በራያ ሕዝብ ላይ እየደረሰ ያለውን ግድያና ግፍ እናወግዛለን

ኢሕአፓ:  ባለፈው እሁድ ጥቅምት 11 ቀን 2011 ዓ.ም በአላማጣ ከተማ  የማንነት ጥያቄያቸውን በማቅረብ በሰላማዊ መንገድ ተቃውሟችውን  ለማሰማት አደባባይ በወጡ ዜጎች ላይ የትግራይ ክልል ልዩ ኃይል በወሰደው የጥቃት እርምጃ ዜጎች  EPRPመገደላቸውንና መቁሰላቸው ታውቋል። ኢሕአፓ ይህንን የወያኔን አረመኔያዊ እርምጃ በጽኑ እያወገዘ በግፍ የተገደሉ ቤተሰቦችና ወዳጆች መጽናናትን እንዲያገኙ ያለውን ልባዊ ምኞት ይገልጻል።

የዛሬ 27 ዓመት የወያኔ ዘረኛ አገዛዝ በማንአለብኝነትና በእብሪት አገሪቱን በቋንቋ ክልሎች ሲከፋፍል የወልቃይት  የጠገዴ፤ የጠለምትና እንዲሁም የራያን አካባቢ ሕዝብ በኃይል ወደ ትግራይ ክልል መጨመሩ ይታወቃል።   በእነዚህ አካባቢዎች የሚኖሩ ዜጎች ማንነታቸው ተከብሮ፤ በፍላጎታቸውና በፈቃዳቸው ከሚወስኑት ክልል ውስጥ  መኖር መብታቸው ሆኖ ሳለ የወያኔ አገዛዝ በአምባገነንነትና በእብሪት ወደ ትግራይ ክልል አስገብቶ ላለፉት 27 ዓመታት አለፍላጎታችው ከፍተኛ ግፍና በደል ሲያደርስባችው ቆይቷል።  ይህ ግፈኛ ቡድን ቀደም ብሎ  በወልቃይት፤ በጠገዴና በጠለምት የማንነት ጥያቄ ባነሱ ዜጎች ላይ የኃይል እርምጃ ወስዶ ለግድያና ለአካል ጉዳት እንደዳረገው ሁሉ በአሁኑ ወቅትም በራያ አካባቢ ተመሳሳይ ግፍ በመፈጸም ላይ ይገኛል። የራያ የማንነት  እንቅስቃሴ ለበርካታ አመታት ሲካሄድ የነበረ ሲሆን ባለፉት ጥቂት ቀናት ተጥናክሮ መቀጠሉ ይታወቃል። ባለፈው እሁድ በአላማጣ ከተማ ተቃውሟቸውን ለማሰማት አደባባይ የወጡት ዜጎች በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው  ለመማርና ለመስራት የማንነት ጥያቄ  መብታቸው እንዲከበር የጠየቁ  እንጅ ሌላ አጀንዳ የነበራቸው አልነበሩም።   በአማርነታቸው ላይ ትግሬነትን በግድ ሊጭንባቸው የቆረጠው አረመኔው አገዛዝ የትግራይን ልዩ ኃይል ልኮ  ግድያውን አካሄዷል።

የትግራዩ ልዩ ኃይል በንጹሃን ዜጎች ላይ የፈጸመው ግድያና የአካል ማጉደል በጽኑ መወገዝ ያለበት ሲሆን የራያም  ሆነ የሌሎች ዜጎች የማንነት ጥያቄ እንዲፈታ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ከራያ ሕዝብ ጎን መቆም ይገባዋል እንላለን።  የወያኔ/ኢሕአዴግ አገዛዝ መልኩን ለውጦና የጥገና ለውጥ በማካሄድ ተጠናክሮ እስከቀጠለ ድረስ የሕዝባችን ችግር ውስብስብ ሆኖ የሚቀጥል መሆኑን ተረድተን ይህንን አምባገነንና ዘረኛ ኃይል በሕዝባዊ ትግል እንድናስወግድ  ትግላችንን እናጠናክር እንላለን።

አምባገነን አገዛዝ ይወገድ!

ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ !