ድንጋጤ የወለደው ትካዜ፤ ፀፀት የሌለው ኑዛዜ

(በፍኖተ ዴሞክራሲ የኢትዮጵያ አንድነት ድምፅ ራዲዮ) – በቅርቡ በተካሄደው የወያኔ ማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ ላይ፤ ስዩም መስፈን የተሰኘ   የወያኔ ነባር አባል  ባደረገው ንግግር፤ የዘረኛው አገዛዝ አራማጆች፤ ምን ያኽል ሰማይ ምድሩ እንደተደፋባቸው በማያሻማ መልኩ ፤ እንደሚከተለው   ለመናገር ተገድዷል።

“ጓዶች፤ ከፊታችን የተጋረጠው ዐደጋ እጅግ በጣም አሳሳቢ ነው። ፀሐይ ሳትጠልቅብን፤ በሩጫ፤ ያውም በፈጣን  ሩጫ ደርስን ካልመከትነው፤ ቀጣይነታችን ያጠያይቃል።”  በማለት  ባልተለመደ ድፍረት  ዕቅጩን ለመናገር ድፍረቱን አግኝቷል። ንግግሩ ጭንቀትና ፍርሃት የወለደው ቢሆንም፤ ለተባባሪዎቹ የማስጠንቀቂያና የመለበሚያ ደወል እንዲሆን የታሰበ እንጅ፤ ስህተትን አምኖ፤ ተፀፅቶ ሀገሪቱ ለገጠሟት ሁለንተናዊ ችግሮች  መፍተሄ ለመፈለግ የከጀለ አልነበረም። ይሆናልም ተብሎ አይጠበቅም ነበር።

በኖኅ ዘመን፤ በጥፋት ውሃው የመጨረሻ  ሰዓት  እንደተቅዘበዙት  ሃጢያተኞች   “አስረሽ ምችው!”  በማለት ውሃው ከአንገታቸው በላይ እያጥለቀለቃቸው ሲሄድ፤ ለፀፀትና ለኑዛዜ እንኳን ጊዜ አላገኙም። ወዲያውኑ፤ በጥፋቱ ውሃ ጠፍተው ቀርተዋል። ወያኔን የሚያጥለቀለቀው የጥፋት ውሃ አንገቱ ላይ ደርሶ እየደፈቀው ቢገኝም፤ በጊዜው የኢትዮጵያን ሕዝብ ይቅርታ በመጠየቅ ምህረት ሊያገኝ አልፈለገም።  አሁንም፤ “ትግራይ ብቻ፤ ወይ ሞት!” ብሎ ደርቆ ቀርቷል።

ትግራይና ኢትዮጵያ፤ ድርና ማግ፤  የዦሮ- ጉትቻና  የአንገት ማትብ፤ አልፋና  ዖሜጋ፤  ቀዳማይና ድሃራይ፤ መሆናቸውን አልተረዱትም ወያኔዎቹ!  ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዝብ ይቅር ባይ ነው። የበደሉትን ይቅር ሲላቸው፤ ካሣ መካካሻ አይጠይቃቸውም።  እንኳንስ ለራሱን ወገኖች፤ ለውጭ ጠላቶቹንም ቢሆን፤  ምህረት ያደርግላቸዋል። ይኽንንም በአስራ ስምንት መቶ ሰማንያ ስምንት/ 1888 ዓም በአደዋ ላይ አመስክሯል። ያችን  ቅድስት ቦታ አደዋን ግን፤ ዛሬ፤ ከአደዋ መጥተናል የሚሉት ዎያኔዎቹ አርክሰዋታል።  ቢሆንም፤ የነገዋ አደዋ ፤ ነገ በኢትዮጵያ ልጆች ትቀደሳለች።
ትላንትም፤

“አደዋ ሥላሴን ጠላት አረከሰው፤
ገበየሁ በሞቴ ግባና ቀድሰው!” ተብሎ ነበር እኮ!

አደዋ ነገ በመላው ኢትዮጵያ ልጆቿ ተቀደሳለች። የቆየ ታሪካዊ ቦታዋ  ይታደሳል።  በዘመናዊቷ ኢትዮጵያ ታሪክ ተገቢውን ቦታ ታገኛለች።  የወያኔ ዘረኛ አገዛዝ ሲደመሰስ!

ወያኔዎቹ ለፀፀትና ለይቅርታ  አልተጨነቁም። የጥፋቱ ውሃ እያሳሳቀ ሲወስዳቸው፤ የኢትዮጵያን ሕዝብ ተንበርከከው ይቅርታ ለመለመን፤ ድፍረትና ዕውቀት አላገኙም። የሕዝቡን  ኃያልነትና  ይቅር ባይነት አልተገነዘቡትም።    መላው  የኢትዮጵያ ሕዝብ፤ ከመጥፋታቸው  በፊት  ሊያድናቸው   ይችል  ነበር፡፡ “ያደቆነ ሠይጣን ሳያቀስስ አይተውም” ሆኖባቸው፤ አሁንም ከጠባብ አመለካከትና ድርጊት ሊድኑ አልተቻላቸውም።

የስዩም መስፍን ንግግር ትኩረቱ፤ በትግራይ ሕዝብ ላይ ብቻ እንጅ፤  ቀሪውን የሀገራችንን ሕዝብ ችግር ሊመለከት አልቻለም።  የመላዋን ኢትዮጵያ ጉዳይ ከመጤፍ አልቆጠረውም። ይኽ መሆኑ ደግሞ አያስገርም። ምክንያቱም፤ ዱሮም ቢሆን፤ ስዩምና ጓደኞቹ አመጣጣቸው ለትግራይ ብቻ እንጅ፤ ለቀሪዋ ኢትዮጵያ፤ ጉዳያቸው ባለመሆኑ ነበር።

ስዩም መስፈን፤ ፀፀት አልቦ  ኑዛዜውን በመቀጠል፤ እንደሚከተለው፤ ይናገራል።

“ያ፤ ሠላም፤ ፍትህና ዴሞክራሲ ያመጡልኛል ብሎ አምኖ፤ ድሮ  ደም  ዕንባ አልቅሶ ልጆቹን የገበረው የትግራይ ሕዝብ፤ ከከዳነው ረዥም፤ በጣም ረዥም ጊዜ ሆኗል።   ድሮ የከዳነው ሕዝብ፤ ዛሬ ሁለት ጊዜ  እንደ ሞተ ሆኖ  ይሰመዋል።   ወዴት እንደሚሄድም ግራ ገብቶታል።   ያ የኛን ቅርስ ወርሶ ወደፊት ይኖራል ያልነው ወጣትም፤  እንዲሁ መሪ ድርጅቱን  ከድቶት ግራ ተጋብቶ ይኖራል።  ይቅርታ አድርግልን  ማለትኮ፤ ጭምትነት ነው።  ይቅርታ መጠየቅ ብልህነትና ለሥራ ዝግጁነትን  ያመለክታል።   ያ፤ ያስቀየምነውን ሕዝብ ተንበርክከን ይቅርታ መጠየቅ አለብን።  ጊዜ የለንም! ጓዶች፤  ፈጽሞ የምንዘናጋበት ጊዜ አይደለም!” እያለ የአደጋ ጥሪውን  ያስተላልፋል። የነፍስ አድን ማስጠንቀቂያ ዕሪታውን  ያስተጋባል።  ይማልላ።  የዕሣት  ዐደጋውን አስደንጋጭ ጥሩምባ  ይነፋል።

የስዩምና የጓደኞቹ ጭንቀት፤ መላዋ ኢትዮጵያ ምን ያኽል ዐደጋ እንደወደቀች መጨነቅ  ሳይሆን፤ እንዴትስ ሥልጣናቸውን  ማዳን እንዳለባቸውና፤ ከተቃጣባቸው ሕዝባዊ ቁጣ መከላከል የሚችሉትን የነፍስ አድን ዘዴ ከመፈለጉ ላይ ብቻ ነው።   “ሁሉም ጎዳናዎች  ወደ ሮማ ያመራሉ”  እንደ ሚባለው፤ የወያኔ መሪዎች ሁለንተናዊ ጥረትና  ጭንቀት ሁሉ፤ በመንገዳገድ ላይ የሚገኘውን ሥልጣናቸውን  ነፍስ እንዲዘራ  የሚቻለውን ሁሉ  ጥረትና ርብርቦሽ  ከማድረጉ ላይ ብቻ ነው።

ይኽንን ተግባራዊ ለማድረግ፤ መጀመሪያ የትግራይን ህዝብ ባዲስ ፕሮፓጋንዳ እየቀሰቀሱ ድጋፉን እንዳይከለክላቸው ማድረግ መሆኑን አምነውበታል። የትግራይን ወጣት ትውልድ ለመሸንገልም፤ “በድለንሃልና ይቅርታ አድርግልን! ረስተንሃልና አለመርሳታችንን ለማረጋገጥ እንድንችል ጊዜ ስጠን። እኛም፤ አንተ እንድትንሰራራ  እድል እንሰጥሃለን።  የጋራ ጠላት ተባብሮ ተንስቶባሃልና፤ ከመሪ ድርጅትህ  ጋር ወግነህ በመነሳት እራስክን አድን!   መሪ ድርጅትህ ወያኔ  ከጠፋ የቀን ጅብ ይበልሃል። ዙሪያውን በጠላት ተከብበሃል። ከዚህ የአጥፊህ ከበባ ለመዳን፤ ተነሳ!  በማለት፤ በአዲስ አደገኛና መርዘኛ  የጥላቻ ፕሮፓጋንዳ ቅስቀሳ፤ አዕምሮውን እየመረዙ፤  ልቡን እያላሸቁ፤  ከወገኑ  ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ተባብሮ እንዳይነሳባቸው  ለመከፋፈል የሚያደርጉት ዕኩይና አጥፊ ዘመቻ ነው። ለአለፉት 27 ዐመታት ሞከረው ያልተሳካላቸውንና ወደ ከርሰ መቀብሩ  እያቆለቆለ በመሄድ ላይ ያለውን  የነፈሰበትን ቅስቀሳ እንደገና ነፍስ ለመዝራት እየሞከሩ ነው።  ግን አይሳካም።

ይኽንን ለማለት የሚያስችል በቂ ምክንያት አለ።

1ኛ. ዛሬ የትግራይ ሕዝብ  ሁሉን ነገር በሚገባ ስለተረዳ፤  ለወያኔ ዕኩይ ፕሮፓጋንዳ ዦሮውን እንደማይሰጠው እያሳወቀ በመሄድ ላይ ነው።  ወገኑ ከሆነው ከሌላው ኢትዮጵያዊ  ወንድሙ ጋር አብሮ በሠላምና ጤና መኖር እንዳለበት ከሚያምንበት ደረጃ ደርሷል። ቀሪው የኢትዮጵያ ሕዝብ፤ ወያኔንና የትግራይን ሕዝብ ለይቶ በመገምገም፤ የራሱን ፍርድ  የመስጠት ዐቅምና ቁመና  ዕውቀትና ትኅትና እንዳለው ተገንዝቧል። በመሆኑም፤  ሕዝብ ትግራይ፤ ከእንግዲህ ወዲህ ፤ በወያኔ አፍራሽና ከፋፋይ ቅስቀሳ ለሁለተኛ ጊዜ አይታለልም።

2ኛ. ቀሪው የኢትዮጵያ ሕዝብም በበኩሉ፤ የሀገሩ ጠላት ወያኔ እንጅ የትግራይ ሕዝብ እንዳልሆነ አሳምሮ ያውቀዋል። በዚኽ ምክንያት፤ ከወድሙ ከትግራይ ሕዝብ ጋር አሁንም ቢሆን  አብሮ በሠላም ይኖራል።   ከታሪክም አኳያ  ሲገመገም፤ በተለያዩ ዘመናት የሀገራችን ጠላቶች ወረራ ሲያካሂዱ፤ ወረራውን ለመከላከል የመጀመሪያው ገፈታ ቀማሽ  ሆኖ የኖረው የትግራይ ህዝብ መሆኑን በሚገባ ያውቃል።  በዚኽም የተነሳ፤ የትግራይ ሕዝብ፤ ቢያገኝ ቢበለፅግ፤ ቢያድግ  ቢመነደግ፤ ሌላው ወገኑ ይደሰታል እንጅ  አይከፋውም። መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ፤ የሌላው  ወገኑ ዕድገትና ብልፅግና የራሱ ዕድገትና ብልፅግና መሆኑን ያምናል። ባጭሩ፤ ወያኔንና የትግራይን ሕዝብ ለይቶ በመገምገም፤ የራሱን ፍርድ የመስጠት ዕቅም፤ ዕውቀትና ትኅትና አለው።

3ኛ. የስዩም መስፍን የድረሱልን ፕሮፓጋንዳ ቅስቀሳ ፤ ከቁራ ጩኽት የዘለለ ፋይዳ እንደማያስገኝ የሀገራችን ተጨባጭና ነባራዊ ሁኔታዎች ያረጋግጣሉ። ዛሬ በሀገራችን ውስጥ፤ ከአፅናፍ እስከ አፅናፍ ሕዝባዊው አመፅ  እየተቀጣጠለና   የወያኔንም  አገዛዝ  እያርበተበተ መሄዱን እየተመለከተው፤ የትግራይ ሕዝብ፤ ወያኔና ሥርዓቱን በመደገፍ፤ የኢትዮጵያን ሕዝብ  ዐላማና ጥቅም  ተጻርሮ ይቆማል ማለት አጠራጠሪ ነው።  ምክንያቱም፤ ለትግራይ ሕዝብ ስትራተጂያዊ ወዳጁ፤ቀሪው የኢትዮጵያ ሕዝብ እንጅ፤ ነገ እንደ ጤዛ ረግፎ ከሚከስመው ከወያኔ  ጋር እንዳልሆነ  ይረዳዋል፡፡

4ኛ. የትግራይ ወጣት ትውልድና ወላጆቹ ፤ በወያኔ አፍራሽና ከፋፋይ ቅስቀሳ  ዳግመኛ እንደማይሳሳቱና  ለሌላ ዙር ጥፋት እንደማይዳረጉ  መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከልቡ ይተማመናል። ያ እንዳይመጣም በአንክሮ ይፀልያል።  ከእንግዲህ ወዲህ፤ የትግራይ ወጣት፤ ለእርሱ ለራሱ አውዳሚ እንጅ፤ አትራፊ በማይሆን  የእርስ በእርስ እልቂትና ፍጅት ሊማገድ የሚፈልግ አይመስለንም። ከብልህ ሕዝብ  አብራክ የወጣ ትውልድ፤ ለዳግመኛ ጥፋት ራሱን እንዲያዘጋጅ አይጠበቅበትም።

5ኛ.  የነስዩም መስፍን  ፕሮፕጋንዳ፤  ተከድኖ ይብሰል ሊባለልት  የሚገባው ቅስቀሳ  ብቻ ሳይሆን፤ የሁለት  ባህርያት አመልካች እንደሆነ መረዳት ያስፍልጋል። እነርሱም:

ሀ. ወያኔዎች   የተደናገጡ መሆናቸውን የሚያሳይ ፍንጭ መስሎ  ሊታይ ቢችልም፤ አዘናጊና  እንዝህላልነትን   ጋባዥ ስለሚሆን መጠንቀቅ  ይገባል።  “ወያኔ አንድ ሐሙስ  ቀርቷታል”   በማለት፤ የህዝቡን አመፅ ቱማታና ግለት ወደ ሚያቀዘቅዝ ቸልተኝነት  እንዳያስገባ  ጥንቃቄ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑ ተገቢ ነው። ወያኔ፤ ወስጡ ጃርት የበላው ዱባ መስሎ ቢታይም፤ ቁስሉን እያላሰ የማገገም ልምድ ስለአለው፤  ትንሽ የመተንፈሻ ጭላንጭል የማየት ዕድል ካጋጠመው፤ ሊንሰራራ ይችል ይሆናል ብሎ መገመት፤ ተገቢም፤ በልኅነት፤ ትክክልም ነው።

ለ. የሕዝቡ አመፅ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያተጋጋለ መምጣቱን  የተገነዘበው ወያኔ፤ በዕርግጥም የመደናገጥ ባኅርይ እያሳየ እንደሆነ አያከረክርም።  ማያዥ መጨበጫና ተቅበዝባዥነት  /Desparet/     ደረጃ  በመድረሱ ቆዳውን ለማትረፍ ብሄራዊ ዕርቅ  ሊጠራ ይችል ይሆን ይሆናል ብሎ፤ የመርበትበት፣ ቅጥ የማጣትና የመቅበዝበዝ   ባኅርይ /Confusion/  በተጻጻሪዎቹ መካከል ሊከስት ይችል ይሆናል ብሎ መስጋት፤ ቂልነት አይደለም፡፡ በተቃዋሚ ጎራ መካከል የበለጠ ክፍፍልና አለመግባባት  ተፈጥሮ፤ ገብተን  ከወያኔ ጋር፤ እንደራደር /አንደራደር፤  ሕዝባዊው  ዐመፁን እናፋፍ/ አናፋፍም  ….. ወዘተ  የሚል ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል ብሎ በተንበይ፤ ኃሳባዊነት ነው ማለት አይቻልም።

የሚሆነው ሆኖ ወይም ያማይሆነውም ባለመሆኑ ሳይሆን  ቢቀርም፤  የሚከተሉትን ዐውደ ኃሳቦችና ጥሪዎች በግምት አስገብቶ፤ ሕዝባዊ አመፁን በሙሉ ኃይል ከመደገፍ ሌላ አማራጭ አይኖረውም።

1ኛ.  አሁንም እንደ ትላንቱ፤  የወያኔ መሪዎች፤ ለኢትዮጵያ ችግር  ደንታ ቢሶች መሆናቸውን የስዩም መስፈን  የድርሡልን አቤቱታ በማያሻማ መልኩ ግልጾታል።  ወያኔን ማመን  “ዕባብን ተለማምደነዋል ተብሎ፤ እኪስ ወስጥ እንደማስገባት  ይቆጠራል” የሚባለውን ይትበሃል መርሳት ነው።  የሚያዋጣው መንገድ በራስ ትግል መተማመን ብቻ ነው!

2ኛ. ኣሁንም እንደ ትላንቱ ፤ የወያኔ መሪዎች ፤ የትግራይን ሕዝብ ከቀሪው ኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር በበለጠ ተለያይቶ እንዲኖር ማድረግ፤ በሥልጣን ለመቆየታቸው ስትራተጃዊ ሥሌታቸው እንደሆነ ስዩም መስፍን አረጋግጦታል። ይኽን ከፋፋይ ዐላማ ለማክሸፍ፤ የትግራይ ሕዝብና ወጣቱ ትውልድ ተግቶ መስራት ይጠበቅበታል። በጋራ ሀገር ለመኖር፤ በጋራ ስትራተጂያዊ ዐላማ በኅብረት መሥራት አማራጭ አይኖረውም።

3ኛ. መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ፤ የወያኔን እኩይ ተግባር እያወገዘ እየታገለ፤ ከወገኑ ከትግራይ ሕዝብ ጋር ያለውን በመልካም አብሮ የመኖሩን ባኅልና ሥነ ምግባር አጠናክሮ መቀጠል አለበት። በቅርቡ በወሎ ክፍለ ሀገር፤  በወልደያ፤ በቆቦ፤  ዋድላ- ደላንታ፤ በመርሣና በሌሎች ቦታዎች የወያኔ ነፍሰ ገዳዮች  ባደረጉት ወንጀል ተጠያቂዎች መሆናቸው እንደ ተጠበቀ ሆኖ፤በወሎ ሕዝብና በኩታ ገጠሙ ትግራይ የሚኖረው ሕዝብ መከከል  የተፈጠረውን አሳዛኙ አጋጣሚ፤ ለራሳቸው ግል ጥቅም ፍጆታ ለማድረግ የሚሞክሩትን ሁሉ መኮነን፣ ማውገዝ የሁሉም ሠላም ፈላጊ ዜጋ ኃላፊነት እንደሆነ መገንዘብ ያስፈልጋል።

4ኛ. ወያኔ በሥልጣን እያለ ሕዝቡ ሠላም አያገኝም። በሀገሪቱም ላይ  መረጋጋት አይሰፍንም።  አልገዝም ባይነትና ዕምቢተኝነት በሁሉም አቅጣጫ እየተጋጋለ መሄዱን ይቀጥላል።  ወያኔም የንፁሀንን ደም ከማፍሰስ አይመለስም።

ድንጋጤ የወለደው  ትካዜ፤ ሀዘኔታን አያመጣም!
ፀፀጥ አልባ ኑዛዜ፤ ሥርዕየት አያስገኝም!
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም  ትኖራለች!

pdf_print