867 ተማሪዎች ከዩኒቨርስቲ ለማባረር ታቅዷል

የፍኖተ ዴሞክራሲ ዜናና ኃተታ – የተሾሙት ሚኒስትሮች የወያኔ ባለሟሎች መሆናቸው  – የወያኔው ኮማንድ ፖስት ባወጣው መግለጫ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንደሚቀጥል በአንደምታ  – የሃሮሚያ ዩኒቨርስቲ አስተዳደር 867 ተማሪዎች ለማባረር ማቀዱን ገለጸ – በኢትዮጵያ ዕድሚያቸው የገፋ ዜጎች እንክብካቤ እንዲደረግላቸው ሄልፕ ኤጅ ኢንተርናሽናል የተባለ ድርጅት ጠየቀ – በደቡብ ሱዳን ተጻራሪ ኃይሎች መካከል ሊደረግ የታቀደው ስብሰባ እንዲዘገይ ተደረገ – በኬኒያ የስልክ እና የኢንተርኔት ጠለፋ ህገ ወጥ ነው ተባለ።

በትናንት የዜና ዘገባችን እንደቀረበው የወያኔ ጠቅላይ ሚኒስትር ተብየው ሐሙስ ሚያዚያ 11 ቀን 10 የሚሆኑ አዳዲስ የካቢኔ ሚኒስትሮችን የሾመ ሲሆን ቀደም ብለው ከነበሩት መካከል ስድስቱን የቦታ ለውጥ ያደረገ መሆኑ ታውቋል። ብዙዎቹ ተሿሚዎች ለዓመታት አገዛዙን ሲያገለግሉ የቆዩ መሆናቸው የሚታወቅ ሲሆን የማስመሰል ሚናቸውን እንዲጫወቱ በወያኔው ድርጅት እና በሌሎች ኃይሎች የተመረጡ ሳይሆን አይቀሩም በማለት ብዙዎች ግምታቸውን ይሰጣሉ። ጠቅላይ አቃቤ ህግ ሆነ የተሾመው ለበርካታ ጊዜያት የጸረ ሽብር ህጉን ደግፎ ሲናገር የቆየ፣ “መንግስት በፍርድ ቤት ሂደት ጣልቃ ገብቶ አያውቅም፤ በምርመራ ወቅት ግርፋት የለም ድብደባ የለም፤ የሚዲያ ህግም፤ የበጎ አድራጎት ህግም፤ የጸረሽብር ህግም ምንም ችግር የለውም” በማለት ሽንጡን ገትሮ ሲገከራከር የነበረ የወያኔ አገልጋይ መሆኑ ይታወቃል። ለረጅም ዓመታት የፓርላማ አፈጉባዔ በመሆንና በኋላም በአውሮፓው ህብረት አምባስደር በመሆን ወያኔን በግምባር ቀደምትነት በማገልገል የሚታወቀው ተሾመ ቶጋም አሁን ብቅ ብሏል። በተለይም የማእድንና ኤኔርጂ ሚኒስትር የነበረው ሞቶማ መቀሳ አሁን የመከላከያ ሚኒስትር ሆኖ መሾሙ ትልቅ ለውጥ ሊያመጣ ይችላል በሚል በበርካታ የምዕራባዊ የዜና አውታሮች መናፈሱ የማስመሰሉ ሂደት ሆን ተብሎ በተለያዩ ኃይሎች የተቀየሰ መሆኑን ያረጋግጣል በማለት ብዙዎች ይናገራሉ። እንደተጠበቀውም ቁልፍ የሆኑ ተቋሞች አሁንም በወያኔ ቁጥጥር ስር መሆናቸው ግልጽ ነው። በወታደሩና በጸጥታው መዋቅር ውስጥ መሰረታዊ ለውጥ እስካልተካሄደ ድረስ የካቢኔው ሹም ሽር ከማስመለል አልፎ ምንም የሚያመጣው ፋይዳ የለም ተብሏል፡፡ አባዱላ ገመዳም ከፓርላማ አፈ ጉባዔነቱ ተነስቶ ሙፈሪያት ካሚል በተባለች ሴት ተተክቷል። ባሁኑ ወቅት የፓርላማው ዋናም ሆነ ምክትል አፈጉባኤዎች ሴቶች የሆኑ ሲሆን አባዱላም የአቢይ የጸጥታ አማካሪ ተብሎ መሾሙ ተነግሯል፡፡

በአንድ በኩል የሚኒስትሮች ሹም ሽር ቲያትር እየተካሄደ በሌላ በኩል የወያኔው ኮማንድ ፖስት ሚያዚያ 11 ቀን ባወጣው መግለጫ የአስቸኳይ ጊዜው አዋጅ ሊቀጥል የሚችል መሆኑን ጠቁሟል። መግለጫው በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ምክንያት በአገሪቱ የጸጥታ ሁኔታ ተሻሽሎ መረጋጋት ተፈጥሯል ካለ በኋላ በአንዳንድ ቦታዎች በአገዛዙ ቆስቋሽነት የተከሰቱትን ሁኔታዎች በመዘረዝርና የጸጥታ መደፈረስ መኖሩን ጎላ በማድረግ አዋጁ እንደሚቀጥል በአንደምታ ገልጿል። በሞያሌ በአግአዚ ወታደሮች የተገደሉትን ሰዎችና አሁንም በቅርቡ በአገዛዙ ደጋፊነትና ተባብሪነት ወንጀል በመፈጸም የሚታወቁት የሶማሌ ልዩ ፖሊስ ታጣቂዎች ቦምብ ወርውረው ጉዳት ያደረሱትን እንደምሳሌ በመውሰድ እንዲሁም የኮንትሮባንድና የህገ ወጥ መሳሪያ ዝውውር በዝቷል በማለት ኮማንድ ፖስቱ ሥራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል በመግለጫው ግልጽ አድርጓል።

የሃሮሚያ ዩኒቨርስቲ ባለስልጣኖች 867 ተማሪዎችን ለማስወጣት የወሰኑ መሆናቸውን ገልጸዋል። የኮማንድ ፖስት አባላት በርካታ የሃሮሚያ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ከትምህርት ገበታቸው ላይ በመልቀም ያሰሩ መሆናቸው ሲታወቅ ይህንን በመቃወም የዩኒቨርቲው ተማሪዎች ትምህርት ካቆሙ ከወር በላይ እንደሆናቸው ተዘግቧል። የዩኒቨርቲው ባለስልጣኖች ተማሪዎችን ለማስወጣት የደረሱበት ውሳኔ ችግሮችን ይበልጥ አባብሶ ዩኒቨርስቲውን እስከናካቴው ሊያዘጋ ይችላል የሚሉ ወገኖች መፍትሄው የታሰሩትን ተማሪዎች መፍታት ነው በማለት ሀሳባቸውን ይሰጣሉ። በተያያዘ ዜና የሶማሌው ልዩ ፖሊስ አባላት ከጥቂት ቀናት በፊት ሞያሌ ከተማ ውስጥ የእጅ ቦምብ ወርውረው አራት ሰዎች መግደላቸውና ከ 65 በላይ የሆኑ ሰዎች ማቁሰላቸው የሚታወቅ ሲሆን በትናንትናው ዕለት በምስራቅ ሀረርጌ በመኢሶ አካባቢ አንድ ሰው ገድለው አንድ ተጨማሪ ሰው ያቆሰሉ መሆናቸው ተዘግቧል።

ሙሉውን ዝርዝር ዜና ከግኖተ ዴሞክራሲ የኢትዮጵያ  አንድነት ድምጽ ሬዲዮ ያዳምጡ