ወቅታዊ ዜና

ከፍኖተ ዴሞክራሲ የኢትዮጵያ አንድነት ድምጽ ሬዲዮ (ጥቅምት 8 ቀን 2009 ዓ. ም.)– ርዕሰ ዜና: በጎንደር ከተማ የሙት ከተማ አድማው ለሁለተኛ ቀን ቀጥሏል – በተለያዩ ቦታዎች የሚካሄዱ የጅምላ እስሮች ቀጥለዋል – የተመድ ዋና ጸሐፊ ለወያኔ አገዛዝ ባለስልጣኖች መልክት ያስተላለፉ መሆኑ ተነገረ – የአገዛዙ ወታደሮች ኬኒያ ግዛት ውስጥ ወሰን ጥሰው ገቡ ተባለ – ከጋምቤላ ከተወሰዱት ህጻናት መካከል 68 የሚሆኑት አሁንም እንዳልተመለሱ ተነገረ።

ሰኞ ጥቅምት 7 ቀን በጎንደር ከተማ የተጀመረው የሙት ከተማ አድማ ለሁለተኛ ቀን የተካሄደ መሆኑ ታወቀ። የወያኔ አግአዚ ጦር አባላት ባካሄዱት ከፍተኛ ተጽእኖ በፒያሳ፤ በገነት ተራራ፤ በብሎኮ እና በሌሎች አካባቢዎች አንዳንድ ሱቆች የተከፈቱ ቢሆንም አብዛኞቹ ሱቆች ዝግ ሆነው መዋላቸውን ነዋሪዎች ይገልጻሉ። በትናንትናው ዕለት አድማውን ተጻርረው ሲንቀሳቀሱ በነበሩ የባጃጅ ተሽከርካሪዎች ላይ እርምጃ የተወሰደ መሆኑ ይነገራል። ማክሰኞ ጥቅምት 8 ቀን 2008 በባህር ዳር ቀበሌ 5 እና ስድስት አካባቢ የወያኔ አግአዚ ጦር ወጣቶችን ለመያዝ ባደረገው ጥረት በወጣቶቹ በኩል ከፍተኛ ተቃውሞ እና ግጭት ያስነሳ መሆኑ ተሰምቷል። በግጭቱ የተጎዱ ወጣቶች ያሉ ሲሆን የተወሰኑት ታስረው የሄዱ መሄዳቸውም ተስምቷል።

በተለያዩ ቦታዎች የሚካሄዱት የጅምላ እስሮች በሰፊው መቀጠላቸው ታውቋል። በወሊሶ በሻሸመኔና በሌሎች ቦታዎች ቁጥራቸው በውል ያልተገለጸ ዜጎች የታሰሩ ከመሆናቸውም በላይ ከምስራቅ ሐርርጌ ኤጀርሳ ጉሮ ከተማ 50 የሚሆኑ ሰዎች እንዲሁም በምስራቅ ጉጂ 13 ሰዎች ታፍነው የተወሰዱ መሆናችው ታውቋል። ከኢጄርሳ ጉሮ የተወሰዱት መዳራሻቸው እስካሁን ያልታወቀ መሆኑን ቤተሰቦቻቸው ይናገራሉ።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ በኢትዮጵያ ያለውን ሁኔታ በቅርብ እንደሚከታተሉ የድርጅቱ ቃል አቀባይ ገለጹ። ቃል አቀባዩ ዋና ጸሐፊው በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ ያሳሰባቸው መሆኑን ገልጸው የወያኔ አገዛዝ የሕዝቡን መሰረታዊ መብት መገደብ የሌለበት መሆኑን እና የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት ከተቃዋሚዎች ጋር ባስቸኳይ ውይይት እንዲያካሄድ መልክት አስተላልፈዋል ብለዋል።

የወያኔ አግአዚ ወታደሮች ባለፈው እሁድ ጥቅምት 6 ቀን 2009 ዓም. ወሰን ጥሰው ወደ ኬኒያ ግዛት መግባታቸውን ዘ ኔሽን የተባለው የኬኒያ ጋዘጣ ዘግቧል። ድንበር ጥሰው የገቡት ወታደሮች ወደ 100 የሚጠጉ ሲሆን የገቡት በመሳርቤት ግዛት ውስጥ በሚገኝ ጎለሌ በተባለ መንደር ውስጥ እንደሆነ ተገልጿል። ወታደሮቹ ወደ ግዛቱ ለመግባታቸው የሰጡት ምክንያት መኮንኖንች የገደሉ ታጣቂዎችን ለመፈለግ እንደሆነ ተናግረዋል። የኬኒያ መከላከያ ኃይል የኬኒያ ወታደሮችን ወደ ወሰን አካባቢ የላከ መሆኑ የታወቀ ቢሆንም ምን ዓይነት መመሪያ እንደተሰጣችው የታወቀ ነገር የለም በማለት ጋዜጣው ዘግቧል። ባለፈው ዓመት የወያኔ አግአዚ ጦር አባላት ከአምስት ላላነሰ ጊዜ ወሰን ጥሰው ወደኬኒያ መግባታቸውን የኬኒያ ባለስልጣኖች ይናገራሉ።

ራዲዮ ታማጁጅ ኦርግ የተባለው የደቡብ ሱዳን ድረ ገጽ ሰኞ ዕለት ባወጣው ዕትም ባለፈው ዓመት ከጋምቤላ ታፍነው ወደ ደቡብ ሱዳን ከተወሰዱ የኑዌር ህጻናት መካከል 68 የሚሆኑት እስካሁን ያልተመለሱ መሆናቸውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ባለስልጣኖች ባለፈው ሳምንት የሰጡትን መግለጫ ዋቢ በማድረግ ገልጿል። ባለስልጣኖቹ በሰጡት መግለጫ ያልተገኙት ህጻናት ሁሉም ከ 13 አመት በታች እድሚያ ያለቸው መሆኑን ገልጸው የወያኔ እና የደቡብ ሱዳን ባለስልጣኖች ፍለጋውን እንዲቀጥሉ የተመድ ባለስልጣኖች ያሳሰቡ መሆናችውን ድረ ገጹ ዘግቧል።  በዝርዝር:

ያዳምጡ ወይም ያንብቡ