በጎንደር ትግሉ ቀጥሏል፣ በባህርዳር አንዳንድ ት/ቤቶች ትምህርት አቆሙ፣ ወያኔ ከቱሪስቶች የሚያገኘው ገቢ እጅግ ቀነሰበት

ፍኖተ ዴሞክራሲ የኢትዮጵያ አንድነት ድምጽ ሬዲዮ (ኅዳር 05 ቀን 2009 ዓ.ም.) – በጎንደር የተፈጠረው ውጥረት አሁንም ቀጥሏል –  በባህር ዳር አንዳንድ ትምህርት ቤቶች ትምህርት አቆሙ – የአገሪቱ የቱሪስት እንቅስቃሴና ገቢ እያሽቆለቆለ ነው።

በጎንደር በበወገራ አውራጃ በእንቅሽ አካባቢ የተፈጠረው ውጥረት እስከዛሬ የቀጠለ መሆኑ ታውቋል። የወያኔ አገዛዝ ብዛት ያለው ጦር በአካባቢው ከማሰባሰብ በስተቀር ወታደራዊ እርምጃ ለመውሰድ ያልደፈረ ሲሆን የሃይማኖት አባቶችን በተደጋጋሚ በመላክ በአማላጅ ሕዝቡን ትጥቅ ለማስፈታት ያደረገው ሙከራ ያልተሳካለት መሆኑ ይነገራል። ሕዝቡ በተለያዩ አካባቢዎች ያሉ የጎበዝ አለቆች እንዲደርሱለት ጥሪ ከማድረገ አልተቆጠበም። በተለያዩ የአርማጭሆ ክፍሎችም በሕዝቡና በወያኔ የጸጥታ ኃይሎች መካከል ግጭቶች እንደነበሩ በአካባቢው ከፍተኛ ውጥረት እንዳለ ይነገራል።

በባህር ዳር አንዳንድ ትምህርት ቤቶች ትምህርት ያቆሙበት ሁኔታ እንዳለ ተሰምቷል። ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ቤት ለመመለስ የአገዛዙ ባለሥልጣኖች ወላጆችንና መምህራንን በመሰብሰብ እየመከረ ቢሆንም ተማሪዎቹ ወደ ትምህርት ገበታቸው ያልተመለሱ መሆኑ ታውቋል። በተወሰኑ ትምህርት ቤቶች የተጀመረው ትምህርት በማቆም ተቃውሞ የማድረጉ እንቅስቃሴ ወደ ሌሎች ትምህርት ቤቶች ይዛመታል ተብሎ ተገምቷል። በጢስ አባይ አካባቢ የወያኔን አፈና ለመሸሽ ከቦታው የተሰወሩ ልጆችን ካላመጣችሁ በሚል ወላጆች በአገዛዙ እየተሰቃዩና እየተንገላቱ መሆናችውን ከስፍራው የሚደርሱ ዜናዎች ይገልጻሉ።

ሕዝባዊ አመጹን ለመግታት የወያኔ አገዛዝ በወሰደው የኃይል እርምጃና ተከትሎም ባወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ምክንያት አገሪቱ ከቱሪዝም ንግድ የምታገኘው ገንዘብ በከፍተኛ ደረጃ ያሽቆለቆለ መሆኑ እየተነገረ ይገኛል። ባለፉት ሶስት ወራት ብቻ አገሪቱ ከቱሪዝም ንግድ ከ7 ሚሊዮን ዶላር በላይ ያጣች መሆኑ ታውቋል። ባለፈው የፈረንጆቹ አመት ወደ ዘጠኝ መቶ ሺ የሚደርሱ ቱሪስቶች አገሪቱን የጎበኙ ሲሆን በዚህ ዓመት የቱሪስት እንቅስቃሴ በመቀነሱ ምክንያት የወያኔ አገዛዝ ከ400 ሚሊዮን ዶላር በላይ ሊያጣ ይችላል ተብሎ ተገምቷል። ባለፈው ሳምንት ስድስት የስሎቫክና 4 የቼክ ተወላጅ የሆኑ ቱሪስቶች ሚዛን አካባቢ ገንዘብ፤ ክሬዲት ካርድ እና ሌሎች ዕቃዎችን መዘረፋቸው ለቱሪስቱ እንቅስቃሴ መቀነሰ ተጨማሪ ምክንያት ሊሆን ይችላል ተብሏል።