ባህርዳር ሰማዕታቷን አስባ ዋለች፣ በለንደን ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች በሆቴላቸው ገንዘብ ተሠረቁ

ፍኖተ ዴሞክራሲ – በባህር ዳር የፈነዳው ቦምብ ጉዳት አላደረሰም፤ በአገዛዙ የተጨፈጨፉትን ዜጎች ለማስታወስ በከተማዋ አድማና አመጽ ተደረገ – የቀድሞ የገቢዎችና የጉምሩክ ዋና ዳይሬክተር ወደ ውጭ ስትወጣ ተያዘች – በአገር ውስጥ ተፈናቃይ የሆኑ ዜጎች በቂ እርዳታ አያገኙም ተባለ – ባለፈው ሳምንት በአልሸባብ የተያዘችውን ከተማ ለማስለቀቅ ወያኔ ወታደሮችን ላከ – በለንደኑ የአትሌቲክስ ውድድር ኢትዮጵያውያን አሸናፊዎች ሆኑ፤ አንዳንዶቹ ከሆቴላቸው ተዘረፉ።

እሁድ ሐምሌ 30 ቀን 2009 ዓ.ም. ማታ በባህር ዳር ከተማ አቦ ክፍለ ከተማ ፖሊ ሜዳ በሚባለው አካባቢ በአስፋልት መንገድ ላይ አንድ ቦምብ የፈነዳ መሆኑ የተነገረ ሲሆን ፍንዳታው በህይወትም ሆነ በንብረት ላይ ጉዳት ያላደረሰ መሆኑ ታውቋል። የወያኔ አገዛዝ ቦምቡን በማፈንዳት የተጠረጠሩ አምስት ሰዎችን ከነመኪናቸው በቁጥጥር ስር ማዋሉን የገለጠ ከመሆኑም በላይ በጠቅላላው እስከ 12 የሚደርሱ ሰዎችን አሸባሪዎች በማለት ያሰረ መሆኑን ይፋ አድርጓል። ዛሬ ነሐሴ 1 ቀን 2009 ዓ.ም. ባለፈው ዓመት የወያኔ አግአዚ ጦር በግፍ የጨፈጨፋቸውን ሰላማዊ ሰዎች ለማስታወስ የባህር ዳር ከተማ ነዋሪ አድማ በማድረግ ሀዘኑን ሲገልጽ የዋለ ሲሆን ሱቆች በአብዛኛው መዘጋታቸውና የትራንስፖርት መኪናዎችም መቆማቸው ተነግሯል። በተያያዘ ዜና አምቦ ወሊሶ እና ደብረብርሃንን ጨምሮ በተለያዩ ከተሞች የግብሩን ጭማሪ በመቃወም ነጋዴዎች ሲያካሄዱ የቆዩትን የአድማና የአመጽ እንቅስቃሴ መቀጠላቸውን ከየቦታው ከሚገኙ መረጃዎች ለማወቅ ተችሏል።

የቀድሞ የገቢዎችና የጉምሩክ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር የነበረችው ወ/ሮ አለምጸሐይ ግርማይ በፖሊስ ቁጥጥር ስር መደረጓን ሪፖርተር የተባለው አፍቃሪ ወያኔ ጋዜጣ ዘግቧል። ግለሰቧ በሥልጣን ላይ በነበረችበት ወቅት ከ9 ሚሊዮን ብር በላይ የቀረጥ ገቢ ሳታስከፍል ለግል ጥቅሟ አውለዋለች በማለት ፖሊስ ምርመራ እያካሄደባት የነበረ ሲሆን በድንገት ከአገር ለመውጣት ስትሞክር ተይዛ ታስራለች ተብሏል።

በኢትዮጵያ የደቡብ ምሥራቅ በሆነው በኦጋዴን ግዛት በረሃብ ምክንያት ቤት ንብረታቸውን ጥለው የተፈናቀሉ 600000 የሚሆኑ ዜጎች በ264 ካምፖች ውስጥ ሰፍረው እንደሚኖሩ የዜና ምንጮች ጠቁመውል። ለእነዚህ የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች የሚደረገው እርዳታና ትብብር ከሌሎች ጎረቤት አገሮች ማለትም ከሶማሊያ ከደቡብ ሱዳንና ከኤርትራ በስደተኛነት ወደ አገር ውስጥ ለሚገቡት ስደተኞች ከሚሰጠው እርዳታና ትብብር የሚያንስ መሆኑን መረጃዎች እየቀረቡ ናቸው። በአገር ውስጥ በረሃብ ምክንያት የተፈናቀሉት ከጎረቤት አገሮች በጦርነትና በመሳሳሰሉት ተፈናቅለው በካምፕ ውስጥ ከሚኖሩት እኩል የተረጅዎችን ቀልብ አያገኙም በማለት ጉዳዩን በቅርብ የሚከታተሉት የእርዳታ ሰጭ ድርጅቶች ባለሙያዎች እየተናገሩ ይገኛል።

ባለፈው ዓርብ በአልሸባብ ኃይሎች የተያዘችውን ሊጎ ከተማን ለማስለቀቅ የወያኔ አገዛዝ ወታደሮቹን ወደ ቦታው ያንቀሳቀሰ መሆኑ ታውቋል። በሶማሊያ ዋና ከተማ በሞቃዲሾ እና በባይደዋ ከተማ መካከል የምተገኘውና ቁልፍ ቦታ የያዘችው ሊጎ ከተማ ባለፈው ዓርብ በአልሸባብ ኃይሎች የተያዘችው በከተማይቱ ወስጥ የነበሩት የአፍሪካ ኅብረት የሰላም አስከባሪ ኃይሎች ባልታወቀ ምክንያት ከተማዋን ለቀው ከወጡ በኋላ ነው ተብሏል። ከተማዋን ለማስለቀቅ ከባይደዋ ከተማ ወደ ሊጎ የተንቀሳቀሱ አርባ የሚሆኑ የኢትዮጵያ ወታደሮች በአልሸባብ ኃይሎች ጥቃት የተሰነዘረባቸው መሆኑ ሲታወቅ ምን ጉዳት እንደደረሰ ግን እስካሁን የተገኘ መረጃ የለም።

እሁድ ሐምሌ 30 በለንደን እየተካሄደ ባለው ዓለምአቀፍ የአትሌትክስ ውድድር ላይ አልማዝ አያና በ10000 ሜትር የወርቅ ሚዳሊያ ስታገኝ ጥሩነሽ ዲባባ አልማዝን ተከትላ ሁለተኛ በመውጣት የብር ሚዳሊያ አግኝታለች። በወንዶች ማራቶን አትሌት ታምራት ቶላ ሁለተኛ ወጥቶ የብር ሚዳሊያ አግኝቷል። በተያያዘ ዜና እዚሁ ለንደን ውስጥ በአትሌቲክስ ውድድር ተሳታፊዎች በነበሩ አትሌቶች ላይ የዝርፊያ ተግባር የተፈጸመ መሆኑ ተነግሯል። ጥሩነሽ ዲባባ ከሁለት እህቶቿ ጋር በያዘችው የሆቴል ክፍልና እና ማሬ ዲባባና አሰልፈች መርጊያ በያዙት ክፍሎች ውስጥ ከአትሌቶች የልብስ ኪስ ከቦርሳ ውስጥ እና ከመሳቢያ ውስጥ ገንዘብ የተሰረቀ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል። ዘራፊዎቹ የሆቴሉ ጠራጊዎች ሳይሆኑ አይቀሩም የሚል ጥርጣሬም ተፈጥሯል።

ለዝርዝር ዜና ፍኖተ ዴሞክራሲ የኢትዮጵያ አንድነት ድምጽ ሬዲዮን ያዳምጡ