ዳኛውማ ሁሌም የኢትዮጵያ ጭቁን ህዝብ ነው

ኢያሱ ዓለማየሁ (ኢሕአፓ) – በቅርቡ የመጀመሪያው አንጃ መሪ የነበረው የብርሃነ መስቀል ረዳ ባለቤት የነበረችው የታደለች ኃይለሚካኤል “ዳኛው ማነው” የሚል መጽሃፍ ታትሞ ኢትዮጵያ በገበያ ላይ ውሏል። ጥራዝ ነጥቁ የወያኔ ኮለኔል ኢሕአፓን ማጥቂያ አንድ መረጃ ሙሉ ያገኘ መስሎት መጽሃፉን እንዳነበበ ሰው እየጠቀሰ በድርጅታችን ላይ ሊዘምትም ሞክሯል። የጌታቸው ማሩ ተቆርቋሪ ነኝ ሊል እንደሚቃጣው ማለት ነው። መጽሃፉ የወጣ ሰሞንም መላኩ ተገኝ የሚባል የእሷ ብጤ እንዲሁ በድርጅታችን ላይ ዘለፋና የሀሰት ክሶችን በቃለ መጠይቅ ሲደረድር ተደምጧል። የማያውቁትን ለማደናገር፤ የሚያውቁትን በሀሰት ለመክሰሰ ለመወንጀል ዘመቻው ሳያቋርጥ በኢሕአፓ ላይ ቀጥሏል ማለት ይቻላል።


በበኩሌ የግለሰቦቹን ስም ለማንሳት ቅንጣትም ፍላጎት ሳይኖረኝ ዓመታት አልፈዋል። ሁለቱም ለወያኔ ካደሩ ጊዜ ጀምሮ ለእኔ ሞተዋል። ገጣሚ አሊ ሁሴን አንጃዎችን ሟቾቹ የሚለውን እቀበላለሁና። ታደለች ከእሥር ወጥታ የወያኔ ሚኒስቴርና አምባሳደር ከሆነች ጀምሮ፤ ዛሬ ስላለፈው አቅዋሙ መተንፈስ ማይሻው ሰውዬ ደግሞ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ወያኔን ደግፎ፣ ኢሕአፓን አውግዞ፤ ከዚያም በሲአዬ ቅጥረኛው በአብዱል አባ ቦራ በዩኒሴፍና ቀጥሎም ፓኖስ በተባለ የአሜሪካ ግብረ ሰናይ ድርጅት ተቀጥሮ የወያኔ የወጣለት ደጋፊ ሆኖ አዲስ አበባ ከገባና ኢህአዴግ ከወደቀ፣ ኢትዮጵያ ትፈርሳለች ብሎ ራሱን ካዋረደ ጊዜ ጀምሮ ለእኔ ሞቷል። በዚህ ግድ ሆኖ ስማቸውን ሳነሳ እየቀፈፈኝ ነው። በአጭሩ፤ ዓይነታ ወያኔ፤ ለወደል ዘረኞች የተጎነበሰ ማንም ቢሆን ማን ኢሕአፓን ሊተች ቅንጣትም የሞራል ብቃት የለውምና ጉዳዩ በዚህ ሊያልቅ የሚገባው ነው ማለቱም ይቻላል።

ታዲያ ለምን ምላሽ አስፈለጋቸው? የተሰዉ የተለዩንና በህይወት የሌሉ ጓዶችን በሀሰት እያነሱ ስላወገዙና በሥልጣን ያለ የመሰለው ኮለኔልም ቅጥፈታቸውን ይዞ ጸረ ኢሕአፓ ዘመቻውን በማጧጧፉ በዝምታ የማይታለፍ ሆኖ በመገኝታቸው ነው። ይብላኝና ለቀባጣሪዎቹ አሁንም በህይወት ያለሁ ስለሆነ የሰማዕት ጓዶችን ክቡር ስምና የድርጅቱን ሀቀኛ ታሪክ መከላከልም ግዴታዬ ነው በሚልም ነው። እንደ ዘመኑ አልባሌ ጋዜጠኞችና ቃለ መጠይቅ አቅራቢዎች እርስዎን በመጀመሪያ ማን ልበል በሚል ዘር ቁጠርልን ሽፍንፍን ጥያቄ ገብቼ መልስ ልሰጥ ብችልም ስለነሱ አልሞክረውም። ኢሕአፓ ነበርኩ፤ ነኝና ዘር ቆጠራ መቸም አይሆንልኝም እንጂ ሟቾቹን በሚገባ አውቃቸዋለሁ። የእሷም የፍቅር ትረካዋ የማነበው መጽሃፍ ሆኖ ከቶም ባልተገኘ– ኢሕአፓን ባትነክካ ኖሮ፤ ወርቅ ጓዶችን ስም ልታጎድፍ ባትጥር ኖሮ። የሰውየውን መጻፍም አለማንበብ ብቻ ሳይሆን የሞቱ ሰዎችን ቃለ መጠይቅ/ድምጽ ላለመስማት የወሰንኩት ገና ሲሞቱ፤ ወያኔ ሲሆኑ ነው። እንደ ጥላሁን ሆድ ይፍጀው ያልኩት ብዙ ነገር እንዳለ እነሱም ይረዱታል ብየ እገምታለሁ። ለነገሩ ውርቹ የጠና ባንዳና እንኩቶ አንጃ ከእኔ ምላሽ አያሻውም። ወደሚቀጥለው ከመግባቴ በፊት አንድ ሳላነነው የማላልፈው ነጥብ በኢሕአፓ ላይ መጽሃፍ ብለው ሚሞነጫጭሩት አብዛኞቹ ኢሕአፓን ዛሬ ሊተቹ ሲነሱ ድርጅቱን ከተለዩ ግን ቢያንስ ሰላሳ አርባ አመት እንዳለፋቸው ነው። አመራር ብለን ከሰጠናቸው ስም ውጪ በዕውን መሪዎቹን እንኳን አያውቁም።

ወደ ዋናው ትችት ከመግባቴ በፊት አንዳንድ – ዛሬ ቡራ ከረዩ፤ የባጥ የቆጡን መቀባጠርና ጥራዝ ነጠቅነት ሰፍኗልና– ጥያቄዎችን ሀቅን መሠረት አድርጌ ለማቅረብ ልሞክር። የድርጅት መሥራች፤ የሠራዊት መሥራች የሚባሉ ፈልተዋል።


በእርግጥ ኢሕአፓን በተመለከተ እነማን ናቸው በሀቅ መሥራቾች ሊባሉ የሚችሉት? ተመልምለው በጉባኤው የተገኙት? ከመጀመሪያው አመራር የተመረጡት? ከመጀመሪያው አደራጅና ቆርቋሪ የነበሩት? በዚህ መስክ ብዙዎች በርካታ ውሸት ነዝተዋል። ማረም የእኔ ግዴታዪ ነው – ከመጀመሪያው እስካሁን በኢሕአፓነት አለሁና። በበኩሌ ለጥያቄው ብዙ ክብደት የምሰጠው አልነበርኩም– ከታሪክ አጋጣሚና አቅዋም ጋር የተያያዘ ነውና። የዛሬ የአመራር አባሎች ለምን በምስረታው አልነበራችሁም ብሎ ሊተች የሚነሳ ጅል ብቻ ነው። በኢሕአፓ መሥራች ጉባኤ በስህተት ተገኝተው ወዲያውኑ ወደመጡበት ሲመለሱ የከዱን አሉ። በጉባኤው ቢገኙም ለአመራር ቦታ ብቃት የላቸውም ተብለው ያልተመደቡም ነበሩ – የምንተቸውን ግለሰብ ጨምሮ።

የአንጃው ባለቤት በመጽሃፏ ባሏን ሁሉን አድራጊና ፈጣሪ አድርጋዋለችና የአይሮጵላን ጠለፋውንም ቢሆን እሱ የጠነሰሠው አለመሆኑን መጥቀስ እፈልጋለሁ። በወቅቱ የተማሪው እንቅስቃሴ ካለው ሚናና አቅም ውጪ ሁኔታው በመለወጥ ላይ ነውና የፖለቲካ ድርጅት መመስረት አለበት በሚል ተራማጅ ተማሪዎች መሰበሰብና መምከር ሲጀምሩ ባሏ ለፖሊስና ጸጥታ የተጋለጠ ስለነበር ቢያንስ እኔ በነበርኩባቸው የጥናት ስብሰባዎች ላይ አላየሁትም። ከዚህ በተያያዘ በተማሪዎች ማህበር የአድማ ኮሚቴ በምስጢር የሚሰሩ ሲመለመሉ ብርሃን መስቀልና አብዱል መጂድ ሁሴን ቀድመው የሚያዙ ስለነበሩ ያድማ ኮሚቴ አባሎችንም አያውቁም ነበር። የጠለፋውን ዕቅድ የወሰነውና የተስማማንበት ብንያም፤ ገዛኸኝ፤ እኔና አማኑኢል የተባለና ሳይቆይ የባከነ ተማሪ ነን። በእኔና ብንያም ቤት እየተፈራረቅን የመከርንበት ሲሆን ኃይለ የሱስን ብንያም ጠቁሞ ሲያመጣው አብዲሳን ደግሞ እሱ ጠቁሞ አምጥቶታል። የአጼው አገዛዝ በተማሪዎች ላይ ቁርጥ እርምጃ ሊወስድ ወስኗል የተባለውን ስንሰማ ደግሞ ብርሃነ መስቀል ቢለቀቅ አይበረክትምና አብሮ ከእኛ ጋር መውጣት አለበት፤ ይጠቅመናልም እሱ ብለን ሲፈታ አናግረነው ስለተስማማ አብሮን በጠለፋው ላይ ተሳትፏል። ለነገሩ ምግብ በመስራት ሆነ የአማርኛ ታይፕ ጸሃፊ በመሆንም በከፍተኛው ረድቶናል። ማደራጀት የሚለውን ስራ በሀገር ቤት ጸጋዬ ገብረ መድህን፤ ዋለልኝ፤ ጸሎተ ሕዝቅያስ እንዲቀጥሉት በሚልም እነሱም በዚሁ ተሰማርተዋል። መስፍን ሐብቱ ወደ በአልጄሪያ መጥቶ እዚያ ካለነው ተመካክሮ የማደራጅቱን ስራ አሜሪካ ሊሰራ ተወስኖ ወደዚያው ዘልቋል። የጊዜያዊ አደራጅ ኮሚቴ የተመሰረተው በአልጄርያ በነበሩት ጓዶች ሲሆን ወደ አውሮጳ በብራዚል የሀሰት ፓስፖርት ሄዶ የዛሬውን መስራች ነኝ ባይ የመለመለው (ከአሉታዊ ግምገማ ጋር) አሁንም በህይወት ያለው ገዛኸኝ ነው። በተመሳሳይ መንገድ ብንያም አዳነ በሞስኮ እህቱ ስለነበረች እሷ ጋ ሊያርፍና እዚያ የነበሩትን በድርጅት ጥረት አንዲይዝ ተልኮ እህቱን ንግሥትንም ባሏንም፤ ክፍሉ ታደሰንም ሊመለምል ችሏል። በምስረታ ጉባኤው የተገኘው ደስታ ታደሰ ሳይውል ሳያድር የከዳንና ከሷም ጋር በመኢሶን የተጠቃለለ ሲሆን ዓለሙ አበበም ወዲያውኑ ወደ አዲስ አበባ ገብቶ ከመኢሶንና ከደርግ ተቃቅፏል። ክፍሉ ታደሰም ጊዜውን ጠብቆ የሠራዊትና ድርጅት በታኝ ሚና ይዞ ኢሕአፓን በከፍተኛ ደረጃ ጎድቷል።

በድርጅት ምስረታ ሂደት እንዴትስ ተሰራ? በአልጀርስ የነበርነው የሰራነው በጋራ ሀላፊነት በስብሰባ እየወስን ነበር። መኢሶኖች ሁሉን ሰሪ ብርሃነ መስቀል ነው የሚለውን አምነው ብዙ ተሳስተው ሰው አሳስተዋል። በአልጄሪያ የወጣው
የጥላሁን ታከለ ጽሁፍ (በብሄር ጥያቄ ላይ) የጋራ ስራ ውጤት ሲሆን ብርሃነ መስቀል በራሱ ለብቻውም አልጻፈውም፤ ጥላሁን ታከለ የሚለውንም የሽፋን ስምም ብቻውን አላወጣ ወይም ሁሉም ተስማምቶበት ሳይሆን በብዙሃን ድምጽ ድጋፍ ነው። የምንተቸው ሰው ባልተሰናበተበት ምክንያት ለቀቅኩ ሲል ቢቀጥፍም (የከተማው ተኩስ ዋና ደጋፊ ነበርና) የጥላሁን ታከለን ጽሁፍ ለምሳሌ ያኔም ስታሊን ወዘተ ማለቱም ከግራ ሆኖ የማይጥመው ገዛኸኝ እንዳለ አልደግፍም አልቀበልም፤ ስታሊኒስት አማራጭም ነው ብሎ ከመጀመሪያው በግልጽ ተቃውሟል። በምስረታው ሂደት ዋና ሚና የነበረው ሌላው ዘሩ ክህሸን ሲሆን ከኢትዮጵያ ለትምህርት ብሎ ወደ አሜሪካ ሲጓዝ በአልጄሪያ አልፎ ተማክረን ስራውንም ለይተን ተስማምተንበት ወደዚያ መሄዱን ታደለች ስለማታውቅ የጻፈችው ባሏ – ከዘሩ ስለማይስማማ – የነገራትን በጭፍን ተቀብላ ነው። በዚህ ላይ ያኔ በአዲስ አበባ በተራማጅ ተማሪዎች አካባቢ የነበረውን ውዝግብና ችግር ማንሳቱ ተገቢ ይሆናል። ውዝግቡ የጀመረው በዩኒቨርስቲ አካባቢ ሲሆን በሀገር ውስጥ የማደራጀት ሥራ የተሰጣቸው እነ ጸጋዬ ታስሮ የነበረውን ዋለልኝን ለማስፈታት ጥረት ያደርጉ ነበርና ጥረቱን የሚያደናቅፍ ሰላማዊ ሰልፍ እንዳይደረግ በመቃወማቸው ነበር። የድርጅት ምስረታ ጥረት መጀመሩን የሚያውቁት እነ ዘሩና ጸጋዬ የተሰጣቸው መመሪያ ይፋ ፖለቲካ እንቅስቃሴን ትተው/ርቀው ስልችቷቸው ስራ ፍለጋ እንደገቡ እንዲያስመስሉና የህቡዕ ማደራጀቱን እንዲቀጥሉ ነበር። ስራ ሊይዙ ሲፈልጉ በየመስሪያ ቤቱ በጸጥታው ትዕዛዝ አንቀጥራችሁም ስለታባሉ የጊዜውን የጸጥታ ሀላፊ የሆኑ ሰዎች እንዲያናግሩት አድርገናቸው መጥተው ያናግሩኝ ባለው መሠረት ጸጋዬና ዘሩ ሄደው አርፈን እንስራበት ብለው አናግረውት የጸጋዬ ትዝ ባይለኝም ዘሩ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ተቀጥሯል። በሰፈር ልጅነት እሱን ሳይሆን እህት ወንድሞቹን አውቅ የነበረው ጌታቸው ማሩ እኛ ሀገር ልንለቅ ስንል ወደ ፖለቲካ የገባ ስለነበርና እነሱም በቀና መንፈስ ለመደራጀት እየሞከሩ ስለነበር የነዘሩና ጸጋዬ ስራ ፍለጋና ትምህርት እንማር አልዋጥላቸው ብሎ ተቀየሙና በመሃላቸውም ልዩነቱ ሰፋ። ተራማጆች ትምህርት ሲጨርሱ አድሃሪ እና ግለኛ ቢሮክራቶች መሆናቸው የተለመደ ነበርና የሚፈረድባቸውም አልነበሩም። ሁኔታው ከሮ ወደኋላም ኢሕአፓ ሊታወጅ ሲል ሳሙኤል ዓለማየሁ ካሜሪካ መልስ አስታራቂ ሆኖ አብዮትና (የነጌታቸው ቡድን) ዴሞክራሲያ/ኢሕአድ ቡድን ተዋህደው ኢሕአፓ ብለው ይፋ ሊሆኑ ችሏል። እኔና ብርሃነመስቀል ከስራ አስኪያጅ ኮሚቴው ስንነሳ ጌታቸው ማሩና ሌሎች በስራ አስኪያጅ ኮሚቴውም በማዕከላዊ ኮሚቴም ገብተዋል። ዘረኛ ኮለኔል ሶስት ትግሬውች የፖለት ቢሮ ሀላፊ ሆኑ በሚል ሊዘቅጥ ሲሞክር ራሱን አዋረደ እንጂ ብርሃነመስቀል የሥራ አስኪያጁ የአመራር አባል ኮሚቴ ውስጥ አልነበረም። ኮለኔሉ የድርጅቱ ሊቀመንበር ብሎ አቅፎት የታየውም የዘንድሮ አንጃ መሪ እንኳን ሊቀመንበር ከማዕከላዊ ኮሚቴ ደጃፍ አካባቢም አልነበረም።

ዘሩ ወደ አሜሪካ እንዲወጣ የተባለውም ከቆየ አይበረክትም በሚል ሲሆን በአልጄሪያ ቆይታው ስናናግረው የተወሰነው በአሜሪካ ስለላ ድርጅቶች ዓይን የገባ ስለሆነ እነ መስፍን ሀብቱንም እንዳያስበላብን ከፖለቲካ የራቀ ጆሊ ጃክ ይባል የነበረው ዓይነት የሆነ መስሎ እንዲታይ ነበር። ይህንንም ማስጠንቅቂያና ሀሳብ የሰጠው “እኔ አውቀዋለሁ እንደልቡ ነው” ያለው ራሱ ብርሃነ ስለነበር ሴትየዋ የጻፈችው አስገርሞኛል። ዘሩ ከድርጅት እስኪሰናበት ድረስ ጸንቶ የሰራ ሲሆን ካንሰሩ ሊገድለው ሲልም አምስተርዳም ደውዬለት ሀገር ገብተህ ዘመድ አዝማድ ተሰናበት ስለው ምላሹ ቁጣና እነ ጸጋዬ ደብተራውን ወያኔ ፈታቸው እንዴ የሚል ብስጭት ነበር። አንዳንዶች አሁን አሜሪካ ያለ ፊልም አንሺው ኢትዮጵያዊ አዛውንት ዘሩን ቃለ መጠያቅ አቅርቦለት እንዲህ እንዲያ አለው ቢሉም ጉዳዬ ካለመሆኑ በላይ ለሀቅ ከቆመ ፊልም አንሺውም ዘሩ የተናገረውን ቅጂ አትሞ ቢያወጣና ሀቁ ቢታወቅ ደግ ይሆናል። ተሰናብቶ ከሄደ በኋላ ብንራራቅም ገነት ግርማ በወያኔ ስትያዝ ደውሎልኝ ስለ እሷም ሁኔታም ሆነ ስለመስራች ነን ባዮች የወያኔ ወዳጆች በዝርዝር ተነጋግረናል፤ ውይይት የጀመርነውና የቀጠልነውም ከዚህ ወዲያ ነው። ወደዚህ ሁሉ ዝርዝር የገባሁት በዘሩ ላይ ተነሱ የተባሉ በዚህም በዚያም ዘመቻ ስለከፈቱበት ነው። በማያውቀው ቀባጣሪ መሆን ልምዱ የሆነው ኮለኔል ለምሳሌ ጌታቸው ማሩን ያስገደለው ዘሩ ነው ብሎ ወጥ ሲረግጥ በዝምታ ማለፍ የሚቻል አይደለም። ለነገሩ ጌታቸው ማሩ በቅድሚያ አንጃ በሞት ይቀጣል የሚል ህግ ባለው ድርጅት ውስጥ ባልገባም ነበር – ለጥቆም ፖሊት ቢሮ አባል ስለነበር ይህ ህጋችን ይሰረዝ ባለም ብሎ ቀድሞ በተቃወመ ነበር እንደሌሎች። አልሆነም። ግደሉት ብሎ ኢሕአፓ እንደ ድርጅት አልወሰነም እንጂ ቢሆንም፣ በህግ መሠረት እስከሆነ ድረስ ማንም ሊከሰው መሠረት አይኖረውም። ኮለኔሉ ሚቀጥፈው ግን ጌታቸው ማሩ የተገደለው በዘሩ ነው በማለት ነው። መገደሉን ዘሩም፤ ጸጋዬም እኔም ተጽፎልን የተነገረን አሲምባ ሳለን ነው። በቦታው – ቢያንስ በከተማ — የነበረውና አሁንም የዛሬውን አንጃና ኮለኔሉን ደግፎ አዲስ አበባ ሚመላለሰውን ያውቃል ተብሎም የተጠቆመውን ግለሰብ ቢጠይቁ የተሻለ ይሆናል– ያልወሰነውን ሰው ወሰነ ብሎ ክመክሰስ። ለነገሩማ የድርጅት አባሎችን አጠፉ ብሎ በሚያውቁትና በተቀበሉት ህግ መሠረት ድርጅቱ ቢቀጣ ከዘመዶቻቸው ውጪ ስንቱን ሀገር ወዳድ የበሉት ዘረኞች ምን አገባቸው? ለአንጃ ተቆርቋሪ መስሎ የአሜሪካው ሹም ኮለኔል ሚብከነከነው ለፖለቲካ ፍጆታ ነው። ብዙዎቹ ከሳሾች – ሀፍረተ ቢስ ደርጎች፤ ባንዳዎችና መሰል አንጃዎች– ሰውየውንም ሚከሱትንም ግለሰብ ሆነ ድርጅቱን በሚገባ አያውቁም።

ሴትየዋ በአካል ሆነ በሌላ ዘሩን አታውቀውም – ጭራሽ – እሷም አልካደችም። ዶክተር ተስፋዬ ደበሳይን ሆነ ሌሎችን ያታለለ ያደናገረ ግን እሱ ነው ስትል ግግም ብላለች። ለሟቹ ባሏ አለኝ ነበረኝ ባለችው ፍቅር መሠረት እሷ ጠላቶች ያለቻቸውን ሁሉ ብትጠላ መብቷ ነው። ደርግ ወድቆ ከእስር እንደወጣች ሳይገዳት መወየን በመረጠችበትም ጊዜ ለነታምራት ላይኔ አንድ ተለጣፊ መጽሄት ክሊኩ ይሰቀል ብላ ጸያፍ ጥሪ ማቅረቧን አልረሳንም። በጥፋት አጃቢዋ ደግም የሩቁን ከቅርብ ስናየው ብሎ ስም ጠርቶም ያወገዘን ከመሆኑ በላይ ወያኔ የሚለውን ክቡር ስም የኢሕአፓ ክሊክ በሕዝብ አስጠላው ብሎ ከሶ የብዙዎችን ተቃውሞ ያተረፈ ነበር። በቅርቡም ዘሩ “ማኒፑሌተር”(ሰውን አደናጋሪ ሸዋጅ) ነበር ሲል ተደምጧል – – እሱም ቢሆን እኔ እስከማውቀው ዘሩን በቅርቡ አያውቀውም። ተስፋዬ ደበሳይን የመሰለ የበሰለ ምሁር መናቅ ነው እንጂ ተስፋዬን ዘሩ ሆነ ማንም ባላመነበት የዘወረው ሰው አልነበረም። ያስተማራትን፤ ያነቃትን ተስፋዬን እሷም ከድታዋለች በአሳዛኝ!

እሷም ሆነ አጃቢዋም ሰውዬ ለምን ከድርጅቱ እንደተለዩ ሲያወሱ ጭራሽ ቅጥፈትን ማድረጋቸው አሳዛኝ ሆኖ አግኝቼዋለሁ። እውነት አይደለምና። በሚያስገርም ሁኔታ ሰውየው በከተማው ትግል ሁኔታ ልዩነት ኖሮት እንደሄደ ሊያስመስል ሲሞክር እሷም ደግሞ ልዩነቱ በከተማ ለምን ደርግና አጋሮቹ ላይ ተተኮሰ በሚል ተቃውሞ ወደክፍፍል እንዳመራ ልታሳምነንም ትሞክራለች። ቅጥፈት። ለእኔም ደብዳቤ ጽፎ መልስ እንዳላገኝም ትጠቅሳለች። እሱም በምን ተዓመር እንደሆነ ስለ ከተማው ውሳኔ ተጽፎለት ለእኔ ደብዳቤውን ልኮ ምን እንደደረሰ እንዳላወቀ ሊጠቅስ ሞክሯል። ለነገሩ ያኔም ቢሆን ተቃዋሞውን ባስታወቀኝ ነበር ግን ከሀገር ቤት ግንኙነት እሱን የማይመለክተው ስለሆነ ረስቶ ካልሆነ ለእሱ የጻፍለት አልነበረም። ከሆነም በክተማው የራስ መከላከል እርምጃ አልስማማም ማለት ይችል ነበር። ብሎም አያውቅም። በተጻራሪ ደግፎና የሰሜን አሜሪካ የነበሩ የያኔ ጓዶችን ተቃውሞ በአየለች ሽፋን ስም ሁለት በራሪ ወረቀቶችን (ፓማፍሌቶችን) አሳትሞ አውጥቷል። ምናለ ያኔ እንዲህ መስሎን እንዲህ ጽፈን ነበር ቢባል? በበኩሌ የራስ መከላከል እርምጀውን የደገፍኩ ስለነበር ዛሬም ቢሆን በበቂ አላደረግነውም – አሁንም ይደረግ ባይ ነኝ እንጂ – ምደብቀው ምንም የለኝም። እሷም እሱም ግን በገሃድ ይዋሻሉ። ብርሃነ መስቀልም ከመጀመሪያው ለከተማ አስፈላጊ ሊሆኑ ለሚችሉ አንዳንድ እርምጃዎች መዘጋጀት እንዳለብን ምንም ተቃውሞ አልነበረውም። ሜዳ ሊገቡ ካልቻሉት ስዩሜ ከበደ (ማታ ማየት ስለማይችል) ወይስ ዘርዓብሩክ (በውልደት ኤርትራዊ ስለሆነ ሻዕቢያ አላሳልፈውም ካለው) ማን የተሻለ ይሆናል በሚለው ምርጫም ላይ ስዩሜ ብሎ ከሌሎች ጋር ወሳኝ ነበርና በዚህ ላይ ምንም ያልተካፈለና ያላወቀ ድንግል አስመስለው ሊያቀርቡት ሚጥሩት ትክክል አይደለም። የሁሉም ተቃውሞ ዛሬ ውሎ አድሮ በከተማ ተኩስ ላይ ነው የሚሉት በቂ መረጃና ማጠየቂያ የለውም። በሚገባው እንበለው ካልን ውሸታቸውን ነው። መረጃውን እንቀጥልበት….