ሕዝብና ሀገርን ለመታደግ በቁርጠኛነት እንነሳ

በፍኖተ ዴሞክራሲ የኢትዮጵያ አንድነት ድምጽ ራዲዮ (በ ህዳር 12 ቀን 2012 ዓም የተላለፈ ጥሪ) –

በተለያየ ዘመን በተደረጉ የህዝብ ቆጠራዎች ፥ እንደተረጋገጠው 70% በላይ የሚሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከተለያዩ
ብሔረሰቦች የተወለደና የተቀላቀለ ነው። የኔ ብሔረሰብ ትልቅና ብዙ ነው የሚል አስተሳሰብ ያላቸው ግብዝ ፖለቲከኞች ያልታያቸውና ለመገንዘብ የተሳናቸው ፥ ሌሎች ብሔር ብሔረሰቦች ባንድ ሲቆሙና ሲሰለፉ ፥ ከሁሉም በላይ ብዙ መሆናቸውንና እነሱ አናሳ ሆነው እንደሚገኙ አለማሰባቸው ነው።

ለሺዎች ዓመታት አብሮ ታሪክ የሠራው ህዝብ ፥ አብሮ ስንቱን መከራና ችግር በጋራ ተቋቁሞ ፥ ለዘመናት ሊወሩትና ሀገሩን ሊቀሙት ፥ በተለያየ አቅጣጫ የመጡበትን ባዕዳን ኃይላት በአንድነት መክቶ ነጻነቱን ጠብቆ ፤ ኢትዮጵያን ታድጎ አቆይቷል። በዘር በቋንቋ ሊከፋፍሉት የሞከሩትን አሳፍሮ አንድነቱን ጠብቆ ፥ ተጋብቶና ተዋልዶ እዚህ አድርሶናል። የእስልምና ሃይማኖት አባቶች፤ አዋላጆች በሀግራቸው መኖር አቅቷቸው ከባህር ማዶ ሲሰደዱ በወቅቱ የነበሩ ክርስቲያን ነገሥታቶች ተቀብለውና አስተናግደው በአገር እንዲኖሩ አድርገዋል። በዚህና ባጠቃላይ ሀገር እንደሀገር በቆየችበት የታሪክ ሂደት፤ ክብርና ምስጋና ለጀግኖች እናቶቻችንና አባቶቻችን ፥ ሁላችን ኢትዮጵያውያን ፥ እስከቅርብ ጊዜ ድረስ፥ የትም ሀገር ሄደን አንገታችንን ቀና አድርገን በታሪካችን ኮርተን እንድንሄድ በቅተናል።


ይሁንና፥ ባሳለፍነው ታሪካዊ ሂደት ውስጥ ከተለያዩ የውጭ ወራሪዎችና ጠላቶቻችን ጋር የተሰለፉና የተባበሩ ፥ ሀገርና ህዝብን ከድተው ብዙ ጉዳት ያደረሱብን ባንዶችና ከሀዲዎችም ነበሩን። በቅርቡ ታሪካችንም ቢሆን የሀገርንና የህዝብን ጥቅም አሳልፈው የሰጡ ፥ ሀገራችንንና ዳር ድንበራችንን ከጠላቶቻችን ጋር በመተባበር ያስደፈሩ እንደ ወያኔና ጸረ-ኢትዮጵያ ጠባብ ብሄርተኞች አሉ። አሁን አሁን ደግሞ ከለየላቸው የውጪ ጠላቶቻችን ጋር ተቀናጅተው ፥ ሀገራችንን ለመበታተንና ለማፍረስ ተደራጅተው ቆርጠው ተነስተውብናል። ጥቂቶች ቢሆኑም ፥ የተደራጁና በየመንግሥት ተብዬው መዋቅር ጭምር እየታገዙ ፥ ከሕዝብና ሀገር የተዘረፈ ሃብትና ከውጭ ጠላቶቻችን በገፍ የተመደበላቸውን ገንዘብ እየተጠቀሙ፥ የተቀነባበረ ዘመቻ ከፍተውብናል። ይህንን ያልተገነዘበ ካለ በጥቅም ተደልሎ የገባ ወዶ ገብ ባንዳና ከሀዲ ብቻ ነው።


ስለሆነም፥ እኛ እውነተኛ የኢትዮጵያ ልጆች፥ በዘር ቋንቋና ሃይማኖት ሳንገደብ ወይም እነሱ በከለሉልን የክልል አጥር
ሳንታጠር አገራችንን ለማዳን እንነሳ። በውሁዳን ጯሂዎችና ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ተገደን፥ በዘውግ በተቀደደልን ቦይ አንፍሰስ። እምቢ ለሀገሬ እምቢ ለህዝቤ ብለን ድምጻችንን እናሰማ። የኛ የብዙሀኑ ዝምታ ለነሱ የልብልብ ሰጥቶ ፥ እርስ በርስ ሲያጫርሱን ፥ የህዝባችንን ኑሮና ህይወት ከምንጊዜውም በላይ ሲያመሰቃቅሉና ሰላምና ዕረፍት ነስተው ሲያዋክቡት ፥ እያየን ዝም ማለትና መፍቀድ የለብንም። ጥቂት ቅጥረኞቻቸውንና ቦዘኔዎችን በአንድ ጎሳና ህዝብ ስም በሌላ ምስኪን ዜጋ ላይ አሰማርተው ፥ አሰቃቂ ግድያዎችን እየፈጸሙና ያንንም አሳፋሪና ዘግናኝ ድርጊት በንጹሃን ዜጎችና ምንም ወንጀል በሌላቸው የሌላ ቋንቋ ተናጋሪ ላይም እያደረሱ ፥ ይህንኑም እኩይ ድርጊት በቪድዮና በማህበራዊ ድረ ገጾች በማሰራጨት፥ የስነ ልቦና ሽብር በመልቀቅ፥ የዘርና የሃይማኖት ግጭት ለመቆስቆስ የሚያደርጉትን ሩጫና ጥረት ባስቸኳይ ማስቆም አለብን።


ዛሬ የህዝቡን ትግል ውጤት ቀምተው፥ በባዕዳን ኃይሎች ሴራ፥ በሥልጣን ላይ የተቀመጡት ፥ የወያኔ/ኢሕአዴግን ገዳይና አፋኝ ሥርዓት ሊያድኑ የመጡ የነሱ ተወካዮች ናቸው። ከከፍተኛ እርከን እስከቀበሌ በተዋረድ ያለው መዋቅሩም ፥ ያው የነበረውና በነሱ የሚዘወረው የወንጀለኞች ጥርቅም የተሰገሰጉበት ነው። አሁን እየሆነ ላለው ግድያና ማፈናቀል ከላይ እስከታች ሁሉም እያወቁና እየደገፉት በተቀናጀ መልኩ እያስኬዱት ለመሆናቸው፥ ዋናው መገለጫ የፖሊስና የደህንነት ኃይሎች በተጎጂዎች ዒላማ የተደረጉ ዜጎችን ማዳንና መከላከል ትተው ፥ እራሳቸውን ሊከላከሉ የሚሞክሩትን ሲያጠቁና ሲያስሩ፥ ለወጀለኞች ግን ከለላ ሲሆኑ እንድነበር በበቂ የተጋለጠ የአደባባይ ሚስጢር መሆኑ ነው። ከእንግዲህ በኋላም የልብልብ እየተሰማቸው ይበልጥ ጉዳት ሊያደርሱና መጠነ ሰፊ ጥቃትም ሊፈጽሙ ስለሚችሉ ፥ ሀገራችንንና ህዝቧንም ለመበታተን ቆርጠው ዘመቻቸውን እንደሚቀጥሉ ተገንዝበን ፥ መዘጋጀት አለብን።

የወያኔ እኩይ ዘረኛ ቡድንና በነጃህዋር የሚመራው ጠባብና ጸረ ኢትዮጵያ፥ ጥምር ኀይል ፥ በመቀሌና በሌሎችም ድብቅ ቦታዎች መክረውና አቅደው ሥራ ተከፋፍለው እየሰሩ ይገኛሉ። ለዚህም የነ ግብጽና እንዲሁም የሌሎች የዓረብ መንግሥታትም ትብብርና ቅንጅት እንዳለበት ሳይታለም የተፈታ ነው። በብዛት እየተዘገበ እንዳለው ፥ ይህ ቅንጅት በፕሮፓጋንዳ ፥ በቅስቀሳና በተለያዩ መንገዶች የሀሰት ወሬዎችን ሳይቀር በማሰራጨት የኢትዮጵያና የኢትዮጵያዊነት መሰረት በሆኑት ተቋማትና ማዕከላት ላይ ኣፍራሽ ወሬዎችንና አሉታዊ ድርጊቶችን እያካሄዱ ይገኛሉ። ለምሳሌም የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ላይና የኢትዮጵያ እስልምና ዕምነት ተከታዮች ላይ እየተሞከረ ያለው የማጋጨት ሙከራ አሁን ባይሳካላቸው ፥ ይበልጥ አጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚችሉ መገመት ተገቢ ነው። በኢትዮጵያዊነታቸው በማይደርደሩ የየትኛውም ብሔረሰብ ሕዝብና አባላት ላይ ፥ በተቀናጀ መልኩ የመከፋፈል የማዳከም እንቅስቃሴ ያደርጋሉ። በደቡብ ህዝብና ብሔረሰቦች መሀል የወያኔና የጠባቦች ደህንነቶችና ቅጥረኞቻቸው፥ የሚቀሰቅሱት ግጭት እንዲሁም በአማራው ክልል ቅማንትና አማራውን፤ አገውና አማራውን ደም ለማቃባት የሚደረጉት ደባዎች ፥ ሀገር ያወቃቸው ፀሀይ የሞቃቸው ናቸው። ድምጺ ወያኔና ኦኤምኤን የነጆዋር ሬድዮና ቴሌቪዥን እንዴት ተቀናጅተው እንደሚሰሩ ጥሩ ምሳሌዎች ናቸው።


የእነዚህን የሀገር ጠላቶች ሴራዎችና ተግባራዊ እንቅስቃሴዎች በውል የተረዳን ወገኖች ፥ ለምን እንዲህ ሆነ ? እኛስ ምን ማድረግ አለብን ብለን እራሳችንን መጠየቅ ግድ ይሆንብናል። በመጀመሪያ ስላለው ተጨባጭ ሁኔታ ግልጽነት ሊኖረን ይገባል። ከዚያም በሀገራችንና በህዝቧ ላይ ማን ምን እያደረገ እንደሆነ መረዳት ተገቢ ይሆናል። ወዳጅንና ጠላትንም በትክክል መረዳት ይኖርብናል። ሁከት ፈጣሪ የሆኑት ኃይሎች በጣም ትንሽ ቢሆኑም የተደራጁ ናቸው፥ ሃብትና ገንዘብ አላቸው። የመንግሥት መዋቅርና ኃይልን ይጠቀማሉ። እነሱ ሲገድሉ ፥ ሲያፈናቅሉ የሚያግዝና የሚያዘናጋ መሪና ካድሬዎች አሏቸው። በአዲስ አበባው የባላደራ ምክር ቤት አባላት ላይ የሚደረገውን አይን ያወጣ ወከባ ልብ ይሏል። ኢትዮጵያዊ በሆኑ ሀገር ወዳድ ኃይሎችና ቡድኖች ላይ ፥ ፈጥኖ እርምጃ የሚወስድና የሚያገል አገዛዝ አላቸው። እንደ ኢሕአፓ ያሉ ሀቀኛ ተቃዋሚ ኃይሎች ተገልለው ፥ አቅመቢስ ተለጣፊ ቡድኖችና አንጃዎች በድጋፍ እንዲንቀሳቀሱ ሆኗል። በአማራ ክልል የነበሩ ለወያኔና ለሥርዓቱ ያልተመቹ መሪዎች በሴራ እንዲገደሉና እንዲወገዱ ሁኗል። ሌሎች ደግሞ በጠራራ ጸሐይ በርካታ ባንኮች ሲዘረፉ ማንም ሲጠይቃቸው አልታየም።

ስለሆነም፥ እኛ ብዙሃንና በኢትዮጵያዊነታችን የማንደራደር ዜጎች ሁሉ ፥ ሀገራችንና ህዝባችንን የሚረዳ ሌላ የውጪ ኃይልም ሆነ አጋዥ ይኖረናል ብለን ሳንዘናጋና ሳናመነታ ፥ በራሳችን ብቃትና ችሎታ ላይ ብቻ በመተማመን አገራችንንና ህዝባችንን ለመታደግ በቁርጠኝነት መነሳት አለብን። ባመቸንና በሚያዛልቅ መልኩ መደራጀት አለብን። ያልተደራጀ ህዝብ ሁሌም የማንም እኩይ መጫወቻና የጥቃት ሰለባ ይሆናል። ስለዚህ ፥ እኛ ፤ መላው የሀገራችን ህዝብ ሰላም አግኝቶ ፥ ከድህነት ከረሀብና ድንቁርና ተላቅቆ ፥ በማንነቱ ኮርቶ በዕኩልነትና በነጻነት ፥ ተከባብሮና ተፋቅሮ ኢትዮጵያን አገሬ ብሎ እንዲኖር የምንሻ ሁሉ፤ መሰባሰብና መደራጀት አለብን። ለኛ ሀገር ህዝብ ፤ ህዝብም ሀገር ነውና ሊያጠፉን እያዘናጉ ወደ ቆፈሩልን ገደል ሊጥሉን ለቋመጡ ሁሉ እርም ይሁንባችሁ ፥ በቃችሁ ብለን ተደራጅተን ዕቅዳቸውን ልናመክን እንነሳ።


ለሺዎች ዓመታት በደም በሥጋና በአጥንት ተደበላልቀን ፥ ተሳስረንና ተጋምደን አብረን የጋራ የሆነችውን አገራችንን ያቆየንና የገነባን ዜጎች፥ የተለያዩ ጨቋኝ ሥርዓቶችን አብረን ታግለን ክፉና ደጉን አሳልፈን ፥ በየጊዜውም ድሎቻችንን በሌሎች እየተነጠቅን እዚህ ደርሰናል። አሁን ግን ነጻነታችንን ብቻ ሳይሆን ሀገራችንንና ህዝባችንን ሊበታትኑ ያቆበቆቡ አጥፍቶ ጠፊዎች ከፊታችን ተጋርጠዋል። ዝምታን በመምረጥ አንገታችንን ደፍተን ያዩን ብኩን የውስጥና የውጭ ጠላቶቻችን የደከምን ያነስን መስሏቸው ከሆነ ፤ ብዥታቸው ነውና ማንነታችንን አሁንም በድጋሚ እንዲያዩን ይሆናል ። እኛም የጥንቶቹ ጀግኖች አባቶቻችን ዝርያዎች መሆናችንን እናሳያቸዋለን። ከሰሜን እስከ ደቡብ ፥ ከምስራቅ እስከ ምዕራብ ፥ በየቀያችንና ጎጣችን በሚስጥርና በሚመቸው ዘዴ ሁሉ እንደራጃለን እየተደራጀንም ነው።


በየአካባቢው ያሉትን ቡከን የህዝብ ጠላቶች በዘዴ እየለየን በጥንቃቄ በማግለል ። የራሳችንን የአካባቢ አስተዳደር በህቡዕም ቢሆን እያቋቋምን እነሱን መነጠል ይኖርብናል። ከሁሉም በላይ በያካባቢው እንደ እብድ ውሻ የተለቀቁብንን ገዳይ መንጋዎች ትምህርት የሚሆን እራስንና ቤተሰብን አደራጅተንና ሰብሰብ ብለን ለመከላከል በየአካባቢያችን ቅድመ ዝግጅት ማድረግ አለብን ። የእርስበርስ ግንኙንት የማይቋረጥበትን መንገድና ዘዴዎችን ሁሉ ከወዲሁ ማዘጋጀት የጎበዝ አለቆቻችንና የመሪዎቻችን ተግባር ቢሆንም ሁላችንም ምንጊዜም ዝግጁ መሆን አለብን – ሞትን ሞተን አንጠብቅምና።


ሀገርን ለመታደግና ክብራችንን ለማስመለስ የቆመ መንግሥትም ሆነ፥ በሀገር ውስጥ ይህንን ከፊታችን የተደቀነውን
የአጥፊዎችና የበታኞችን ሴራ መቋቋም የሚችል ፥ የተደራጀና የተዘጋጀ ኃይል ገና አልፈጠርንም። ስለሆነም ፥ በሙያ
ማህበር፥ በእድር ፥ በተማሪና አስተማሪ ፥ በሰፈርና በቀበሌም የተሰባሰባችሁ ሁሉ እርስበርስ በመናበብ የአርበኝነት ትግሉን የጎበዝ አለቆቻችንና አገናኝ መሪዎቻችንን በመምረጥ፤ ሀገርን በመታደግ ወገንተኝነት የሚያሳዩትን እያሰባሰብን አጠራጣሪዎችንና ወላዋዮችን፣ በሀገርና በሕዝብ ሉዓላዊነት ላይ ጥርት ያለ አቋም የሌላቸውን እየነጠልን፤ ከነሱም የሚመሳሰሉ የውስጥ አርበኞችንም በየቦታው እያደራጀን ሁለገብ ትግሉን በሁሉም ዘርፍ ማፋፋም አለብን።


ለዚህ የትም የምትገኙ ሀገር ወዳድ ምሁራን ህዝቡ አንድነቱ ተጠብቆ እንዲቀጥል፤ ሀገርም እንደሀገር ኢትዮጵያዊ ሰንደቋ ከፍ ብሎ እንዲቀጥል፤ ከፍተኛ የሥርዓቱ ሰላዮችና ጥቅመኛ አገልጋዮች ፥ በሃይማኖትና በጎሳ እንደለመዱት እንዳይለያዩት ፥ ማዘጋጀትና እቅዶቻቸውን ማምከን ይጠበቅባችኋል። በሠራዊቱ ውስጥ የምትገኙ የኢትዮጵያ ልጆች፤ ሀገራችሁ እስክትበታተን ለመጠበቅ የምትፈልጉ አይሆንም። ስለዚህ በዚህ አሳሳቢና አደናጋሪ ወቅት ፥ ከሁሉም በላይ የሀገራችንን ህልውና አደጋ ላይ ከሚጥሉ ጠባቦችና ጸረ-ሕዝብ ቡድኖችና ኃይሎች ጋር በሚደረገው የአርበኝነት ተጋድሎ ሚናችሁን ለይታችሁ ከሀገር ወዳዶች ጋር ሰልፋችሁን አስተካክሉ። ዛሬ ምንም የቅንጦት ጊዜ የለንምና፥ በሀገር ውስጥና ውጭ ያላችሁ የቁርጥ ቀን የኢትዮጵያ ልጆች በሚመቻችሁ ዘዴና መንገድ ተሰባሰቡ። ዛሬ የገጠመን አደገኛና ህልውናችንን፥ እንደ ህዝብና ሀገር የሚፈታተን ሁኔታ መሆኑን ጠንቅቀን መገንዘብ አለብን።


እንደ ነብር ዥንጉርጉር ኅብረ ቀለማዊ ውበታችን ፥ ከሀገርና ሕዝብ ፍቅር ጋር የተላበስነው ኢትዮጵያዊነት ክብራችን ነው። በጋራ ታግለው ፤ ደማቸውን አፍሰው ፥ አጥንታቸውን ከስክሰው ጊዜውና ሁኔታው በፈቀደላቸው መንገድ ተጉዘው ፤ ከገነቡልንና ካስረከቡን ሀገር ፍንክች አንልም። እንደ ጀግኖቹ ህብረ ብሄራዊ እናቶቻችንና አባቶቻችን ሁሉ፥ እኛም እንደነሱ ዘመኑ በፈቀደልን ዘዴና ስልት ፥ ታሪካዊ ግዴታችንን እንወጣለን። ሀገራችን በኢትዮጵያዊነታቸውና በሀገርና ህዝብ ፍቅር በእጥፍ ድርብ የሚንገበገቡ ምሁራን ፥ ጠበብት ፥ ወዘተ. ሞልተዋታል። ሚሊዮኖች ወጣቶች ለሀገርና ለወገን አንድነት መስዋዕት የሚሆኑ ፤ ጨቅላና መከታ የሌላቸውን ዜጎች በመንጋ የሚያጠቁትን ጥቂት ፈሪዎችና ቡከን መሪዎቻቸው ታድነው አድነው ለፍርድ እንዲቀርቡ የሚሆንበት ሁኔታ እንዲፈጠር ሳናሰልስ መታገል ይኖርብናል። በየአደባባዩ የሚካሄደው የዜጎች አሰቃቂ ግድያን፤ የቤተክርስቲያናትና የመስጊዶች ቃጠሎን፤ የንብረቶች ውድመትን፤ በዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ላይ እየተደረገ ያለውን ጥቃት ጥቃትና ሌሎች የጅምላ ወንጀሎችን ችላ ብሎ ከሚገኘው አገዛዝም ሆነ ከመሪው ብዙ መጠበቅ አይቻልም። ዜጎች ወደነሱ ማንጋጠጡን አቁመው ጸሎታቸውን በየእምነታቸው ይዘው ሕዝብ በፍቅርና በመተሳሰብ ለዘመናት አብሮ የኖረበትን ሁኔታ ለማስከበር ተደራጅቶ መንቀሳቀስ አለበት። የሀገራችን ሉዓላዊነት ከነ ሙሉ ክብሯ ጋር እንዲረጋገጥ ክንድን
አስተባብሮ የጋራ ርብርቦሽ ማድረግ ሁኔታው ግድ የሚል ነው። ለሀራችን ኢትዮጵያና ሕዝቧ የምንቆረቆር ዜጎች ሁሉ በተራችን ባንዶችንና ሀገር ገንጣዮችን ወደ ተገቢ ቦታቸው ወደ ታሪካዊ ትቢያ መጣያ፥ እንዳይመለሱ ለማድረግ በጋራ መቆም፤ በጋራ አሻፈረኝ ማለት እንዲሁም የጎጠኝነት ቀንበር በቃኝ ማለት ይኖርብናል። ከዘመን ዘመን ተሻጋሪ ታሪክና አኩሪ ሀገር ለልጅ ልጆቻችን በክብር ለማስተላለፍም እጅ ለእጅ ተያየዘን እንነሳ፤ እንታገላቸው።