በሰሜን ጎንደር ፀረወያኔው ጦርነት ቀጥሏል፣ የአዲስ አበባ መውጫ ኬላዎች ፍተሻ ህዝቡን እያስመረረው ነው፣ በካናዳ የወያኔዋ አምባሳደር የጉዲፈቻ ልጇን ከዳች፣ የወንጂ መሬት ቅርምት በህዝብ እምቢታ ቀረ

ፍኖተ ዴሞክራሲ የኢትዮጵያ አንድነት ድምጽ ሬዲዮ (ኅዳር 1 ቀን 2009 ዓ.ም.) – በሰሜን ጎንደር አንቅሽ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ጦርነት በመካሄድ ላይ ይገኛል – ሕዝባዊ አመጹን አንደኛ ዓመት አስመልክቶ የሰብአዊ መብት ተከራካሪ ድርጅቶች መግለጫ አወጡ  – ከአዲስ አበባ በሚወጡ አምስት መውጫ መንገዶች የሚደረገው ፍተሻ ሕዝቡን እያስመረረው ነው – በካናዳ የወያኔ አምባሳደር በጉዲፈቻ ለማሳደግ የወሰደችውን ልጅ ለወላጆቹ ጥላ መሄዷ ታወቀ – ከወንጂ ሱካር ፋብሪካ መሬት ላይ ተቀንሶ ለአንድ ኩባንያ የተሰጠው መሬት በህዝብ ተቃውሞ ተግባራዊ ሳይሆን ቀረ – በሱማሊያ በአፍሪካ ህብረት ስር በሰላም ማስከበር ተግባር ላይ የተሰማራው የወያኔ ጦር ሰባት ሰዎችን ገደለ።

በሰሜን ጎንደር በወገራ ወረዳ አንቅሽ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ከትናንት ከጥቅምት 30 ቀን ጀምሮ ከፍተኛ ጦርነት በመካሄድ ላይ ይገኛል። ከገበሬዎች መሣሪያ ለመንጠቅ ወደ ቦታው የተንቀሳቀሰው የወያኔ አግአዚ ጦር በሕዝብ በኩል ከፍተኛ ጦርነት ገጥሞት በተደረገው ጦርነት በርካታ የወያኔ ወታደሮች መሞታቸው ሲነገር እስከዛሬጠዋት ድረስ በተካሄደ ውጊያ ከ50 በላይ ወታደሮች እስከሙሉ ትጥቃቸው የተማረኩ መሆናቸውን አንዳንድ ምንጮች ይጠቅሳሉ። የተወሰኑ የሕዝብ ወገኖች የሞቱና የቆሰሉ መሆናቸው ሲነገር ከመካከላቸውም አንድ የጎበዝ አለቃ ይገኙባቸዋል። በአካባቢው የሚገኙ የሕዝብ ወገኖችና የጎበዝ አለቆች እርዳታና ትብብር እንዲደርጉ ጥሪ ቀርቧል።

በወያኔ አገዛዝ ላይ ሕዝባዊ አመጽ የተጫረበትን አንደኛ ዓመት ለማስታወስ ሂውማን ራይትስ ዎች እና አምነስቲ ኢንተርናሽናል የተባሉ የሰብአዊ መብት ተከራካሪ ድርጅቶች በየበኩላቸው መግለጫዎች ያወጡ መሆኑ ታውቋል። ሂውማን ራይትስ ዎች ባወጣው መግለጫ የአዲስ አበባ ማስተር ፕላንን በመቃወም በየቦታው የተቀጣጠለውን ሕዝባዊ አመጽ ለመግታት የወያኔ የጸጥታ ኃይሎች በመቶ የሚቆጠሩ ዜጎችን መግደሉን፤ በሺ የሚቆጠሩን ማሰሩንና የብዙ ቤተሰቦችን ህይወት ያመሰቃቀለ መሆኑን፤ በተጨማሪም በኢሬቻ በዐል ላይ ዜጎች በግፍ መገደላቸውን በመቃወም ሕዝባዊ አመጹ አገርሽቶ የመንግስትና የግል ንብርት መውደማቸውን ዘግቧል። የወያኔ አገዛዝ የሕዝቡን አመጽ ለመቆጣጠር ያወጣው አስቸኳይ አዋጅ ወታደራዊ አገዛዙን ይበልጥ ያጠናከረው መሆኑን ገልጾ ኢንተርኔትና ሶሻል ሚዲያ በመዘጋታችውም መረጃ እንዳይወጣ አድርጓል ብሏል። ድርጅቱ በመግለጫው ማጠናቀቂያ የወያኔ አገዛዝ ምንም ዓይነት የፖለቲካ ለውጥ ለማድረግም ሆነ ከተቃዋሚዎች ጋር ለመነጋገር ምንም ዓይነት ፍላጎት የሌለው በመሆኑ ቀውሱ ሊቀጥል እንደሚችል ተንብይዋል። አገዛዙም ሆነ ዓለም አቀፍ ደጋፊዎቹ ፍትህንና ተጠያቂነትን መሰረት ያደረጉ ለውጦችን ማድረግ አስፈላጊ መሆኑ መረዳት ያለባቸው መሆኑን ገልጾ ይህ ተግባራዊ እስካልተደረገ ድረስ የሚቀጥለው አመትም ተስፋ አስቆራጭ ሊሆን እንደሚችል ግልጽ ነው በማለት ዘገባውን ደምድሟል። አምነስቲ ኢንተርናሽናል የተባለው ድርጅትም ባለፈው ዓመት የፈጠረውን ሁኔታ አስመልክቶ ተመሳሳይ ዘገባ ያቀረበ ከመሆኑም በላይ ከወልቃይት የማንነት ጥያቄ ጋር ተያይዞ የኮሚቴው አባል ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱን ለመያዝ ጋር የተደረገውን እርምጃ በመቃወም ሕዝባዊ አመጽ መነሳሳቱን ጠቅሶ እንደ ሌሎች ቦታዎች ሁሉ የወያኔ አገዛዝ የጸጥታ ኃይሎች በርካታ ሰዎች መግደላችውንና ማቁሰላችውን እንዲሁም የጅምላ እስራት ማካሄዳችው ዘርዝሯል። በዘገባው መጨረሻም በአገሪቱ ውስጥ ያለውን የሰብአዊ መብት ይዞታን ለመለወጥ አገዛዙ አስመሳይ የይስሙላ ተግባሮችን ከመውሰድ ተቆጥቦ ተጨባጭ እርምጃዎች መውሰድ አለበት ብሏል።

ከአዲስ አበባ በአምስቱም መውጫዎች ወደ ክፍለ ሀገራት በሚደረጉ ጉዞዎች የፍተሻ ኬላዎች ከመብዛታቸው የተነሳ አንድ የመንገደኞች አውቶብስ መድረስ ከሚገባው ከሁለት ሰዓት በላይ እንደሚዘገይና መንገደኞችን ለተለያዩ ችግሮች እያጋለጠ እንደሆን ዜጎች እየተናገሩ ነው። ከሽብር አዋጁ ጋር ተያያዞ በየቦታው የተቋቋሙት የፍተሻ ኬላዎች በዜጎች ላይ በዜጎች ላይ ከፍተኛ ወከባና ስቃይ እያደረሱ መሆናቸውን ወደ ተለያዩ አካባቢዎች የተጓዙና ከተለያዩ አካባዎች ወደ አዲስ አበባ የመጡ በምሬት ሲገልጹ ይሰማሉ፡፡ ወያኔ እያካሄደ ያለው የፍተሻ ተግባር አረመኔው ደርግ በ1969 እና በ1970ዎቹ መጀመሪያ ላይ እያካደ ከነበረው ጋር በቀጥታ ተመሳሳይነት እንዳለው ብዙዎች ያስረዳሉ፡፡

በካናዳ የወያኔ አምባሳደር የሆነችው ብርቱካን አያኖ በጉዲፈቻ ለማሳደግ የተረከበችውን ህፃን መልሳ ለወላጆቹ ጥላ መሄዷ እያነጋገረ መሆኑ ታወቀ፡፡ አምባሳደር ተብየዋ ህፃን የአብ ፍቅሩ የተባለውን ልጅ ተገቢውን ህጋዊ ውል ፈጽማ ከተረከበች በኋላ ባልታወቀ ሁኔታ ሀሳቧን ቀይራ ህፃኑን ለወላጆቹ ትታ ወደ ካናዳ መሄዷና እዛም ከሄደች በኋላ ላለፉት አራት አመታት ለህፃኑ ማድረግ የሚገባትን ባለማድረጓ መጠየቅ እንደሚገባት ዜጎች ሀሳባቸውን ሲሰነዝሩ ይሰማሉ፡፡ ሴትየዋ ህፃኑን ላለመውሰድ የወሰነችበት ምክንያት በገሀድ የሚታወቅ ባይሆንም ህጻኑን ካናዳ ከወሰደች በኋላ ጠቀም ያለ ገንዘብ በመቀበል ለሌሎች አሳልፋ ለመስጠት ወይም ለመሸጥ ያደረገችው ድርድር ባልታወቀ ምክንያት በመፍረሱ ሊሆን እንደሚችል ጥርጣሬያቸውን የሚሰነዝሩ ብዙዎች ናቸው፡፡

ከወንጂ ሸዋ ስኳር ፋብሪካ ይዘታ ላይ 500 ሄክታር ስፋት ያለው መሬት ተቆርሶ የፍራፍሬ ልማትን ለሚያካሂድ ለአንድ የኳታር ኩባንያ እንዲሰጠ ከሁለት አመት በፊት በአገዛዙ መወሰኑ የሚታወስ ሲሆን በአካባቢው ሕዝብና በወንጂ ሸዋ ስኳር ፋብሪካ ሠራተኞች የህብረት ትግል እስካሁን ድረስ የኳታሩ ኩባንያ መሬቱን ማግኘት አልቻለም፡፡ የአካባቢው ሕዝብና የሠራተኞቹ ጥያቄዎች ተመሳሳይ ናቸው፡፡ ይህ መሬት በስኳር ፋብሪካው ይዞታነት ከቆየ ወደፊት ፋብሪካው ሊስፋፋበትና ልጆቻቸው የሥራ እድል ሊያገኙ እንደሚችሉና ግልጽ ሲሆን መሬቱ ከባዕድ ኩባንያ ከተሰጠ ግን መሬቱን የዘረ-መል (ለጄኔቲካሊ ሞዲፋይድ) ዘር የሙከራ ጣቢያ በማድረግ አካባቢውን ሁሉ ሊበክሉ ይችላሉ የሚል ስጋት አለ፡፡ የወያኔ አገዛዝ አስቸኳይና አፋኝ አዋጁን በመጠቀም የህዝቡንና የሠራተኛው ድምጽ አፍኖ መሬቱን ለመስጠት አቅዷል የሚል ፍንጭ በመታየቱ የአካባቢው ህብረተሰብ ይህን ድርጊት ለማስቆም በለው መንገድ ሁሉ ለመታገል ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ከደረሰን መረጃ ተገንዝበናል፡፡

በሱማሊያ ውስጥ በአፍሪካ ህብረት የሰላም አስከባሪ ስር ተሰማርቶ የሚገኘው የወያኔ ጦር ዳካ በሚባለው ግዛት ውስጥ ሰባት ሰዎችን መገደሉን ሸበሌ ኒውስ የሚባለው የዜና ተቋም ካሰራጨው መረጃ ማወቅ ተችሏል። ከተገድሉት ሰዎች መካከል አንድ የሰማንያ አምስት ሽማግሌና አንዲት ነፍሰ ጡር ይገኙባቸዋል። ድርጊቱ የተፈጸመው የወያኔ ወታደሮች በኮንቮይ ታጅበው ሲሄዱ በአልሽባብ ወታደሮች በመጠቃታችው ለዚያ የተወሰደ የአጸፋ እርምጃ መሆኑን ዜናው ይጠቁማል።

ዝርዝር ዜና ያዳምጡ