የዓለም የሰብዓዊ መብቶች ቀን: በኢትዮጵያ መብት ረገጣና ጸረ ህዝብ ወንጀል በጣም ተስፋፍቷል

የኢትዮጵያ ፖለቲካ እስረኞች አንድነት ኮሚቴ መግለጫ (ህዳር 30 ቀን 2012) – ምንም እንኳ አገዛዙ እስረኞችን ፈታ እየተባለ በተለያዩ ሚዲያዎች እና በሀገር በቀል አወዳሾቹ ቢሞገስም ከመጋረጃ ጀርባ እስካሁንም ድረስ በተለያዩ ድብቅ ማሰቃያዎች የእስር ሰንሰለቱ ያልተፈታላቸው በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ግፉዐን አሉ። ለዚህም እንደማሳያ:

⦁ ላለፉት 28 ዓመታት በአገዛዙ የደህንነትና የጸጥታ አካላት ታፍነው የደረሱበት የማይታወቀው የኢሕአፓ ነባር አመራሮችና አባላት፣
⦁ የሰሜን ሸዋው ጀግና አርበኛ የደጃዝማች ተሰማ እርገጤ ልጆች 4ወንድማማቾች (ምኒሊክ ተሰማ፣ ዓለማየሁ ተሰማ፣ ወንደሰን ተሰማ እና ዳኔኤል አጎናፍር ያክስታቸዉ ልጅ)፣
⦁ የጐንደሩ ሊቁ መምህር አግማሴ እና ሌሎችንም በምሳሌነት መጥቀስ ይቻላል።

በዚህ ሁኔታ ቤቱ የሚቆጥራቸው በሺህ የሚቆጠሩ ግፉዐንና በተለያዩ የሀገሪቱ ቦታዎች የሚኖሩ ቤተሰቦቻቸው፣ ወዳጅ ዘመዶቻቸው እስካሁንም ፍትህ እየጠየቁ ነው። የግፉዐኑን መዳረሻ አያውቁም፣ ግፍ አድራሾችም በህግ ሲጠየቁ ሳይሆን ሹመት ሲሰጣቸው ወይንም በመንግስት ውሎ አበል እና ጥበቃ እየተደረገላቸው የተንፈላሰሰ ኑሮ ሲኖሩ ነው የሚስተዋለው። የቀደመው የደህንነትና የአፈና ዋና መሪ ከነበረው ከቁንጮው ጠቅላይ ሚኒስተር ጀምሮ እስከ ታች ያሉት የአገዛዙ የሃላፊነት ወንበሮች የተያዙት ባለፉት 28 ዓመታት ውስጥ በእመቃው እጃቸው በነበረበት ግለሰቦች ሲሆን፣ እያደረጉ ያለውም ስለፈጸሙት ወንጀል የሚመሰክሩ ማስረጃዎችን ለማጥፋት ጊዜ መግዛት ነው። የማይቀረውን የፍትህ ባቡር ጉዞ በማዘግየት፣ ደርሶ እንዳይዛቸው ለማድረግ። አሁንም የጠቅላይ አቃቤ ህግነቱን ስልጣን እንደያዘ ያለውን አቶ ብርሃኑ ጸጋዬን እዚህ ላይ በምሳሌነት ማንሳት እንሻለን። ይህ ግለሰብ ላለፉት 28 ዐመታት የውሸት ማስረጃዎችን እያዘጋጀና ዐባይ ምስክሮችን እየመለመለ ንፁሃን ዜጋዎችን በሀሰት ያሳስር፣ በተንዛዛ የችሎት ሂደት ያሰቃይ፣ በእስርና ድብደባ አካላዊና ሥነልቦናዊ ስዬል ያደርስ የነበረው ዐቃቤ ህግ ሃላፊ ነበር፣ አሁንም ነው። በቅርቡም የተጠቀሱት ግፎች ማዕከል የነበረው ማዕከላዊ እስር ቤት ተዘጋ በሚል ሰበብ የዐመታት ማስረጃዎች እንዲጠፉ አድርጎ ለጎብኝዎች ማብራሪያ ሲስጥ በቴሌቭዥን መስኮት አስተውለናል። ጳጉሜ 1 ቀን 2011 ተዘጋ የተባለው እና ከሃይለስላሴ አንስቶ እስካሁን ባሉት አገዛዞች የተቃዋሚዎች ማሰቃያ የነበረው ማዕከላዊ አሁን ገጽታው በቀለም ቅብ ተቀይሯል፣ መብራት በመብራት ሆኗል። እዚያው ህይወታቸው ያለፉትም ሆኑ አሁን በነፍስ ያሉት የግፉ ሰለባዎች ይደርስባቸው የነበረውን ስቃይና ማንነታቸውን በተመለከተ በደማቸውና ባገኟቸው ሌሎች መጻፊያዎች በየግርግዳዎቹ ላይ የከተቧቸው የመከራ ታሪክ ማስረጃ ማስታወሻዎች ቀለም ተቀብተው እንዲጠፉ ተደርገዋል። የታሪኩ ማስረጃዎች በዚህ መልክ እንዲጠፉ ከተደረገው ማዕከላዊ እስር ቤት በጥቂት እርምጃዎች ርቀት ላይ ግን ሌላ ህንጻ ተሰርቶ፣ የባሰ የጠበቡና የሚበርዱ ጨለማ ክፍሎቹን ጨምሮ በውስጡ እስረኞችን በሀሰት እያጎሩ ማሰቃየቱ ቀጥሏል።

በሀገሪቱ ያለው አገዛዝ ሊዩተናንት ኮለኔል ዐብይ አህመድ ወደ ሥልጣን የመጣ ሰሞን ከመስከረም 3 ቀን 2011 ጀምሮ ለሶስት ተከታታይ ቀናት፣ በአዲስ አበባ ዳርቻ በቡራዩ ከተማ በተካሄደው ዘር ተኮር የመንጋ ጭፍጨፋ፣ ቢያንስ 33 ሰላማዊ ዜጎች በግፍ ተገድለዋል፣ ከፍተኛ ግምት ያለው ቤትና ንብረት ተቃጥሏል ፈራርሷል። በአጠቃላይ አዲስ አበባና አካባቢዋን ጨምሮ በተለያዩ የሀገሪቱ ቦታዎች ዜጎች ለዓመታት ለፍተው ጥረው የሰሩትን ቤት እና ያፈሩትን ንብረት ማፈራረስና ማቃጠል፣ መንጋዎችን ጃስ በማለት ዘርና ሃይማኖት ተኮር ጥቃቶችን ማካሄድ የአገዛዙ ሹማምንት የተለመደ የዕለት በዕለት ተግባር እየሆነ መጥቷል።

ባህርዳር ከተማ ውስጥ ሰኔ 15 ቀን 2011 ተሞከረ የተባለውን የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ተከትሎም፣ በአሁኑ ወቅት በቁንጮነት ሀገሪቱን እየገዛ ያለው የኦሮሞ አክራሪዎች ቡድን የአዲስ አበባ ከተማን ኗሪዎች የጎሳ ስብጥር ለመቀየር የሚያካሂደውን ጥረት የሚቃወመውን የባለአደራ ምክር ቤት አባላትን፣ ጋዜጠኞችን፣ የአማራ ህዝብ ድርጅት አመራሮችንና አባላትን፣ እና ሌሎችንም የማኅረሰብ አነቃቂዎች ጨምሮ ከ1 ሺህ በላይ ዜጎች በግፍ ታፍሰው ታስረዋል። የተባለውን ሙከራ መርተዋል የተባሉት ጄኔራል አሳምነው ጽጌም በተድበሰበሰ ሁኔታ እጅ አልሰጥም ብለው ሲታኮሱ ሞቱ ተብሏል። ነፍሰ ጡር የነበሩት ባለቤታቸውም ክስ ሳይመሰረትባቸው ቆይተው ያለፈው ሰሞን ተፈተዋል፡፡ የጄኔራሉ ወንድምም የደረሱበት አይታወቅም። የአገዛዙ ቁንጮ ዐብይ አህመድ እና ቃል አቀባዩ፣ በዕለቱ ባህርዳር ውስጥ በአማራ ክልል ባለሥልጣናት፣ አዲስ አበባ ውስጥ በሁለት ጄኔራሎች ላይ የተካሄደውን ግድያ በተመለከተ በሀገሪቱ ቴሌቭዥን ላይ ወጥተው፣ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ነው ለማለት እና ጄኔራል አሳምነውን በሙከራው መሪነት ለመክሰስ ከአንድ ሰዓት በታች ነው የወሰደባቸው። ሙከራው በክልል ደረጃ ያውም በአማራ ክልል መሆኑ፣ የአገዛዙ የደህንነትና የጸጥታ ክፍል በኦሮሞ አክራሪዎች መዘወሩ፣ ሁኔታው በብዙ አጠራጣሪ መጠይቆች መከበቡም የአገዛዙን ክስ ለማመን አስቸጋሪ ያደርገዋል። ስለዚህም ነው የተባለው ሙከራ አገዛዙ፣ ጄኔራል አሳምነውን ጨምሮ በአማራ ክልል ውስጥ ተፎካካሪው የነበሩ አክራሪ ብሄርተኞችን ለማስወገድ ያቀናበረው ግድያ ሊሆን ይችላል የሚሉ ክሶች መብዛታቸው።

ከጥቅምት 12 ቀን 2012 ጀምሮ ደግሞ ለሶስት ተከታታይ ቀናት አገዛዙ ኦሮሚያ ብሎ በሚጠራው ክልል ውስጥ ቄሮ በሚል የመንጋ ስም በተካሄደው ዘር እና ሃይማኖት ተኮር ጭፍጨፋና ጥፋት ከ139 በላይ ንፁሃን ዜጎች ተገድለዋል፣ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች የአካል እና የሥነልቦና ጉዳት ደርሶባቸዋል፣ ከፍተኛ ግምት ያለው ቤትና ንብረት ወድሟል። ግድያዎቹ እጅግ አሰቃቂ ነበሩ። በግፍ ከተገደሉት ዜጎች ውስጥ ጥቂቶቹን ለመዘከር:

⦁ በኮፈሌ ተወልደው ያደጉት የ60 ዓመቱ አዛውንት አቶ ታምራት ጸጋዬ እና
⦁ ልጃቸው ሄኖክ ታምራት በድንጋይ ተቀጥቅጠው ከተገደሉ በኋላ አስክሬናቸው በሞተር ሳይክል ሲጎተት ውሏል። በኮፈሌ እና በሻሸመኔ ይገኝ የነበረ ቤት ንብረታቸው ወድሟል። በወቅቱ ኮፈሌ የነበሩት እህታቸውም ጎረቤቶቻቸው ጭድ ውስጥ ደብቀዋቸው በመንጋው ከመገደል ተርፈዋል።
⦁ ፓስተር ኢሳያስ ሰበታ ከተማ ውስጥ የሙሉ ወንጌል አገልጋይ እና
⦁ ፓስተር አሰፋ ተስፋዬ በዚሁ ከተማ የመካነ ኢየሱስ ቤተክርስቲያን አገልጋይ የነበሩ በድንጋይና በስለት ተቀጥቅጠው ተገድለዋል። ፓስተር አሰፋ ዕድሜያቸው ሁለት ዓመት በሆነው ሁለት መንታ ልጆቻቸው እና በባለቤታቸው ፊት ነው ተቀጥቅጠው የተገደሉት። ግድያው እንደተፈጸመ ወዲያውኑ የደረሱት ፖሊሶችም ገዳዮቹን ለመያዝና ሌላም ጥፋት እንዳያደርሱ በማስቆም ፈንታ በሟቹ ሚስት እና በልጆቻቸው ይሳለቁባቸው፣ ያንጓጥጧቸው ነበር።
⦁ አበባየሁ ካሣ በድሬደዋ ዩኒቨርስቲ የጨርቃጨርቅ ኢንጅነሪን ሶስተኛ ዓመት ተማሪ፣ ከፎቅ ላይ ተወርውሮ ተገደሏል።
⦁ በዚሁ ከተማ ኗሪና የ4 ልጆች እናት የሆኑት ወይዘሮ አማሩ ደረጀም ከከተማው ውጭ ተግዘው በመጡ የቄሮ መንጋዎች በደረሰባቸው ድብደባ ኅዳር 8 ቀን 2012 አርፈዋል።
⦁ አራሷ መምህርት እርቀሰላም ሞገስም ምዕራብ ሀረርጌ ውስጥ በተኛችበት በድንጋይ ተቀጥቅጣ ተገድላለች።
⦁ ፍፁም ወጋየሁ ዘንድሮ የአስረኛ ክፍል ተማሪ ነበር። በያዘው ሳምንት ነበር አስራ ሰባተኛ አመቱን ያከበረው። ተምሮ መሃንዲስ የመሆን እቅድ ነበረዉ። ዶዶላ ውስጥ በዚሁ የቄሮ መንጋ በቁሙ ተጨፍጭፎ ተገደለ።
⦁ አቶ ደረጀ ኃይሌ ተወልዶ ያደገው በሀረርጌ በሮዳ ከተማ ነው። ሃይማኖቱ ኦርቶዶክስ ክርስቲያን ነው። አክራሪ የኦሮሚያ ፖሊሶች ለጥያቄ ትፈለጋለህ ብለው ወደ ፖሊስ ጣቢያ ከወሰዱት በኋላ ለአክራሪ የቄሮ መንጋዎች አሳልፈው ሰጥተውት በአሰቃቂ ሁኔታ ተገድሏል። አክራሪዎቹ አራጆች የአቶ ደረጀን እግርና እጅ ይዘው በቁሙ ዓይኑን በካራ ካወጡ በኋላ፣ ምላሱን ቆርጠዋል፣ ብልቱንም ቆርጠው በደም በተጨማለቀ አፉ ውስጥ በመክተት፣ በመጨረሻም በያዙት ሜንጫ፣ ድንጋይና በገጀራ ጨፍጭፈው ገድለውታል። አስከሬኑንም ከተማ ላይ አውጥተው ኣላህ ወአክበር ብለው ፎክረውበታል።
⦁ አቶ ደመና ኃይሌም የአቶ ደረጀ ኃይሌ ወንድምና በዚሁ ከተማ ውስጥ የግፉ ሰለባ ናቸው። በሃይማኖታቸው ኦርቶዶክስ ክርስቲያን የሆኑት አቶ ደመናና ባለቤታቸው ወይዘሮ ወላንሳ ፍቅር በዚሁ የቄሮ አክራሪ መንጋ ታርደው ከአቶ ደረጀ ጋር በአንድ ጉርጓድ ተቀብረዋል።

ከእነኝህና ሌሎች መሰል አሰቃቂ ወንጀል ፈፃሚዎች ውስጥ አንድም ወንጀለኛ ተይዞ በህግ አግባብ አልተዳኘም። ወንጀሉ የሚካሄደው አክራሪዎቹ ገዥዎች ከተቆጣጠሩት የየአካባቢ ባለሥልጣናት፣ የፖሊስና የደህንነት መንግሥታዊ ተቋማት ጋር በመናበብና ሽፋን በመሰጣጣት ስለሆነ፣ የወንጀሉ ድርጊት ከተፈጸመ በኋላ ጉዳዩን ለማደባበስ የሚታሰሩትና የሚዋከቡት የወንጀሉ ተጠቂዎችና ወንጀሉን ለመከላከል የሞከሩ ሰላማዊ ዜጎች ናቸው። በብዙ ቦታዎችም የፖሊስና የደህንነት አባላት በግልጽ ለወንጀል ፈፃሚዎቹ ከለላና ሽፋን ሲሰጡ ታይተዋል። ሌላው ቀርቶ በፍርድ ቤቶች ደጃፍ እንኳ ጋዜጠኞች ሥራቸውን ለማከናወን ሲንቀሳቀሱ የአገዛዙ የጸጥታና የደህንነት አካላት የሚያደርሱት እስርና ማዋከብ አሁንም አልቆመም። በአለንበት ዓመት የፈረንጆቹ ኦገስት ወር ውስጥ በፍርድ ቤት አጠገብ ቃለመጠይቅ ሲያካሂድ የታሰረው ጋዜጠኛ ምስጋናው ጌታቸው ለዚህ ጥሩ ማሳያ ነው። ምስጋናው የታሰረው አገዛዙ በሀሰት የሽብር ክስ የመሰረተባቸውን ሌሎች ሁለት የህዝብ መገናኛ ባለሙያዎች ጉዳይ አስመልክቶ ለመዘገብ ቃለመጠይቅ በማካሄድ ላይ እያለ ነበር።

 ከሺ በላይ ዜጋ በግፍ ተጨፍጯል፡፡ በተለይም ተጠቂ የሆኑት ህጻናትና አዛውንት ናቸው ሲባል ብዙዎች ሴቶችም ሰለባ መሆናቸው ተረጋግጧል፡፡ ለዚህም ተጠያቂው አገዛዙ ነው፡፡ ይህ አገዛዝ በዘር በሃይማኖት ክፍፍል ፖለቲካውና ጥላቻንም እያስፋፋ፤ የዘር ማጽዳትንም ወንጀል እየፈጸመ ነው፡፡ የፖለቲካ ጉዳይና ሻጥር ሆኖ እንጂ በዛሬው ቀን የዘረኛው መንጋ ዋና አለቃ የሰላም ሰው ተብሎ ለሽልማት ባልቀረበም ነበር፡፡ ዛሬም ከአርባ ሺ በላይ የፖለቲካ እስረኞች በስቃይ ላይ ናቸው፤ ፍትህ ደብዛዋ እንደጠፋም ነው፡፡

በአጠቃላይ በሀገሪቱ ውስጥ የሚደርሰው ዘር እና ሃይማኖት ተኮር ጥቃት በብዛትም ሆነ ከሀገሪቱ የቆዳ ሽፋን የሚያካልለው ቦታ እየሰፋ መጥቷል። ከአዲስ አበባ ወደ መቀሌ ሄደው የመሸጉት ወያኔዎች፣ በአዲስ አበባ ቤተመንግሥቱን የተቆጣጠሩት የኦሮም እስላማዊ አክራሪዎች፣ በየአካባቢው የጦር ሃይል እያደራጁ ያሉት አክራሪ በሄርተኞች በተለያዩ የውጭ ሃይላት እየታገዙ በሚያደርጉት የሥልጣን ሽኩቻ በየቀኑ ዜጎች እየተገደሉ ነው። በሀገር ውስጥ ተፈናቃዩች ቁጥርም ኢትዮጵያ በዓለም ግንባር ቀደም ሆናለች። ላለፉት 28 ዓመታት በሰብአዊ መብት ጥሰት እጆቻቸው በደም ከተነከረው የአገዛዙ ሸሪክ ድርጅቶችና ባለስልጣናት ውስጥ የትግራይ ወያኔንና እነስብሃት ነጋን በኦሮሞዎቹ ኦዴፓና ዐብይ አህመድ በመተካት እውነተኛ ለውጥ በኢትዮጵያ ማምጣት እንደማይቻል እየታዬ ነው። ሀገሪቱን ከእርስ በርስ መጠፋፋት ለማዳን፣ የፖለቲካ ድርጅቶችን ጨምሮ ሁሉም በሀገራችን ያገባናል የሚሉ አካላት የሚሳተፉበት ብሄራዊ ውይይትና በምክክር የሚያቋቁሙት የሽግግር መንግሥት ነው መፍትሄው።

ሁሉም የፖለቲካ እስረኞች ይፈቱ!
ዘረኝነትና የአገዛዙ ወንጀል ይወገድ !!