የተገኘ ሞገስ አቦዬ አጭር የህይወት ታሪክ

ህይዎት አበክሮ የዕድሜ ገመዷ የተሰፈረ የነፍስና የስጋ ቅልቅል ፈራሽ አካል ነች። ህይዎት ልደቷ በዕልልታና በደስታ

ሚያዚያ 18 ቀን 1946 ዓ.ም. – መጋቢት 13 ቀን 2012 ዓ.ም

ሲበሰር፤ ህልፈቷ ግን በለቅሶ፣ በዋይታና በሙሾ የሚሸኝ የመድረክ ላይ ቲያትር ነች። የሰው ልጆች በተለምዶ ህይዎት የምንለው ሞት በኛ ውስጥ በአደራ ያስቀመጠውን ዕቃ ነው። የህይዎት ጎዳና ወጣ ገባ የበዛበት፤ ደስታ፣ መከራ፣ ፈተና ማጣትና ማግኘት የሚፈራረቁበት መንገድ ነው። የሰው ልጅም በዚህ ጎዳና ሲጓዝ ህልውናውን በራሱ እጅ ያልጨበጠ ተሠርቶ ፈራሽ ፍጥረት መሆኑን ልብ ብሎት የሚያውቅ አይመስልም። ስለሆነም የሰው ልጅ ዛሬን አልፎ ነገን ለማየት እርግጠኛ ባልሆነበት ጎዳና የሚጓዝ የህይዎት መንገደኛ ነው። የሰ ልጅ መኖርን ለመኖር ይለፋል፣ ይደክማል፣ ረዥምና አጭር ዕቅድ ነድፎ ሲንቀሳቀስም ይስተዋላል። ዳሩ ህልሙ ተፈትቶ ዕውን ሲሆን ማየት የሚችለው የሰው ልጅ ቁጥር ግን ውሱን ነው። አመዛኙ ፍጥረት እንደ ተገኘ ሞገስ ያለመውን ህልም ሳይፈታ፣ የተለመውን ሾር ሳይደፍን፣ የወጠነውንም ውጥን ሳይቋጭ ወደማይቀረው ዓለም ቀድሞ የሚጠራ ፍጥረት ነው።


ተገኘ ሞገስ ለራሱ ያልኖረ፤ ሙሉ ህይዎቱን ለሀገርና ለህዝብ ሰውቶ ያለፈ ብርቅየ ታጋይ ነበር። ተገኘ ሞገስ ሳይመንን ገዳም የገባ፤ ሳይመነኩስ ቆብ የጫነ የእግዜር ሰው ነበር። ተገኘ ለህዝብና ለሀገር ሲል ራሱን አጎሳቁሎ የኖረ የህዝብ ልጅ ነበር። ድሎት በኢህአፓ ታሪክ የሚታወቀው በስም ብቻ ነው። ዳሩ እንደ ተገኘ ሞገስ ግን የችጋር ቋት ሆኖ ያለፈ መሪ አይታወቅም። ተገኘ ግን ለድህነት ሳይበገር እስከ ህይዎቱ ፍጻሜ ለፍትህ፣ ለዕኩለነትና ለዴሞክራሲ ዕውንነት ግንባር ቀደም ሆኖ ሲታገል ዕድሜውን የጨረሰ መሪ ነበር።


ተገኘ ሞገስ ይህችን ዓለም ለመጀመያ ጊዜ የተዋወቃት ሚያዚያ 18 ቀን 1946 ዓ ም ነበር። ጎንደር ጃናሞራ፤ ደረስጌ ማርያም ላይ። እናቱ ወ/ሮ ጥሩየ ማዘንጊያና አባቱ ሃምሳ አለቃ ሞገስ አቦዬ ትንሳኤ በዋለ በማግሥቱ በዕለተ ሰኞ ያገኙትን ወንድ ልጅ ተገኘ ሲሉ ስም አወጡለት። ስምን መላዕክ ያወጣዋል እንዲሉ ተገኘ ሞገስ ዕውነትም ተፈልጎ የተገኘ ልዩ ፍጥረት ነበር። ለምን ቢሉ ድምጽ ለሌላቸው ድምጽ ሆኖ ሲጮህ፤ መብታቸውን ለተነጠቁም ጥብቅና ቆሞ ሲሟገት ህይዎትን ለራሱ ሳይሆን ለሌሎች የኖረ ታጋይ ነበርና።

ተገኘ ሰባት ዓመት ሲሞላው ወደ አብነት ት/ቤት አቅንቶ ዳዊት ደግሟል። ቀጥሎም ወደ ዘመናዊ ት/ቤት ገብቶ የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በጻዲቁ ዮሐንስና በጎንደር ቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ ሁለተኛ ደረጃ (ቀ. ኃ. ሥ) ት/ቤት ጨረሰ። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን እንደጨረሰም የአባቱን ፈለግ በመከተል ህልሙን እውን ያደርግ ዘንድ ለአባዲና ፖሊስ ኮሌጅ አመለከተ። አካዳሚው ግን በቁመቱ ማጠር ሳቢያ ሳይቀበለው ቀረና የመጀመሪያውን ህልሙን አመከነበት።

የመጀመሪያ ህልሙ የመከነበት ተገኘ ሞገስም ሁለተኛውን ህልሙን ዕውን ለማድረግ ሐረር መምህራን ማሰልጠኛ ተቋም ገብቶ በመምህርነት ተመረቀ። እንደተመረቀም የመጀመሪያዎቹን ዓመታት በሐረር ክፍለ ሀገር በመስታሂልና በጅጅጋ ከዚያም በድሬዳዋ ና በአዲስ አበባ በመምህርነት አገሩን አገልግሏል። አዲስ አበባ እንደገባም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በማታው የትምህርት ክፍል በህግ ፋካሊቲ ኮሌጅ ተመዝግቦ የከፍተኛ ትምህርቱን በመከታተል ላይ ሳለ የ66ቱ አብዮት ፈነዳ።

አብዮቱ ከመፈንዳቱ አንድ ዓመት ቀደም ብሎ ግን በ1965 ዓ ም የትምህርት ሚኒስቴር “ሴክተር ሪቬው” የተሰኘ አዲስ ሥርዓተ ትምህርት ነድፎ ነበር። ትምህርት ሚኒስቴር እቅዱን በሥራ ለመተርጎም ሲንቀሳቀስ ግን ከመምህራኑ ከፍተኛ ተቃውሞ ገጠመው። የመምህራን ማህበርም ተቃውሞውን የበለጠ ለማጠናክር መስከረም 1966 ዓ.ም ጠቅላላ ጉባኤ ጠራ። አርባ ምንጭ ላይ ጉባኤ የተቀመጠው ኢመማ አዲሱን ሥርዓተ ትምህርት “የድሃ ልጆችን የትምህርት እድል የሚነፍግ ሥርዓተ ተምህርት” ነው ሲል ሴክተር ሪቬውን በሙሉ ድምጽ አውግዞ ውሳኔ አስተላለፈ።

ኢመማ ተቃውሞውን ቀጥሎም ታህሳስ 12/1966 ዓ ም ልዩ ጉባኤ ጠራ። አዲስ አበባ ላይ። ቀደም ሲል የአርባ ምንጩ ጉባኤ በሴክተር ሪቬው ላይ የወሰናቸውን ውሳኔዎች አጠናክሮ ልዩ ጉባኤው የመምህራን የደሞዝ ልክ (scale) እንዲስተካከልና ሌሎችንም ጥያቄዎች አቅርቦ፤ ጥያቄዎቹ መልስ የማያገኙ ከሆነ ግን የከቲት 11/1966 ጠቅላላ የሥራ ማቅም እንደሚጠራ አሳወቀ። ተገኘ ሞገስ በዚህኛውና ቀደም በተካሄዱት ጉባኤዎች ተሳታፊ ነበር።
በተለይ የታህሳሱ ጉባኤ ግን ለተገኘ ሞገስ ታሪካዊ ነበር። በዚህ ጉባኤ ነበር የኢመማ አመራሮች በፀጥታ ኃይሎች እጅ ቢወድቁ የማህበሩ ትግል እንዳይሽመደመድ እነርሱን ተክቶ ኢመማን የሚመራ ድብቅ ኮሚቴ

ይቋቋም ዘንድ ሃሳብ የቀረበው። ይህ ሀሳብ ጊዜና ቦታን ያላገናዘበ መሆኑን ከሁሉ ቀድሞ የተረዳው ግን ተገኘ ሞገስ ነበር። እናም “ለ12ቱ ሐዋርያት አንድ ይሁዳ እንደተመደበላቸው ለዚህም ጉባኤ ይሁዳዎች ላለመመደባቸው ማረጋገጫ ሳይኖረን የድብቅ ኮሚቴውን (shadow committee) ባደባባይ መሰየም አደጋ አለው” ሲል ለጉባኤው አሳሰበ። ማሳሰቢያውን ታሳቢ ያደረገው የኢመማ ምክር ቤትም ባለአምስት አባላት የድብቅ ኮሚቴውን ሲሰይም ተገኘ ሞገስን ከአምስቱ አንዱ አድርጎ መረጠው።

የጠሉት ይነግሳል የፈሩት ይደርሳል እንዲሉም የተገኘ ሞገስ የፈራው ደረሰና በፀጥታ ሹሙ ተጠራ። ብሎም የዕምነት የክህደት ቃሉን እንዲሰጥ ተጠየቀ። ተገኘም ብለሃል የተባለውን አባባል ማለቱን በልበ ሙሉነትና በድፍረት ካረጋገጠ በኋላ አባባሉ ዕውን መተግበሩንም ለሹሙ አስርገጦ የተናገረ ደፋርና ቆራጥ ታጋይ ነበር። ከዚያ በኋላ ክትትል እንደሚያደርግበት ቢረዳም ተገኘ ሞገስ ግን ከጀመረው ትግል አንድ ጋት እንኳ ፈቀቅ አላለም።

ይልቁንም ተገኘና ኢመማ ትግላቸውን አጠናክረው የካቲት 11/1966 ዓ.ም አዲሱን ሥርዓተ ትምህርት በሰላማዊ ሰልፍ ሲያወግዙ ንጉሡ ሴክተር ሪቬውን ለጊዜው እንዲገታ አድርገው፤ የመምህራን የደሞዝ እስኬልም ተጠንቶ እንዲስተካከል ወሰኑ። የሚኒስትሮች ም/ቤት ግን ውሳኔውን ሳይቀበለው ስለቀረ ትግሉ እየጋመና እየጎመራ ሄዶ የዘውዱ አገዛዝ ተገረሰሰ።

ደርግ የዘውዱን አገዛዝ ገልብጦ ወደ ስልጣን እንደወጣ ያቋቋመው የትምህርት ኮሚቴም የመምህራኑን ጥያቄ ሊመልስ ባለመቻሉ ኢመማ በመጋቢት ወር 1967 ዓ ም ሌላ ጉባኤ ለመጥራት ተገደደ። ነቀምት ላይ። የነቀምቱ ጉባኤ ደርግ ያቋቋመውን የትምህርት ኮሚቴና ኮሚቴው ያወጣውን የትምህርት መመሪያ አውግዞ ኢመማ ቀደም ላነሳቸውና ለአዲሶቹ ጥያቄዎችም መልስ ያገኝ ዘንድ ውሳኔ አስተላለፈ።

ደርግ ወደ ስልጣን እንደወጣ የአፄውን ፓርላማ አፍርሶ ከየሚኒስቴር መ/ቤቶችና ከሙያ ማህበራት የተውጣጣ የመማክርት ሸንጎ ሲሰይም ተገኘ ሞገስ ኢመማን ወክሎ የሸንጎው አባል ሆነ። ተገኘ ሞገስ በሸንጎ ቆይታው ከክቡር አቶ ሀዲስ ዓለማየሁ፣ ከፕሮፈሰር ጌታቸው ኃይሌ፣ ከህግ ባለሙያው ከአቶ አሰፋ ሊበንና ከመሰል የሸንጎ አባል ምሁራን ጋር አብሮ ሲሠራ የገበየውን ከፍተኛ ተመክሮ በህይዎት ዘመኑ አዘውትሮ ይናገር ነበር።

ደርግ ያቋቋመው የትምህርት ኮሚቴ ለመምህራኑ ጥያቄዎች መልስ ባለመስጠቱና እየተባባሰ ለሄደው የሀገሪቱ የፖለቲካ ችግርም መፍትሔ ሊሰጥ ባለመቻሉ ኢመማን ሌላ ጉባኤ እንዲጠራ አስገደደው። ጅማ ላይ። መስከረም 1968 ዓ ም ጅማ ላይ የተካሄደው 18ኛው የኢመማ ጉባኤ የደርግን የትምህርት ኮሚቴና ዝግጅቱንም ተቃውሞ ሀገራዊ ጥያቄዎችን ያካተተ ውሳኔ አስተላለፈ። በውሳኔውም የጊዚያዊ ህዝባዊ መንግሥትን መቋቋም አስፈላጊነት ጠቅሶ የህዝብን በነጻነት የመናገር፣ የመደራጀትና የመሰብሰብ መብት፤ ለዕኩል ሥራ ዕኩል ክፍያ፤ የትምህርት ዕድል ለሁሉም ዜጎች ይዳረስ የሚሉና ሌሎችንም ሀገራዊ ጥያቄዎችን ያካተተ መግለጫ አወጣ። ጥያቄዎቹ የማይመለሱ ከሆነም በህዳር ወር 1968 ዓ ም ጠቅላላ የሥራ ማቆም አድማ እንደሚያደርግ ሲያሳውቅ ተገኘ ሞገስ የኢመማ አመራር አባል ነበር።

ቀደም ሲል ኢመማን ወክሎ ከሠራተኛው ማህበር አመራሮች ጋር ሲገናኝ እግረመንገዱንም ከኢህአፓ ጋር የመተዋወቅ እድል የገጠመው ተገኘ ሞገስ ትግሉ ከሙያ ማህበር ወደ ፓርቲ ትግል ክፍ እንዲል በመምህራኑ ውስጥ የራሱን ድርሻ አበርክቷል። ተገኘ ሞገስ ሁለት እጁ ቀኝ እንደሸማኔ እንዲሉ የኢመማ አመራር፤ የሸንጎና የኢህአፓ አባል ሆኖ ታግሎ ያታገለ አርበኛ ነበር። በ1968 ዓ ም በሰሜናዊ ምዕራብ የሀገሪቱ ክፍል በተለይም በጎንደር የተፈጠረውን የፀጥታ መደፍረስ ለማረጋጋት ደርግ አንድ የምሁራን ልኡክ ሲሰይም ተገኘ ሞገስ የዚህ ልኡኩ አካል ሆኖ ለግዳጅ ተሰማርቷል።

ልኡኩ ከግዳጅ ሲመለስ ግን ተገኘ ሞገስ ከሚታደኑት የኢመማ አመራሮች አንዱ ሆኖ ማደኛ እንደወጣበትም ተነገረውና ህቡዕ ገባ። በህቡዕም ወደ ጎንደር ተመልሶ በወቅቱ የኢመማ ፕሬዘዳንት ከነበረው ከአቶ ካሳሁን ብሥራት ጋር ወደ ሱዳን አቀና። በሱዳን ከድርጅቱ ጋር ተገናኝቶ ወደ ካይሮ በማቅናት በካይሮ የድርጅቱን ሥራ ካይሮ ከነበረው የኢትዮጵያ ተማሪዎች ማህበር ጋር አቀናጅቶ በመታገል ላይ ሳለ በ1980ዎቹ መጀመሪያ ላይ ድርጅቱ የመበታተን አደጋ ሲገጥመው ወደ አሜሪካ የመምጣት እድል አግኝቶ አሜሪካ ገባ።

አሜሪካ እንደገባም ወደ ቦስተን አቅንቶ ያቋረጠውን የከፍተኛ ትምህርት ቀጥሎ በፖለቲካል ሳይንስ ተመረቀ። ከምረቃ በኃላም ትምህርቱን ቀጥሎ በህግ ሙያ ሁለተኛ ዲግሪውን እንዲይዝ ስፖንሰር ያደረገው ቤተሰብ እድሉን አመቻችቶለት ነበር። ተገኘ ግን እድሉን ሳይጠቀምበት ቀርቷል። የተመቻቸለትን ዕድል ወደ ጎን ገፍቶም በሰሜን አሜሪካ የኢህአፓን ትግል ለማስቀጠል ወደ ዋሽንግቶን ዲሲ ገሰገሰ።

ተገኘ ከግል ህይዎቱ ይልቅ የህዝቡንና የአገሩን ችግር አስቀድሞ ሙሉ ዕድሜውን በትግል ያሳለፈ ታጋይ ነበር። ተገኘ ሞገስ ዋሽንግቶን ዲሲ ከገባበት ጊዜ አንስቶ እስከ ይህዎቱ ህልፈት ድረስ ከተራ አባልነት እስከ ከፍተኛ የአመራር እርከኖች በሃላፊነት ድርጅቱን መርቷል። ድርጅቱ ኢህአፓ ከሌሎች ቡድኖች ጋር በቅንጅት በፈጠራቸው ህብረቶችም ቀደም ሲል በኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች ቅንጅት (ኢ ዴ ኃ ቅ) የሥራ አስኪያጅ ኮሚቴ አባል ሆኖ ትግሉን መርቷል። በኋላም የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች ሕብረት (ኢ ዴ ኃ ኅ) ሲመሰረት የመሥራች ጉባኤው አባል ነበር።

ተገኘ ሞገስ ከፍ ብሎ እንደተጠቀሰው ለራሱ ያልኖረ የህዝብ ጠበቃ ነበር። ተገኘና የግል ህይዎት አይከባበሩም። የግል ህይዎት ለተገኘ ሞገስ እራፊ ጨርቅ ነው። ተገኘ ሞገስ በህዝብና በሀገር ፍቅር ልቡ የደማ የግል ህይዎትን ተፀይፎ ለራሱ ያልኖረ ትሁት፤ ግን ደግሞ ቆራጥና ቆፍጣና ታጋይ ነበር። ተገኘ ትዕግሥትን ከትህትና ጋር አዛምዶ ሰብዕናውን የገነባ ጨዋ ሰው ነበር። ተገኘ ለቆመለት ዓላማ ራሱን አዋርዶ የኖረ ሰው ነበር። ተገኘ የማስተዋል ማህደር፤ የዕውቀት ጮራ፣ የፍቅር ባህር፤ ለቂምና ቁርሾ ብሎም ለበቀል ቦታ የማይሰጥ የዕውነት ሰው ነበር። ሁሉም ሰው በተገኘ ፊት እኩል ነው። ትንሽም ይሁን ትልቅ ባለስልጣንም ይሁን ሀብታም ወይም ድሃ ለተገኘ ሁሉም ዕኩል ሰዎች ናቸው። ተገኘ ቀልዱ የማይጠገብ፤ ቁምነገሩና ምክሩ ለሁሉም ሰው ምኩራብ የነበረ ትልቅ ሰው ነው።

ተገኘ ሁሉንም ጓዶች አባዬ ሲል ስብዕናውን የሚያንጸባርቅ የፍቅር ሰው ነበር። የትም ይሁን የት፤ መቸውንም ቢሆን ተገኘ በሰዎች ላይ ድምጹን ከፍ አድርጎ የተናገረበት ጊዜ ኖሮ አያውቅም። ተገኘ ለልጆች ያለውን ፍቅር ቃላት አይገልጹትም። ተግባቢኑቱ መሳሂብ ስላለው ሁሉም ልጆች ይቀልዱታል። እርሱም ስቆ ስለሚያስቃቸው ይወዱታል።
ተገኘ ትንሽም ብትሆን ባለው ተደስቶ ማደርን ባህሉ ያደረገ ሰው ነበር። አጣሁ ብሎ አያማርርም። ድሮ የነበረውን የድሎት ህይዎት በኋላ ላይ ከገፋው ጎስቋላ አኗኗር ጋር አነፃፅሮ የተፀፀተበት ጊዜ ኖሮ አያውቅም። ተገኘ ቢከፋውም ሁልጊዜ ደስተኛ ነው። እርጋታው ማንንም ያስቀናል። ለገንዘብ

ዋጋ አይሰጥም። ወደ ትግል ዓለም ከገባ በኋላ ተገኘ ከመጻህፍቱ ሌላ የኔ የሚለው ሀብትና ንብረት አላፈራም። ለተገኘ ሀብቱ፣ ንብረቱና ትዳሩ ኢትዮጵያ ነበረች።

ንባብና ተገኘ ቀለምና ወረቅት ናቸው። በንባብ ያዳበረው እውቀቱ በምልከታ ከገበየው ክህሎቱ ጋር ተዋህደው ተገኘን የታሪክ ማህደር አድርገውት ኖረዋል። የተገኘ ብዕር እንደ አእምሮው የተባና ስሉ ነበር። የማስታወስ ችሎታውን እርጅና ያልነጠቀው ሽማግሌ ቢኖር ተገኘ ሞገስ ብቻ ነው። ተገኘ ሞገስ ሰው ሆኖ እንደተፈጠረ ሰው ሆኖ ወደ መቃብር የወረደ ሰው ነበር።

ህይዎት ከሞት በፊትና ከሞት በኃላ የምትጠራባቸው ሁለት ስሞች አሏት። በህይዎት ዘመኑ የምናውቀው ትሁቱ አባዬ ስሙ ተገኘ ሞገስ ነበር። ከሞተ በኃላ ግን ስሙ ተለውጦ አስከሬን ተብሏል።

አፈር ነህና ወደ አፈር ትመለሳለህ እንደተባለው ተገኘ ሞገስም የአዳም ልጅ ሆነና አፈር ሆኖ ወደ አፈር ተመልሶ አፈር ለብሷል።

የሰማዕቱን የአባዬን ነፍስ ይማር።
አሜን!!!!
መጋቢት 2012