በኢሕአዴግ ውስጥ ሽኩቻው ተባብሷል፣ የወያኔና የጁባ መቃቃር …

ከፍኖተ ዴሞክራሲ የኢትዮጵያ  አንድነት ድምጽ (ጥር 16 ቀን 2009 ዓ.ም.) – በኢሕአዴግ ውስጥ ሽኩቻና መሳሳብ ተጠናክሯል – በወያኔ እና በደቡብ ሱዳን መካከል የዲፕሎማሲያዊ ግጭት ተፈጥሯል በሚል የተሰራጨውን ዜና የወያኔ ባለስልጣኖች አስተባበሉ – ካሌ በሚባለው የፈርስንሳይ ከተማ አንድ ኢትዮጵያዊ በከባድ መኪና ተገጭቶ ሞተ – በሱማሊያ በአንድ ወታደራዊ ካምፕ አጠገብ መንገድ ላይ የተቀበረ ፈንጅ አራት ወታደሮችን ሲገድል ሌሎች አምስት አቆሰለ- ከጥቂት ቀናት በፊት የናይጄሪያ አየር ኃይል ባካሄደው የአየር ጥቃት የሞቱት ስደተኞች ቁጥር 236 ደረሰ – ሰሞኑን ቃለ መሀላ የፈጸሙት የጋምቢያ ፕሬዚዳንት ም/ፕሬዚዳንታቸውን ሾሙ፤ የቀደሞ ፕሬዚዳንት ከአገር ሲወጡ ከፍተኛ ሀብት ይዘው ወጡ።

ኢሕአዴግ በሚባለው የወያኔ ጭምብል ድርጅት ውስጥ ያለው ሽኩቻና የእርስ በርስ መሳሳብ በከፍተኛ ደረጃ የቀጠለ መሆኑን ከተለያዩ ምንጮች ከሚሰሙት ዜናዎች ማወቅ ተችሏል። የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጭ ግምባር በሚባለው የወያኔ ድርጅት እና በተለጣፊዎቹ በኦህዴድ በባዕዴን እና በደህዴድ መካከል ልዩነቱ እየሰፋ መሆኑ ሲገለጽ ሁሉም የወያኔን የበላይነትና ቁጥጥር እየተጋፉ ነው የሚል ወሬ ውስጥ አዋቂዎች እያራገቡት ይገኛሉ። በሁሉም የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች ውስጥ በአዲሶቹና በነባሮቹ መካከልም የአመለካከት የእምነትና የቁርጠኝነት ልዩነት ሰፊ መሆኑ ሲታወቅ በብዙ ጉዳዮች ላይ አለመጣጣምና አለመስማማት እየታየ ነው ተብሏል። የኢሕአዴግ ምክር ቤት የተባለው በአንድ ወቅት በከፍተኛ ደረጃ የመወሰንና የማስፈጽም ችሎታ ነበረው የሚባለለት አካልም ምንም የማይሰራ ልፍስፍስ እየሆነ መጥቷልም ይባላል። ሁሉንም ሥልጣን በቁጥጥሩ ስር በማድረግ በበላይነት ይመራ በነበረው በወያኔ ድርጅት ውስጥም በአመራሩ መካከል የነበረው ልዩነት እየጎላ መምጣቱም ይነገራል። ቀደም ብሎ የተነሳው ሕዝባዊ አመጽ ይበልጥ ተጠናክሮ ሊቀጥል ስለሚችል አንዳንድ እርምጃዎች መወሰድ አለባቸው በማለት ሀሳብ የሚያቀርቡ ጥቂት የወያኔ አመራር አባላት ፊሪዎችና ወላዋዮች በመባል እየተከሰሱ መሆናቸውም እየተሰማ ነው።

ራዲዮ ታማዙጅ የተባለው የደቡብ ሱዳን የዜና ወኪል ሰኞ ጥር 15 ቀን 2009 ዓ.ም. ባቀረበው ዘገባ በወያኔ አገዛዝ እና በደቡብ ሱዳን መንግስት መካከል የዲፕሎማሲያዊ ግጭት የተፈጠረ መሆኑን ጠቅሶ የወያኔ አገዛዝ የደቡብ ሱዳን አምባሰደሩን ከአገር እንዲወጣ ያዘዘ መሆኑን ገልጿል። ለግጭቱ መንስኤ የሆነው ጉዳይ በቅርቡ የደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት የግብጽ ከ ፕሬዚዳንት አልሲሲ ጋር ባደረጉት ንግግር የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ኃይሎች ጁባ ውስጥ ቢሮ እንዲከፍቱና ትግላቸውን በደቡብ ሱዳን እና በግብጽ ትብብር እንዲያጠናክሩ ተስማምተዋል በሚል በሶሻል ሚዲያ በተሰራጨው ዜና ምክንያት ነው በማለት አንድ ስማቸው ያልተገለጸ የደቡብ ሱዳን ባለስልጣን የተናገሩትን ዋቢ በማደረግ የዜና ምንጩ አትቷል። በባለስልጣኑ መግለጫ መሰረት ይህ ስምምነት በሚስጥር ቢደረግም የተቃዋሚው የሪክ ማቻር ቡድን በሶሻል ሚዲያ አማካይነት ጉዳዩን ይፋ በማደረጉ በሁኔታው የተበሳጨው የወያኔ አገዛዝ የወሰደው የአጸፋ እርምጃ ነው ብለዋል ተብሏል። በወያኔና በደቡብ ሱዳን መካከል ልዩነት ቢኖር እንኳ አዲስ አበባ የሚገኘው የደቡብ ሱዳን አምባሰደር በአፍሪካ ኅበረት ውስጥ የአገሩ ተወካይ በመሆኑ የወያኔ አገዛዝ ከአገሩ ሊያስወጣው አይችልም በማለት ባለስልጣኑ ጨምረው የገለጹ መሆናቸውን የዜና ምንጩ ጠቅሷል። የወያኔ አገዛዝ የውጭ ጉዳይ ባለስልጣኖች በሶሻል ሚዲያ የተስፋፋው ዜና ሀሰት መሆኑን ገልጸው በአገዛዙ በኩል ምንም ዓይነት እርምጃ እንዳልተወሰደ ይፋ አድርገዋል።

ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ ካሌ በሚባለው የፈረንሳይ የወደብ ከተማ አንድ ኢትዮጵያዊ ስደተኛ በከባድ መኪና ተገጭቶ ህይወቱ ያለፈ መሆኑ ታውቋል። ሟቹ የ20 ዓመት ወጣት ሲሆን ወደ እንግሊዝ አገር በሚሄድ የጭነት መኪና ላይ ዘሎ ለመውጣት ሲሞክር ተገጭቶ የሞተ መሆኑ ተነግሯል። ካሌ ከፈረንሳይ ወደ እንግሊዝ የሚገቡ በርካታ ስድተኞች ማዕከል የነበረች መሆኗ ሲታወቅ ከጥቂትቀናት በፊት የፈረንሳይ ባለስልጣኖች በዚያ የነበረውን የስደተኞች ካምፕ ማፍረሳቸውና ስደተኞችንም ወደ ሌሎች ስፍራዎች መበተናቸው ይታወቃል። የካምፑ መፍረስ ስደተኛውን ወደ አካባቢው ከመምጣት ያላቆመው መሆኑና በቀን ከ50 በላይ ስደተኞች እንደሚመጡ ተገልጿል። ከስደተኞቹ መካከል በርከት ያሉት የወያኔ አገዛዝን አስከፊ አገዛዝ በመሸሽ የሚሰደዱ ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን በመግለጽ በየጊዜው መዘገቡ ይታወሳል።

ማክሰኞ ጥር 16 ቀን 2009 ዓ.ም. ከሶማሊያ ዋና ከተማ ከሞጋዲሾ 18 ኪ.ሜ ርቃ በምትገኘው አፍጎዬ በምትባለው ከተማ በሚገኘው አንድ የወታደር ካምፕ አጠገብ መንገድ ላይ የተቀበረ ቦምብ ፈንድቶ ቢያንስ አራት ወታደሮች ሲገደሉ ሌሎች አምስት የቆሰሉ መሆናቸው ታውቋል። ሰኞ ጥር 15 ቀን ማምሻውን የአልሸባብ ታጣቂዎች በካምፑ ላይ ጥቃት ፈጽመው በተደረገው የተኩስ ልውውጥ ሸሽተው መሄዳቸው ሲታወቅ ቦምቡን ለመቅበር የቻሉት በዚህ ወቅት ሳይሆን አይቀርም የሚል ግምት አለ። የአልሸባብ ታጣቂዎች ቦምቡን መቅበራቸውን አምነው 7 ወታደሮችን የገደሉ መሆናቸውንና በርካታ ያቆሰሉ መሆናችውን ተናግረዋል።

ዝርዝር ዜና ከፍኖተ ዴሞክራሲ ያዳምጡ