የልዩነቱ ሀቅ የመሠረታዊ ዐቋም እንጅ የፊደል አጻጻፍ ጉዳይ አልነበረም !

(በፍኖተ ዴሞክራሲ   የኢትዮጵያ አንድነት ራዲዮ በመስከረም 7 ቀን  2011 ዓም  የተላለፈ  ሐተታ)

ተወደደም ተጠላ፤ ሀገሪቱ ፤ አሁን በአልተጠበቀ  የለውጥ ሂደት ላይ  ትገኛለች። የለውጡን መንስዔ  እንጅ ሂደቱን፤ አቅጣጫውንና መዳረሻውን  በትክክል ተንትኖ ለማወቅ በቂ ግንዛቤ ያላቸው በጣም  ውኅዳን ናቸው ቢባል፤ ከዕውነት የራቀ አይሆንም።  ለውጡን እንመረዋልን የሚሉ ወገኖች፤  ሁኔታውን ያመጣው፤ ሕዝባዊ ዐመፅ መሆኑን  ሊገነዘቡት ይገባል። ዐይነተኛ ባለቤቱም ፤ ያው የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደሆነ  ዕርግጥ ነው።   ታሪኩም ሆነ ሀገሩ የመላው ሕዝብ ብቻ እንደሆነ ሊታወቅ ይገባል።

ከዚኽ መሠረታዊ  ዕምነት ውጭ  መመልከት ታሪካዊ ሀቁን መሳት  ይሆናል።  የታሪክ ባለቤት ምልአተ- ሕዝብ ነው እስከተባለ ድረስ፤    ማንም ኃይል ቢሆን፤ ባለፈው  ትውልድ መሃል የተከናወነውን ትግል ዕውነተኛውን  ሀቅ፤ ሆን ብሎ ማዛባት አይገባውም።   የሞራል  ልዕልና ሊኖርውም  አይችልም ።  ሕዝቡ ግን፤ ታሪኩን ባግባቡ እያዛመደ ማየቱን አይተውም ። ፍርድና ትዝብት ምን ጊዜም ቢሆን ዕውነትን አንግበው  ከቆሙ ጋር ይኖራሉ ። ዕውነት ልትታመም ትችል ይሆናል ። ግን አትሞትም። አትከስምም። አትጠፋምም።

በዚያ ትውልድ  በኩል የመሠረታዊ  አቋም ልዩነት ነበር። ደርግን እንደግፍ  እና እንቃወም የሚል  የስትርተጂያዊ አመለካከት  ልዩነት  እንደነበር የተመዘገበ  ውነታ ነው።  በአንድ በኩል፤ በታክቲክ ሽፋን   የሥልጣን  ጉጉትን ለማሳካት በደከሙ ግለሰቦች ፤ በሌላ በኩል ደግሞ፤  የሀገርን ስትራተጂያዊ  ጥቅም  ለማስጠበቅ  በታገለው   የመርኅ ተገዥና  የሕዝብ  ታማኝ በሆነው ወገን  የተደረገ  ፍልሚያ ነበር።  ደርግ የጥቂት ደጋፊ ምሁሮችን ትብብር አግኝቶ፤  ወደ ሥልጣን   የመቆናጠጥ  አጋጣሚ ተመቻቸለት። ከዚያ በኋላ የሆነ ሁሉ ታሪክ ሆኖ ቀርቷል ። ቀሪውን ለታክሪ ተመራማሪዎች መተው  ይመረጣል።

ዛሬ  በሥልጣን ላይ ያሉ ክፍሎች ይኽንን ሀቅ ሊቀበሉት ይገባል። የሚካሄደው ሕዝባዊ ለውጥ፤ ሁሉንም ወገን አካትቶ መራመድ አለበት  ከተባለ፤  የሀገራችንን   የትግል  ታሪክ  እያገናዘቡ  ማየት፤ ለዘለቄታው  መረጋጋትና ሠላም የሚያስገኘው   አስተዋፅዕዎ ቀላል አይደለም።  የኢትዮጵያ ሕዝብ  ማየት የሚፈልገው፤ “ሲሮጡ የታጠቁት ሲሮጡ ይፈታልን ” ሳይሆን   “የረጋ ወተት የሚያስገኘውን  ቅቤ ማየትን ብቻ ነው። ”  ለሃያ ሰባት የመከራ ዘመን ፤ ወያኔ የሀገራችንን ሕዝብ  በዕርጎ  ባኅር  እያስዋኘ  ቀልዶበታል። ዛሬ ሁኔታው በመለወጥ ላይ ይገኛል ። ወያኔ ወደ መቀሌ ሄዶ መሽጓል። አድፍጦ የለውጡን  ሂደት በጭንቀት ይከታተላል። ግን አልተኛም !

በሥልጣን ላይ የሚገኙት ክፍሎች፤ ትግሉን የቀጠለውን ያን ዐርበኛ ትውልድ፤ ሌላው ቢቀር፤ ሊያሽሟትጡት አይገባቸውም።  በታሪኩ ላይ ማንም ተነስቶ ያላግባብ ሲፎትተው ይከፈዋል። በመሆኑም ይኽን ኃላፊነት የጎደለውን አነጋገር አይቀበልም። ፎታቾች በሚሰነዝሩት  አባባል፤  ሆደ-ባሻ ሆኖ ግንባሩን አያጥፍም ።   እንዳስፈላጊነቱ  ሁኔታውን  እየገመገመ  ቃል ኪዳኑን ጠብቆ ይታገላል።  ተለዋውጭ ሥርዓቶችን የመደገፍ  መብት እንደሚኖር ሁሉ፤ ያንኑ ሥርዓት፤ ሌላው የመቃወም አቋም እንደሚይዝ  ደግሞ  የዴሞራሲ መብት  ነው። ልዩነቶችን በአግባቡ  እያቻቻሉ  ማስተናገድ የዴሞክራሲ ሀ ሁ እንደሆነ ማመን ያስፈልጋል።  ያንድን ወገን አመለካክት ብቻ እያስተናገዱ፤ የሌላውን ኃሳብ ያለማስተናገድ አባዜ፤ ጊዜው ያለፈበት ነው ብሎ መቀበል ከስህተት ያድናል።

ዛሬ  ከአምሳ ዐመት በኋላ፤  የታሪክን ሀቅ ለማጣመምና  ብሎም፤ የዚያን ጀግና ትውልድ መሥዋዕታዊ   አኩሪ ገድል ጥላሸት ለመቀባት መሞከር፤ ትዝብትን እንጅ ከበሬታን አያተርፍም። የዛሬው ተተኪ ትውልድ  እውነተኛውን የታሪክ  ትምህርት  እንዳያገኝም ማድረግ ይሆናል።    የነበረውን  የትግል ሂደት፤ ባልሆነ ሁኔታ ለመፈረጅ  የሚደረግ ጥረት፤  ትውልድንና ሀገርን እንደ መበደል ይቆጠራል።

”  በ ቸ እና  በ ሸ  ፊዳላት ምክንያት  ልዩነት ፈጥረው ተፋጁ ”  ማለት፤ ከታሪክ አንጻር ተቀባይነት የማያገኝ ከመሆኑም ባሻገር፤ ለወቅቱ ፖለቲካ ሂደት አይጠቅምም። የነበሩትን ሀቆች ክብደትና መጠን እንደ ማሳነስም  ይቆጠራል።  እንቅስቃሴንም  ያኮስሠዋል።  መቀናነስን እንጅ መደማመርን አያስገንኝም።  መከፋፈልን እንጅ መተባበርን  አያመጣም።  ትውልድንና ዜጋን ለማቀራረብ በሚደረገው መልካም ጥረት አሉታዊ እንጅ አውንታዊ  ሁኔታን አመልካች አይሆንም። የትላንቱን ትውልድ የትግል ታሪከ እያንቋሸሹ፤ ወቅታዊውን ሁኔታ  ብቻ እያሞገሱና  እያሞካሹ መሄድ የአንድን ሀገር ታሪክ የተሟላ አያደርገውም።

ያ መሥዋዕታዊ  ትውልድ ፤ ለሀገሩ፤ ነፃነትና ለሕዝቡ ፍቅር ቀናዒ እንደመሆኑ ሁሉ፤ ለአኩሪ  ታሪኩም በዚያው መጠን ቀናተኛ ነው። አኩሪ ታሪኩን ለመጠበቅና ለማስከበር  እስከ መጨረሻው  ምዕራፍ መጓዝ አይታክተውም ።አግባብ በሆነ መልኩ ዕውነተኛ ታሪኩን፤ ባመቸው  ዕድል ሁሉ ማስከበር ግዴታው እንደሆነ ያምናል።  ይህንን ሀቅ  ለማስረዳትም  ቁመና አለው። በዕቢት ሳይሆን፤  ኢትዮጵያዊ ትኅትናን በተላበሰ ባኅርይ፤ በሚያመቸው መድርክ ሁሉ ታሪኩን እያስከበረ ይታገላል።

የሀገር መሪዎች ማሰብና መጨነቅ  ያለባቸው  ” የኋላ ልጅ ይጨነቅበት “  ከሚል፤ ሃላፊነት ከጎደለው እንዝኅላልነት  እንዳይወድቁ ነው።  አብሮ ተባብሮ ለመኖር ከሚታሰበው ስትራተጂያዊ  አመለካከት ጋር መራመድ ከፈለጉ፤  መሪዎች ለሕዝብ በሚናገሩት ይፋዊም ሆነ ግላዊ አስተያየት፤ ከሕዝብ ትዝብት ጋር እንዳይጋጩ  ጥንቃቄ  ሊያደርጉ ይገባቸዋል። ለወቅቱ ፖለቲካዊ ጠቀሜታ ሳይሆን፤ ከረዥሙ ሀገራዊ ጥቅም አኳያ ማሰብ አለባቸው።  የራሱን አኩሪ ታሪክ አክብሮ የማያስከብር ትውልድ፤ ለሀገሩም ሆነ ለራሱ ፍይዳ ሊያስገኝ አይችልም ። ቀዳሚው ትውልድ የፈፀመውን  አኩሪ ታሪክም ሆነ የከፈለውን መሥዋዕት፤ ተተኪው ትውልድ እያከበረ ካልተማረበት፤ ሀገርን እንደ ሀገር ለማስቀጠል  አስቸጋሪ ይሆናል። የነበረውንና ያለውን እያፈረሱ፤ አዲስ ለመገንባት የሚያስችል መሠረት አይገኝም። እያፈረሱ ካልገነቡ፤  እየገነቡ  ማፍረስ  ይመጣል። የሀገር ጉዳይ  ሁሉ ሚዛኑን ጠብቆ መራመድ ይኖበታል።

ለወቅታዊው  የፖለቲካ ጠቀሜታ ሲባል፤ ራሱን አውርዶና ሰድቦ  ለሰዳቢ መዳረግ፤ የመሥዋዕታዊ ጀግኖችን  የፀጥታ    ዕረፍት  መንሳት   እንደሆነ   ይቆጠራል።   የፖለቲካ   ሥልጣን   ነጣቂዎች፤   ” ሁሉ በእጃችን ሁሉ በደጃችን ” ነው  ብለው  ይመኛሉ። ግን ይኽ እንዳይደለ  መገንዘብ ያስፈለጋል።  ያ ትውልድ  “ትጥቅህን  ሲነጥቁህ   ሱሪህን  ጨምርላቸው” ከሚባሉት ወገኖች አይደለም።  ገናና ታሪኩን ለአላፊ-ጠፊ ሥልጣን ብሎ የሚደራደር አይደለም። ታጋይ ሲሰዋ የኋላውን እያየ በመሆኑ፤ የልተሰዋው ቀሪው ታጋይ፤ ትግሉን እዳር ያደርሰውል በሚል ጽፅኑ ዕመነት ነው።  ትዕግሥትና   ፅናት  ለታጋይ የማይነጣጠሉ ባኅርያት ናቸው። ፅናትን እንደ አክራሪነት፤ ትዕግስትን እንደ ተላላነት መቁጠር፤ የዚያን ኢትዮጵያዊ  ትውልድ ዕውነተኛ ማንነት በሚገባ አለመረዳት ነው።  ጀግንነት፤  በተለምዶ ለአቸናፊዎች ሊሰጥ ይችል ይሆናል። ቢሆንም፤ ተቸናፊዎቹም ድንቅ ተቸናፊዎች  ሆነው   በመቆጠራቸው፤ የታሪክ መፃህፍት ቦታ ይሰጧቸዋል። ሆኖም ግን ፤ የአንዱ ውድቀት ለሌላው ትርፍ ነው በሚል ዕሳቤ የሚረኩ ካሉ ዕርካታን አያገኟትም።  ያ ትውልድ ግን  በራሱ ወድቀት ኢትዮጵያ ከዳነችለት፤ ዘለዓለማዊ ዕርካታን እንዳገኘ  ይቆጥረዋል። ከዚህ  ጽኑ ዕምነት ተንስቶ የራሱን  ታሪኩ የሚያጎድፉበትን ባለሥልጣናት፤

” ወይ ተሟግተው አይረቱ፤

ተኩሰው አይመቱ ፤

የተኛውን ነብር ቀሰቀሱት ከንቱ ።     ይላቸዋል።

ከብስለት ደረጃ ለማድረስ የሚያስችል ጭንቅላት እንዲኖረው ዝግጅት የማያደርግ ሁሉ፤ የሥልጣኔ መሪ ሊሆን አይችልም እንደሚባለው፤ እንደ ኢትዮጵያ ውስብስብ ችግር ያላትን ሀገር ለመምራትም እንዲሁ፤ ዐዋቂ ሆኖ መገኘትን ይጠይቃል። የለውጡ እንቅስቃሴ ዘንቦ ሳያባራ ጤዛ ሆኖ እንዳይቀርና የነበረውም አሰቃቂ ሁኔታ እንደነበረው እንዲቀጥል ለማድረግ የሚርመሰመሱትን  ፀረ ለውጥ ኃይሎች እንዳይንሰራሩ ለመቆጣጠር፤  መሥዋዕት የከፈለውን ኃይል በአግባቡ ማስተናገድ ጠቃሚ ነው። ይኽ ከሆነ፤ ሀገሪቱን ወደ አዲስ ተስፋ ሰጭ  ምዕራፍ ለማሸጋገር የሚደረገው ርምጃ  የቀለለ ይሆናል።

” ኢትዮጵያ ወይም ሞት  ነበር  ፀሎታችን፤

ሁለቱንም  ሰጠን ቸሩ ፈጣሪያችን።  ”

ብለው የመጡት ሁሉ  በመጥፎ አጋጣሚ  ሁለቱንም አጥተው  እንደቀሩ ሁሉ እኛም ፤ ለኢትዮጵያ እየሞትን፤ ኢትዮጵያ በህይወት መኖሯን እንፈልጋለን። ይህ ምኞታችን እንዲሳካለን በምናደርገው ትግል የማንንም ፈቃድና ብራኬ አያስፍልገንም። የኢትዮጵያን ሕዝብ ሙሉ ድጋፍና ትብብር ግን  አናጣውም።  ለሌሎች ጥቅም ሲባል ህይወትን መክፈል ግን ከሞት በላይ ውርደት ነው።  ተዋርዶ ከመኖር ፤ በከብር መሞት ፤ ህይወት እንደሆነ፤  የዚያ ትውልድ አባል የሆነው ሁሉ  አምኖ የገባበት ቃል ኪዳን ነው።

” እምቢ አሻፈርን እኛ አንሆንም ባንዳ፤

የታሰበው ይሁን ያበጠው ይፈንዳ! ”

ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኖራለች!