ዜና ዕረፍት: ጓድ ተገኜ ሞገስ

ከኢሕአፓ የተሰጠ መግለጫ ( መጋቢት 15 ቀን 2012 ዓ.ም.) – የኢሕአፓ ከፍተኛ አመራር አባል የሆነው ጓድ ተገኜ ሞገስ በድንገተኛ ህመም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቶናል።  ጓድ ተገኜ ሞገስ በረጅም ዘመን የትግል ታሪኩ በአባልነት ሆነ የድርጅቱ ከፍተኛ አመራር አባል በመሆን በአመራር ሰጭነት ያበረከተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ሲሆን ለአገሪቱ ሉዓላዊነትና ለሕዝብ አንድነት እስካሁን ድረስ ያለውን ህይወቱን ሰጥቶ አልፏል። በፓርቲው ውስጥ ለረዥም ዘመናት የአመራር አባል ሆኖ ከማገልገሉ በተጨማሪ  ከብዙ ጥረትና ውጣ ውረድ በኋላ ፓርቲው ከሌሎች ድርጅቶች ጋር በመሆን በፈጠራቸው የኅብረት ድርጅቶች ውስጥ ፓርቲውን ወክሎ ተሳትፏል።  በኢትዮጵያ ዴሞራሲያዊ ኃይሎች ቅንጅት በአመራር  አባልነትና  በሸንጎ አባልነት ኢሕአፓን በመወከል የተንቀሳቀሰ ሲሆን በኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች ኅብረት የምስረታ ጉባኤ ላይ ድርጅቱን ወክሎ ተገኝቷል።

በኢትዮጵያ መምህራን ማሕበር የትግል ታሪክ ውስጥም የጓድ ተገኘ ሞገስ ሚና ላቅ ያለ እንደነበር በወቅቱ የነበሩት ይመሰክሩለታል። 1966 ..  በተከሰተው ሕዝባዊ እንቅስቃሴ ወቅት የኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር አመራር አባል በመሆን ከፍተኛ ተሳትፎ ያደረገ ሲሆን በምክር/ቤት አባልነትም አገልግሏል። ትምህርት  ለሕዝብ ልጆች በእኩልነት በጥራት እንዲሰጥ ብዙ ትግል ያደረገና አርአያ የሆነ ጓዳችን ነው፡፡ በ1967 ዓም በጂማ  የተካሄደው የኢትዮጵያ መምህራን ጠቅላላ ጉባኤ የሥርዓተ ትምህርት ኮሚቴንና የትምህርት ዝግጅቱን የሚቃወም፣ ጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግሥት እንዲቋቋም፣ ዴሞክራሲያዊ  መብቶች እንዲከበሩ የሚጠይቁ  ጥያቄዎችን ሲያጸድቅና ጥያቂዎቹ የማይመለሱ ከሆነ የሥራ ማቆም አድማ እንዲደረግ ሲወስን ጓድ ተገኝ አብሮ የነበረ ጽኑ ታጋይ ነበር፡፡

ደርግ አቋቁሞት በነበረው ብሐራዊ ሸንጎ ውስጥ መምህራንን በመወከል ከነ አቶ ሀዲሽ ዓለማየሁና ሌሎችም ጋር ሆኖ የተሳተፈና በወቅቱም ለሕዝብ የቆመ ከመሆኑ ባሻገር ደርግ ተቀናቃኝ በማደረግ ሊያጠፋቸው ከሞከሩት የሕዝብ ልጆች አንዱ ነበር፡፡ በ1969 .. ከደርግ የጽጥታ ኃይሎች በማምለጥ በመጀመሪያ ወደ ሱዳን ከዚያም ወደ ግብጽ በመሄድ በኢሕአፓ መዋቅር ውስጥ በመንቀሳቀስ ትግሉን አጠናክሯል። መንፈሰ ጠንካራውና ለችግርና ለውጣ ውረድ የማይበገረው ጓድ ተገኜ  ምንም እንኳ ህይወቱን በመሉ የከፈለበት የኢትዮጵያ ሕዝብ ትግል ከዳር ሳይደርስ በድንገት ህይወቱ ቢያልፍም የሕዝብና የወገን ስቃይና መከራ በሚሰማው ወጣት ትውልድ ዘንድ ህያው ሆኖ እንደሚኖር ጥርጥር ሊኖር አይችልም።

በትግላችን ሂደት ባጋጠሙን ችግሮች ግዜ ሁሉ ጓድ ተገኜ ጸንቶ ለድርጅቱ መርህ፤ አቅዋምና ህልውና በመቆም መናጢዎች ያላቸውን ሁሉ በቁርጠኝነት ታግሏል፡፡ ለጓዶችም ህብረትና አንድነት ቀና አስተዋጽዖን ለማድረግ ሳይታክት የታገለ ነው፡፡ ወያኔን እንደ ታገለው ሁሉ የዘንድሮውቹንም ዘረኞች ቆርጦ በመታገል ላይ እያለ በሞት የተለየን ጓድ ተገኜ በአሁኑ ወቅት በጎናችን ባለመገኘቱ የደረሰብን ጉዳትም ቀላል ባይሆንም ትግላችንን በመቀጠል እንዘክረዋለን፣ እናከብረዋለን፡፡

ክብሩን ጠብቆ፤ ለኢትዮጵያ መከራ ተቀብሎ ችሎ ያለፈ ጓዳችን ነውና መቸም አንረሳውም፡፡

ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ ትግል!

በትግል መሞት ህይወት፤ ዳግም ትንሳኤ ልደት !!

to read/print in pdf