ቴዎድሮስ አድሃኖምን ማጋለጡ ቀጥሏል

(ግንቦት 10 ቀን 2009 ዓ.ም.) – በቴዎድሮስ አድሃኖም ላይ የሚደረገው ማጋለጥ ቀጥሏል – የወያኔ ፍርድ ቤት የአልቃይዳና የአልሸባብ አባላት በሚል የፈረደባቸው ግለሰቦች የፈጠራ ክስ ሰለባ ሳይሆኑ አይቀርም ተባለ – የወያኔ አገዛዝ ሶማሌላንድ ኢምባሲ እንድትከፍት ፈቀደ – ተደጋጋሚ የድርቅ ሁኔታ ኢትዮጵያውያንን በጽኑ እየጎዳ ነው – በዩናይትድ ስቴትስ ሁለት ሴናተሮች የወያኔን የሰብዓዊ መብት አፈና የሚያጋልጥ የውሳኔ ረቂቅ አቀረቡ – የአውሮፓው ምክር ቤት አባላት ዶክተር መራራ ባስቸኳይ እንዲፈቱ ጠየቁ።

ለሚቀጥሉት ዓመታት የዓለም የጤና ድርጅትን የሚመራው ግለሰብ የሚመረጠው ግንቦት 14 ቀን 2009 ዓ.ም ሲሆን ቀኑ እየታቀርበ ሲመጣ ተወዳዳሪ ሆኖ በቀረበው በወያኔው ባለሥልጣን በቴዎድሮስ አድሃኖም ላይ የተለያዩ የዜና ማሰራጫዎች ትችቶችን እያቀረቡ መሆናቸው ታውቋል። የዋሽንግተን ፖስት ጋዜጣ በግንቦት 10 ቀን ባወጣው ዘገባ በርካታ የምዕራብ አፍሪካ አገሮች የአገራቸው ኢኮኖሚ እንዳይጎዳ በማለት የኢቦላ በሽታ ተስፋፍቶ በርካታ ሰዎች እስኪገድል ድረስ ደብቀው እንዳቆዩት ሁሉ ከ1997 እስከ 2004 ድረስ የጤና ሚኒስትር የነበረው ቴዎድሮስ አድሃኖም በአገሪቱ ውስጥ በተለያዩ ወቅቶች ተከስተው የነበሩትን የኮሌራ በሽታዎች ሌላ ሽፋን ስም በመስጠት ሲደብቅ መቆየቱን አጋልጧል። ዘ ዋየር ኢን የተባለው የድረ-ገጽ ጋዜጣም የወያኔ አገዛዝ ከፍተኛ ገንዘብ በማውጣት ቴዎድሮስ አድሃኖም እንዲመረጥ ከፍተኛ የዲፕሎማሲያዊ ጥረት ማድረጉንና ግለሰቡም ከ122 አገሮች በላይ ሄዶ የምረጡኝ ቅስቀሳ ያካሄደ መሆኑን ጠቅሶ በቅርቡ የደረሰበት መጋለጥ የመመረጡን ዕድል አጠራጣሪ አድርጎታል ብሏል።

የወያኔው አገዛዝ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የአልቃይዳና የአልሸባብ አባላት ናቸው ያላቸውን 23 ሰዎች እስከ አስራ አምስት ዓመት በሚደርስ እስራት የፈረደባቸው መሆኑን አንዳንድ የዜና ማሰራጫዎች ገልጸዋል። የአልቃይዳና የአልሸባብ አባላት የተባሉት ተከሳሾች በተለያዩ ቦታዎች የሽብር ተግባር ለመፈጸም ማቀዳችውንና ይህንኑ ተግባራዊ ለማድረግ ሲዘጋጁ የተያዙ መሆኑ ተገልጿል። ከመካከላቸው ሶስቱም የአስላማዊ መንግስት ለመመስረት እቅድ የነበራቸው መሆኑንም ተነግሯል። ተከሳሾቹ ድርጊቱን ለመፈጸም ተንቀሳቅሰዋል የተባሉበት ወቅት የሙስሊሙ ኅብረተሰብ አባላት በሃይማኖታቸው ላይ አገዛዙ እያካሄደ ያለውን ተጽዕኖ እንዲያነሳና መብታቸውን እንዲያከብር ከፍተኛ እንቅስቃሴና ትግል በሚያደርጉበት ወቅት በመሆኑ ግለሰቦቹ የተከሰሱ በፈጠራ ክስ መሆኑንና የወያኔን አምባገነን አገዛዝ በሰላማዊ መንገድ ከመቃወም ውጭ ሌላ ወንጀል እንደሌለባቸው በርካታ ወገኖች እየገለጹ ይገኛሉ።

የወያኔ አገዛዝ ከበርበራ ወደብ 19 ከመቶ የባለቤትነት መብት ካገኘ በኋላ ሶማሌላንድ አዲስ አበባ ላይ ኤምባሲ እንድትከፍት የፈቀደ መሆኑን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ገልጸዋል። ሶማሌላንድ ከ20 ዓመታት በላይ ከሶማሊያ ተገንጥላ የራሷን አስተዳደር ያቋቋመች ቢሆንም በተመድ እና በሌሎች የምዕራብ አገሮች እውቅና ሳይሰጣጥ መቆየቷና ከአንዳንድ የአረብ አገሮችና ከወያኔ በኩል ግን የተለሳለሰ ግንኙነት እንደነበራት ይታወቃል። በተመድ እውቅና ያላገኘች አገር አዲስ አበባ ላይ ኤምባሲ መክፈቷ ምን ሊያስከትል እንደሚችል ወደፊት የሚታይ ይሆናል በማለት አንዳንድ ወገኖች ይገልጻሉ።

ተደጋጋሚ የድርቅ ሁኔታ ኢትዮጵያውያንን ክፉኛ እየጎዳ መሆኑን ባለሙያዎች እየገለጹ ይገኛሉ። በ2007 እና በ2008 በኢትዮጵያ ውስጥ በገባው ድርቅ ምክንያት 10.2 ሚሊዮን ሕዝብ የአስቸኳይ ጊዜ የምግብ እርዳታ የሚያስፈልገው መሆኑና 7.9 ሚሊዮን ሕዝብ አስተማማኝ የሆነ የምግብ አቅርቦት እንዳልነበረው በወቅቱ ይታወቅ የነበረ ሲሆን ዘንድሮ ደግሞ የረሃብተኛውና የእርዳታ ፈላጊው ብዛት ከ5.5. ሚሊዮን ወደ 7.8 ሚሊዮን ከፍ እንዳለ ይታወቃል። የዓለም ባንክ ባለሙያዎች በሚሰጡት መረጃ መሰረት በአንድ ወቅት በድርቅ የተጎዱ ቤተሰቦች ለማገገም ከአራት ዓመት በላይ የሚወስድባቸው ሲሆን በተከሰተው ተደጋጋሚ ድርቅ የተጎዱት ለማገገም የረጅም ጊዜ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል ተብሏል። በርካታ አርብቶ አደሮች በተደጋጋሚ ድርቅ መናጢ ደሃዎች ከመሆናቸው በላይ የቀንድ ከብቶቻቸውን ሙሉ በሙሉ እንዳጡ ተነግሯል። በአሁኑ ወቅት በአገር ውስጥ ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ዜጎች ቁጥር 696 ሲሆን ከሱዳንና ከሶማሊያ የመጡት ስደተኞች ወደ 830 ሺህ ከፍ ብሏል ተብሏል።

ረቡዕ ግንቦት 9 ቀን 2009 ዓ.ም. በዩናይትድ ሴትስ የሴኔቱ ምክር ቤት የዴሞክራቲክ ፓርቲ ሴናተር ቤን ካርደንና የሪፐብሊካኑ ሴናተር ማርክ ሩቢዮ የወያኔ አገዛዝ የሕዝብን መብት በመርገጥ እየወሰደ ያለውን የጭካኔና የኃይል እርምጃ አስመልክቶ አንድ የውሳኔ ረቂቅ ያቀረቡ መሆናቸው ታውቋል። የውሳኔ ረቂቅ የወያኔ አገዛዝ በኢትዮጵያውያን ላይ የወሰደውን አሰቃቂ የኃይል እርምጃ ያወገዘ ሲሆን አገዛዙ በብዙ ሺ የሚቆጠሩ የፖለቲካ ድርጅት አባሎችና መሪዎችን፤ የፖለቲካ አንቀሳቅሾቹን፤ አክቲቪስቶችንና ጋዜጠኞችን በአስቸኳይ እንዲፈታና ዜጎች በህገ መንግስት የተሰጣቸውን መብት እንዲያከብር የሚጠይቅ ነው። በርካታ ሰዎች የታሰሩ መሆናቸውና በርካታ መገደላቸው ቢታወቅም እስካሁን ትክክለኛ ቁጥሩ በውል አልታወቀም በማለት የውሳኔው ረቂቅ ይገልጻል። የሴኔት የውጭ ጉንኙነት ኮሚቴ አባል የሆኑት ሴናተር ካርደን የወያኔ አገዛዝ በሰብአዊ መብት ዙሪያ ትልቅ እርምጃ ማድረግ አለበት ካሉ በኋላ ሽብርተኛነትና በመዋጋቱ ዙሪያ ተባባብሪ ነን ማለት የሰብአዊ መብት ሲጣስ ዓይናችንን እንጨፍናለን ማለት አይደለም ብለዋል። ሴናተር ሩቢዮም በበኩላቸው የወያኔ አገዛዝ የሰብአዊ መብት በማስተጠበቅ በኩል ወደ ኋላ እየሄደ በሄደ ቁጥር የአሜሪካ መንግስት ድርጊቱን ለማውገዝ ወደ ኋላ ማለት የለበትም ብለዋል። በአሁኑ ወቅት የውሳኔውን ረቂቅ ከ12 በላይ የሆኑ ሴናተሮች ደግፈውታል ተብሏል።

በተያያዘ ዜና የአውሮፓው የምክር ቤት አባላት የዶክተር መረራ መታሰር ያሳሰባቸው መሆኑን ገልጸው ባስቸኳይ እንዲፈቱ ጠይቀዋል። የምክር ቤቱ አባላት ዶ/መረራ የተያዙት በአውሮፓው ምክር ቤት በተደረገ ስብሰባ ላይ ተሳታፊ ሆነው ወደ አገራቸው ሲመለሱ መሆኑን አስታውሰው ህገ ወጥ በሆነ ሁኔታ በመያዛቸው በአስቸኳይ እንዲፈቱ ለወያኔ አገዛዝ ማሳሰቢያ ልከዋል። በተጨማሪም በተለያዩ ቦታዎች በዜጎች ላይ የወያኔ የጸጥታ ኃይላት የወሰዱትን አረመኔያዊ እርምጃ ነጻ ገለልተኛና ተዓማኒነት ያለው አካል እንዲመረምረው የሚያስፈልግ መሆኑን ገልጸዋል።

ከፍኖተ ዴሞክራሲ የኢትዮጵያ አንድነት ድምጽ ሬዲዮ ዜናና ሀተታ ያዳምጡ