመለሱም።ሥርዓቱ ከማርጀቱ የተነሳ እነዚህን ጥያቄዎች በአግባቡ ለመመለስ አልቻለም። ቀጥሎ የመጣዉ የወታደር አምባገነን ሥርዓት ሆነ። እርሱ ደግሞ ቀኑን ጠብቆ ሲሄድ ህዝቡን በጎሳና ኃይማኖት ከፋፍሎ የሚገዛ የኢሕአዴግ አምባገነን ቡድን ተቀመጠ። ከ27 ዓመታት ትግል በኋላ እርሱም ተዳከመ። ለዉጥ ሊደረግ ነዉ ሲባል ብዙ ሰዉ ትልቅ ተስፋ አደረገ። ሆኖም ግን ከባድ ችግሮች ይታያሉ። ዛሬ በግፍ የሚፈሰዉ የንፁሐን ደም፤ የሚታገቱት ተማሪዎች (በተለይ ሴቶች)፤ የሚፈናቀለዉ ዜጋና የሚቃጠሉት አቢያተ ክርስቲያናትና መስጊዶች እጅግ በጣም ያሳዝኑኛል። በመሻሻል ምትክ ሁኔታዎች እንደዚህ እየተባባሱ መሄዳቸዉን ስመለከት ሰዉ ሆኜ መፈጠሬን ያስጠላኛል፤ እጅግ በጣም ያሳፍረኛል። ቶሎ መቆም አለባቸዉ። ካለበለዚያ ሰላም አይኖርም። ሰላም ሳይኖር ምርጫም ሆነ ዕድገት በቅጡ ሊሳካ አይችልም። ከነሩዋንዳ ለምን አንማርም? በ1994 (በፈረንጆች አቆጣጠር) ወደሚሊዮን ሕዝብ ነዉ በእርስ በርስ የጎሳ ግጭት በጥቂት ወራት ዉስጥ ሕይወቱን ያጣዉ። ዛሬ ግን ከዚያ ከባድ ዉድቀት በመማር የጎሳ ግጭት በአዋጅና በሕግ ተከለከለ፤ በመሆኑም አገሪቷ ከፍተኛ እድገት በማሳየት ላይ ትገኛለች። ደቡብ አፍሪቃ፤ ኬኒያ፤ ጋና፤ ወዘተ መልካም የዲሞክራሲ ሥርዓትና ዕድገት በማሳየት ላይ ይገኛሉ። ምነዉሳ እኛ ከጊዜ ወደጊዚ የቁልቁለት ጎዳና እየተከተልን ሴይጣን ስንመግብ የምንኖረዉ? ከወጣቶች ደም፤ ከእናቶች እንባና ከሺማግሌዎች ሃዘን የሚመጣ መቅሰፍት አትርሱ። እንንቃ፤ ፈሪሃ እግዚአብሔር ይኑረን፤ እንደሰለጠኑ ሰዎች እናስብ፤ ሕይወት አጭር ናት፤ በ21ኛዉ ክፍለ ዘመን ዉስጥ መሆናችንን አንዘንጋ።

፩ኛ/ የጠንካራ ሽግግር መንግሥት አስፈላጊነት፤

በግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት ማብቂያ ላይ የተጠየቀዉ ትክክለኛ ጥያቄ ወደ ዲሞክራሲ ሊመራ የሚችል የጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግሥት ምስረታ አስፈላጊነት ነበር። ወታደሩ ግን ይሄን ጥያቄ ከለከለ። ከዚያ በኋላ የተከተለዉን አሰቃቂ እልቂት ታሪክ ቁልጭ አድርጎ አስቀምጦታል። ለ27 ዓመታት ገደማ በወያኔዎቹ ሲመራ የነበረዉ የኢሕአደግ መንግሥት በአገሪቷ ከላይ እስከታች በተቀጣጠለዉ ተቃዉሞ ሲዳከም ለዉጥ ሊመጣ ነዉ ተባለ። ኢሕአደግ ከልቡ ከጥፋቶቹ በመማር ጠንካራና ሁሉ-አቀፍ የሆነ የሽግግር መንግሥት ተቋቁሞና እርቀ ሰላም ወርዶ ወደ ትክክለኛዉ ዲሞክራሲ እናመራለን ብለን ተስፋ አድርገን ነበረ። ይሄ ግን አለመሳካቱ እጅግ በጣም ያሳዝናል። ቢሳካ ኖሮ ዛሬ የምናያቸዉ እጅግ አሰቃቂ ክስተቶች ባልተፈጠሩ ነበር። ከእጃችን የወጣ ወርቃማ ዕድል አድርጌ ነዉ የምቆጥረዉ። አሁንም በእጅጉ ሊታሰብበት የሚገባ ጉዳይ ነዉ ብዬ አምናለሁ።

፪ኛ/ ሕገ መንግሥት የማሻሻል አስፈላጊነት

ጎሳና ኃይማኖትን በተመለከተ በአገራችን ዉስጥ ከባድ አለመግባባትና ግጭቶች እየተፈጠሩ ናቸዉ። በቅርቡ ሕዝቡን ከፋፍለዉ ለመግዛት የረጩት መርዝ ነዉ እንጂ በቀደሙት ዘመናት እንደዚህ ዓይነት ግጭቶችና እልቂቶች አላየንም፤ አልሰማንም። አማራዉ፤ ትግሬዉ፤ ኦሮሞዉ፤ ወዘተ የርስ በርስ ጠላትነት አልነበራቸዉም። የጋራ ችግራቸዉ የዲሞክራሲ አስተዳደር እጦት ነዉ (በፊት በባላባታዊ፤ ቀጥሎ በወታደራዊ አምባገነን፤ በኋላ ደግሞ ከፋፍሎ በሚገዛዉ የጎሳ አምባገነንነት ምክንያት)። እንደዚሁም ኦርቶዶክስ ሃይማኖት የማንኛዉም እምነት ጠላት ሆኖ እንደማያዉቅ የአገራችን ታሪክ ቁልጭ አድርጎ አስቀምጦታል፤ እኛም ሕያዉ ምስክሮች ነን።

ሕገ መንግሥት በግልፅ ማስቀመጥና ማረጋገጥ ከሚገባቸዉ ዐበይት ነገሮች መካከል የሚከተሉትን የእያንዳንዱን ዜጋ መሰረታዊ ሰብዓዊ መብቶች ይጠይቃል፤

• የጎሳን ግጭት ማስወገድ፤
• የእያንዳንዱን ሃይማኖት ነፃነት ማክበርና ማስከበር ይሆናሉ።

በዚህም ሂደት ዉስጥ ሁሉም ዜጎች እኩል መሳተፍ ይገባቸዋል።

፫ኛ/ አገራዊ ምርጫን በተመለከተ

ከዚያ ሁሉ ረዥምና እልህ አስጨራሽ ትግልና መስዋዕትነትም በኋላ እስከዛሬ ድረስ በአገራችን ዉስጥ ነፃ ምርጫ ተካሂዶ አያዉቅም። በእነኬኒያ፤ ደቡብ አፍሪቃና ጋና ያሉትን የዲሞክራሲ ግንባታዎች ስመለከት የኛ ኋላ ቀርነት እጅግ በጣም ያሳዝነኛል፤ ያስገርመኛል፤ ያሳፍረኛልም።በ97ቱ ምርጫ ትንሽ ለቀቅ ያደረጉ አስመስለዉ ነበር። ድምፅ ቆጠራዉን ግን አጭበርብሮ አምባገነኑ ኢሕአዴግ ራሱ መልሶ ጠቀለለዉ። የአሁኑስ ምርጫ ምን ሊሆን ነዉ? ምርጫ እንዲሳካ መስተካከል የሚገቧቸዉ አንዳንድ ቅድመ ሁኔታዎች አሉ። ተቃዋሚ ድርጅቶች በሁሉም የአገሪቷ ክፍሎች በነፃ መንቀሳቀስና ዓላማቸዉን ለሕዝቡ ለመግለፅ የሚችሉበት ዕድል መኖር አለበት። እስከዞን፤ ወረዳና ቀበሌ ድረስ ነፃ የሆኑ የምርጫ አስፈፃሚ ተቋማት መኖር ይገባቸዋል። ዛሬ እኮ ተማሪዎች እንኳን እየታገቱ መድረሻቸዉ የማይታወቅበት እጅግ አሳዛኝና አስደንጋጭ ሁኔታ ዉስጥ ነዉ ያለነዉ። ታዲያ በዚህ ሁኔታ ነፃ ምርጫ ይካሄዳል ብሎ መጠበቅ ይቻላል ወይ? እንደእኔ አስተያየት ከምርጫዉ በፊት እላይ ባጭሩ የተቀመጡት ቅድመ ሁኔታዎች ቢስተካከሉ ይሻላል ብዬ አምናለሁ።

፬ኛ/ ዘለቄታ ያለዉን ዕድገት ለማምጣት፤

ዘለቄታ የሚኖረዉን አገራዊ ዕድገት ለማምጣት ብዙ ቅድመ ሁኔታዎች መሟላት ይጠበቅባቸዋል። ከእነዚህም መካከል፤

• አርሶ ለማምረት ሰላምና እርጋታ ያስፈልጋሉ፤ ሕዝቡ እርስ በርሱ እየተጋጨና እየተፈናቀለ በሰላም አርሶ ማምረት እንደማይችል ግልፅ ነዉ። በዚህም ላይ ደኖቻችን ክፉኛ ተጨፍጭፈዋል፤ አፈሮች ተሸርሽረዋል፤ የአየር ንብረት እየተቃወሰ ይገኛል። የገጠር ገበሬዎች አርሰዉ ምርታቸዉን ለማሳደግ እንዲችሉ ብዙ ሙያዊና መንግሥታዊ ዕርዳታዎች ያስፈልጓቸዋል። ባገር ዉስጥ ሰላምና እርጋታ ሳይኖሩ እነዚህን ድጋፎች ማዳረስ አይቻልም፤ አገር ሊገነቡ የሚችሉ የተማሩ ኃይሎች መሰብሰብና ማሰማራት ከባድ ነዉ።

• ነግደዉም ለመብላት ዜጎች በአገራቸዉ ውስጥ በነፃ የመንቀሳቀስ ዕድል ያስፈልጋቸዋል፤ ዛሬ እነዚህ ዕድሎች በሰፊዉ አይታዩም።

• ተምረዉ ለመሥራት ወጣቶች ሰላምና እርጋታ ያስፈልጋቸዋል። በተፃራሪዉ ግን ብዙ የዩኒቬርስቲ ተማሪዎች እየተገደሉና እየታገቱ ይገኛሉ። ወጣቶች በገዛ አገራቸዉ ተምረዉና ተመርቀዉ መሥራት ካልቻሉ ዕጣ ፈንታቸዉ ያዉ የተለመደዉ ስደትና እንግልት ነዉ። ይሄ ችግር ቶሎ መቀረፍ አለበት። ይሄ ካልሆነ አገርስ እንዴት ሊታድግ ትችላለች?

• የግድብ ሥራዎች ለማሳካት ሰላምና ጠንካራ አንድነት ይጠይቃል። የዉጪ ጠላቶች ራሳችንን እንድንችል አይፈልጉም። ማንንም ሳንጎዳ ወንዞቻችንን እንኳን ገድበንና ተጠቅመን ከችጋርና ከጭለማ እንድንወጣ አይፈልጉም። የአገራችን ነፃነት ተከብሮ እስከዛሬ ድረስ የቆየዉ በአንድነታችንና በእግዚአብሔር ፈቃድ ነዉ። አሁንም ያንን አንድነት መልሰን መገንባት ይኖርብናል። ካለዚያ የታወቁት የዉጪ ታሪካዊ ጠላቶቻችን እየከፋፈሉን ቡችሎች አድርገዉ ያስቀሩናል።

፭ኛ/ መደምደሚያ

በቀደሙት ጽሑፎቼ ደጋግሜ ለማስተላለፍ እንደሞከርኩት፤ እንኳንስ አገራዊ ሁከት ተጨምሮበት ይቅርና በሰላምም እንኳን ካለንበት የኋላ ቀርነት ለመላቀቅ ቀላል ሥራ አይሆንም። የዉጪ መንግሥታት የየራሳቸዉን ጥቅም ነዉ የሚያስቀድሙት። እኛ ተባብረን መበርታት ይኖርብናል። ለመሬት ላራሹና ለዲሞክራሲ ግንባታ ያ ትዉልድ የከፈለዉን ከፍተኛ መስዋእትነት ታሪክ ሲያስታዉሰዉ ይኖራል። ከዚያ ሁሉ ጥረትና መስዋዕትነት በኋላ ከአሁኑ የተሻለ ሁኔታ ነበር የጠበቅነዉ። አለመሆኑ እጅግ በጣም ያሳዝናል፤ያሳፍራል።

ዛሬ በዉዲቷ አገራችን ላይ ጥቁር ደመና ተጋርጦባታል። ከስህተቶችና ጥፋቶች መማር ይገባናል። አያቶቻችንና ቅድመ አያቶቻችን ደማቸዉን አፍስሰዉ አጥንታቸዉን ከስክሰዉ በነፃነት ያቆዩዋት ቅድስት አገር በሁላችንም ትብብር ህልዉናዋ ተረጋግጦ አብባ ለዘለዓለም እንድትኖር ለማድረግ ኃላፊነቱ የሁላችንም መሆኑን መገንዘብ ይኖርብናል። ዉድ አገራችን ለልጆቻችንና ለሚቀጥሉትም ትዉልዶች መትረፍ ይኖርባታል። ቁጭ ብለን ሁኔታዎች እስከሚባባሱ ድረስ መጠበቅ አይኖርብንም። በዚያች ምድር አንድም ዜጋ በጎሳ ምክንያት መገደል፤ መታገት ወይም መፈናቀል የለበትም። ማንኛዉም ቤተ እምነት መነካት የለበትም። ተያይዞ መጥፋት ለምን ይመረጣል? ለማያዉቁት ማስተማር ነዉ። እያወቁ ሽብር የሚፈጥሩትን ለፍርድ ማቅረብ ነዉ። ሩዋንዳን ከመሳሰሉ የዓለም ታሪኮች መማር ይኖርብናል።

ቸሩ አምላካችን ቅን ልቦና ይስጠን፤ ይታረቀን፤ ወገኖቻችንና ውድ አገራችንን ይጠብቅልን፤ አሜን