በደቡብ አፍሪካ ዘራፊዎ ች ያፈኗቸው ነጋዴ ተለቀቁ

( ግንቦት 21 ቀን 2009 ዓ.ም.) –  ከሳኡዲ አረቢያ የተመለሱ ስደተኞች ቁጥር ከ30 ሺህ አይበልጥም – ኢትዮጵያና ሌሎች የአፍሪካ አገሮች ለአዛውንቶች የሚሰጡት የጤና አገልግሎት ደካማ መሆኑን አንድ ጥናት አጋለጠ – በደቡብ አፍሪካ በዘራፊዎች ታፍነው የነበሩ አንድ ኢትዮጵያዊ ነጋዴ ተለቀቁ – በኢትዮጵያ ወታደሮች ጉዳት ደረሰብን ያሉ የሶማሊያ ዜጎች የቅሬታ ክስ ለአፍሪካ ኅብረት የሰላም አስከባሪ ኃይል አቀረቡ – በተለያዩ ቦታዎች በተደረጉ የሩጫ ውድድሮች ኢትዮጵያውያን አሸናፊዎች ሆኑ።

የመኖሪያ ፈቃድ ሳይኖራቸው በሳኡዲ አረቢያ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ቁጥር ከ150 እስከ 200 ሺ ሲገመት የሳኡዲ መንግስት እስከ ሰኔ 20 2009 ዓ.ም እንዲወጡ ያስተላለፈውን ትዕዛዝ አክብረው እስካሁን የተመለሱ ዜጎች ቁጥር ከ30 ሺ አይበልጥም ተብሏል። የወያኔ አገዛዝ ባለስልጣኖች፤ የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን መሪ ተብየው እና የዲያስፖራ ማህበር የተባለው አፍቃሪ ወያኔ ድርጅት ስደተኞች እንዲመለሱ ከፍተኛ ቅስቀሳ ቢያደርጉም ቅስቀሳዎቹ የስደተኞቹን ቀልብና ጆሮ ሊስቡያልቻሉ መሆኑ ታውቋል። የወያኔ አገዛዝ ስደተኞቹ እንዲመለሱ ከፍተኛ እንቅስቃሴ የሚያደርገው ለስደተኞቹ አዝኖ ሳይሆን አንድም ቀደም ብሎ እንደተጠቀሰው የፖለቲካ ስደተኞችን በቁጥጥር ስር ለማድረግ ካለው ከፍተኛ ፍላጎት የተነሳ ሲሆን በሌላ በኩልም ወደ ፊት ወደ ፊት ዜጎች ወደ ሳኡዲ የሚዘልቁበትን ተቋም በግሉ ለመቆጣጠር በመፈለግ ተብሏል። የዛሬ ሁለት ዓመት የሳኡዲ መንግስት ህገ ወጥ ስደተኞችን ለማስወጣት ተመሳሳይ እርምጃ ወስዶ እንደነበርም ይታወሳል።

ባለፈው ሳምንት አርብ ዕለት በታንዛኒያ ዋና ከተማ በዳሬሰላም የአዛውንቶች የጤና አገልግሎት አስመልክቶ በተካሄደ ኮንፈረንስ ላይ በሁለት ተቋሞች የቀረበ ጥናት ኢትዮጵያ፣ ሞዛምቢክ ታንዛኒያና ዚምባብዌ በእድሜ ለገፉ አዛውንት ዜጎቻቸው በቂ የህክምና አገልግሎት እንደማይሰጡ አረጋግጧል። በእነዚህ አገሮች ለአዛውንቶች ጤና የሚመደበው በጀት አነስተኛ ከመሆኑ ሌላ የተለያዩ አገልግሎት በመስጠት በኩልም ምንም እንዳልተጀመረ ይገልጻል። ከአራቱ አገሮች መካከል አዛውንቶችን ለመንከባከብ ስልጣና የወሰዱ ጥቂት ባለሙያዎች ያሏት ዚምባብዌ ስትሆን ሞዛምቢክ የስልጠና ማዕከል ያላት መሆኑ ተጠቁሟል። በተጠቀሱት አራት አገሮች ውስጥ ወደ ሆስፒታል ለመሄድ እድል ያላቸው በሽተኛ አዛውንቶች በጣም ጥቂት ሲሆኑ እድል አገኝተው ወደ ሆስፒታል የሚሄዱትም በሽታቸው በእድሜ መግፋት የሚመጣ መሆኑና ምንም ማድረግ እንደማይቻል በሀኪሞች ተነግረው ይመለሳሉ ተብሏል። ከመንግስት ምንም ዓይነት ድጋፍ የማይደረግላቸው አዛውንቶች ያስቀመጡት ወይም ከዘመድ አዝማድ የሚያገኙት ገንዘብ ወደ ሆስፒታል ለመጓጓዝም ሆነ በሆስፒታል የህክምና አግልግሎት ለማግኝት የሚያስፈልገውን ገንዘብ ለመክፍል የማይበቃቸው መሆኑን ጥናቱ አጋልጧል።

ባለፈው ሳምንት በደቡብ አፍሪካ በጆሃንስበርግ ከተማ አንድ ኢትዮጵያዊ ሀብታም ነጋዴ ካሳ በሚጠይቁ ሌቦች ታፍነው ተወስደው እንደነበረና በአንድ ቤቱ ውስጥ እጃቸውን ታስረው መሰንበታቸውን የደቡብ አፍሪካ ፖሊስ ቃለ አቀባይ ቅዳሜ ግንቦት 19 ቀን በሰጠው መግለጫ ገልጿል። ጠለፋው የተካሄደው ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ ግንቦት 15 ቀን ኢትዮጵያዊው በግላቸው የንግድ ውል ስምምነት ለማደረግ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ ሲሆን ሶስት ሰዎች በመኪና ወደ አንድ ቤት ወስደው እጃቸውን አስረው ካሰቃይዋቸው በኋላ ቤተሰባቸውን በስልክ በመገናኘት በካሳ እንደሚለቋቸው ተናገረዋል። መረጃው የደረሳቸው የነጋዴው ቤተሰቦች ጉዳዩን ለፖሊስ በማሳወቃቸው ሰዎች በቀላሉ ሊያዙና በቁጥጥር ስር ሊውሉ ችለዋል ተብሏል። በመሃሉ ሌቦቹ በነጋዴዎች ክሬዲት ካርድ በርካታ ገንዘብ ለማውጣት እንደቻሉም ተገልጿል።

በሶማሊያ የሰብዓዊ እርዳታ ሰራተኛ የሆነችው አሚና አብዱል ቃድር እና ለቻይና ቴሌቪዥን የሚሰራው አብዱልአዚዝ ቡሌ በሶማሊያ ባይደዋ ግዛት ውስጥ የወያኔ አገዛዝ ባሰማራቸው የኢትዮጵያ ወታደሮች ጥቃት የደረሰባቸው መሆኑን ገልጸው ለአፍሪካ ህብረት የሰላም አስከባሪ ኃይል ክስ ያቀረቡ መሆኑ ታውቋል። ለሶማሊያ ሰብዓዊ መብት ተቋም የምትሰራዋ አሚና ሐሙስ ግንቦት 17 ቀን አንድ የኢትዮጵያ ወታደር አካላዊ ጥቃት እንደፈጸመባትና ለአንድ ሰዓት አስሮ እንደፈታት ገልጻለች። ለቻይና ቴሌቪዥን የሚሰራው አብዱል አዚዝ ደግሞ ከባይደዋ ወደ ሞቃዲሾ በሚጓዝበት ወቅት የኢትዮጵያው ወታደር ፍተሻ ካካሄደ በኋላ ከያዘው ቦርሳ ውስጥ ልብሱን አውጥቶ መሬት ላይ ረጋግጦ ካበላሸው በኋላ ለመግደል በማስፈራራት እንደተናገረው ገልጿል። ጉዳዩን ለበላይ አለቃ ቢያሳውቅም ከማላገጥ በስተቀር ምንም እርምጃ እንዳልተወሰደ ተናገሯል። የሶማሊያ ዜጎች በወታደሮች ላይ ተመሳሳይና ተከታታይ ቅሬታዎች ሲያቀርቡ የቆዩ መሆናቸው የሚታወቅ ሲሆን የአፍሪካ ኅብረት የሰላም አስከባሪ መምሪያ በዚህ ላይ ምን እርምጃ እንደሚወስድ የሚታወቅ ነገር የለም።

እሁድ ግንቦት 20 ቀን በእንግሊዝ አገር በተደረገ የግሬት ማራቶን ውድድር ጥሩነሽ ዲባባ 31 ደቂቃ ከሶስት ሰከንድ በሆነ ጊዜ በመግባት አሸናፊ ስትሆን በዚያኑ ቀን በኦታዋ ካናዳ ውስጥ በተደረገ የ10 ኪሎሜትር የጎዳና ውድድር፤ ከሴቶች ነጻነት ጉደታ፣ ከወንዶች ልዑል ገብረሥላሴ አሸናፊ ሆነው ገብተዋል።

ከፍኖተ ዴሞክራሲ የኢትዮጵያ አንድነት ድምጽ ሬዲዮ ዝርዝር ዜና ያዳምጡ