ሥር ነቀል የሥርዓት ለውጥ በሽግግር ሂደት

ዴሞክራሲያ (የኢሕአፓ ልሳን) – ዛሬም በየአቅጣጫው የሚታየውና እየሆነ ያለው ሁሉ ፥ በቅርበት ቢመረመርና ቢገመገም ፥ በአንድ በኩል፥ በወያኔው መዋቅር ውስጥ የተሰገሰጉ ቡድኖች፥ የነበረውን መዋቅር በመጠቀም ቀድሞ ወደ ነበሩበት የሥልጣን ቦታ ለመመለስ እየጣሩ መሆናቸው በግልፅ የሚታይ ነው። ሌሎች ደግሞ ይህንን ክፍተት በመጠቀም ፅንፈኛ አስተሳሰባቸውን በሕዝብ ላይ ለመጫን የጥላቻና የሽብር አጀንዳቸውን ከነዚሁ ፀረ ህዝብ ኃይሎች ጋር በማጣመርም ሆነ በተናጠል የሕዝብ ወገን መስለው መርዛቸውን እየረጩ ይገኛሉ። የለውጥ ተብዬው እንቅስቃሴ እንግዲህ፤ እነዚህን ሁሉ አቅፎ ጥገናዊ ለውጥ ለማምጣት ሲውተረተር ይታያል። በአሁኑ ወቅት ሽግግር እያደረግን ነው የሚለው ክፍል በሕዝብ ያልተመረጠ አካል መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል። ባለፈው አገራዊ ምርጫ ከፍተኛ የማጭበርበር ተግባር ፈጽሞ መቶ በመቶ አሸነፌያለሁ በማለት በሥልጣን የተሰየመ አካል መሆኑ መታወቅ አለበት። ይህንን አይን ያወጣ ማጭበርበር ትክክል አይደለም የሚባልበት የፍትህ ሥርዓት የሌለበት፤ ቀማኛውም ዳኛውም እራሱ የሆነበት ሁኔታ አሁንም እንዳለ ነው። ከዚህ በተጨማሪ በአሁኑ ወቅት በሥልጣን ያሉትን ወያኔዎችና የዛሬ ለውጥ አምጪ በሉን ባዮች ሥልጣን ላይ ያስቀመጣቸው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሳይሆን አሜሪካና አረቦች ለመሆናቸው ደግሞ በቂ መረጃ ሲቀርብ ቆይቷል። ይህ በመሆኑም የተከሰተው ሁኔታ በሀገሪቱና በሕዝብ ላይ ታይቶ የማይታወቅ ከፍተኛ ችግር እየፈጠረ ይገኛል። ያላለፉት 10 ወራት እንቅስቃሴ እንዳሳየው ፤ የችግሩ ፈጣሪና ምክንያት የሆነው ኃይል የመፍትሄው አካል ነኝ በሚል አማጭና አዋላጅ ጨርሶ ሊሆን እንደማይችል በበቂ ያስመሰከረበት ሁኔታ ጎልቶ ታይቷል።

ይህ አሳሳቢ ሁኔታ ጊዜ አግኝቶ ከቀጠለ ከፍተኛ ሀገራዊና ማኅበራዊ ቀውስ ሊከተል እንደሚችል መገመት አያስቸግርም። ለዚህም ኢሕአፓ ደግሞ ደጋግሞ ለማሳወቅ እንደሞከረው፣ የኢትዮጵያ ሕዝብና ሐቀኛ ዜጎች መሠረታዊና ሥር ነቀል ለውጥ ሊያስገኝ የሚችለውን የሽግግር ሂደት በእጃቸው ሊያስገቡት ይገባል ይላል። ሰላማዊና አስተማማኝ የሽግግር ሂደት እንዴት ተግባራዊ ሊሆን ይችላል የሚለው ወሳኝ ጥያቄ መልስ ማግኘት አለበት። ከዚህ በፊት የኢሕአፓ ልሳን ዴሞክራሲያ ስለ ሽግግር ምንነት እንዲህ ብሎም ነበር። ሙሉውን ጽሁፍ ያንብቡ ...