መረን የለቀቀውን የወያኔ አገዛዝ አምነስቲ ኢንተርናሽናል አጋለጠ፣ የታቀዱት የምጣኔ ሃብት ፓርኮችም ችግር ቀፍቃፊ ይሆናሉ፣ ባለሥልጣናት በስብሰባቸው ላይ የወያኔ የጎሳ ፌደራሊዝም ችግር እንደፈጠረ ገመገሙ

ፍኖተ ዴሞክራሲ የኢትዮጵያ አንድነት ድምጽ (የካቲት 04 ቀን 2009 ዓ.ም.) –  የወያኔ አገዛዝ የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ስምምነቶችንና መርሆዎችን የጣሰ መሆኑን አምነስቲ ኢንተርናሽናል አጋለጠ – በየቦታው የታቀዱ የኢንዱስትሪ ፓርኮች የኢኮኖሚ ችግር ሊያስከትሉ ይችላል ተባለ – የወያኔ ባለሥልጣናት ባካሄዱት ስብስባ የጎሳ ፌዴራሊዝም ችግር የፈጠረ መሆኑን ገመገሙ ተባለ።

አምነስቲ ኢንተርናሽናል የተባለው የሰብአዊ መብት ተከራካሪ ድርጅት አርብ የካቲት 3 ቀን 2009 ዓ.ም ባወጣው ሰፊ ዘገባ በቅርቡ ወያኔ ያወጀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አስመልክቶ የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት የአሰራር መርሆዎችና ልምዶች፤ በሰብዓዊ መብትና የፖለቲካ ጉዳዮች የተደረጉ የዓለም አቀፍ ስምምነቶች እንዲሁም የአፍሪካ የሰብዓዊ መብት ቻርተር በአገዛዙ የተጣሱ መሆናቸውን ገልጿል። የወያኔ አገዛዝ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ካወጀ በኋላ በዓለም አቀፉ ስምምነት መሰረት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ያስፈለገበትን ምክንያት እንዲሁም ዝርዝር አፈጻጸሙን ለተባበሩት መንግስታት ዋና ጸሐፊ ማሳወቅ ሲገባው ይህንን አለማድረጉ ስምምነቱን የተጣሰ መሆኑን ገልጿል። የወያኔ አገዛዝ ስለ አስቸኳይ አዋጁ ዝርዝር ይዘት በይፋ የገለጸው ባለመኖሩና አገዛዙ የሚወስደው እርምጃና ቁጥጥር ግልጽነት የሌለውና ትክክለኛነቱን ማረጋገጥ የማይቻል በመሆኑ በተጨማሪም ቀደም ብለው የተደረጉ ጥፋቶች ወደ ኋላ እየተወሰዱ ቅጣት የተበየነባቸው በመሆኑ የሕግ ጥሰት ተደርጓል ብሏል። በዓለም አቀፍ ስምምነት መሰረት በምርመራ ላይ እስረኛን ማሰቃየት(ቶርቸር) ማድረግ፤ በእስር ላይ የሚገኙ ዜጎችን ሳይንከባከቡ በተለያዩ መንገዶች ማሰቃየት፤ የቀድሞ ህጎችን ጠቅሶ ጥፋቶችን መወሰን በሰፊው እየተካሄዱ በመሆናቸው አገዛዙን በኋላፊነት ያስጠይቀዋል ብሏል። እነዚህ የተዘረዘሩትን ጉዳዮች አገዛዙ ጥፋት መሆናቸውን አምኖ ባስቸኳይ እንዲያስተካከል ሲጠይቅ ሁኔታውን የሚከታተልና የሚያሳውቅ ነጻና ገለልተኛ የሆነ አካል መቋቋም እንዳለበትም ሀሳብ አቅርቧል።

በየቦታው የታቀዱ የኢንዱስትሪ ፓርኮች በአገዛዙ የአሰራር ችግርና ሙስና ምክንያት በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ችግር ያመጣሉ በሚል አንዳንድ ዜጎች ስጋታቸውን እየገለጹ ነው ተባለ። ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ በርከት ያሉት በብድር የሚገነቡ በመሆናቸው በአሁኑ ወቅት በከፍተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘውን የአገሪቱን እዳ ወደ ላይ ያንረዋል ተብሏል። ከዚህ በተረፈ ምንም እንኳ እያንዳንዱ አምራች 80 ከመቶ የሚሆነውን ምርቱን ወደ ውጭ እንዲያወጣ ስምምነት ያለ ቢሆንም ለእቃዎቹ በውጭ ያለው የግዥ ፍላጎት ከቀነሰ በሙስና እና በዝርክርክ አሠራር ምርቶቹ በአገር ውስጥ እንዲሸጡ ስለሚደረግ ሁኔታው ትናንሽ አምራቾችን ከሥራ ውጭ ያደርጋል የሚል ስጋት እየተፈጠረ ይገኛል።

ከ20 ዓመታት በኋላ ወያኔ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ የጫነው የጎሳ ፌዴራሊዝም ችግር እየፈጠረ ነው በሚል የአገዛዙ ከፍተኛ ባለሥልጣናት እየተወያዩበት መሆኑ ተገልጿል። በክልል ተብየዎችና በማእከላዊ መንግስት በኩል ያለው ግንኙነት የላላና የተወሰነ ከመሆኑ በላይ አስተማማኝ ጸጥታ፤ ዘላቂ ልማትና ቀጣይነት ያለው ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት በማጣት በኩል ችግር ነበረበት ተብሎ እንደተገመገመና ለውጥ እንዲደርግበት ወደ በላይ አካል የሚተላለፍ መሆኑ ተገልጿል። ከአንድ ብሔረሰብ የተውጣጣው የወያኔ ቡድን በክልሎችና በማዕከላዊ መንግስት በኩል ያለውን ሥልጣንና የኃላፊነት ለመለወጥ የወሰነበት ምክንያት በቅርቡ በአንዳንድ የክልል ባለሥልጣናት የደረሰበትን ማፈንገጥና ተቃውሞ ለመግታትና ቁጥጥሩን እንደገና ለማጥበቅ መሆኑ ታውቋል። በሕዝብ ላይ የጫነውን ሕገ መንግሥቱ ሳይለውጥ በምን ዓይነት መንገድ ተግባራዊ እንደሚያደርገው ወደፊት የሚታይ ይሆናል ተብሏል።

የወያኔ ፕሬዚዳንት ከእነ ቤተሰቦቹ መኖሪያውን በቀድሞ የልኡል መኮንን ግቢ ወደ ተሰራው ግዙፍ ቪላ እንድሚያዛውር ተገለጸ፡፤ ይህን ከፍተኛ የሆነ የቅንጦት ሕንጻ ለመሥራት የፈጀው 130 ሚሊዮን ብር ሲሆን ግቢው የ40 ሺህ ካሬሜትር ስፋት ያለው ሆኖ የቴኒሲና የውሃ መዋኚያ ቦታዎች እንዳሉት ተነግሯል።

ዝርዝር ዜና ከፍኖተ ዴሞክራሲ የኢትዮጵያ አንድነት ድምጽ ያዳምጡ