ምን ነው ቲም ለማ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መቆጣት፣ መሳደብና ለቅሶ አበዙ!?

ያሬድ ከደሴ – ዜጐች በሚያዩትና በሚሰሙት ነገር ስጋት ስላደረባቸውና ስለአዘኑ በቲም ለማ ተብዬው ላይ የተለያዩ ጥያቄዎች እያነሱና እየተቃወሙ ነው። ቲም ለማዎች ደግሞ እንዴት ሆኖ እንደፈራለን፣ ለምን እንጠየቃለን፣ ለምን እንተቻለን? ለምን ተነካን እያሉ መንጨርጨርና ማስፈራራት ይዘዋል። እንዲህ ዓይነት ነገር ደግሞ ችግሩን አይፈታውም ወይም ለጥያቄው መልስ አይሰጠም። ይቺ ባለጊዜዎቹ ዶ/ር አብይም፣ አቶ ለማም፣ አቶ ታከለም በዩኒፎርም ይዘዋት የመጡ እያለቃቀሱ፣ የተጎጅነት ዲስኩር እያሰሙ አንጀት የመብላት ሰሞነኛ ዘዴ መሆንዋ ነው።

  • ዶ/ር አብይ የኢትዮጵያ ሕዝብ ችግር አለበት፣ ማንን ከማን ጋር እንደሚያወዳድር አያውቅም ብሎ ዘለፈው፤ ሕዝቡ እሱን በተናገረው አምኖት፤ ከወያኔ ጋር አወዳድሮና ይሻል ይሆናል ብሎ በሙሉ ልብ እንዳልደገፈው፤ ሰው ሲታጣ ይመለመላል ጐባጣ እንዲሉ ቢሆንም።
  • አቶ ለማ ደግሞ የአዲስ አበባ የብሔር ስብጥርን አዛንፋለሁ በማለቱ ዜጐች በቃል አባይነቱ ቢወቅሱትና ቢያወግዙት እንዴት ከሃዲ እባላለሁ? ኢትዮጵያዊ ሁን ብሎ ቀብድ የሰጠኝ አለ እንዴ? ብሎን እርፍ አለ፤ እርሱንና ጓደኞቹን ሊደፈጥጣቸው ደርሶ ከነበረው የሕዝብ አመጽ ኢትዮጵያ ሱሴ ነው የሚል ቀብድ ሰጥቶ መትረፉን ዘንግቶ።
  • ኢንጂነር ታከለም ደግሞ ያው ከአንድ ምንጭ እንደመቀዳቱ፣ በመመሪያ ወይም በኩረጃ ያንኑ ዘዴ ተጠቅሞ እንዴት ብሔረተኛ ነህ እባላለሁ ብሎ አጓራብን። ጭራሹንም ከአንድ ተራ አክቲቪስት ጋር የምነፃጸር አይደለሁም ብሎ የሹም ዶሮ ነኝ አለን።

ነገር ግን፤ ነገሩ እንትን ያለበት እንትን አይችልም ሆነና ነው እንጂ ይህ ሁሉ መቀባጠርና ያዙኝ ልቀቁኝ ባላስፈለገ ነበር። መልካም ቃላት ማንጋጋትም አያስፈልግም። መፍትሄው በጣም አጭርና ቀላል ነው፤ ግልጽነትና ዜጎች ያነሱዋቸውን ጥያቄዎች በአግባቡ መመለስ ነው። ጥያቄዎቹ ደግሞ ግልጽ ናቸው፤ – አዲስ አበባ የኦሮሚያ ነው ብላችሁ ታምናላችሁ ወይ፤ ለዚያስ እየሰራችሁ አይደለምን? – ከአዲስ አበባና አዲስ አበባ ዙርያ የተፈናቀሉ ነዋሪዎችና ገበሬዎች ተገቢው ክፍያና ካሣ ሊሰጣቸውና መልሰው ሊቋቋሙ ይገባል፤ ሌላውም የአገሪቱ ዜጋ እንዲሁ። ከዚያ ውጭ ግን ኦሮሚያ በአዲስ አበባ የተለየ ጥቅም አላት ወይስ ሊኖራት ይገባል ብላችሁ ታምናላችሁ ወይ? – ከዚያ ላይ ኢ/ር ታከለ አዲስ አበቤ ሳይሆን በቀዶ ጥገና መንገድ በምክትል ከንቲባነት መሾሙ ህጋዊም ሞራላዊም አግባብነት የሌለውና ልክ ወያኔ ያደርገው እንደነበረው ሁሉንም በአንድ ጐሣ የማግበስበስ አባዜ አይደለም ወይ? እና የመሳሰሉት ናቸው።

ኢ/ር ታከለ ብሔረተኛ አይደለሁም ላለው ጉዳይ፤ እንዴት ሆኖ ነው ብሔረተኛ ሳይሆን የኦዴፓ አባል የሆነው?! ኦዴፓ የኦሮም ድርጅት ነኝ የሚል የኢህ ኣዴግ አባል ድርጅት ነው። ኢህኣዴግ ደግሞ አንድም አገራዊ ፓርቲ ያላካተተና የአገራዊ ኅብረ-ብሔራዊ ፓርቲ ህልውና የሚፀየፍ የጠባብ ዘውገኛ ድርጅቶች ስብስብ ነው። በያ ላይ ደግሞ ታከለን ለአዲስ አበባ ጥቅም ሳይሆን ለኦሮሚያ ነው የቆመው ያለው እኰ ሕዝቡ ወይም አክቲቪስቶች አይደሉም፤ የገዛ ድርጅቱ የኦነጋዊው ኦዴፓ አመራር አባል የሆነው ሰው ነው። ችግሩን እዚያው ነው መወጣት ያለበት። ባለጊዜ ቅል ድንጋይ ይሰብራል ሆነ እንጂ ባልመረጠው፣ ሥራልኝ ባላለው ሕዝብ ላይ የሚያቅራራበት ምክንያት የለም።

ኢ/ር ታከለ ከማንም ተራ አክቲቪስት ጋር አታወዳድሩኝ ያለው ነገር በጣሙን ያስቃል። እራሱን ለማወዳደር እየሞከረ ያለው፤ የእርሱ ድርጅት ለወያኔ ሎሌነት አድሮ በህዝብ ላይ መከራና ሰቆቃ ሲፈጽም፣ ሕዝብ ሲያፈናቅል፣ የሃሳብ ነፃነት ሲያፍን፣ ስዬል ሲፍጽም፣ … አውግዘውና ተቃውመው ከታገሉት ከሞት አይፈሬዎቹ ከእነ አጅሬ ጋር ከሆነ ዳግም ሊያስብበት ይገባል፤ እንቁራሪት ምን ብላ ምን አለች እንዳይሆንበት ያሰጋል። ደግሞም እኰ ዋናው ጉዳይ መሆን ያለበት ማን ነው ጥያቄውን ያቀረበው ሳይሆን የተጠየቀው ጥያቄ ቁምነገርነትና ይዘት ነው። ከዚያም ጥያቄውን መመለስ ነው። ዋነኛው ጉዳይ የጠያቂው ማንነት አይደለም። ከዚያ ላይ ደግሞ ትልቅ ጋን እኰ በአንዲት ትንሽ ጠጠር ሊደገፍና ጠጠሪቱ ስትከዳው ጋኑ ተከንብሎ ሊፈረካከስ እንደሚችል አያውቁም እንዴ የኦዴፓ/ኦነግ ሹሙ? አሳቸውና አለቆቻቸው የትላንት የወያኔ ሎሌዎች በወያኔ ጀርባ ታዝለው ለሥልጣን የበቁ እንጂ በብቃት ምክንያት በሕዝብ ምርጫ የተመረጡ አይደሉምና ምንም መመጻደቅ አይገባቸውም። ከዚያ በቀር ደግሞ ፊት ለፊት አስቀምጦ ሊመክራቸው ከጣረው ከዶ/ር በድሉ መልዕክት መማር ይበጃችዋል።

ኢ/ር ታከለ ሰው በለፈለፈ ቁጥር መናገር አለብን እንዴ፤ እኛ እኰ ዝም ብለን ሥራችንን እየሠራን ነው ያለው ነገር ጦሽ አስብሎኛል፤ እሱ እኰ ነው ጥያቄው፥ ግልጽነትና ተጠያቂነት። ምንድን ነው እያደረጋችሁት ያላችሁት? ምንድን ነው በአገራችን ሥም እየተዋዋላችሁ ያላችሁት? ኢትዮጵያን በዝምተኛ ሂደት አፈራርሶ የምሥራቅ አፍሪካ ኰንፌዴሬሽን መመስረት? በዘር ማጥራት አዲስ አበባን በድምጽ ብልጫ አስወስኖ የኦሮሞ ጐሣ ብቻ ማድረግ (Oromization of Addis Abeba through democratic engineering) ልክ አሁን በወልቃይት ድምጽ ቢሰጥ ሊሆን እንደሚችለው አይነት?

ቲም ለማዎች፤ እንዲያ የሚባል ነገር ካለ፤ ማወቅ ያለባቸው፤ የትላንትና ጌቶቻቸው የወያኔዎች ባላንጣ የሆነው አቶ ኢሳይያስ ወያኔዎችን Game over እንዳላቸው ሁሉ ኢትዮጵያዊ ዜጎችም፥ ኦዴፓ/ኦነግ፤ game over! እያልዋቸው መሆኑን ነው። አሁን ጊዜው ምላስ እያሾሉ የማታለል፣ እየተቅለሰለሱና እየተሸጎጡ አንጀት የመብላት ሳይሆን ለተጠየቁት ጥያቄዎች ተግባራዊ ምላሽ የመስጠት ነው። ሚሊዮን ጊዜ ለመታለል የሚፈቅዱ ከንቱዎች ለመኖርቸው አሌ ባይባልም፤ ድሮውም በእነርሱ ብልጥነት ሳይሆን በቅንነት አምኖአቸው የነበረው አብዛኛው አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ ግን ነቅቶባቸዋልና ወይ አቋማቸውን ያስተካክሉ፤ ወይም ደግሞ ለይቶላቸው የጀመሩትን ጦርነት አቀጣጥለው እንደለመዱት ይጨፍጭፉን። ያኔ የሚሆነው ደግሞ ለያኔ ይቆዬን።

በነገራችን ላይ ግን፤ ለክፉም ለደጉም፤ እነ አቶ ለማ ሊቁ አለቃ ገብረሃና ያሉትን ነገር አይርሱብን። እንዲህ ነበር አለቃ ያጋጠማቸውና ያሉት፥

ከእለታት አንድ ቀን የአለቃ ሚስት ወ/ሮ ማዘንጊያ ገበያ ይሄዳሉ። በወቅቱ ገና ዓመት ያልሞላው ህፃን ልጅ ነበራቸውና ልጁን ከአባቱ ከአለቃ ዘንድ ትተዉት ሄዱ። አለቃ ሆዬ ሴት አይምሬ ነበሩና የለመድዋቸውን ጎረቤታቸው ሴትዮን እቤታቸው ጠርተው በፍቅር ጨዋታ ያስተናግዱ ገቡ። ዳሩ ግን ጨዋታው ጨርሶ ሳይጠናቀቅ ሚስታቸው ተመለሱና መምጣታቸውን ለማመልከት ያህል እውጭ ሆነው አለቃ እንደምን ዋሉ ብለው ጓዛቸውን ለመወገን ወደጓሮ ዞር ሲሉ የአለቃ ውሽሜ ሆዬ የአለቃ ህፃን ልጅ እኩያ የሆነውን የራስዋን ህፃን ለጅ ወሰድኩ ብላ የአለቃን ልጅ አፈፍ አድርጋ ሳትታይ ወደቤትዋ ትሄዳለች። ወ/ሮ ማለፊያ ሆዬ ልጃቸውን ሊያጠቡ ብድግ አድርገው ሲያዩ ልጁ የጐረቤት እንጂ የሳቸው አለመሆኑን ያስተውላሉ። በዚያን ጊዜ ተናድደው አለቃን ‘አንቱ ቀላል፤ አሁን ይህን ልጅ እዚህ የጋመው እሳት ውስጥ ልጨምረው’ ብለው ያፈጡባቸዋል። የደንገጡት አለቃ እንደ ምንም ቀልባቸውን ሰብስበው ተይ ‘ማዘንጊያዬ፤ እዛም ቤት እሣት አለና ተይ’ አሉዋቸው ይባላል።

እናማ እዚህ ቤትም ቄሮ አለና፤ እዚህ ቤትም ሸዋጅም፣ እንደ እነ እንትና አይነት አሸባሪም አይጠፋምና በጊዜ አደብ ይግዙ።