አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቢወጣም ህዝባዊ ተቃውሞው ቀጥሏል፣ የወያኔ አገዛዝ የሱማሌ አካባቢ ሚሊሺያዎችን አመጽ ወዳለባቸው አካባቢዎች አሰማራ

(ፍኖተ ዴሞክራሲ የኢትዮጵያ  አንድነት ድምጽ ሬዲዮ) – እሁድ መስከረም 29 ቀን የወያኔ አገዛዝ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቢያውጅም ሕዝባዊ ተቃውሞ በየቦታው እየተካሄደ መሆኑን ከየአካባቢው የሚደርሱት ዜናዎች ይገልጻሉ። በጅማ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች የተቃውሞ ሰልፍ አድርገው ቢያንስ 200 ተማሪዎች በአካባቢው በነበሩ የአግዓዚ ጦር አባላት ታፍነው ተወስደዋል። ሆሳዕና በሚገኘውም የዎቻሞ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች እሁድ ዕለት የምግብ አድማ አድርገው የዋሉ ሲሆን ሌሊቱን የተቃውሞ ሰልፍ በማካሄዳቸው እስከ 150 የሚደርሱ ተማሪዎች ታስረው ተወስደዋል። የአርሲ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች የረሃብ አድማ እያካሄዱ መሆናቸው ታውቋል። በደብረብርሃን ዩኒቨርስቲ ውስጥም ተቃውሞ እንደነገሰ ይሰማል። በጎንደር ከዳባት ከደባርቅና ከሌሎች የቆላ ወገራ አካባቢዎች ወጣቶች በብዛት ወደ አርማጭሆ እየሄዱ መሆናቸው ይወራል።

 

በምስራቅ ሸዋ በአወዳይና እና በወሊሶ አካባቢዎች ከሕዝብ ጋር በተደረጉ ግጭቶች በርከት ያሉ የአግአዚ ጦር አባላት የተገደሉ መሆናቸው ዘገባዎች እየደረሱ ነው። በምስራቅ ሸዋ ፈንታሌ ውስጥ 32 ወታደሮች ሲገደሉ ሶስት የቆሰሉ መሆናቸው ታውቋል። በወሊሶ አንድ ወታደር የተገደለ ሲሆን በአወዳይ አጽብሃ አስገዶም የተባለ የሻለቅነት ማዕረግ ያለው አዛዥ ተገድሏል። በተያያዘ ዜና እሁድ መስከረም 29 በአወዳይ በሚገኘው የወያኔ ጦር ውስጥ በተነሳው አመጽ ምክንያት ቁጥራቸው ለጊዜው በውል ያልታወቁ ወታደሮች ከድተው ሕዝባዊ አመጹን ተቀላቅለዋል። በጉጂ ሕዝብና በወያኔ ወታደሮች መካከል በተነሳ ግጭት 24 የአግአዚ ወታደሮች የተገደሉ መሆናቸውም መረጃዎች እየደረሱ ነው። በሌላ በኩል እሁድ መስከረም 29 ቀን 2009 ዓ.ም. በምዕራብ ሸዋ ኢጃጅ ውስጥ አንድ ወታደር ተኩስ ከፍቶ ቢያንስ ሁለት ሰዎች የገደለ መሆኑ ታውቋል።

 

የወያኔ አገዛዝ በሱማሌ አካባቢ ያስታጠቃቸውን ሚሊሺያዎች አመጾች እየተካሄዱ ወዳሉባቸው አካባቢዎች እያንቀሳቀሰ መሆኑ ተነግሯል። በተጨማሪም ከባድ መሳሪዎች የታጠቁ ወታደሮች ከዚሁ ክልል እያንቀሳቀሰ ነው ተብሏል። በአንዳንድ የወያኔ አገዛዝ ወታደራዊ ዘርፍ ውስጥ በወያኔ ወታደሮችና ከሌሎች ብሔረሰቦች በመጡ ወታደሮች መካከል ቅራኔዎች እየተፈጠሩ መሆናቸው ይነገራል። ይህ ቅራኔ ወዴት ሊያመራ እንደሚችል ማወቅ ባይቻልም የአንዳንድ ወታደሮች ሥርዓቱን መክዳትና ከሕዝብ ጎራ መደባለቅ የዚሁ ነጸብራቅ ሳይሆን አይቀርም የሚሉ ብዙ ናቸው።

ዝርዝር ዜና  ያንብቡ ወይም ያዳምጡ