በወሎ ወያኔ የጠራው የመምህራን ስብሰባ ሳይሳካ ቀረ

ፍኖተ ዴሞክራሲ ሬዲዮ (መጋቢት 9 ቀን 2009 ዓ.ም.) – በወሎ ወያኔ የጠራው የመምህራን ስብሰባ ሳይሳካ ቀረ – ወደ ቤጂንግ ይጓዝ የነበረ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ባስቸኳይ እንዲያርፍ ተደረገ – የአንዳርጋቸው ጽጌ ቤተሰቦች ጉብኝት ተፈቀዳላቸው ተባለ።

የመምህራንን የሙያ ፈቃድና እድሳት በሚል ሰበብ የደሴ ከተማ ት/ቤቶች ጽ/ቤት ከመጋቢት 7 ጀመሮ ዓ.ም ለሁለት ቀናት በሚል የጠራው ስብሰባ መምህራን ስብሰባው ባለመገኘታቸው ሳይሳካ መቅረቱ ከቦታው የደረሰን ዜና ገልጿል። በመምህራን እርምጃ የተበሳጩት የወያኔ ካድሬዎች መምህራኑ ከስብሰባ የቀሩበትን ምክንያት ካላመጡ ሕጋዊ አርምጃ ይወሰዳል በማለት በየትቤቶቹ ማስታወቂያ የለጠፉ ሲሆን መምህራንን አስተባብረዋል ተብለው የተጠረጠሩ ሶስት መምህራን እንደታሰሩ በተጨማሪ ማወቅ ተችሏል። የወያኔ አገዛዝ በሙያ ፈቃድና እድሳት ሽፋን ስብሰባ ስብሰባ የጠራበት ምክንያት ከሰሞኑ በመምህራን እየተካሄዱ ያሉትን የስራ ማቆም አድማዎች ለማክሸፍ የታሰበ መሆኑም ታውቋል። በሌላ በኩል በደቡብ ጎንዳር ካንድ ት/ቤት28 መምህራን በጎጃም በብቸና ወረዳ ከበላይ ዘለቀ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ከ40 በላይ መምህራን በላይ በወያኔ የጸጥታ ኃይሎች እንደታሰሩ ከተለያዩ ቦታዎች ካገኘናቸው መረጃዎች ለማወቅ ችለናል።

መጋቢት 9 ቀን 2009 ዓ.ም. 300 መንገደኞችን አሳፍሮ ከ አዲስ አበባ ወደ ቤጂንግ ይጓዝ የነበረ አንድ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ላሆር ፓኪስታን ውስጥ ተገድዶ ያረፈ መሆኑ ታውቋል። አውሮፕላኑ ያለቅዱ በአስቸኳይ ለማረፍ የተገደደው ሁለት ተሳፋሪዎች አውሮፕላን ውስጥ እርስ በርሳቸው በቡጢ በመደባደባቸው መሆኑ ተነግሯል። የቻይና ዜጎች ናቸው የተባሉት ሁለቱ ግለሰቦች አንደኛው የአእምሮ በሽተኛ ሌላኛው ደግሞ ሃኪሙ ነበር የተባለው ሲሆን እነሱና ሌላው በመገላገል ላይ የነበረ የአውሮፕላኑ አስተናጋጅ መለስተኛ የአካል ጉዳት የደረሰባቸው መሆኑን ለማወቅ ተችሏል። ሁለቱ ግለሰቦች በፓኪስታን የጸጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ስር ውለው ወደ ሆስፒታል የተወሰዱ ሲሆን ከተወሰነ ምርመራ በኋላም አውሮፕላኑም ጉዞውን ወደ ቻይና እንዲያመራ የተፈቀደለት መሆኑ ተዘግቧል።

የእንግሊዙ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በሰጡት መግለጫ በኢትዮጵያ ቆይታቸው ለአንዳርጋቸው ጽጌ ጠበቃ መያዝና የቤተሰብ ጉብኝት መፈቀዱን ያረጋገጡ መሆኑን ገልጸዋል። ከሶስት ዓመታት እስር በኋላ የወያኔ አገዛዝ ባለስልጣኖች ይህንን ቃል መስጠታቸው ሕዝባዊ ተጽአኖ ስለበረከተበተባቸው ነው የሚሉ ዜጎች ከዚህ በፊትም ለተለያዩ ክፍሎች ተመሳሳይ ቃል መግባቱ የሚታወቅ ስለሆነ ተግባራዊነቱ ወደፊት ይታያል ተብሏል።

ዝርዝር ዜና ከፍኖተ ዴሞክራሲ የኢትዮጵያ አንድነት ድምጽ ሬዲዮ ያዳምጡ