ደብተራው ከ58 ዓመት በፊት በፃፈው ምጡቅ ቅኔ መነሻነት

ከታዬ ቶላ ከጎላ ሚካኤል –

ለፍኖተ ዴሞክራሲ የኢትዮጵያ አንድነት ድምጽ፣ የኢሕአፓ ራድዮ፡፡

የዛሬውን ደብዳቤዬን ፀገየ-ወይን ገብረ-መድህን /ደብተራው/ በ 1959 ዓ.ም. እ/ኤ/አ/፣  በዚያን ጊዜ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቭርሲቲ ይታተም በነበረው  “Something`  መጽሔት ቁጥር ስድስት፣ ገጽ አስራ አራት ላይ በእንግሊዘኛ የተቀኘውን “Remember” የተሰኘው ውብ፣ ምጡቅና እረቂቅ ቅኔ  ወደ አማርኛ መልሼው እንዲህ አቅርቤዋለሁ፡፡

አስታውሳለሁ
እንዲህ  አልኩኝ፣ “ለምን እንድመርጥ አላደርግኸኝም እግዜር?”
አያሌ ሰቀላና ሰፋፊ ህንፃዎች፣ በትእንግርት ከተሞሉ መናፈሻዎች ጋር፣
በርካታ ቀላድ፣ መልካም እርሻ፣ እዚህና እዚያ ፏፏቴዎች፣
ለመጎናጸፍ ወርቃማ ክንፎች፣ መነፅሮችና ጫማዎች፣
ሁሉንም ማድረግ የሚሳንህ የለም ትችላለህ፣
ምክንያቱም፣ በክንድህ አንድ ግፊት አውቃለሁ እንደሚሆን፣
ሰጥተህ ማስደመም ስትችል፣ ሕዝብ ሁሉን፣
ህይወት ምጥን እንደማለቷ ይገርመኛል እኔን!”
በኋላ አንድ ልጅ አገኘሁ፣ ልናፈስ ስወጣ፣
በመንገዱ ላይ ቡቱቶ ለብሶ የተሰጣ፣
ድምፁ የሞተና የተሳነው ለማውጣት ቃላት፣
ምንገደኞች እንደ አውሬ ሲመለከቱት፣
እንዲህ አለ፣ “በቅርቡ እሞታለሁኝ፤
ቤትም የለኝ፣ ምግብም የለኝ፣ እግርም የለኝ፣ ዐይንም የለኝ፡፡”

የተከበራችሁ የፍኖተ አዘጋጆች፣

ደብተራው ይህን ምጡቅ ቅኔ የዛሬ ሃምሳ አመት ነው የዘረፈው፡፡ ውድ የፍኖተ አድማጮች በዐይነህሊናችሁ ሃምሳ አመታት ወደ ኋላ ተጉዛችሁ የዚህን ቅኔ መነሻ ዘመን መዝኑትና አሁን ላለንበት ዘመን ነጎድጓዳማ ድምጹን አስተንትናችሁ ውስጡን፣ ጓዳውን፣ እምቡጡን እኝክ፣ ድቅቅ አድርጋችሁ ብሉት፡፡ ኃያል ቅኔ ነው፡፡ ለዚህ ነው ብዙዎች ደብተራውን አራት ዐይናው የሚሉት፡፡ ልብ በሉ ይህ የደብተራው ቅኔ የዛሬዎቹን ዘረኛ ገዢዎችን መሸንቆጥ ብቻ ሳይሆን ይለበልባል፣ ይፋጃል፡፡ ከዚህ ቀደም አንድ ወጣት አድማጫችሁ በአስራ ዘጠኝ ሃምሳዎቹ መጨረሻና በስልሳዎቹ መጀመሪያ ላይ በኢትዮጵያ ትምህርት ቤቶች የነበሩ የተማሪዎች እንቅስቃሴዎች እዴት እንደተነሱና እንደጠነከሩ ማብራሪያ መጠየቁን አስታውሳለሁ፡፡ ይህ የደብተራው ቅኔ የወጣቱን ጥያቄ በአጥጋቢ ይመልሰዋል፡፡ ጥቂቶች ዧ መንዧ ያለ ህይወት ሲቀጩ ዘጠና ዘጠኝ ከመቶ የሚሆነው ሕዝብ ግን እለት እለት ሞቱን እያሸተተ ይኖራል፡፡ አገራችን ኢትዮጵያን የጥቂት ፈላጭ ቆራጭ ገዢዎች የግል ንብረት ነበረች፡፡ የደሀ ልጅ መማር አይችልም ነበር፡፡ የደጃዝማቾቹንና የቢጤዎቻቸውን ከብቶች ያግድ ነበር፡፡ ህክምና ለደሀ እንደ ሰማይ የሰቀቀው ነበር፡፡ ደሀ ከታመመ አይድንም፤ ይሞታል፡፡ የንጉሡ ሹማምንቶችና አሸርጋጆች በሀገሪቱ በአጠቃላይ ለም የተባሉትን የእርሻ መሬቶች ተቀራምተው ይዘው፤ ገበሬዎችን እያሳረሱ ያስገብሩ ነበር፡፡ በዝናብ እጥረት ገበሬው የሚገብረው ሲያጣ፣ እህሉ በእርሻው ላይ ሳይዘረዝር ሲቀር፤ ገበሬዎች የጀርባቸው ሥጋ አልቆ አጥንታቸው እስኪታይ ይገረፉ ነበር፡፡ የንጉሡ መኳንቶችና ሹማምንት እራሳቸው ህግ ነበሩ፡፡ የገበሬዎች ልጆች የመኳንንቶቹ አገልጋዮች ነበሩ፡፡ መልከ-ቀና የሆኑ የገበሬዎች ሚስቶችና የደም ገንቦ የሆኑ ሴት ልጆቻቸው በመኳንንቶቹና በምስለኔዎቹ ይደፈሩ ነበር፡፡ በርካታ ገበሬዎች በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እየሆነባቸው ዲቃላ ልጆችን ያሳድጉ ነበር፡፡ እድሉን አግኝተው ትምህርት ቤት የገቡ የደሀ ልጆች በርሀብ ምክንያት ብዙም ሳይገፉ ለማቋረጥ ይገደዱ  ነበር፡፡ ይህን ግፍ በርህራሄ፣ በመረዳዳት የሚወጡት ባለመሆኑ፣ የሕዝቡ መብት እንዲከበር መጠየቅ የግድ አለ፡፡ ከዚህ የተነሳ ነበር፣

“መሬት ለአራሹ ይገባዋል፣
በላቡ ያስተማረው ይሟገትለታል!”

ቀስቃሽ ኃይለ ቃል ስር ተሰባስቦ መታገል የተጀመረው፡፡ የሰው ልጅ እንደ እቃ “ባርያ” እየተባለ እየተሸጥ የሚለወጥበት ዘመን በአዋጅ እንዲያከትም ቢደረግም መኳንንቱና ሹማምንቱ ከህግ በላይ ነበሩና የሰው ልጆችን ካለምንም ደሞዝ ያሠሩ ነበር፡፡ እንዲሁም መኳንንት ነን ብለው ኢትዮጵያን በግፍ ይገዙ የነበሩ እርስ በእርስ ስጦታ ሲሰጣጡ የሰው ልጆችን እንደ እቃ ይሰጣጡ ነበር፡፡ ንጉሣዊ ቤተሰቦችና በዙሪያው ተኮልኩለው የነበሩ አረመኔዎች በየከተሞች ግንባር ላይ የሚገኙ መሬቶችን ልቅም አድርገው ይዘው ነበር፡፡ በወቅቱ ወጣት የነበረውና በኮሌጆች ትምህርቱን ይከታተል የነበረው ዐይኑን ገልጦ ነበርና በእዚአብሔር የተመረጠ ነው የሚበለውን የንጉሡን ፈላጭ ቆራጭነት ባመቸው መንገድ ሁሉ መቃወምና ሕዝብን መቀስቀሱን ተያያዘው፡፡ የሌሎች ሀገራትን ህዝባዊ ትግሎችን፣ ፍልስፍናዎችን ወዘተ. በማንበብ እራሱን በጠለቀ ሁኔታ አነጸ፡፡ ከዚሁ ጋር አብሮ የሚያያዘው በየማምረቻ ድርጅቶችና ንግድ ድርጅቶች ውስጥ ይሠሩ የነበሩ እጅግ ዘግናኝ በሆነ ሁኔታ ጉልበታቸውን  ይበዘበዙ ነበር፡፡ ከላብ አደሮቹ መሀል ነቃ ያሉት ትግላቸውን አስተባብረውና አቀነባብረው መብታቸውን ለማስከበር ማህበር እንደሚያስፈልጋቸው በመረዳት በርካታ ስቃይና የህይወት መስዋዕትነት በመክፈል ማህበራቸውን ማቋቋም ችለው ነበር፡፡ የላብ-አደሮች ትግል አንዱ የወቅቱን ተማሪዎች እንቅስቃሴ የሳበ እንደነበር ማስታወስ ተገቢ ነው፡፡ በወቅቱ የነበሩ ፋብሪካዎች አብዛኛዎቹ የንጉሣዊ ቤተሰብ ሀብቶች የነበሩ ሲሆን ጥቂቶች ከውጪ በገቡ ባለሀብቶች፣ እንደ ወንጂና መረሀራ ስኳር ፋብሪካዎች፣ ኢንዶ ቴክስታይልና የመሳሰሉ ግዙፍ የሚባሉ ቢኖሩም በሠራተኛ ላይ ይፈጽሙ የነበረው ግፍ እንዲህ በዚህች ደብዳቤ ተዘርዝሮ የሚዘለቅ አይሆንም፡፡ አንዳንዶቹ ለሠራተኞች ይከፍሉ የነበረው ገንዘብ ሳይሆን ዱቄት በመስፈር ነበር፡፡ የብዙዎቹ ሠራተኞች ልጆች በቤተሰቦቻቸው ማጣትና መቸገር ሳቢያ ትምህታቸውን  እያቋረጡ በቀን ሥራ ለመሰማራት ተገደው ነበር፡፡ ይህ ሁሉ ነበር እየነዘረ ለወገናችንና ለሀገራችን ድምጻችንን እንድናሰማ፣ እንድንታገል ያደረገን፡፡ እዩት ደብተራውን፣ ይህን ቅኔ የተቀኘው የኮሌጅ ተማሪ በነበረበት ወቅተ ነው፡፡ ይህ ቅኔ ምጡቅና ረቂቅ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ወገናቸውን፣ የተገፋውን ገበሬ፣ የተመዘበረውን ላብ-አደር ከግፈኛ ስርዐቶች ነፃ ለማውጣት ትግሉን አሀዱ ብለን ስንጀምር ውጣ ውረዱን ተገንዝበን፣ ህይወታችንን ልንሰዋለት ቆርጠን፣  ይትግላችንን ግብ በነጠረ ሁኔታ አማትረንና አስቀምጠን ነበር፡፡ ይህ ደግሞ በወሬ አልቀረም ከንጉሡ ዘመን አንስቶ እስራቱንና መከራውን በአካልና በህሊና ያልተቀበለ ወጣት አይገኝም ብሎ መመስከር ማጋነን አይሆንም፡፡ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ትግል ሲነሳ ጭቆናንና ምዝበራን ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጫንቃ ላይ አሽቀንጥሮ ለመጣል በመሆኑ በኋላ ለዚህ ጉዞ አስፈላጊ ሁኔታን መጣል ስለሚያስፈልግ ኢሕአፓ ተጠነሰሰና ተመሰረተ፡፡ በአንድ ቃል ለማሰር የኢሕአፓ ፍላጎትና ግብ ከላይ ካስቀመጥኩት የኢትዮጵያ ሕዝብን ከግፍ ቀንበር ነፃ ማውጣትና ኢትዮጵያን የሕዝቦቿ ገሀነብነቷ ተሸሮ የሕዝቦቿ አገር እንድትሆን ለማድረግ ነበር፡፡ ዛሬም ድረስ የቀጠለው ትግል ለዚህ ነው፡፡ ፍጹም ለሌላ አይደለም፡፡  አንዳንዶች የእራሳቸውን አመርቃዥ እከክ በኢሕአፓ ላይ ለመላከክ የሚሹ “የስልጣን ጥመኛ” በሚል ስሙን ማጉደፊያና አጉል የመካሰሻ ነገር እየደነጎሩ እንደ ገደል ማሚቶ ሲጮሁ ይሰማሉ፡፡ ፍርዱን እናተው ፍረዱት፡፡ የስልጣን ጥመኛ መንገዱ እጥፍ እጥፍጥፍ ማለት እንደሆነ አታጡትም፡፡ አንዳንዶች “ወጣቱን አስጨረሱ” ብለው የአዞ እምባቸውን ሲያጠባጥቡ ወግዱ እያልን ነው፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ የኢሕአፓ አመራር የነበረ ማን ስየል ያልተቀበለ፣ ማን በሲባጎ ታንቆ ያልተገደለ፣ ማን በእሳት ተጠብሶ ያልተገደ፣ ማን ከፎቅ ተወርውሮ ያልተከሰከሰ፣ ማን በእሩምታ ጥይት ያልተገደለ፣ ማን በጭለማ የወያኔ እስር ቤቶች ታስሮ ያልተገደለ፣ ማን የእግሮቹ ጣቶች ያልረገፉ፣ ማን የእጆቹ ጥፍሮች ያልተነቀሉ፣ ማን ጥርሶቹ መፒንሳ ይልተነቀሉ ወዘተ. ይገኛል? ወንድሜንና እህቴን ገድለውብኝ እኔ አለሁኝ ማለት እንዴት ይሆንልኛል? እናንተው የዚህ ዘመን ወጣቶች ፍረዱት፡፡ እንደው ዝም ብዬ ትዝ ያሉኝን ልጥቀስ፣ ፀሎተ ህስቅያስና ይትባረክ ህስቅያስ ተሰውተዋል፡፡ ዳዊት ዓለማየሁና ሳሙኤል ዓለማየሁ ተሰውተዋል፡፡ ዮሴፍ አዳነና ተስፋዬ ደበሳይ ተሰውተዋል፡፡ ማርቆስ ሀጎስና ታዬ ቶላ ተሰውተዋል፡፡ ትርሲት ተሰውታለች፡፡ መምህር በላይና ኢንጂነር ኦስማን ተሰውተዋል፡፡ የኢሕአፓ የወጣት ሊግ አመራር የነበሩት እነ ቲቶ ህሩይና አለማየሁ እግዜሩ ስየል ተቀብለው ተሰውተዋል፡፡ ወዘተ. የኢሕአፓ አመራር እራሱን እንደሰጎን አሸዋ ውስጥ የሚቀብር ሳይሆን እንደ ማንኛውም አባል ሰቆቃ ወሰቆቃት በመቀበል መስዋዕትነትን የተቀበለ ለመሆኑ በደመቀ ቀለም በታሪክ መዝገብ ላይ ቦግ ብሎ የተመዘገበ ሀቅ ነው፡፡ ወደ ተነሳሁበት ልመለስ የደብተራው ቅኔ በጊዜ የተነቀነበበ ሳይሆን ከተጣፈበት ዘመንም ተሻግሮ የዛሬውን አውሬ ዘረኛ ቡድን ይሸነቁጣል፡፡ በዛሬይቱ ኢትዮጵያ ርሀብ በከተማም በገጠርም ሰፍኗል፤ በዛሬይቱ ኢትዮጵያ መላወስ አንችልም በክልል ተቀንበበናል፡፡ በዛሬይቱ ኢትዮጵያ በዐይናችን እንዳናይ፣ በአንደበታችን እንዳገልጽ፣ በጆሯችን እንዳንሰማ፣ በህሊናን እንዳናመዛዝን ሆነናል፡፡ ይህ ወያኔ የተባለ የግፍና የክፍፍል ቀንበር ከትከሻችን አሽቀንጥረን ለመጣል በአንድነት እንታገላለን፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ በአንድነት ከሚያደርገው ትግል ውጪ ሌላ የነፃነት መንገድ የለም፡፡ በኢትዮጵያ አንድነት ላይ የቆመ ሕዝባዊ ትግል ኃያል ነው፡፡ ያቸንፋል፡፡