ከወያኔ ጓዳ

(ከመላኩ ይስማው) –

ካለፈው አንድ ዓመት ጀምሮ በአባል ድርጅቶቹ መካከል በተፈጠረው የሥልጣን ሽኩቻ ምክንያት ኢሕአዴግ በከፍተኛ ውስጣዊ ቀውስ እየታመሰ ይገኛል። አባል ድርጅቶቹም በውስጣቸው በተፈጠሩ የተለያዩ ቡድኖች መካከል በተፈጠረው የአመለካከት ልዩነትና የሥልጣን ሽምያ ሳቢያ ልክ እንደ ኢሕኣዴግ በውስጠ-ድርጅት መቃቃርና መናቆር ተዘፍቀው ተስተውሏል።

በወያኔ ውስጥ በየአድዋው የስብሃት ነጋ (ኣቦይ ስብሐት) ቤተ-ዘመዳዊ ገዥ ቡድንና ይህንን ገዥ ቡድንን በሚገዳደሩ የምዕራብ ትግራይ ተወላጅ የገዥው መደብ አባላት መካከል ከፍተኛ ፍጥጫ ተፈጥሮ ባጅቷል። ይህ ቡድናዊ ፍልሚያ የሌሎቹ የትግራይ ክፍሎች ተወላጆች የሆኑት እነ አዲስ ዓለም ባሌማ (ግማሽ ደቡብ ኢትዮጵያ)፣ ሥዩም መስፍን (ዓጋመ)፣ ጌታቸው ረዳ (ራያ)፣ አድኃና ኃይለ (ራያ፣ የትግራይ ክፍለ-ሀገር የኢሠፓኣኰ ሥራ አስፈጻሚ ኰሚቴ አባል የነበረ)፣ … ወዘተረፈ ደግሞ መሃል ላይ ሲዋልሉና ለአየለው ወገን ሲያጎበድዱ የታዩበት ነው። ይህ በወያኔ ውስጥ የተፈጠረው ቡድናዊ የሥልጣን ፍትጊያ የኣቦይ ስብሓት ነጋ ቤተ-ዘመዳዊ ገዥ ቡድን የበላይነቱ ይዞ የታየበት ቢሆንም ፍትጊያው ግን አሁንም አልተቋጨም።

በኦዴፓ/ኦህዴድ ውስጥም ተመሳሳይ ግን በአብላጫው ወደ ሥልጣን ሽሚያ ያደላ ቡድናዊ ሽኩቻ ተከስቶ ቆይቷል። በዚህ ድርጅት ውስጥ የተከሰተው ቡድናዊ መራኰት በዋናነት በእነ ለማ መገርሳና ዓብይ አህመድ እና በእነ አባ ዱላና እነ ግርማ ብሩ የመሳሰሉት መካከል የተካሄደው ነው። የኦሕዴድ/ኦዴፓ ወስጣዊ ፍትጊያ መንበረ-ሥልጣን ለመጨበጥ ሁሉንም ዋጋ ለመክፈል ተዘጋጅቶ፣ በወታደርነትም በሰላይነትም ፍጹም አገልጋይ ሆኖና ጎን ለጎን ግን የራሱን ቡድን ሲያደላድል በከረመው የኣብይ አህመድ እና ጓደኞቹ እነ ለማ መገርሳ (ቲም ለማ) የበላይነት ተጠናቋል። የዓብይን የሥልጣን ፍላጐት ዕውን ለማድረግ ደመቀ መኰነን እና ገዱ አንዳርጋቸው ከብዙ የኦሕዴድ/ኦዴፓ ሰዎችም ጭምር የበለጠ ወሳኝ ሚና ተጫውተዋል።

አባ ዱላ ገመዳ በኢትዮጵያ ጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር (ደርግ) እና በኢትዮጵያ ሕዝባዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ (ኢሕዲሪ) መንግሥት ዘመን የመከላከያ ሠራዊት መኰንን ሆኖ ያገለገለና በኋላ ላይ ደግሞ ለኤርትራ ኣርነት ግንባር (ሻዕቢያ) እጁን ሠጥቶ የሻዕቢያ የጦር ምርኮኛ የሆነ ነው። አባዱላ በኋላ ላይ ወያኔ ለዓላማው አስፈጻሚነት እንዲጠቀምበት ከሻዕቢያ የተሠጠ ሲሆን በወያኔ ዘመን በወያኔ ትእዛዝ ከኦሕዴድ መስራችና መሪዎች አንዱ ሆኖ ያገለገለ ነው። ግርማ ብሩም በደርግና በኢሕዲሪ አገዛዝ ወቅት ከፍተኛ የሲቭል ባለሥልጣን ሆኖ ያገለገለ ሰው ነው። ሁሉትም ሰዎችና መሰሎቻቸው የተሓህት/ወያኔ ምርጥ አሽከሮችና ጉዳይ አስፈጻሚ የነበሩ የኦሮሞ ዘውግ ተውላጆች ናቸው። እነ ለማ መገርሳና ዓብይ አህመድ ደግሞ የወያኔው ጥፍጥፍ ኦሕዴድ ኰትኩቶ ያሳደጋቸው የወያኔ ኢሕኣዴግ የፖለቲካና የፀጥታ ሹሞች የነበሩና ወያኔን ከድተው የወያኔ ኢሕኣዴግን ወደ ኦሕዴድ ኢሕኣዴግነት የቀየሩና የለውጥ አራማጆች እየተባለላቸው ሰዎች ናቸው።

በደቡብ ሕዝቦች ድርጅት ተብዬው በደሕዴድ ግን ይህን ያህል የጎላ የሥልጣን ንጥቂያ ቁርቁስ ተከስቶ አልታዬም። ዳሩ ግን የተሓህት/ወያኔ መጋዣ የነበሩትን፣ እንደነ ሽፈራው ሽጉጤና መሰሎቹ የመሰሉቱ ለዓብይ አህመድ የጎረበጡትን የማራገፍ ተግባር ተከናውኖበታል። ደሕዴድ የብዙ ጎሳዎች ስብስብ በመሆኑ በባህርታዊነቱ ለኢትዮጵያዊነት ተምሳሌት መሆን ይችል የነበረ ድርጅት ነው። ዳሩ ግን አመራሩ እንደነ ሽፈራው ሽጉጤ እና ኃይለ-ማርያም ደሳለኝ ዓይነቶች በአንድ ቀን ውስጥ ብቻ እጃቸውን በመቶዎች ደም የሚታጠቡ የአገር ነቀርሳና ማፈሪያ የሆኑ ጸረ ሕዝብና ፀረ-አንድነት ግለሰቦች፣በመያዙ አቅምም ሆነ እርባና ሳይኖረው የኖረነው። አሁንም ቢሆን በአገራዊ ፖለቲካው መድረክ ላይ አሻራ ሊተዉ የሚችሉ ተፎካካሪ ግለሰቦች ባለማፍራቱ በውስጥም ሆነ በውጭ እንደኮሰመነና የመበታተን አደጋ አጥልሎበት ያለ ድርጅት ነው።

በወያኔ ተፈብርኮና ኢሕዴን ተሰኝቶ የቆየው በብኣዴን /አዴፓ የተከሰተው ጉዳይ ግን ከሌሎቹ የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች ለየት ያለ ነው። ብኣዴን የኢሕኣፓ ከጂዎችን፣ የቀድሞው የመከላከያ ሠራዊት አባላት የነበሩ ሠራዊቱን የከዱና በወያኔና በሻዕቢያ የተማረኩ ምርኮኞችን፣ በየህወሓት/ወያኔና የሻዕብያ ጸረ – የኢትዮጵያ አንድነትና “የአማራ” አገዛዝ ትግል አምነው በድርጅቱ የታቀፉ የአማራና የሌሎች ድርጅት ያልተፈጠረላቸው ጐሳዎች ተወላጆችን … ወዘተ ለቃቅሞ ወያኔ የጠፈጠፈው ድርጅት ነው። ብኣዴን ኢሕዴንነቱን ወደ ብኣዴንነት በወያኔ የተቀየረለት በአማራ ሕዝብ ስም ተሰይሞና በአማራ አካባቢዎች ላይ ተሰማርቶ የወያኔንና በፍቅራቸው ዘመን ደግሞ የሻዕቢያንም ዓላማ ለማስፈጸምና አማራን ለማፈን እንዲመች ታስቦ ነው። ይህ ድርጅት በጎንደር ከተማ ደምቆ እስከተንቦገቦገው ጸረ-ወያኔ ህዝባዊ አመጽ ድረስ የወያኔ ጉዳይ አስፈፃሚነቱን ከሚገባው በላይ ሲወጣ የቆዬ ጸረ-ኢትዮጵያዊነትና ፀረ-አማራ ድርጅት ነው።

ብኣዴን በመላው አገሪቱ ሊባል በሚችል ደረጃ በተቀሰቀሰው ፀረ-የወያኔ/ኢሕኣዴግ አገዛዝ ሕዝባዊ ተቃውሞና በአማራ ሕዝብ ትግል ግፊት ውስጣዊ መናጥ ደርሶበት ከፍተኛ ቡድናዊ የሥልጣንና መለስተኛ የአመለካከት ፍትጊያ ተቀስቅሶበት ቆይቷል። የአዴፓ ውስጠ-ድርጅታዊ ቡድናዊ የሥልጣን ፍትጊያ በአመራር ላይ የነበሩትን የአማራ ነገድ ተወላጅ ያልሆኑትን እነ በረከት ስምዖንንና ከእነሱ ጋር የቦደኑትን አማራዎች ጠራርጎ በማስወገድ በእነ ገዱ አንዳርጋቸውና ደመቀ መኰነን የበላይነት የተጠናቀቀ ይመስላል። በአዴፓ ውስጥ በእነዚህ ሁለት ቡድኖች መካከል የተፈጠረው ልዩነትና ግጭት መነሻው በቡድኖቹ በተጠቃለሉት የድርጅቱ የተለያየ እርከን የአመራር አባላት መካከል የተፈጠረው የማይናቅ የአመለካከትና የአቋም ልዩነትና በዋናነት ደግሞ የሥልጣን የበላይነት የመያዝ ትግል ነው።

የእነ በረከት ስምዖን ዓላማ የኢትዮጵያን ሕዝብ አንድነትን እጅግ እየጐዳ ያለውን በመለስ ዜናዊ የተዘጋጀውና በሁሉም የኢሕኣዴግ አባል ድርጅቶች ውስጥ ባሉና በነበሩ ጓዶቹ ተቀባይነት ያገኘውን አብዮታዊ ዴሞክራሲ የተባለውን ስሁት ፖለቲካዊ ርዕዮት ማስቀጠል ነው። ይህ ርዕዮተ-ዓለም በተግባር ላይ የዋለው አሁን ኢትዮጵያ እየተገዛችበት ያለው አዋኪና በጥባጭ ህገ መንግሥት (ህገ-ኢሕኣዴግ) ነው። ይህ የጥፋት ህግ እነ መለሰ ዜናዊ (ህወሓት)፣ እነ ኢሳይያስ አፈ-ወርቅ (ሻዕብያ) እና እነ ሌንጮ (ዮሓንስ) ለታ (ኦነግ) በጋራ የተስማሙበትና የቀመሩት፣ የኢትዮጵያን ሕዝብ ከፋፍሎ ለመግዛትና ለመመዝበር፣ የአገሪቷ አንድነትም ”እንጥስ ቢሉት ብጥስ” የሚል እንዲሆን ለማድረግ ታስቦ የተቀመረ ነው። ከዚህ በላይ ደግሞ ብቁ ልጆች ያጣ ይመስል ከዚህም ከዚያም ተለቃቅመው በኣማራ ላይ የተጫኑበት የእነዚህ ሰዎችና የወያኔና ከአፈነገጡት ውጭ በሌሎቹ የኢሕኣዴግ አባል ድርጅቶችና በአጋር ተብዮዎቹም ጭምር ያሉ የወያኔ ሸሪኮች ዋና ግብ አማራው ባለፉት 27 ዓመታት እየተፈጸመበት ያለውን ግፍና ፍጅት ለማስቀጠልና የወያኔ የበላይነትን እንዳለ ሳይጓደል መጠበቅ ነው።

እነ በረከትን ተፃርረው የቆሙት ደግሞ እነ ገዱ አንዳርጋቸውና ደመቀ መኰነን ናቸው። እነ ገዱ አንዳርጋቸው ላለፉት 27 ዓመታት የተፈጠሩበትን የአማራ ክልል ሕዝብን ክደው፣ እንኳን በራስ ሕዝብ ላይ በጠላት ላይ እንኳ ሲፈጸም የሚሰቀጥጥ ግፍ እያካሄዱ/እያስኬዱ፣ አጥቅተው ለአጥቂ የሰጡት ሰዎች ናቸው። በአሁኑ ወቅት ደግሞ ሲያፍኑት፣ ሲያምቁትና ሲያሰቃዩት የነበረው የአማራ ክልል ሕዝብ ግፍና መከራ በቃኝ ብሎ በመነሳቱ፣ ለሲሦ ምዕተ-ዓመት ያገለገሉትን ወያኔን ክደው፣ የሕዝቡን ጥያቄ ቀምተው የወያኔ የበላይነት ያብቃ! የሚል አመለካከት ማራመድ ጀምረዋል። እዚህ ላይ በእርግጥ በአማራ ሕዝብ በተለየ፣ በአጠቃላይ ደግሞ በመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ የተፈፀመውን መከራና ግፍ ለመረዳት፣ የአገሪቱ ህልውና ክፉኛ አደጋ ላይ መውደቁን ልብ ለማለት 27 ዓመት ይፈጃል ወይ!? የሚለው ሃቅ ፈላጊ ጥያቄ ሊነሳ ይችላል፤ ይገባልም። ነገር ግን ይህንን ጥያቄ በይደር አቆይቶ አሁን በያዙት አካሄድ ላይ ቢተኮር፤ ይህ የህዝቡን ጥያቄ ተቀብለውም ይሁን በሕዝባዊው ማዕበል ከመጠራረግ ለመዳን ዘይደው የወሰዱት አቋም ከእነ በረከት ጋር ጦርነት ውስጥ ሊከታቸው የግድ ነበር። ይህንንም የሕዝብ ጥያቄ ለማራመድ የሥልጣን የበላይነትን ማረጋገጥ የግድ ነበረና ቦድነው ታግለው፣ በኮ/ል ዓብይ ቡድንም ታግዘው ይህንኑ እውን አድርገዋል።

በእያንዳንኑ ድርጅት ጓዳ ውስጥ ያለውን ሁኔታ ለጊዜው ተወት አድርገን በኢሕአዴግ ላይ ስናተኩር በአባል ድርጅቶች መካከል ፈጽሞ ሊታረቅ የማይችል ቅራኔ የተፈጠረ መሆኑን እንታዘባለን። በመካከላቸው ያለው ቅራኔ ደግሞ የሥልጣን ጥያቄ፣ የፖለቲካ አመለካከት ልዩነት፣ የምጣኔ ሃብት ተጠቃሚነት ጥያቄና የአወቅሁሽ ናቅሁሽ እልህ ያካተተ በመሆኑ ሊታረቅ ከሚችል ፍጭው ግጭው በጣም የራቀ ነው። እነ ዓቢይ ከእነ ገዱ ጋር ውስጥ ለውስጥ ሲያደራጁት የከረሙት ኃይል አንቀሳቅሰው አለቅጥ ተኰፍሶ ሲያንቀላፋና በዘረፋና ስርቆት ተጠምዶ በነበረው በጠባብ ጎሰኛው ወያኔ ላይ ጥቃታቸውን እያጧጧፉት ነው። የዓብይ ቡድን በባዕዳን እየታገዝ፣ በሳውዲ ዓረቢያና እና በኳታር ኒሻንና ብር እየተምነሸነሸ፤ ከኪነ-ጥበብ ሰዎች፣ ከምሁራን … ወዘተ የራሱ የሆኑ ቡድኖች አደራጅቶ እያንቀሳቀስ፣ የእናት ጡት ነካሹን የኤርትራን ሕዝብ በግፍ እየገዛና እያፈለሰ ያለውን ፋሽስቱን ኢሳያስ አፈወርቅን ከጎኑ አሰልፎ ጥቃቱን ያለማሰለስ በእንቅልፋሙ ወያኔ ላይ እየፈጸመ ነው። ወያኔ በበኩሉ ተደናግጦና ተደናብሮ የሰነበተ ቢሆንም ጥቃቱን ለመመከትና ከቻለም መልሶ ለማጥቃት እየመከረና እየተነታረከ መሆኑ ከውስጡ የሚያፈተልኩ ወሬዎች ይጠቁማሉ። ፍንጮቹ እንደሚያመለክቱት ከሆነ የወያኔ አመራር የዓብይን ጥቃት ለመመከትና መልሶ ለማጥቃት በሚያደረገው ማሰላሰል ውስጥ በሦስት ኃሳቦች ተከፋፍሏል። እነዚህ ኃሳቦች ምንድን ናቸው?

በመጀመሪያ ደረጃ በወያኔ ዕይታ የዓብይ አህመድ ቡድን የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ዓላማና መስመርን ክዷል፣ ህገ-መንግሥቱን ረግጧል፣ ኢሕአዴግ ን እያዳከመ ነው። የራሱን ተክለ-ሰውነት እየገነባ ያለ ሕዝበኛ ነው። ጸረ የትግራይ ሕዝብ ነው። የብሔር/ብሔረሰቦች መብቶችን እየረገጠ ነው። ስለዚህ መገታት አለበት! ይህ የሁሉም ወይም የአብላጫው የወያኔ አመራርና አባላቱ እንዲሁም የትግራይ ሊህቃን የጋራ ድምዳሜ ነው። የኃሳብ ልዩነቱ የሚመነጨው እሱን የመግታቱ ተግባር እንዴት ነው ሊተገበር የሚችለው የሚለው ላይ ነው። እላይ ጠቆም እንደተደረገው በዚህ ጥያቄ ዙርያ ወያኔዎች እና የትግራይ ሊህቃን በሶስት አመለካከቶች ተከፍለዋል።

አንደኛው አማራጭ ኃሳብ ዓብይንና ቡድኑን በኃይል ከሥልጣን ማስወገድ አለብን የሚለው ነው። ይህ ኃሳብ የተቀሩትን “የመፍትሄ” ኃሳቦች ከሚያቀነቅኑት ወገኖች በኩል ከፍተኛ ተቃውሞ ደርሶበታል። ይህንን ኃሳብ የተቃወሙት ወገኖች የተለያዩ የመከራከሪያ ነጥቦች ሰንዝረዋል። ከነዚህ መከራከሪያ ነጥቦች አንዱ ዓብይንና ቡድኑን ለማስወገድ ኃይል ከተጠቀምን ምዕራባዊያን መንግሥታትና የአረብ አገሮች በዋናነት ሳውዲ አረቢያና ሸሪኮዎቿ የተለያየ የማግለልና የምጣኔ ሃብት ጥቃት ይፈጽሙብናል የሚል ስጋት ነው። ሁለተኛው ነጥብ አብዛኛው የኦሮሚያ ክልል እና የአማራ ክልል ሕዝብ ፣ ከሌሎችም ክልሎች ውስን ሊሆን ቢችልም ሕዝብ ስለሚደግፋቸው ይህንን ብናደርግ ሕዝቡ ይነሳብናል፤ ይህም ከቁጥጥራችን ውጭ ወጥቶ የእርስ በእርስ ጦርነት ሊያስነሳ ይችላል። እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ከተከሰተ ከትግራይ ውጭ ያሉት ተጋሩን ለአደጋ ያጋልጣል፣ የባዕዳን ውግዘትም ይቀሰቀስብናል የሚል ነው። ሶስተኛው አሁን ባለው ሁኔታ ውስጥ ሆነን ከዓብይ ቡድን ጋር ግጭት ውስጥ ከገባን በዓብይ ቡድንና በአረብ አገሮች ትብብር ከፖለቲካዊ የሙታን ዓለም ለትንሣኤ የበቃው የኢሳያስ አፈወርቅ መንግሥትም ከነ ዓብይ ጋር አብሮ ሊወጋንና በሁለት ግንባር ልንጠቃ እንችላለንና አደገኛ ነው የሚል ነው።

የኃይል መጠቀም አማራጭ የሚያቀነቅኑ ወገኖች በበኩላቸው ተግባሩ በአንድ አማፂ ወይም አፈንጋጭ ኃይል የተፈጸመ በማስመሰልና ተግባሩን በግንባር ቀደምነት በማውገዝ፣ እንዲሁም ሂደቱን በማያጨናግፍ መንገድ ለእነ ዓብይ ድጋፍ በመስጠት በጉዳዩ የሌለንበት ማስመሰል ስለሚቻል የምዕራባዊያኑንም ሆነ የአረቦቹን ወይም የኢትዮጵያ ሕዝብን ተቃውሞና ትኩረት ማስወገድ ይቻላል የሚል መከራከሪያ በማቅረብ ይሞግታሉ። የዚህ ሃሳብ አቀንቃኞች የም ዕራባዊያን ጣልቃ ገብነትና ማዓቀብ እንደ ምክንያት ማቅረብ መለስ በሆነ ምክንያት የኢሳይያስን መንግሥት ከጥፋት ያዳነበት ሰንካላ ምክንያት ነው በማለት ያጣጥሉታል። የኢሳያስን ጉዳይ በተመለከተ ደግሞ ድሮውም ቢሆን በኛና በሻዕቢያ መካከል የተፈጠረው ግጭት እጅግ የተሳሳተና ፈጽሞ ሊከሰት የማይገባው ነው፤ የብሔራችን አባል የሆነውን አብዛኛውን የኤርትራን ሕዝብ በነፍጠኞችና ትምህክተኞች አመለካከት ተበክለንና ተሸንፈን ጎድተነዋል። ስለዚህም ከፍተኛ ጥረት አድርገን የእርቅ እርምጃ በማከናወን የብሔራችንን አንድነት ማጠናከር ከቻልን ችግሩን ለዘለቄታው ለመፍታት ይቻላል፣ ለጊዜውም ቢሆን አሁን በተፈጠረው የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትና መቀራረብ ምክንያት ይህ ችግር የመከሰት ዕድሉ መናኛ ነው የሚል መሟገቻ በማቅረብ ይህንን ስጋት ያጣጥላሉ።  በኃይል እርምጃ አቀንቃኞች ዕይታ፣ አስፈላጊው ድጋፍና ትብብር ከተደረገላቸው እነ ኦነግም በዚሁ ነገር ሊስማሙና በኦሮሚያ ውስጥ ዓብይና ጓደኞቹ ያላቸውን ድጋፍ የማዳከም ሥራ ሊሰሩ እንደሚችሉ ያምናሉ። የዚህ አማራጭ ኃሳብ አራማጆች እላይ በተዘረዘሩት ምክንያቶች ዓብይንና ጓደኞቹን በኃይል ማስወገድ ፈጣን መፍትሄ የሚሰጥና መዘዙ ያነሰ ነው በማለት ይከራከራሉ።

ሁለተኛው የዓብይንና ቡድኑን (ቲም ለማን) የመመከትና ከሥልጣን የማስወገድ አማራጭ ኃሳብ የሹሙንና ጓዶቹን ሥልጣን መገደብና መንጠቅ ወይም ማሳጣት የሚቻለው ኢሕአዴግን በማዳከምና በማፍረስ ነው የሚል ነው። በዚህ ኃሳብ አራምጆች አመለካከት በመጀመሪያ ደረጃ ኢሕአዴግ ከአብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ መስመር. አፈንግጧል። ሁለተኛም የአድርባይ የአማራ ተወላጅ ሕዝበኞችና የኦህዴድ/ኦዴፓ አመራሮች መፈንጫና የግል አላማ ማራመጃ ሆኗል። ሦስተኛ፤ በእነዚህ ሁለት ምክንያቶች ኢሕአዴግ ከስሙ በስተቀር እንደ ኦህዴድ ሞቷል። ሕይወት አለው ቢባል እንኳ የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን መብት የሚደፈጥጥ የፍጹም አኃዳዊት ዓላማ አራማጅ የመጨቆኛ መሳሪያ ከመሆን አያልፍም። ስለዚህ ኢሕአዴግን በማዳከምና በማፍረስ፣ ከኢሕአዴግ ውጭ ካሉ የብሔርና የብሔር ያልሆኑ ድርጅቶች ጋር በመተባበርና የጋራ ግንባር በመፍጠር የዚህን ሕዝበኛና የሥልጣን ጥመኛ ብለው የሚከሱትን ቡድንን ዓላማ ማምከንና ማስወገድ የተሻለና ብዙ ችግር የማያመጣ አማራጭ ነው ብለው ያምናሉ።

ዳሩ ግን ይህንን ኢሕአዴግን የማዳከምና የማፍረስ አማራጭ የሚቃወሙ የወያኔ አባላትና የትግራይ ሊህቃን አሉ። እነዚህ ወገኖች አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ኢሕአዴግን ለማዳከምና ለማፍረስ መንቀሳቀስ የኢሕአዴግን መስመር ለካደው የእነ ዓብይ ቡድን ዱላ ማቀበል ነው ብለው ይሞግታሉ። በዚህ ሃሳብ አቀንቃኞች አመለካከት ወያኔ በዚህ መንገድ ከተንቀሳቀሰ እነ ዓብይ ወያኔን አግደው፣ ቀሪዎቹን አባል ድርጅቶች አሰተባብረው እና አጋር ድርጅቶችን በሆነ ቀመር አካትተው የበለጠ ጠንካራ ሊሆኑና የበለጠ ወያኔንም ሊያስነጥሉና ሊያጠቁ ይችላሉ ብለው ያምናሉ። እነዚህ ወገኖች እንኳንስ እንዲህ ዓይነት እርምጃ ወስደን ይቅርና ባናደርግ እንኳን እነ ዓብይ ህወሓትን ከኢሕኣዴግ ለማስወጣት ጥረት ማድረጋቸው አይቀርም ብለው ይሞግታሉ፤ ዓብይና ቲምለማ ባጠቃላይ ህወሓትን ለማስኰረፍ ሆን ብለው ብዙ ህወሓት የሚቃወማቸውን ኃሳቦችና ተግባራት እያራመዱ ያሉ መሆናቸውን እንደ ማረጋገጫ ያቀርባሉ።

ይህንንን ስጋት የሚያጣጥሉ ኃይሎች፣ አነስተኛ የሕዝብ ቁጥር ያላቸው ብሔሮችና ሕዝቦችን አስተባብረን በመንግሥት መዋቅር ውስጥ የላቀ ውክልና እንዲኖራቸውና ይህም የሕዝብ ብዛትን መሠረት ባደረገ ኮታ ሳይሆን በብሔሮችና ሕዝቦች እኩል ውክል እንዲሆን ከታገልንና ካረጋገጥን፣ በምጣኔ ሃብት ሽርክና የኢኮኖሚ ሁኔታቸውን ካሻሻልንላቸው፣ … ወዘተ አጋር ድርጅቶችም ቢሆኑ ስትራቴጂያዊ ውግናቸው ከህወሓት/ወያኔ ጋር ይሆናል ብለው ይከራከራሉ።

ሦስተኛው ወገን ትግራይን መገንጠልና ለሌሎች ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የሁለቱን ትልልቅ ብሔሮች አፋኝ የመሆን አደጋን በማሳየት የነፃነት መንገድ እንዲመርጡ ማድረግ ብቻ ነው አማራጩ ባይ ናቸው። እንደነዚህ ወገኖች አመለካከት አሁን ያለው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሁኔታ ለህወሓት ለድርጅቱ ብቻ ሳይሆን ለትግራይ ሕዝብም አደገኛ ነው። በእነሱ እምነት ዓብይ አህመድ ንጉሥ የመሆን ቅዠት ተጣብቶት፣ ለዚህ ግቡ መሳካት ማንንም ጭዳ ለማድረግ ቆርጦ የተነሳ ሕዝበኛና አድርባይ ግለሰብ ነው። ዓብይ እራሱ እንደተናገረው በትግራይ ሕዝብ መሀል ኖሮ ጥንካሬውን፣ የዓላማ ጽናቱንና ከመሪ ድርጅቱ ከህወሓት ጋር ያለውን ቁርኝት አበክሮ ልብ ብሏል። በተጨማሪም የትግራይ ሕዝብ በግንባር ቀደምነት ታግሎ እና እጅግ ከፍተኛ መስዋዕትነት ከፍሎ ያመጣውን የሕዝቦች እኩልነት ለድርድር የማያቀርብና ለአምባገነኖችም የሚጎረብጥ መሆኑን ተገንዝቧል። ስለዚህ የሥልጣን ጥማቱን ለማርካትና ወደዚያ የሚያበቃውን ድጋፍ ለማግኘት፣ እንቅፋት ይሆኑኛል ያላቸውን ህወሓትንና የትግራይን ሕዝብ ለማጥቃትና ለማሸማቀቅ ቆርጦ ተነስቶ በተግባር እያሳየ ነው። ይህንንም ተግባር የሚፈጽመው የድሮ ሥርዓት ርዥራዦችን፣ ትምህክተኞችን፣ ጠባቦችን እና በትግራይ ሕዝብና በመሪ ድርጅቱ በህወሓት ላይ ከፍተኛ ጥላቻ ያላቸውን የባዕድ ኃይሎችን ለማስደሰት፣ በዚያም በኩል ርካሽ ተወዳጅነትና ድጋፍ ለማገኘትም ጭምር ነው። ዓብይ የትግራይ ሕዝብንና ህወሓትን ምን ያህል እንደሚጠላና እነሱንም ለማስጠላትና ጥርስ ውስጥ ለማስገባት ከሚያደርጋቸው ጥረቶች ውስጥ በአክሱም መስጊድ ስለ መሥራት ጉዳይ አስመልክቶ ለቀረበለት ጥያቄ የሰጠው መልስ፣ በአሜሪካ ጉብኝቱ ወቅት የትግራይ ተወላጅ የሆኑ ግለሰቦች ላቀረቡለት ጥያቄ የተጠቀመበት የአመላለስ ዘይቤ፣ የተጠቀማቸው ቃላትና አነጋገሩ፤ ኢሕኣዴግ በጋራ የወሰነውን የዕርቅና የይቅርታ መንገድን አምታትቶና ወገኖቹን ለማዳኛና በዋናነት የአንድ ብሔር አባለት የሆኑ የሚቃወሙትን ወገኖች ማጥቂያ መሳሪያ እያደረገ ያለበት ሁኔታ እንደ ምሳሌ መጥቀስ በቂ ነው ይላሉ።

በእነኝህ የሦስተኛው አማራጭ አራማጅ ወገኖች ዕይታ ዓብይን ለሥልጣን ለማብቃት በኦህድዴ/ኦዴፓ ውስጥ በህቡዕ ከተደራጀው የለማ መገርሳና ዓብይ አሕመድ ቡድን ያልተናነሰና ምናልባትም የበለጠ ሚና የተጫወተው የአድርባዮቹ የደመቀ መኰንንና የገዱ አንዳርጋቸው ቡድን ነው። እነዚህ ሁለት ግለሰቦችና ቡድናቸው፣ በጭቁኑ የአማራ ሕዝብ ውስጥ ለተሰገሰጉና በእሱ ስም ለሚነግዱ የቀድሞው ሥርዓት ርዝራዦች፣ ትምህክተኞችና ጠባቦች ግፊትና ጫና ተንበርክከው ነው በዚህ ተግባር ላይ የተሰማሩት። ከዚህ በተጨማሪ የገዱና ደመቀ ቡድን አባላት የሥልጣን ጥማቸውን ለማርካት በማለም ሲምሉለት የነበረውን የአብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ መስመር በመካድ ነው በአድርባይነት ለለማ መገርሳና ለዓብይ አሕመድ ቡድን ለማገልግል ያጎበደዱት። የሦስተኛው አማራጭ አቀንቃኞች የብኣዴን/አዴፓ ሕዝበኛና ትምህክተኛ አድርባይ የአመራር አባላት ያላቸው ታዛዥነትና አገልጋይነት ለማረጋገጥ የእነ ዓብይ ቡድን ለኦሕዴድ የመረጠውን ስም እስከመኮረጅ የሄዱ አሳፋሪ መጋዣዎች ናቸው ብለው ያምናሉ። ለእነዚህ ወገኖች እነ ገዱና ደመቀ ድሮዉኑም ቢሆን ሲጠገኑና ሲደጐሙ የኖሩ፣ የዓላማ ጽናት የሚጎድላቸው፣ ጥቅመኞችና አድርባዮች ስለሆኑ የዓብይ አሕመድን ቡድን ትዕዛዝ ከመፈጸም ያለፈ ሚና አይኖራቸውም፤ በእርግጥ ሌላ የፈረጠመ ኃይል ያለው ወገን ከተከሰተ እጥፍ ብለው ለዚያም መነጠፋቸው የማይቀር ነው ብለውም ይሞግታሉ። አማራጩ ትግራይን ማስገንጠል ብቻ ነው በሚሉት በእነዚህ የሦስተኛው አማራጭ አቀንቃኞች ዕይታ እንደነ ደመቀና ገዱ በመሰሉ ሕዝበኛና ጥቅመኛ የሆኑ አድርባዮች፣ ጠባብና ትምህክተኛ ሰዎች የሚመራው ብኣዴን/አዴፓ የተካተተበት ኢሕአዴግ የእነ ዓብይ ዓላማ አራማጅ ከመሆን ያለፈ እርባና አይኖረውም፣ ስለዚህ በኢሕአዴግ ውስጥ በኃሳብ የበላይነት ማምጣትና ለሕዝብና ለሀገር የሚበጅ ዓላማ ለማራመድ ማሰቡ ከንቱ ቅዠት ነው። በእነዚህ ወገኖች አመለካከት እነ ገዱ/ደመቀ ደግሞ የሌሎች ትምህክተኞችና ጠባቦችን አጀንዳ ቀምተውና የዚህ ዓላማ ግንባር ቀደም አራማጅ ሆነው፣ የአማራን ሕዝብ በማደናገርና በተሳሳተ መንገድ በትግራይ ሕዝብ ላይ በማነሳሳት ተግባር ላይ ተጠምደው ያሉና ከዚህም የዕብዶች ገበያ እያተረፉ ስለሆነ ከዚህ የተሳሳተ አካሄድ ታርመው ለጋራ ሀገራዊ ጥቅም የሚቆሙበት ሁኔታ የመፈጠር ዕድሉ በጣም የኮሰመነ ነው። በዚህ በሦስተኛው አማራጭ አራማጆች እምነት በተገለጹት ምክንያቶች የትግራይ ሕዝብና መሪ ድርጅቱ በአገራችን የፖለቲካ ምህዳር ውስጥ እየተፈጸመባቸው ያለው የማጥላላት፣ የመነጠልና የማጥቃት ተግባር ተጠናክሮ መቀጠሉ የማይቀር ነው። በእነዚህ ወገኖች ዕይታ የተለያዩ ብሔር፣ በሔረሰቦችና ሕዝቦችን ወክለው የተደራጁ በጋራ የመሰረቱት ግንባር (ኢሕአዴግ) ሲመራው የነበረው መንግሥት አጠፋቸው የሚባሉ ጥፋቶችን በትግራይ ተወላጆች ላይ ብቻ የማላከክ ሙከራና ዘመቻው የዚህ ተግባር ዓብይ ምሳሌ ነው።

ከዚህ ላይ ደግሞ በእነዚህ ወገኖች ዕይታ ይህ አሁን ሥልጣኑን ተቆጣጥሮት የሚገኘው ቡድን በድንገተኛ የምርጫ ውጤት ሥልጣን ማማ ላይ ለመውጣት የበቃ ሳይሆን የረጅም ጊዜ ዝግጅት አድርጎና በልዩ ልዩ የኢሕአዴግና የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ጠላቶች ተረድቶ የመጣ ኃይል ነው። በእነኝህ አመለካከት ይህን ኃይል ወደ ሥልጣን ለማምጣት የደርግ መንግሥት ባለሥልጣኖች የነበሩ፣ አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ መስመርን የሚቃወሙ ኒዮሊብራሊስት ምዕራባዊያን ኃይሎች፣ በቀይ ባህርና በአካባቢው የሚገኙ የአረብ ሀገሮች፣ የሻዕቢያ መንግሥት፣ በአንድነት ስም የተደራጁ አክራሪ አንድነታዊያን ተቃዋሚ ኃይሎችና ግለሰቦች ጭምር ግንባር ፈጥረው ታግለውለታል። ትግራይን የማስገንጠል ሃሳብ በሚያቀነቅኑት ወገኖች አመለካከት ይህ በሥልጣን ላይ ያለው ቡድን የሥልጣን ጥመኛ ብቻ ሳይሆን የኢሕአዴግንም ዓላማና የአብዮታዊ ዴሞክራሲ መስመርን የሚቃወም፣ የአዲሱ ሊብራሊዝም አመለካከትን አንግቦ የተነሳ፣ በምርጫ ሊስተካከልና አብረኸው ልትቀጥል የማይቻል ቡድን ነው። እንደ የመገንጠል አማራጭ አቀንቃኞች አመለካከት፣ ምንም እንኳን የዓብይ ቡድን ሙስናንና ጭቆናን እየደጋገመ ቢኰንንም፣ ዘመቻው በሁሉም መዝበረዋል፣ ግፍ ፈጽመዋል በሚባሉ ግለሰቦችና ድርጅቶች ላይ ላይ ከማተኮር ይልቅ መደመር በሚባለው ትርጉም አልባ ንድፈ ሃሳብ አማካኝነት የተንበረከኩለትን በመተው፣ ይቃወሙኛል ባላቸው በአብላጫው የትግራይ ብሔር ተወላጆች በሆኑ ግለሰቦች ላይ አነጣጥሯል። ይህም ጸረ ትግራይ ሕዝብና መሪ ድርጅቱ ዘመቻ በኦህዴድ/ኦዴፓ እና በብኣዴን/አዴፓ ትብብር፣ በሻዕቢያ ድጋፍ እየተካሄደ ነው ይላሉ። ስለዚህም የትግራይ ሕዝብ ነፃ ሀገር መስርቶ ክብሩንና ነፃነቱን ማረጋገጥ እና ከሁሉም የነፃነት ኃይሎች ጋር የጋራ ትግል በማካሄድ በመላው ምሥራቅ አፍሪካ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ነፃነት እንዲከበር መሥራት አለበት፤ እንደ እነሱ አተያይ።

ይህን ትግራይን ገንጥሎ ነፃ ሀገር የመመሥረት ሃሳብ በመሠረተ ኃሳቡ ደግፈዉት ሲያበቁ በተለያየ ምክንያት አማራጩን የማይደግፉ ወገኖችም አሉ። በእነኝህ ወገኖች ዕይታ አሁን ባላው የምጣኔ ሀብትና የፖለቲካ ሁኔታ ጥያቄው ተቀባይነት ሊያጣና የሀገርነት ዕውቅና ማግኘት የማይቻል ይሆናል። ከዚያም አልፎ በዓብይና ጓደኞቹ የሚመራው መንግሥት ትግራይን ሊወር ይችላል ብለው ያምናሉ። የበለጠ ስጋታቸው ደግሞ ዓለም አቀፍ ዕውቅና የማግኘት ዕድሉ በጣም የጠበበ ሊሆን መቻሉ ነው። ይህም በእነ ዓብይ አሰናካይነት ሊጋረጥ ይችላል ብለው ያስባሉ። የዓብይ አሰተዳደር የወረራ ሙከራ ሊያደርግ ቢችልም መመከት ብዙም አስቸጋሪ እንደማይሆንና መልሶ ማጥቃትም እንደሚቻል ያምናሉ። በእነሱ ዕይታ አሳሳቢ የሚሆነው ነገር ከዚህ ጋር ተያይዞ ሊከተል የሚችለው የውጭ ኃይሎች ተፅዕኖና ጣልቃ ገብነት ነው።

ሌላው የዚህ ሶስተኛ አማራጭ ተቃዋሚዎች ስጋት እንደዚህ ዓይነት ሁኔታ ቢከሰት ከትግራይ ውጭ ባለው ትግራዋይ ህይወትና ንብረት እና የትግራይ ሕዝብ ንብረት ላይ ሊደርስ የሚችለው አደጋ ነው። በእነዚህ ወገኖች እምነት እንኳንስ ወደ ግጭት ተገብቶ፣ አሁን እንኳን በትግራይ ተወላጆች፣ በትግራይና በህወሓት ላይ እየተፈጸመ ያለው ጥቃት፣ ማጥላላት፣ መነጠልና ማሸማቀቅ እጅግ ከፍተኛ ነው። የትግራይ ምርቶች ላይና በሚያስፈልጓት ነገሮች ላይ ሊጣል የሚችለው ማዕቀብ ደግሞ ሌላው የሥጋት ምንጭ ነው።

የመገንጠል ዓላማ ተቃዋሚዎች ሌላኛው ስጋት በትግራይና በኤርትራ መካከል ያለው የሻከረ ግንኙነት ነው። እንደነዚህ ወገኖች አመለካከት የኤርትራ ሕዝብ በአምባገነን አገዛዝ ሥር ያለና ፍላጎቱን መግለጽ የተከለከለ ነው ። አሁን ደግሞ የዓብይ ቡድን ለሥልጣን ለመብቃት የሚያስፈለገውን ድጋፍ በመሻት ምክንያት የኤርትራ ሕዝብ ሁኔታ ምንም ሳይገደው አምባገነኑን የኢሳያስ አገዛዝ ከመቃብር አውጥቶ ነፍስ ዘርቶበታል። በዚህ ሁኔታ የኢሳያስ አገዛዝ በትግራይ ሕዝብ ላይ የጥላቻ ዘመቻውን አጠናክሮ በዋናነት የአንድ ብሔር አባላት የሚገኙባቸውን የሁለቱን አካባቢዎች ሕዝቦች እንዳይቀራረቡና የብሔር አንድነታቸውን እንዳያጠናክሩ ሊሰራ ይችላል። በተጨማሪም የሁለቱ ክልሎች ነዋሪ የሆኑ የትግራይ ብሔር ተወላጆች አንድነት መጠናከር ለሥልጣኑ አስጊ የሚሆንበት የኢሳያስ አገዛዝ በትግራይ ሕዝብና በአማራ ሕዝብ መካከል ግጭት እንዲፈጠርና ውጥረት እንዲነግስ በማድረግ የትግራይ ሕዝብንና መንግሥትን ለማዳከም መሥራቱ የማይቀር ነው፣ ምልክቶችም እየታዩ ነው። ስለዚህ በእነኝህ ወገኖች እምነት የትግራይ ነፃ መንግሥት ከመመሥረት በፊት በዋናነት የአንድ ብሔር አባል የሆኑ ሕዝቦች የሚገኙበትን የኤርትራንና የትግራይን ሕዝብ አንድነት ማጎልበትና ማደላደል፣ የኤርትራ ሕዝብ የዴሞክራሲ መብቶች እንዲረጋገጡ መጣርና የተፈጸሙ ስህተቶችን በግልጽነት መርምሮ እልባት መስጠት ያስፈልጋል። እነዚህ ወገኖች እነ ዓብይ አህመድ፣ እነ ገዱ አንዳርጋቸውና ኢሳይያስ አጼ ምኒልክ የፈጸሙትን የትግራይ ብሔርን ለሁለት ከፍሎ ማዳከም የሚል ፕሮጄክት እያካሄዱ ነው ብለው ይከራከራሉ።

እንደነዚህ ወገኖች አተያይ የትግራይ መንግሥትና ሕዝብ ከሻዕቢያ ጋር ግጭት ውስጥ የገባው በህወሓት አመራር ውስጥ በተፈጠረው የበለጠ ለኢትዮጵያ ተቆርቋሪ የመሆን አመለካከት ያራምደ ቡድን የተሳሳተ አካሄድ ሰበብ ነው። ይህ መደረግ ያልነበረበት ስህተት ነው። እንደ እነኝህ ወገኖች፣ የትግራይ ሕዝብ አብዛኛው መሰሉ ከሆነው የኤርትራ ሕዝብ የበለጠ ሊቆራኝና አንድነቱን አጠናክሮ ለጋራ ተጠቃሚነት ሊሠሰራ ነው ይገባ የነበረው። የሁለቱን ሕዝብ አንድነት ለማጠናከር በሚደረገው ጥረት ውስጥ እንቅፋት የሚሆን ኃይል ቢፈጠር እንኳን ህወሓት ማድረግ የነበረበት ይህንን ኃይል ማጋለጥና ነጥሎ መምታት እንጂ የትግራይ ወጣት ለነፃነቱ የሕይወት ዋጋ ሳይቀር የከፈለለትን ወንድሙን የኤርትራን ሕዝብን የሚጎዳ ተግባር መፈፀም አልነበረበትም ብለው ያምናሉ።

ከዚህ በላይ ለማብራራት እንደተሞከረው የህወሓትን አመራርንና የትግራይ ሊሂቃን በአሁኑ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሁኔታ ውስጥ የትግራይ ሕዝብና ድርጅቱ ምን ድርሻ አላቸው? ምንስ ድርሻ ሊኖራቸው ይገባል? ምንስ ሊያደርጉ ይገባቸዋል? የትግራይ መፃኢ ዕድል ምን መሆን አለበት? ለሚሉት ጥያቄዎች በሚሰጧቸው መልሶች በዋናነት እላይ በተጠቀሱት ሦስት የመፍትሄ አማራጮች ዙሪያ ተቧድነው እየተከራከሩና እየተወዛገቡ ይገኛሉ። ነገር ግን መንም እንኳን እላይ በተዘረዘሩት ሶስት አማራጮች ማለትም፥ 1ኛ/ የዓብይን ቡድን በኃይል ማስወገድ ይገባል፣ 2ኛ/ ኢሕአዴግ ን አፍርሶ ወይም ጥሎ ወጥቶ ከጥበትና ከትምህክት ከጸዱ የብሔርና የብሔር ያልሆኑ ድርጅቶችና ኃይሎች ጋር ተባብሮ ፌደራላዊ ሥርዓቱን የሚያጠናክርና የሚያስቀጥል ድርጅትና መንግሥት መፍጠር ይገባናል እና፣ 3ኛ/ ትግራይን ገንጥሎ ነፃ ሀገር መመስረትና የሌሎች ብሔሮች፣ በሔረሰቦችና ሕዝቦችም መሰል መብቶች እንዲረጋገጡ መጣር ይገባል የሚሉ ሃሳቦች እየተቀነቀኑ ቢሆንም ከሰሞኑ የመጨረሻው የበለጠ እየጠነከረ መጥቷል።

እርግጥ ነው የትግራይ ሕዝብ እንደ ሕዝብ የአሁኑን የሀገራችንን ሁኔታና መጪው ህይወቱን አስመልክቶ ምን እንደሚያስብ የተደረገ ጥናት ወይም ነፃና ገለልተኛ መድረክ ተመቻችቶለት የገለጸው ነገር የለም። የዚህ ጽሁፍ አቅራቢ ግን ስለዚህ ጉዳይ የህዝቡን አሰተያየት ለማግኘት በተለያዩ አካባቢዎች የሚኖሩ፣ በተለያየ የትምህርትና የህይወት ተመክሮ ያለፉ ጥቂት ሰዎችን አሰተያየት ለማሰባሰብ ሞክሯል። ፀሀፊው ከእነዚህ ግለሰቦች ያገኛቸው አስተያየቶች የትግራይ ተወላጆች አሁን በሀገሪቱ ውስጥ ያለው ሁኔታ ከፍተኛ ስጋት ውስጥ የከተታቸው መሆኑን የሚያመላክቱ ናቸው። የተገኙት አስተያየቶች የትግራይ ሕዝብ የዓብይ ወደ ጠቅላይ ሚኒስቴርነት መምጣትና ማቀንቀን የጀመረው የእርቅ፣ የነፃነትና የፍትህ ዓላማ እኩል ተጠቃሚ ሊያደርገውና እንዲያውም ከትግራይ አልፎ ለሌላው የሀገሪቱ ሕዝብ እንኳን ከተረፈው ክህወሓት ፍፁማዊ እመቃ ይገላግለኛል የሚል እምነት አሳድሮ የነበረ ለመሆኑ ያመላክታሉ። ይህም በሕዝቡ ልብ ውስጥ ተስፋ በመዝራቱ የህወሓት መሪዎችን መገዳደር ጀምሮ የነበረ መሆኑን ይጠቅሳሉ። ነገር ግን ዓብይ ሀገርና ሕዝብን የመምራት አደራና ኃላፊነት ክብደትን ዘንግቶ ከህወሓት መሪዎች ጋር ለመበሻሸቅና እነሱን ለማሸማቀቅ ብቻ በማሰብ የጉዳዩ ዋነኛ ተዋናይ የሆነውን የትግራይ ሕዝብን ፍላጎትና ስሜት ወደ ጎን በመተው ከኤርትራ አገዛዝ ጋር የጀመረውና እስካሁንም የትግራይን ሊሂቃን ብቻ ያገለለ አሸሸ ገዳሜን ከተመለከተ በኋላ ነገሩን በጥርጣሬ መመልከት መጀመሩን ይገልፃሉ። በእነዚህ አሰተያየት ሰጭዎች እምነት ተወደደም ተጠላም ትግራይ በህወሓት ነውና የምትመራውና የምትተዳደረው ህወሓት በሌላ ባልተተካበት ሁኔታ ህወሓትን አግልሎ፣ የብኣዴንን፣ የሶማሌ ክልልን፣ የኦህዴድንና የደህዴንን አመራሮች ብቻ ይዞ፣ ከአምባገነኑ ኢሳያስ መንግሥት ጋር መላላስ ንቀትና አደጋው ለህወሓት ሳይሆን ለትግራይ ሕዝብ ነው። እንደነሱ አመለካከት ከሆነ የዓብይ መንግሥት ህወሓትን ቢጠላና ከህወሓት ጋር የመበሻሻቅ ጥማቱን እንኳን ማርካት ከፈለገ ሌሎች የትግራይ ፖለቲከኞችን ለምሳሌ የዓረና ትግራይን አመራሮች በዚህ ሠርግና ምላሹ ማካተት ይችል ነበር። አላደረገም። እንደነዚህ ሰዎች እምነት ሠረቁና ገደሉ፣ ዘረፉ … ወዘተ ከሚባሉት የህወሓት ሰዎች ያላነሰ ተጠያቂዎች ሊሆኑ የሚገባቸው የኦሮሞ፣ የአማራና የደቡብ ፖለቲከኞች ቢኖሩም ዓብይ ግን እነዚህ ሰዎችን ሲብስ እየሾመና እየሸለመ፣ ሲያንስ ደግሞ እያሞካሸ፣ ወይም ጫፋቸውን ሳይነካ የትግራይ ተወላጅ የሆኑትን ግን አብዝቶ በማሳደድና በማዋረድ ላይ ይገኛል። ይህ ተግባሩ የሚያሳየው ነገር ቢኖር ደግሞ የሰውየው ኃላፊነት የጎደለው አካሄድንና ያው ያሳደገው የኢሕአዴግ አምባገነንነት ትክክለኛ አልጋ ወራሽነቱን ነው ብለው ይሞግታሉ። በዚህ ላይ ደግሞ. ዓብይ በስድቡ፣ በአንጓጣጭነቱና ከሁሉም የበለጠ አውቃለሁ ባይነቱ ቁርጥ መለስ ዜናዊ ብለው ይገልጹታል። እንደ አስተያየት ሰጪዎቹ ዕምነት፤ ማንም አመነም አላመነ ኢሕአዴግ የበለጠ ደም ያስለቀሰው የትግራይ ሕዝብን ነው። ይህ ሕዝብ ደግሞ የህወሓትን የበላይነት በኦዴፓና አዴፓ (ኦህዴድ እና ብኣዴን) የበላይነት ስለተካ ብቻ ኢሕኣዴግ አምባገነንነቱን ይተዋል ብለው አያምኑም ጥቂቶቹ ሁኔታውን ’’ወጮስያ ተገምጠልካዮ ዎጮ’’ በማለት ይገልጹታል፤ ጉልቻ ቢቀየር ወጥ አያጣፍጥም የማለት ያህል። ለዚህ ለዚህማ ህወሓትስ ምን አለው? ከማያውቁት መልአክ የሚያውቁት ሰይጣን ይሻላል የሚባለው እኰ አማራጭ ስታጣ ነው በማለት ይከራከራሉ። የዚህ ጸሁፍ አቅራቢ በአነጋገራቸው ሰዎች አሰተያየት የዓብይ ቡድን የትግርይን ሕዝብ የለውጡ ተቋዳሽ እንዲሆን ከመጣር ይልቅ ከህወሓት ጋር እየተበሻሸቀ ህዝቡን እንደፍጥርጥርህ በማለት ከኑግ ጋር የተገኘህ ሠሊጥ አብረህ ተወቀጥ ብሎታል። እሱ ከሚያስተዳድረው ከትግራይ ሕዝብና ከመሪዎቹ፣ ከተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶችና ታጋዮች ይልቅ ከባዕድ ሀገር ገዥዎች ጋር መወገን መርጧል። እርሱ ራሱ እንዳለው የኤርትራ የውጭ ጉዳይ ሚ/ር ሆኖ የመላዋ ኢትዮጵያንና በተለይ ደግሞ የትግራይን ሕዝብ ጥቅሞች በዘላቂው የሚጐዱ ሥራዎች እየሠራ ነው። በዚህ ሁኔታ የትግራይ ሕዝብ በእንዴት ዓይነት ሁኔታ በዓብይ ቡድንም ሆነ በመጭው የሀገሩ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ዕምነት ሊያድርበት እንደሚጠበቅ እነኚሁ አስተያየት ሰጪዎች ይጠይቃሉ። እንደ አስተያየት ሰጪዎቹ አመለካከት የትግራይ ሕዝብ በመጪው ጊዜ የሚገጥሙትን ተግዳሮቶች ለመቋቋም ያለው አንድ አማራጭ ወደደም ጠላም ከህወሓት ጋርም ሆነ ከሌላ ደህንነነቱን ከሚያስጠብቅለት ጋር መቆም ነው። ይህም ሁኔታ የዛሬ 40 ዓመት በፊት ትግራይን ለማስገንጠል ተንቀሳቅሰው በህዝቡ ተቃውሞ ሳይሳካላቸው የቀረ በህወሓት ውስጥ የመሸጉ ወገኖችን ተሰሚነት የሚያጠናክር ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ያመለክታል።