አስሩ የዘር ፍጅት ደረጃዎች እና ኢትዮጵያ

ከዓለሙ ተበጀ –

በዓለማችን የሚካሄዱ የዘር ፍጅቶችን የሚከታተለው Gnocide Watch ፕሬዚዴንት ግሪጎሪ ኤ ስታንተን የዘር ፍጅት ሊከሰት መሆኑን የሚያመላክቱ 10 ክስተቶችን/ምልክቶችን ዘርዝረዋል። እነኝህም ሲከሰቱ ልብ ማለት ጉዳዩ በቀጥታ ለሚመለከተው ህብረሰሰብም ሆነ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በጊዜና በየደረጃው እርምት በመውሰድ ጥፋቱን ማስቀረት እንዲቻል ካልሆነም ቢያንስ ለመቀነስ እንደሚረዳ ባለሙያዎች ይመክራሉ። እኛ ኢትዮጵያዊያንም ካለፉት ብዙ ዓመታት ጀምሮ ሀገራችን እየተጓዘች ያለችበትን እውነታ በማጤን ዓይናችን እያየ ሙሉ ለሙሉ ወደ እርስ በርስ መተላለቅ ለመግባት ከጀመርነው መንገድ ብንገታ በማለት እና በመመኘት ምልክቶቹን እንደሚከተለው አቀርባለሁ::

  1. ምደባ – በህዝብ መካከል ያሉ ልዩነቶች አይከበሩም። የተሳሳቱ አመለካከቶችን ለጥፎ ስም በመስጠት ወይም የተለዩ ናቸው የሚባሉ ወገኖችን በማግለል “እኛ” እና “እነሱ” በማለት ህዝቡን ይከፋፍሉታል። በእኛም ሀገር እውነታ በቋንቋ መስመር ያለውን የክልል ሽንሸና ልብ ይሏል።
  2. ምልክቶች – እነኝህ የጥላቻው ማሳያ ምልክቶች ናቸው። በናዚ ጊዜ አይሁዳዊያን የተለዩ መሆናቸውን ለማሳየት ቢጫ ኮከብ ያለበት ይለብሱ ዘንድ ይገደዱ ነበር። በእኛም ሀገር እውነታ አኖሌ የጡት ሀውልትን ልብ ይሏል። በየመታወቂያው ላይ ያለውንም የብሄር ስም እንደዚሁ ልብ እንበል። የየክልሎቹ አርማዎችም ኢትዮጵያን ቀስ በቀስ ገድሎ አራሳቸውን የቻሉ አዳዲስ ሀገራት በመፍጠር ለመውለድ አላማ ሲውሉ ይስተዋላል:: ችግሩ ግን በፍጹም መውለድ የማትችል ሴት ግን በምጥ ለመሞት መርጣ እንደምታረግዝ ሴት መሆናችን ነው:: እርስ በርስ ለመተላለቅ መሮጣችን::
  3. መድለዎ (ልዩነት ማድረግ) – የበላይነት ያለው ቡድን በእጁ ያለውን ህግ የማውጣትና ስራ ላይ የማዋል እንዲሁም የፖለቲካ ኃይል በመጠቀም የተቀረውን ማኅበረተሰብ አባላት የሲቪል መብቶች ሌላው ቀርቶ የዜግነት መብት ይገፋል። እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር በ1935 የጀርመን ህግ በሀገሪቱ ያሉትን አይሁዳዊያን የጀርመን ዜግነት ገፏቸው፡ ብዙ ስራዎችን እንዳይሰሩ ወይም አይሁዳዊ ካልሆኑ ጀርመናዊያን ጋር ጋብቻ እንዳይመሠርቱ ከልክሎ ነበር። በሀገራችንም ስራ ላይ ያለው የየክልሎቹ ህገመንግስት እያንዳንዱን ክልል ለተወሰነ(ኑ) ቋንቋ ተናጋሪ በመስጠት የተወሰኑ ኗሪዎችን ባለሙሉ መብት፣ የተቀሩትን በየክልሉ ኗሪዎች ያነሰ መብት ያላቸው፣ በባለሙሉ መብቶቹ ኗሪዎች በጎ ፈቃድ የሚኖሩ፣ ያነሰ የሥራ፣ የትምህርት፣ ወዘተ እድል ያላቸው እንዲሆኑ ያደረገ የመሆኑን እውነታ ልብ ይሏል። አንድ ኗሪ ያ ክልል ነህ ተብሎ ለተመደበለት ብሄሩ በህግ ተደንግጎ የተሰጠ ካልሆነ በስተቀር የመመረጥ መብትም የለው። በሀገራችን በሕይወት ባሉት ሰዎች ላይ ብቻ አይደለም ከሞቱም በሁዋላ የሚቀበሩበት የሚዘከሩበት ደረጃ ምን ያህል አድልዎ እንደሚደረግበት በቅርቡ ብዙ እየታዘብን ነው:: በአጠቃላይ ሀገሪቱ የምትገዛበት ሕግና አሰራር በእኩልነት ስም እኩል አለመሆንን ለየክልሎቹ ያከፋፈለ የመድልዎ ቀፎ ነው::
  4. ማዋረድ – ከ “እኛ” የተለዩ ናቸው የሚባሉትና በ“እነሱ” በረት ውስጥ የሚመደቡት ሰዎች ሰብአዊ መብት ወይም ከበሬታ ይነፈጋቸዋል፣ ይዋረዳሉ። ሩዋንዳ ውስጥ የዘር ፍጅት ሲካሄድ ቱትሲዎች “በረሮዎች” እየተባሉ በውርደት ይጠሩ ነበር። አሁንም በእኛ ሀገር ያገዛዙን ባለሥልጣናት ጨምሮ የዘር ፖለቲካ አራማጆች በየንግግራቸው፣ አለ የሚሉትን ያለፈ ሂሳብ ለማወራረድ ከአማርኛ ተናጋሪው እና ከኦርቶዶክስ ክርስትና ተከታዩ ሕዝብ ጋር በተያያዘ የሚጠቀሙባቸውን ቅጽሎች ልብ ይሏል። ዛሬ በደረሰባቸው የሰው ሕይወት ጭፍጨፋና የንብረት ውድመት የብዙ ሕዝብ መገናኛዎችን ቀልብ ከሳቡት በዝዋይ መስመር ላይ ከሚገኙት ከተሞች በአንዱ ኑዋሪ የነበረ አንድ የማውቀው ሰው ካመታት በፊት ለቆ ወደትውልድ (እሱ ሳይሆን አባቱ ወደተወለዱበት) ቦታው ሲሄድ ምክንያቱን ጠይቄው ያለኝ ትዝ ይለኛል:: የኦህዴድ ካደሬዎች በአማርኛ ሲናገር ሰምተውት “በዚህ በሚገማ አፍህ አትናገር!” ሲሉት ነበር ውርደቱ ካቅሙ በላይ ሆኖበት ከተወለደበት ካደገበት ከከበደበት ከተማ የለቀቀው::
  5. ድርጅት _ የዘር ፍጅቶች ታቅደው ነው የሚከናወኑት። ብዙ ጊዜም የጥላቻ አገዛዞቹ በሌሎች ላይ የዘር ፍጅት የሚያካሂደውን ኃይል ያሰለጥናሉ። ልዩ የመደበኛ ወታደራዊ ወይም የሚሊሻ ኃይል ያሰለጥናሉ፣ ያስታጥቃሉ። በእኛም ሀገር በመንግሥት መዋቅር እና ከዚያም ውጭ ያለውን የየክልሎች የመከላከያ ኃይል አቅም ግንባታ ልብ ይሏል። ኦሮሚያ በተባለው ክልል ውስጥ በ30 ዙር የሰለጠነው ልዩ ሃይል፡ ከዚህም ጋር በግልጽም በስውርም የተቀናጀው ቄሮ እና እስካሁን ያካሄዱት ጭፍጨፋ ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ይመስለኛል።
  6. ዋልታ ረገጥነት ይስፋፋል – የጥላቻ ቡድኖቹ የቅስቀሳና ፕሮፓጋንዳ ማካሄድ ይጀምራሉ። ናዚዎች ስለ አይሁዳዊያን ጥላቻ ለማስፋፋትና ለማቀጣጠል “አጥቂው” (Der Sturmer) የተባለውን ጋዜጣ አቋቁመው ነበር። በእኛም ሀገር ኦኤምኤን ጥሩ ማሳያ ነው። አንዳንድ ሰዎች ትዳርና ገበያ ሌላው ቀርቶ መነጋገር እንኩዋ በአንድ ቁዋንቁዋ ተናጋሪዎች መካከል ብቻ እንዲሆን ሲሰብኩ ስንሰማ ጥላቻ የወለደው ዋልታ ረገጥነት ምንያህል የከፋ እንደሆነ ምን ያህል ከሰው ልጅ ተፈጥሯዊ ማህበራዊ እንሰሳነት ጋር የሚጣረዝ እንደሆነ ሳያሳዬን አይቀርም:: ዓለማችን ካሳለፈቻቸው የዘር ፍጅት እልቂቶች የእኛውን “አውጣኝ” የሚያስብለው ያለንበት የሶሻል ሚድያ ዘመን መሆኑና አንድ ሰው የሚጭራት እሳት ሀገር አዳርሳ ብዙ እልቂት ልታስከትል መቻሏ ነው። ለዚህም የጃዋር ተከብቢያለሁ የፌስ ቡክ መልዕክትና ከ86 በላይ ወገኖች ላይ የተካሄደው ዘር/ሃይማኖት ተኮር ጭፍጨፋ ጥሩ ማሳያ ይመስለኛል።
  7. ዝግጅት – የፍጅት አካሄጆቹ መሪዎች ያቅዳሉ። ማስፈራሪያ ጭራቅ ቡድን(ኖች) ፈጥረው፣ ወታደራዊ ኃይልና መሣሪያ ያደራጃሉ። ብዙ ጌዜም ዓላማቸውን ለማሳካትና የመጨረሻ እቅዳቸውን ተግባራዊነት መጀመር ለማብሰር አይጎረብጤ አባባሎችን ለምሳሌ “ዘርን ማጽዳት” ወይም “ጸረ ሽብር” ወዘተ የሚሉትን ቅጽሎች ይጠቀማሉ። በእኛ ሀገር እውነታ ደወሉ የጀመረው “ቻርተር” በሚለው ቃል እና በውስጡ ባረባቸው ብዙ አናካሽ ቃላት ይመስለኛል። ማስፈራሪያ ጭራቁም “ነፍጠኛ” የሚለው ቃል ነበር፣ አሁን ደግሞ “አኃዳዊ/አኃዳዊያን” የሚለው ቃል ተደምሮለታል። ማማይዎቹ አይጎረብጤ ቃሎቻቸው/ሀረጎቻቸው/አረፍተ ነገሮቻቸው ደግሞ ብሔር ብሄረሰቦች/ራስን በራስ ማስተዳደር/ህዳሴ ወዘተ ነበሩ:: አሁንም በመደመር አዝማችነት እነኛው መልሰው ሲዜሙ ይስተዋላል::
  8. ማሳደድ – የዘር ፍጅቱ ሰለባዎች (ግፉዓን) በዘራቸው ወይም በሃይማኖታቸው የተነሳ ይለያሉ፣ የተገዳዮች ዝርዝር ይዘጋጃል። ባብዛኛውም ሰዎች በማቆያ ይታጎራሉ፣ ይባረራሉ ወይም እንዲራቡ ይደረጋል። አለዚያም በመሠረታዊነት አስፈላጊ የሆኑ ግብዓቶች ለምሳሌ ውኃ ወይም ምግብ እንዳያገኙ በማድረግ በዝግታ እንዲጠፉ ይበየንባቸዋል። ከፈቃዳቸው ውጭም የማምከን ስራ በጅምላ ሊካሄድባቸው ይችላል። ንብረታቸውም ይዘረፋል፣ ይወድማል። የጥቃቱ ሰለባዎች የሚሆኑት በዋናነት ተለይቶ ኢላማ ተደርጎ(ገው) የተለየው ቡድን አባላት ቢሆኑም ካጥቂው ቡድን አባላትም ውስጥ የተለሳለሰ አቁዋም ያላቸው ወይም የጥፋቱ ተቃዋሚ የሆኑ ለህሊናቸው ታማኝ ሰዎች የፍጅቱ ገፈት ቀማሽ እንደሚሆኑ ታይቷል:: ይህን መሰል እርምጃዎች ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ልብ ሳይል ከመጋረጃ ጀርባ እንዲከናወኑ ይሞከራል። የዘር ፍጅቱም ይጀመራል። በእኛም ሀገር ለዚህ ማሳያ ባለፉት 29 ዓመታት የተካሄዱትን ዘር/ሃይማኖት ተኮር ግድያዎቸና ማፈናቀሎች፣ ማምከንና የመሳሰሉትን ማስታወስ በቂ ነው።
  9. ፍጅት – የዘር ፍጅቱ ይጀመራል፡ እንደ ሰደድ እሳትም ተቀጣጥሎ የብዙዎችን ህይወት ይቀጥፋል። የጥላቻው ቡድን ኃይሎች ሆነኝ ብለውና በተደራጀ ሁኔታ የለዩዋቸውን ግፉዓን ይገድላሉ። ለእነሱ ግፉዓኑ ሙሉ ሰው አይደሉም፣ ምንምን እንደማስወገድ ያህል ናቸው። ልክ እንደ ጦር መሳሪያ፣ የተጠቂውን ማኅበረሰብ አባላት ገጽታ እስከ ወዲያኛው ለመደለዝም አስገድዶ መድፈርን ይጠቀማሉ።
  10. ክህደት – ፍጅት ፈፃሚዎቹ ምንም ወንጀል መፈጸሙን ይክዳሉ። እንዲያውም ግፉዓኑን የግልብጥ ይወነጅላሉ። የወንጀል ምርመራ እንዳይካሄድ ይከላከላሉ። በኃይል ከሥልጣን እስከሚባረሩና ከተረፉም እስከሚሰደዱ/እስከሚታሠሩ/ለህግ እስከሚቀርቡ መግዛታቸውን ይቀጥላሉ። በሀራችንም የዘር ፍጅት ተጀምሮ ባለበት በአሁኑ ወቅት: ከባለስጣናቱ ውስጥ አንዳንዶቹ ግፉአኑን ወይም የግፉአኑን ወገኖች በወንጀል ፈጻሚነት ሲከሱ አስተውለናል:: የገዥው ቡድን ደጋፊ የሆኑ ጣኦት ጠራቢዎችም በውጭ ሀገራት ከተሞችና የህዝብ መገናኛ ተቁዋማት ውስጥ እየተካሄደ ያለውን ወንጀል ለመካድ ወይም አለባብሶ ለማለፍ የሚያደርጉት ጥረት ለህሊና ሰቅጣጭ ነው:: ወደ ህሊናችን ተመልሰን በጊዜ ካልገታነው ተያይዞ የመጠፋፋቱን መንገድ ጀምረነዋል::

አሁን ያለንበትን ነገር ሳስብ የታላቁ አባት ደራሲ የከበደ ሚካኤል ባለሁለት አፍ ወፍ ትዝ ይለኛል:: በጉልበቱ የሚመካው አፍ ሁሉን ምግብ ለኔ ለኔ እያለ ያስመረረው ደካማው አፍ በምሬት መርዘኛ ፍሬ በልቶ ሁለቱም ተያይዘው የሞቱበት ታሪክ:: ስለዚህም በሚከተሉት ስንኞች ሀተታዬን መደምደም ፈለግሁ::

ከበደ ሚካኤል አንዴ ይነሱልኝ እንዲጠይቀዎ!
ያ ሁለት አፍ ያለው የግጥም ወፍዎ:
ባገርዎ ምድር ሰማንያ አፎች ይዞ ይኼው መጣልዎ:
ይህ ነበር ወይ ወርቁ የትላንት ቅኔዎ!?
ተረት በምሳሌ ያሰናሰኑበት ዐብይ መልዕክትዎ!?