የድል አጥቢያ አርበኞች እና የተስፈኞች ባዶ ጩኸት

ከባላንገብ ሚካኤል  – ወያኔ ወደ ስልጣን መንበር ከመምጣቱ በፊትም ሆነ መንግስት ሆንኩ ካለበት ጊዜ ጀምሮ በየደረጃዉ ተቆጥሮ የማያልቅ ክህደት እና ወንጀል የፈፀመ ክሃዲ ቡድን መሆኑ ሃቅ ነው። የዚህ ቡድን ሰለባ ከሆኑት ቡድኖች እና ግለሰቦች በየመድረኩ ስንሰማዉ የቆየነዉ ሃቅም ይህን ተዘርዝሮ የማያልቀውን የወያኔን ወንጀል ነው። በወያኔ የተፈፀመውን ወይንም የሚፈፀመውን በደል በዝርዝር መረዳቱ እና ማስረዳቱ ከመፍትፌ ፍለጋዉ ሂደት ውስጥ አንዱ መሆኑም ሃቅ ነው። ዋናው እና ዋናው ቁምነገር ግን የጠላትን ክፋት እና ደካማ ጎን በሚገባ ተገንዝቦ ትግልን ማፋፋም እና ጠላትን በሚገባው ቋንቋ ማነጋገር መቻልን ይጠይቃል። ነጋ ጠባ የወያኔን ክፋት እና መጥፎነት ማነብነቡ መሳደቡ እና መራገሙ ብቻውን ፋይዳ የለውም። በተመሳሳይ መልኩም በፅናት እና በእውነት እየታገሉ ባሉት ድርጅቶች ላይ ማሟረት እና አሉታዊ ዘመቻ ላይ መሳተፉ ሰህተት ብቻ ሳይሆን ወንጀልም ነው:: በእንደዚህ አይነት የተዛባ አካሄድ እና የወሬ ናዳ ከሚገባዉ በላይ ማጠንጠኑ ስህተት ብቻ ሳይሆን ወሬው መሬት ላይ በሚደረግ እንቅስቃሴ ካልተደገፈ ለትግሉ እንቅፋትም ጭምር ነዉ። አሁን ላይ ታዲያ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ ተደራጅተው በፅናት በሚታገሉ ድርጅቶች ላይ አላግባብ የሚጮሁ ወፍ ዘራሺ ባተሌወች እዚህም እዛም ብቅ ብቅ ማለታቸው ሳያስደምመን አልቀረም። ትግሉ የገሞራ እና የወያኔ ውድቀት የተቃረበ ሲመስላቸው ከየመሸጉበት ጎዳቸው ብቅ ብለው ትግል እና ታጋይ ከኞ በላይ ላሳር የሚሉ የድል አጥቢያ አርበኞች እና ምትሃታዊ ተስፈኞች ተደራጅተዉ በፅናት እየታገሉ ባሉ ድርጅቶች ላይ መዝመታቸው ለምን ይሆን የሚለው ጥያቄ በአግባቡ መታየት አለበት:: የሚያሳዝን ቢሆንም ትግላችን ከወያኔ ጋር ብቻ ሳይሆን በተቃዋሚ ጎራ ነን እያሉ በተጨባጭ ለትግሉ መሰናክል ከሆኑት እና ከሚሆኑት ጭምር ነውና::

የነኝህ ነጭ ለባሾች ባዶ ጫጫታ ምንም ለዉጥ ባያመጣም አሁን ላይ ለምን ብሎ መጠየቁ ግን አግባብነት ይኖረዋል። ለዓብነት ብንወስድ የወያኔ ባለሞሎች አሁን በኢትዮጵያ ያለዉን ህዝባዊ እንቅስቃሴ ከኢትዮጵያ ህዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢህአፓ) ጋር አገናኝተዉ ማዉራት ከጀመሩ በሆላ በኢህአፓ ላይ አይናቸዉ የቀላ እና ምላሳቸዉን የነከሱ የተወሰኑ ተስፈኞች መስተዋላቸዉ አልቀረም። ኢትዮጵያን እና ኢትዮጵያዊነትን መሰረት ያደረገ ትግል እየገፋ እና እየተጠናከረ በመጣ ቍጥር ብርክ የሚይዛቸው ባንዳወች እና ምንደኞች ሁሉ የሚፈሩት ኢህአፓን መሆኑ በተደጋጋሚ የታየ እውነት ሰለሆነ:: በእርግጥም እንደትናንቱ ሁሉ ጠላትን በሚገባው ቋንቋ ለማናገር የሚያስችል ብቃት ያለው ይኅው ድርጅት መሆኑን ስለሚረዱ ተስፈኞች ከወዲሁ መዝመታቸው የሚጠበቅ ነው:: ጒድ ሳይሰማ መስከረም አይጠባም እንዲሉ አሁን አሁን ታዲያ ኢህአፓን በጀግንነት ማነስም የሚከሱም የሳይበሩ ዓለም ወታደሮች ተፈጥረዋል።

ሳይልኳቼው አቤት ሳይጠሯቼው ወዴት የሚሉት የወያኔ ቅጥረኞች ሁሉ በዚኅ ድርጅት ላይ መነሳታችው ባይገርመንም ትናንት ከኛ ናቼው ስንል ዛሬ ሰልፋቼው ከወያኔ ጋር አድርገው በአገኜናቼው ቅሌታሞች ጉዳይ ላይ ግን መገረማችን አልቀረም።  ሲጀመር ኢሕአፓ የጀግንነት ተምሳሌት እንጅ የወረቀት ነብር አልነበረም አይደለምም። ተስፈኞች ጫፍ ይዘዉ ሁሉን እናዉቃለን ስለሚሉ ብዙወቹ የኢህአፓን ታሪክ ያላነበቡ ወይንም የማያነቡ ናችው:: ከዛም አልፎ ከዚህ በፊት ለፈፀሙት ወንጀል ንስሃ በመግባት ፋንታ የኢህአፓ አለመኖርን እንደ ስርየት የሚቆጥሩት ታክለውበታል። ችግራቸዉ የግንዛቤ ማነስ ወይንም ታሪካዊ ባይሆን ኖሮ የኢሕአፓ አባላቶች በጀግንነታቸዉ የሚታሙ እንዳይደሉ ይረዱ ነበር። ይኸን ሃቅ አዉሬዉ መንግስቱ አንኳን አልካደዉም። ሲቀጥል አዎ በኢትዮጵያ ሁሉም የሃገሪቱ ዜጎች የማዕከላዊ መንግስቱ እና የሃገሪቱ ሃብት ተጠቃሚ አልነበሩም አሁንም አይደሉም። በመሆኑም ለሠብዓዊ መብት መከበር እራሱን አሳልፎ የሠጠዉ ኢህአፓ ለሁሉም ዜጎች የመብት ጥያቄወች ታግሎል እየታገለም ነዉ።  ኢህአፓ የነበሩት ፓለቲካዊ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ችግሮች የብሄረሠብ መብትን ጨምሮ ፍትሃዊ መፍትሄ እንዲያገኙ ታገለ እንጅ አልፈበረካቸዉም። ለዓብነት የሜጫ ቱሉማ ስብስብ:የኦጋዴን አንዳንድ እንቅስቃሴወች እና ከፌዴሬሺኑ መፍረስ በሆላ ነፍጥ ያነሱት ጀብሃወች ከኢህአፓ በፊት የነበሩ ናቸዉ።

ሌላው የሚገርመዉ ክስ ኢህአፓ ያደረገዉን የመብት ይከበር ተጋድሎ ከወያኔዉ አንቀፅ 39 ጋር ለማዛመድ የሚሄዱበት አራባ እና ቆቦ መንገድ ነዉ። ኢህአፓ ኤርትራን እንደ ሃገር ቢቀበል እና በመገነጣጠል ቢያምን ኖሮ ከወያኔ እና ከሻዓቢያ ምን አጣላዉ? ኢሕአፓ በእኩልነት ላይ ለተመሠረተች አንድ ኢትዮጵያ ታግሎል እየታገለም ነዉ። ለመሆኑ ኢሕአፓ የኤርትራን ሃገርነት የማይቀበል ብቸኛ ኢትዮጵያዊ ድርጅት መሆኑን አምስተኞ ረድፎች ያዉቃሉ? ካላወቁ ለምን አይጠይቁም::ቸግሩ የማወቅ እና ለማወቅ ከመፈለግ ጋር ምንም ግንኙነት ስለሌለው ነው:: እሚገርመው ተመጣጣኝ መልስ ሲሰጥ ተነካን ብለው ማላዘናቸው ነው::

ሌላኛው የነኝህ ጉዶች ከስ ኢሀአፓ ከሌሎቹ ድርጅቶች ጋር አልሠራም ወይንም ለመስራት ፈቃደኛ አይደለም የሚለው ውሃ የማያነሳ ጩኅት ነው::ይኁኛው በአብላጫው ተገለባባጭ በሆኑ ግለሰቦች ይቀንቀን እንጅ ስለ ኢዲሃቅ እና ህብረት ብሎም ስለ ኢህአፓ ወሳኝ ሚና ሳያዉቁ ቀርተዉ የሚያነሱት አይደለም። ኢህአፓ በዉስጡ ተሰግስጎ የነበረዉን የአንጃ ቡድን አራግፎ በተጠናከረ መልኩ እየተንቀሳቀሰ አንደሆነ ጠላቶቹ እራሳቸዉ እየመሠከሩ ባሉበት በዚህ ወቅት ይኸ መሰረተ ቢስ ከሰ ለምን እንደሚቀነቀን ለሁሉም ግልጽ ነው። ኢህአፓ ተግባር እንጅ ዲስኩር እና ጉራ ስለማይነካካዉ በዕርግጥ የዕወቁልኝ ፌሺታ እና ሰበር ዜና አያቀርብም። የማንም ሃሳዊ ቡራኬም አያስፈልገዉም።

እነኝሁ ባዶወች ሃይማኖትን እና የኢህአፓን ትግል በምናብ ሲያፈራቅቁ ትንሺ አይሰቀጥጣቸውም። እሚገርመው  ከሳሾቹ እራሳቸው የረጅም ጊዜ የፈረንጅ ሃገር ኗሪ እና ሃራማቸውን የበሉ ሆነው ሳለ በምእራቡ ዓለም መንግስት እና ሃይማኖት የተለያየ ነዉ የሚለው ጸንሰ ሃሳብ በስሱ እንኮ የተረዳቸው አይደሉም:: የኢህአፓ ልጆች እማ ካህናትም ሃጅወችም ሌላም ሌላም ናቸዉ ነበሩም። ቤተክህነት የገዥዉን ጥቅም ጠባቂ ሳይሆን የሰማያዊ መንግስት አገልጋይ ትሁን ማለት ምንድነዉ ህፀፁ? ሰማይ አይታረስ ንጉስ አይከሰስ እና “ስዮመ እግዚዓብሄርን” መታገሉ ነዉ ጥፋቱ? እነ ሰዮመ እግዚአብሄር እኮ ናቸዉ ሞታችንም ደህንነታችንም በሃገራችን ላይ ነዉ ብለዉ ሳይሸሹ ወራሪዉን የጠላት ጦር ያርበደበዱትን ጀግኖቻችን እነ በላይ ዘለቀን የሠቀሎቸዉ። ለዛዉስ ስለሃይማኖት ያወራ እና የጠመጠመ ሁሉ ፃድቅ ነዉን? አባ ፓዉሎስም እኮ የቤተክርስቲያን ቁንጮ ነበሩ። እነርሱን አንቀበልም አናምንባቸዉም ብንል ሃይማኖት የሌለን ያደርገናል? የኢህአፓ ልጆችማ እንደ መድሃኒዓለም እነርሱ ሳይቸገሩ የችግረኞች መብት ይጠበቅ ብለዉ ላመኑበት ፀንተዉ ህይወታቸዉን የሰጡ ብፁዓን ናቸዉ። የድርጅታችን አላማ ያኔም ዛሬም ህዝባዊ ነዉ እና የወደቁ ጓዶችችን አርማ ይዘን ትግሉን እያስቀጠልነዉ ነዉ።

ይኸ ማለት ኢህአፓ የመላዕክታን ስብስብ ያልተሳሳተ እና የማይሳሳት ነዉ ማለት አይደለም። ስህተት ቢኖርስ እንኳ ከቅንነት ወይንም ከነበረዉ ተጨባጭ ሁናቴ በመነጨ አንጅ ባዶወች በሚደረደሩት ዝባዝንኬ ምክንያት አይደለም። ኢህአፓ የመጀመሪያዉ ሃገር በቀል ድርጅት መሆኑን ያጤኗል። ድርጅታችን በማያወላዳ መንገድ በእኩልነት ላይ ለተመሠረተች አንድ ኢትዮጵያ እና ለሁሉም ዜጎች መብት መከበር የሚታገል በመሆኑ ከልባችን እንወደዋለን። ይኸ የጓዶቻችን ፅናት እና ቁርጠኝነት ለባዶወች እና ለወሬ ቋቶች ብርክ ያሲዛል። በኢትዮጵያዊነታችን በሠንደቅ አላማችን እና ቢሆን ጥሩ ነዉ ብለን ባአመንበት ዓላማ መደራጀታችን ለምን ይንገበገባሉ? እንደ እነርሱ በደመቀበት መዝፈን አለብን? ደግነቱ ባዶወቹ እየተንጠባጠቡ በየፌርማታው እየወረዱ ነው። ለምሳሌ ወያኔ በቋንቋ እና ሃይማኖት ሊከፋፍለን የሞከረው ሳያንሰን በእድሜ ሊከፋፍለን የሞከረው ግብዝ የቺታ ጄኔሬሺን አቀንቃኝ ሊያጠምደው የሞከረው ቺታ እራሱን ነክሶት አሁን ላይ ብዙም አይሰማም:: ኦሮሞ ሆኖ ኦነግን የማይደግፍ ሰው አላውቅም ያለው ባዶ ቅልም እንዲሁ የጀግናው ጀጋማ ኬሎ እና የሌሎች ብዙ ስመጥር የኢትዮጵያ ጀግኖች ምንጭ የሆኑት የኦሮሞ ወንድም እና እህቶቻችን ኢትዮጵያዊነት የተዳፈነ እሳት መሆኑን ባህር ዳር ኬኛ ጎንደርም ኬኞ ብለው ካሳዮን ወዲህ በረዶ ሆኖ ቀዝቅዞል:: ልቦለድ እና እውነተኛ ታሪከ መለየት የማይችለው ብሎገር ነኝ ባይም መደበሪያችን ከሆነ ውሎ አድሮል ጅል አይሙት እንዲያጫውት አይደል እሚባለው::

ለማንኛውም የተስፈኞች አሰላለፍ ጅብ የማያዉቁት ሃገር ሄዶ እንደሚባለዉ አይነት ነው። ሠከን እንዲሉ እና አደብ እንዲገዙ እንዲሁም የወሬ ገቢያ ሲቀዘቅዝ ጭንቀታቸውን ስም በማጥፋት ለመሸፈን እንዳይሞክሩ ይመከራሉ። በኢህአፓ ላይ ያላቸው ጥላቻ ለበሺታ ይዳርጋቸው እንደሁ እንጅ ኢህአፓን አንድ ጋት አይገፋውም። ኢህአፓ በቃል ኪዳኑ ፀንቶ ኢትዮጵያን ወደ ሚገባት የክብር ቦታዋ ሊመልሳት እየታገለ ነዉ። ያቸንፋልም!!