በዓይነኩሉ ባላገር
እስር ቤቱን ደርግ ለሌላ ጉዳይ ምንዓልባትም ለመጋዘንነት የሰራው እንደነበር ይነገር ነበር ። በወያኔ የእስረኛ ማደሪያ የሆኑት መጋዘኖች ሰፊ አዳራሽ ስለነበሩ ከ350 እስከ 400 እስረኛ ይይዙ ነበር ። ለአንድ እስረኛ የሚሰጠው የምኝታ ቦታ ስፋት አንድ ክንድ ነበር ። ሁሉም አዳራሾች በውሃ የሚጸዳ ሽንት ቤት ነበራቸው ።ግን የእስር ቤት ኃላፊዎች ውሃ ቧንቧ እየዘጉብን ለበሽታ ያጋልጡን ነበር ። የእስር ቤት ጠባቂዎች ሁሉም ጨካኝ በጥላቻ የተሞሉ ወያኔዎች ነበሩ ። በጭካኔ ባህሪያቸው እንኳን ለሰው ለከብት እረኝነት አይሆኑም ለምን ከብት ደብድበው ይገድላሉ ። እስረኞቹ በሁለት ጎራ የተከፈሉ ሲሆኑ ደረቅ ወንጀል የሰሩ የህግ እስረኞች እና በፖለቲካ አቋማቸው ስም ተሰጥቷቸው የታሰሩ የፖለቲካ እስረኞች ናቸው ። በተጨማሪም የፖለቲካ እስረኞችን ለመሰለል እስረኛ መስለው የታሰሩ የደህንነት ሰራተኞች ነበሩ ። የቃሊቲ እስር ቤት ዝዋይ እና ሸዋሮቢት ቅርንጫፎች ነበሩት በኋላ ቂሊንጦም ተጨመረ ። እዚያው ቃሊቲ ውሰጥ ከሰው ተገልለው ምንአልባትም ጨለማ ቤት የታሰሩ የፖለቲካ እስረኞች ነበሩ ። ከነበሩ አሳዛኝ ክስተቶች አንድ ልጥቀስ ። ቃሊቲ ገብቼ የታዋወቅሁት የእስር ጓደኛዬ ነው ዲኮ ይባላል በአባቱ እስራኤላዊ በእናቱ ኢትዮጵያዊ ነው ። ኢትዮጵያዊነቱን የሚወድ እና ለኢትዮጵያ ህይወቱን የሰጠ ሰው ነው ። በደርግ ዘመን የኢህአፓ እስኳድ በመሆን ብዙ ተጋድሎ ፈጽሟል ። ተካ ቱሉን ለማስወገድ በነበረ ኦፕሬሽን ላይ ተሳትፎ እንደነበር አጫውቶኛል ። በደርግ እስርቤት ሊረሸን ከጓዶቹ ጋር ወጥቶ ለቁልቢ ገብርኤል ስእለት አይጥ አስገባለሁ ብሎ ተስሎ ሌሎች ጓደኞቹ ሲረሸኑ እሱ ብቻ ተርፎ እንደተመለሰ አጫውቶኛል ። በነገራችን ላይ አይጥ ካየ ይሮጣል አይወድም ። ይሁን እነጅ በደርግ እስር ቤት ሰባት አመት ከቆየ በኋላ ሲፈታ አአ በሚገኘው ፖስተር የጤና ኢንስቲትዩት አይጥ እንዲለማመድ ሆኖ ለቁልቢ ገብርኤል ስእለቱን ማስገባቱን አጫውቶኛል ። በዘመነ ወያኔ በነበረው የፖለቲካ አቋም ስም ተሰጥቶት ቃሊቲ ታስሮ በነበረበት ጊዜ የአባቱ ልጅ በእናቷ አይሁድ የሆነች ከፈረንሳይ የእስረኛ የስም ዝርዝር አይታ ቃሊቲ መጥታ ለአስፈታህ ብላ ጠይቃው ለአይሁዳውያን አገዛዝ በነበረው ጥላቻ አልፈልግም ብሎ መልሷታል ። በነበረበት የጤና ችግር በቂ ህክምና እንዳያገኝ ተደርጎ እዚያው እስር ቤት ውሰጥ ህይወቱ አልፏል ። በ1997 በነበረው ህዝባዊ አመጽ ንቁ ተሳትፎ ነበረው ። ነፍሰ ይማር