ስለግቤ ላይ ግድቦች ወያኔና የኬንያ ባለሥልጣናት ምን እየተባባሉ ነው?

(የካቲት 11 ቀን 2009 ዓ.ም.) – በግቤ ወንዝ ላይ የተሰሩት ግድቦች በአካባቢው ነዋሪ ላይ ስለፈጠሩት ችግር የኬኒያና የወያኔ ባለስልጣኖች የተለያዩ ሀሳቦች እየሰጡ ይገኛሉ – በሱዳን አገር ለስራ የመጡ ኢትዮጵያውያን ካርቱም በሚገኘው የወያኔ ኤምባሲ ላይ ሰላማዊ ሰልፍ አካሄዱ – ሪሊፍ ዌብ የተባለው ድረ ገጽ በደቡብ ኢትዮጵያ፤ በሶማሊያ፤ በኬኒያና በታንዛኒያ የድርቁ ሁኔታ እየተባባሰ መሄዱን ገለጸ – የዚምባብዌው ፕሬዚዳንት ሙጋቤ ቢሞቱ እንኳ አስከሬናቸው ተወዳድሮ ሊያሸንፍ እንደሚችል ባለቤታቸው ተናገሩ።

የግቤ አንድ ሁለት እና ሶስት ግድቦች በቱርካና ሀይቅ አካባቢ ነዋሪ በሆኑ ሰዎች ላይ ስላስከተሉት አደጋና ችግር በቅርቡ ሂውማን ራይትስ ዎች የተባለው የሰብአዊ መብት ተንከባካቢ ድርጅት ማጋለጡ የሚታወቅ ሲሆን በዚህ ጉዳይ ላይ የኬኒያና የወያኔ ባለስልጣኖች የተለያዩ ሀሳቦች እየሰጡ ይገኛሉ። የኬኒያው የአካባቢ ጥበቃ (ኤንቫይሮመንት) ሚኒስትር በወያኔ አገዛዝ በኩል የተገነበት ግድቦች ለኤሌክትሪክ ማመንጫ እንጅ ለእርሽና ለሌሎች ተግባሮች እንዳይውሉ ቀደም ብሎ ስምምነት ላይ ተደርሶ ነበር የሚል መግለጫ ቢሰጡም በቅርቡ ይፋ የተደረገው የሂውማን ራይትስ ዎች መግለጫ የቱርካና ሀይቅ ማሽቆለሉንና የአሳ አስጋሪዎችን ምርት የቀነሰ መሆኑን ከመዘረዘሩ በተጨማሪ የወያኔ አገዛዝ በሐይቁ ምስራቅና ምዕራብ አካባቢዎች ለሸንኮራ አገዳ እርሻ መሬቱን ወደ 30 ሺ ሄክታር የመነጠረ መሆኑንና ወደፊት ወደ 100 ሺ ሄክተር ለማሳደግ እቅድ እንዳለው አጋልጧል። በኬኒያ የሚገኘው የወያኔ አገዛዝ አምባሰደር በሰጠው መግለጫ የሰብአዊ መብት ተቋሙን ዘገባ መሰረተ ቢስ ነው በሚል አጣጥሎ በኦሞ ሀይቅ ላይ የተገነቡት ግድቦች በአካባቢው ነዋሪ ላይ ምንም ዓይነት እክል እንዳላመጡ ገልጿል።

በሱዳን አገር ለስራ የመጡና ኢትዮጵያውን በካርቱም የወያኔ ኤምባሲ ላይ ሰልፍ ማካሄዳችው ታወቀ። በሱዳን ውስጥ ከፖሊስ ጣቢያ በሚወጣ መታወቂያ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን አዲስ መታወቂያ ለማግኘትም ሆነ ያላቸውን ለማደስ ይከፍሉት የነበረው የአግልግሎት ዋጋ ከሚገባውና ከአቅማቸው ውጭ በሆኑ መጠን መጨመሩን ተከትሎ ያቀረቡት አቤቱታ ሰሚ ባለማግኘቱ የወያኔ ኤምባሲ እንዲያማልዳቸው ጥያቄ አቅርበው ነበር። የኤምባሲው ባለስልጣኖች ጥያቄያቸውን ችላ በማለት የወያኔ 42 ዓመት በሚከበርብት ወቅት ከፍተኛ ሰላማዊ ስልፍ በማድረግና ያዘጋጀውን የሙዚቃ ድግስ እንዲሰረዝ በማድረግ በዓሉን አሰናክለውበታል። ሰልፉን ለመበተን የሱዳን የጸጥታ ኃይል በወያኔ ባለስልጣኖች ተጠርቶ ቢያመጣም ስልፉ ቀጥሎ የነበረ መሆኑም ታውቋል። ከእነዚህ ሌላ የወያኔ አስከፊ አገዛዝ በመሸሽ በስደተኛነት ተመዝግበው የሚኖሩ በብዙ ሺ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በሱዳን ይኖራሉ።

ሪሊፍ ዌብ የተባለው የተመድ የሰብአዊ ርዳታ እና የቅድሚያ ማስጠንቀቂያ ድረ ገጽ አርብ የካቲት 10 ቀን ባወጣው እትሙ በዚህ ዓመት ከጥቅምት እስከ ጥር ባሉት ወራት በደቡብ ኢትዮጵያ በሶማሊያ በኬኒያና በሰሜን ታንዛኒያ የድርቁ ሁኔታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ በመሄዱ በአካባቢው የሚገኙ እጽዋቶች እየደረቁና እየጠፉ መሆናቸውን ገልጿል። ባለፈው ሳምንት በተወሰኑ አካባቢዎች የጣለው ዝናም ጥቂት መሻሻል ያመጣ ሲሆን በሚቀጥሉት ሳምንታትም በአንዳንድ አካባቢዎች ዝናም ሊጥል የተተነበየ መሆኑንና ይህም የእጽዋቱን ሁኔታ ለማሻሻል መጠነኛ ተስፋ የሰጠ መሆኑ ተገልጿል።

ዝርዝር ወቅታዊ ዜና ከፍኖተ ዴሞክራሲ የኢትዮጵያ አንድነት ድምጽ ሬዲዮ ያዳምጡ