በተለያዩ ከተሞች የተጀመረው ሕዝባዊ አድማና አመጽ ቀጥሏል

የፍኖተ ዴሞክራሲ ዜናና ኃተታ – በተለያዩ ከተሞች የተጀመረው ሕዝባዊ አድማና አመጽ ቀጥሏል – በጅማ ከተማ ባልታወቀ ሰው የተጣለው ቦምብ ፈንድቶ 13 ሰዎች አቆሰለ – ከግማሽ ሚሊዮን ዶላር በላይ የሆነ ጥሬ ገንዘብ ወደ ውጭ ሲወጣ ተያዘ – በወያኔ የሚፈርሱት ቤቶች ባለቤት አልባ ናቸው መባላቸው ሀሰት መሆኑ ተጋለጠ – በባህር ዳር ከተማ ቦምብ አፈንድተዋል በሚል የተያዙት የኢሕአፓ አባላት ናቸው በማለት ግብረ ስየል እየተካሄደባቸው ነው።

ረቡዕ ነሐሴ 17 ቀን 2009 ዓ.ም. በተለያዩ ከተሞች የተጀመረው ሕዝባዊ አድማና አመጽ በዛሬውም ዕለት ቀጥሎ የዋለ መሆኑ ከተለያዩ አካባቢዎች ከሚድርሱ መረጃዎች ለማወ ተችሏል። ለአምስት ቀናት የታቀደው አድማ በሚቀጥሉት ቀናትም ውስጥ ሊቀጥል ይችላል የሚል ግምት የተወሰደ ሲሆን ዋናው ዓላማ በነጋዴዎች ላይ የተከመረው ግብር እንዲቀንስና ሁሉም የፖለቲካ እስረኞች በአስቸኳይ እንዲፈቱ እንዲሁም በሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል እየተወሰደ ያለው ጭፍጨፋና መሬት የመንጠቅ እንቅስቃሴ እንዲቆም የሚል ነው። በትናንቱ ዕለት በሐረር፤ በአምቦና በሻሽመኔ ከተሞች ተሽድርካሪዎች የተቃጠሉ ሲሆን በጅማ ከተማ ንብረትነቱ የአዜብ መስፍን የሆነ አንድ የቡና ድርጅት በሕዝብ ጥቃት ደርሶበት በውስጡ የነበረው ቡና ለሕዝብ የተከፋፈለ መሆኑ ታውቋል። ወያኔ የንግድ ሱቆቹ እንዲከፍቱ የሰጠው ማስጠንቀቂያ ያልሰራ ሲሆን በሀረር በአምቦና በሻሽመኔና በሌሎች ቦታዎች ተሽከርካሪዎች እንደተቃጠሉ መረጃዎች ይጠቁማሉ። በተያያዘ ዜና ረቡዕ ነሐሴ 17 ቀን የካናዳ መንግስት ለዜጎቹ የጉዞ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል። በሀረርና በድሬደዋ እንዲሁም በአምቦና በሆለታ መካከል ግጭቶች የነበሩ መሆናቸውን በመጠቆም ዜጎች ወደቦታው እንዳይንቀሳቀሱ እንዲሁም ሁኔታው አስገዷቸው የሚንቀሳቀሱ ካሉ ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ መክሯል። በተመሳሳይ ዜና የምስራቅ ሀረርጌ ከጉርሱም ከተማ የመጡ ሽማግሌዎች የሶማሌው ክልል ልዩ ፖሊስ እየፈጸመባቸው ያለውን በደል በመዘርዝር ግፉ ባስቸኳይ እንዲቆም የሚጠይቅ ማመልከቻ ለወያኔ ባለስልጣኖች ሰጥተዋል ተብሏል። ሽማግሌዎቹ በአቤቱታቸው ውስጥ ባለፊት ጥቂት ወራት በአካባቢ የሉዩ ፖሊስ አባላት 55 ነዋሪዎችን የገደሉ መሆኑን ገልጽዋል።

ጅማ ውስጥ ባልታወቀ ሰው የታጠለ ቦምብ ፈንድቶ 13 ሰዎችን ያቆሰለ መሆኑ ታውቋል። ቦምቡ የተጣለው በከተማው መሀል ለገሃር በተባለው ቦታ ሲሆን ለምን ዓላማና ማን እንደጣለው ግልጽ አይደልም። ቦምቡን አፈንድተዋል የተባሉ አራት ሰዎች መያዛቸውን የዜና ምንጮች ቢገልጽሙ በከተማዋ የሚካሄደውን የሙት ከተማ አድማ ለማደናቀፍ የወያኔ የጸጥታ ኃይሎች ሳያፈነዱት አይቀሩም የሚል ግምት አለ።

ከግማሽ ሚሊዮን ዶላር በላይ የሆነ ገንዘብ ወደ ውጭ ሲወጥ የተያዘ መሆኑ ተነገረ። 541 671 ዶላር ይዞ ሲወጣ የተያዘው ሀብኒ አራብኑር የተበለ ግለሰብ ሲሆን ከወያኔ ባለስልጣኖች ጋር የቅርብ ግንኙነት እንዳለው ይጠረጠራል። የወያኔ ባለስልጣኖች በየአካባቢው የተፈጠረውን ሕዝባዊ እንቅስቃሴ በመፍራት የዘረፉትን የአገር ሀብት በጥቁር ገበያ በዶላር በመለወጥ በተለያየ መንገድ ወደ ውጭ ሲያወጡ መቆየታቸው የታወቀ ሲሆን ይህኛውም የሰሞኑን እንቅስቃሴ በመፍራት ያደረገው ሙከራ ሲያሆን አይቀርም በማለት አንዳንድ ወገኖች አስተያየት ይሰጣሉ።

ወያኔ የሕዝብን ቤቶች እያፈረሰና እያፈናቀለ መሬታቸውን በአዲስ አበባ ለትግራይ ባለሀብቶች እየሰጠ ያለውን አሰቃቂ ተግባር ለመሸፋፈን የሚፈርሱት ቤቶች በአብዛኛው በህገወጥ መንገድ የተሰሩትንና የቤት አልባ ዜጎች ሰፈራዎችን ነው በማለት ለማስተባበል ያደረገው ሙከራ በቅርቡ ተጋልጧል ። ወያኔ ታሪካዊውን የአዲስ አበባ ገዳም ሰፈርን ቅርቡ ለማፍረስ ማቀዱ መነገሩ ይታወሳል ። ወያኔ ሲያፈርሳቸው የቆየውም ሆነ አሁን እያፈረሳቸው ያሉት ቤቶች በለቤት አልባ ወይም መንገድ ሰፋሪዎች የሚቀልሷቸው መጠለያዎች ሳይሆኑ የቆዩ መኖሪያ ቤቶችን ነው ያሉ አዋቂ ምንጮች ወያኔ ሰፈሮችን እያፈረሰና እቁብ እድርና እያወደመ ዜጎችን መበታተኑ ሕዝብን ከመለያየት ጋር የተያያዘ መሆኑ መረሳት የለበትም ብለዋል።

ወያኔ የትግራይን ምድረበዳነትና በረሃነት ሁኔታ ለመቀየርና ልምላሜን ለማምጣት ባደረግኩት ጥረት ከተባበሩት መንግስትስት ጋር የተያያዘ አካል የወርቅ ሜዳሊያ ሰጠኝ ብሎ ቢመጻደቅም በመላ ኢትዮጵያ የአካባቢ ደህንነትን ይዞታ በመጉዳት በኢትዮጵያ ላይ ጥፋትን ፈጽሟል ያሉ ክፍሎች ውግዘትን አሰምተዋል ። የአየር ሁኔታ መዛባትና ድርቅ መስፋፋቱ ብቻ ሳይሆን ወያኔ በማዳበሪያና በሰው ሰራሽ የእህልና ጥጥ ዘሮች መጠቀሙም ያደረሰውን ከፍተኛ ጉዳት ጠቅሰዋል። ደን በማስጨፍጨፍና በመመንጠር እንዲሁም ለም መሬቶችን ለመሬት ዘራፊዎች መለገስና መስል አውዳሚ ተግባሮችን በመፈጸም እያደረሰ ያለው ጉዳት ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመው በወያኔ ስር ያለው የአየር መዛባትና የአካባቢ ድህንነት ዝቅጠት ከቀጠለ የኢትዮጵያ ዋና ምርቶች እንደተለመደው የሚመረቱ አይሆኑም ሲሉ አስጠንቅቀዋል ። ቡና ያመርቱ የነበሩ መሬቶች የጫት አምራች እንዲሆኑ የመደረጋቸው አንደምታ በቀላሉ መታየት ያለበት አይደለም በማለት ከማሳሰባቸው በላይ ትግራይ ለምታ በሆነማ ወያኔ የጎንደርን ለም መሬቶችን መዝረፍ ባላስፈለገው ነበር በማለት ለወያኔ የወርቅ ሜዳሊያ የሰጠው ክፍል ያው የወያኔ የጡት እናቶች አንዱ ነው ሲሉም ነቅፈዋል።

በባህር ዳር ከተማ ባለፈው ሳምንት የፈነዳውን ቦንብ በተመለከተ የከተማዋ የፖሊስ አዛዥ ዋለልኝ ዳኘው ይህ የጸረ ስላሞች ስራ ነው ካለ በኋላ ተጠርጥረው የተያዙት ግብረ ስየል የተፈጸመባቸው መሆኑን ውስጠ አዋቂዎች አጋልጠዋል። ዋለልኝ ዳኘው አፉን አውጥቶ ክስ ባይደረድርም የተያዙትን የኢሕአፓ አባሎች ናችሁ በሚል ወከባ እንደደረሰባቸው ለማወቅ ተችሏል። በጎንደርና ጎጃም በኢሕአፓ መዋቅር ላይ ከፍተኛ ዘመቻ ማድረግ ከተባለ ወራት ያለፉ ሲሆን ወያኔ ለዘመቻው ያገኘው ተጨባጭ መረጃ አለመኖሩንም ታዛቢዎች ገልጸዋል ። ኢሕአፓ በወያኔ ላይ ሁለገብ ትግል እንዲደረግ በይፋ ለዓመታት የጠራና ትጥቅ ትግል ጀምሮ የነበረው የኢትዮጵያ አንድነት ግንባር (ኢአግ) አባል የነበረ ቢሆንም እንዲሁም የሙት ከተማ አድማ ዋና አቀንቃኝና ደጋፊ ሆኖ የቆየ መሆኑንና ከሕዝብ አመጽ ጎን መቆሙን ባይደብቅም በጎንደር ጎጃም ሆነ በሌሎች ቦታዎችም ትግሉን መራሁ፤ እርምጃ ወሰድኩ በሚል ያወጣውና ያሰማው መግለጫ የሌለ ሲሆን ወያኔ በሚጠርጥራቸው ላይ እርምጃ ሊወስድ መነሳቱንም የጠበቀውና ያላስገረመው መሆኑንም አመላክቷል። የድርጅቱ አባላትና ደጋፊዎች ራሳቸውን ለመከላከል መውሰድ ያለባቸውን እርምጃ ያውቃሉና በእኛ በኩል ስጋት የለብንም ሲልም አንድ የኢሕአፓ ምንጭ ገልጿል።

ዝርዝር ዜና ከፍኖተ ዴሞክራሲ የኢትዮጵያ አንድነትድምጽ ሬዲዮ ያዳምጡ