በግፍ የዜጎችን ሕይወት ማጥፋቱ በአስቸኳይ ይቁም

(መግለጫ ከኢሕአፓ) –  በኢትዮጵያ አሰቃቂና በጣም አሳሳቢ የሆኑ ሁኔታዎች እየተመለዱ መምጣታቸው በጉልህ የሚታይ ክስተት ሆኗል።  ሕዝብን እርስ በርስ የሚያፋጁ አውሬዎች ነጻ ተለቀው ዜጎችን ለከፋ እልቂትና አደጋ አጋልጠዋል። ጅግጅጋ፤ ድሬደዋ ሶማሌዎች፤ ኦሮሞዎች፣ አማራዎች፤ ጉራጌዎች ወዘተ መፈናቀል ብቻ ሳይሆን በአሰቃቂ ሁኔታ ተገድለዋል። ጌዴዎ-ኦሮሞ፤ ቤኒሻንጉል አማራ፤ ሻሸሜኔ፤ ቦረና ገሬ፤ ትግሬ ወሎ ሕዝብ በየምክንያቱ እየተፈጀ፤ ንብረቱ እየወደመበት ለዓመታት ከኖረበት ቤትና ቀዬ እየተፈናቀለ ይገኛል። ኢሕአፓ ይህን ክስተት በጥብቅ እያወገዝ ሕዝባችን በወያኔ የተንኮል ድር ተጠልፎና ተከፋፍሎ ወደ እልቂት እንዳያመራና ሀገራችን ኢትዮጵያን ለጥፋት እንዳይዳርግ በጥብቅ ያሳስባል።

እየተከሰተ ያለው ሁኔታ ለአገራችንንና ለሕዝባችን አደጋን ያዘለና ይህ ነው የማይባል ጥፋትን ያረገዘና መውለድም የጀመረ ነው። ወያኔ ሥልጣኑን ጠግኖ ለመቀጠል በየቦታው ያጠመደውን የክፍፍል ፈንጂ ማፈንዳት ጀምሯል።  የኢትዮጵያ ሰላምና መረጋጋት አደጋ ላይ ወድቋል በሚል ላቀደው የመፈንቅል መንግሥት እርምጃ ማጠየቂያ እያዘጋጀ ነው። ፍቅር ሰባኪዎቹ አዳዲስ ሹሞች ይህ የሀገር አንድነት እንዴት በዴሞክራሲ ሊጠበቅ እንደሚችል ከሰብካው ባሻገር ያወቁበት አይመስልም። በጸረ ኢትዮጵያ አንድነት የታወቁና የማሉ ጠላቶችን በዙርያቸው በመሰብሰብና የአንድነት ሳይሆን የክፍፍልና የጥበት እርምጃዎችና አቅዋሞችንም እየወሰዱ መሆናቸው ዓይኑን ለከፈተ ዜጋ ሁሉ አሳሳቢ ሆኖ የሚከሰት ሆኗል። በጥበትና በጥላቻ ነውረኛና ጸረ ሕዝብ ድርጊቶችን– ወንጀሎችን– የሚያበረታቱ ወንጀለኛ ኃይሎች ሁሉ የክብር እንግዳ ሆነዋል። አገዛዙ የሽግግርን ሂደት ሰርዞ የግለሰብና የቡድን አምባገነንነት እንዲቀጥል መምረጡ ራሱ ላለው አስከፊ ሁኔታ መንገድ ጠራጊ መሆኑ ክርክር አያሻውም።

ኢሕአፓ ለተገደሉትና ለተጨፈጨፉት ዜጎች ቤተሰቦች ሁሉ ጽናትን ይስጣችሁ ይላል። ይህ የግፍና የፍጅት ሁኔታ ተከስቶ እንዳይቀጥል የወያኔን አገዛዝ አስወግደን ዴሞክራሲያዊ መንግሥት እንመስርት ሲልም ታግሏል፤ አሁንም እየተጋለ ነው። የወያኔ ኢሕአዴግ ስርዓት ተጠግኖ ቢሆንም እስከቀጠለ ድረስ በጅጅጋ ድሬደዋ ወዘተ የተከሰተው ሀገር አሳፋሪ ዕልቂትና ግድያ መቀጠሉ ከቶም የሚቀር አይደለም። ይህን በመገንዘብ የሀገራችንን ህልውናና የሕዝባችን ደህንነት ለመጠበቅ ጸረ ወያኔ ጸረ ኢሕአዴግ ትግላችን እንዲቀጥል ጥሪያችንን እንደግማለን። በወያኔ ዋና አነሳሽነት በሕዝብ መሃል የተቀሰቀሰው ግጭትና ግድያ በአስቸኳይ ሕዝብ እንዲያቆመውም ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።

የኢትዮጵያ ህልውና በደማችን ይጠበቃል!!
ጸረ ወያኔው ትግል ተፋፍሞ ይቀጥል !!
የኢትዮጵያ ሕዝብ አንድነት ይጠናከር !

pdf