አንጣሪያ ላንጣሪያ ቢደጋገፍ ተያይዞ ዘፍ

(ሊነበብ የሚገባው ወቅታዊ ሀተታ) – የጨነቀው እንዲሉ ወያኔ አንዴ ሚኒስቴሮችን ቀየርኩ ሲል– የጉልቻ ለውጥ እንኳን ሊባል የማይችል ውድቅ ሽግሽግ–በሌላ warningበኩል ደግሞ አቅም ገንቢ ተብለው የአካልም የፖለቲካም በሽታ በድን አድርጎ ያቆያቸውን እነ ተፈራ ዋልዋን (ዓለማየሁ አስፋውን) ወደ አውሮፓ ሊልክና የሕዝብ ትግል አብቅቶለታል፤ ሁሉንም እየተቆጣጠርን ነው ብሎ ሊሰብክ ታዟል። የውሸት አባወራ የነበረው ጌታቸው ረዳ አፍ አዳልጦት የመከፋፈል ዕቅዳችን አልሰራም፤ ትኩረታችንም በሚያሰጉ እንቅስቃሴዎች ሳይሆን በከንቱዎቹ ላይ ሆኖ ጉድ ፈላብን በማለቱ ተባሯል።  ወያኔ በወያኔ በተለጣፊ ተተካክቷል።  ነገር ቢበዛ በአህያ አይጫንም ነውና አንጣሪያ ላንጣሪያ ቢደጋገፍ ሁሉም ተያይዞ ዘፍ ነው።  ወያኔና ባዕዳንም መሰሎቻቸውን አቅፈው ብድግ ሊሉ ሲሉ ውድቀታቸው ያደባያቸዋል።

ትኩረት ሰጥተን በተጋረጡብን ላይ የምናተኩረው፣ በቸልታና በግርግር በደም የምናገኘውን ድል ዳግም እንዳይቀሙን ነው።  ታሪኩን የረሳ ስህተቱን ይደግማል ነውናም፣ ወደትላንቱ የምናተኩረው የትላንት ስህተትን እንዳንደግም፤ ትላንት የከዱን ዛሬ መሪ ተብለው ተሰይመውብን ዳግም አሳልፈው እንዳይሰጡን፤ የምናውቃቸው ተኩላዎች የበግ ለምድ ለብሰው እንዳይመጡብንና በአጭሩ ድላችንን እንዳንቀማ ነው።  የተቃዋሚ ድርጅቶችን ህብረት እንደምንፈልገው ሁሉ፤ ሰፋ ያለ ህብረት እውን እንዲሆን እንደምንመኘው ሁሉ ይህን፣ ፍላጎታችንና ጥረታችንን የሚያፈርሱትን ከወዲሁ ማጋለጡ ደግሞ ግዴታን ሆኖ ይገኛል።  የወያኔ ቅጥረኛ ክህደቱ ለምሳሌ በህብረት በገባ ማዕግስት ህብረቱን የሚያፈርስ እርምጃ ወስዶ በዚያውም ቅንጅት የተባለውንም ለማፍረስ ጎጂ እርምጃን ወስዷ።  ዛሬም ለወያኔ ሊታደግ እየተወራጨ ነው፡፡  የዚህ ከሀዲ ነፍስ አባትና አቋቋሚ የትኛው አዛውንት እንድነበረና ቀጥሎም የትኛውን ቡድን እንዳቋቋመ የምንረሳው ሊሆን አይችልም።  የሀገራችን እጣ፣  ነገ መጥፎ እንዳይሆን ዘብ መውጣት የዜጋ ግዴታችን ነውናም በፖለቲካው መስክ ይሉኝታና ቸልተኛነትን ልናስተናገድ አይጠበቅብንም።  አካፋን አካፋ ማለታችን፣ ይዘት፣ ጠባዩን፣ ስምሪቱን መግለጥ ግዳጅን መወጣት እንጂ ተራ ስድብ አይደለም።

ወደ ሽግግር መንግስት ጠባይ፤ ይዘትና ሂደት ከደርግ ግዜ ጀምሮ ስንተች ስናስረዳና ስናብራራም የቆየ ነው።   አዲስ ግኝት አይደለም የሽግግር ጽንሰ ሀሳብ። መካሄድ ባለበት መልክና ይዘት ባለመካሄዱ ደግሞ ደጋሞ ከሽፏል።  በዘመነ ደርግ ሁሉን አቀፍ የሽግግር ሂደት እውን ይሁን ሲባል፣ “የለም” ብሎ፣ የራሱን ወታደራው መንግስት ጊዜያው ብሎ ሰይሞ፣ የሚያድሩለትን ምሁሮች ከጎኑ ኮልኩሎ ለመቀጠል ሲነሳ የነበረው ተቃውሞና ትግል የሚረሳ አይደለም።  ሰው በላው ኮለኔልም አጋር ያላቸውን በልቶ፤ ሀገርን አዳክሞ ለወያኔ ሰጥቶ፤ የሀገር ንብረት ዘርፎ ፈረጠጠ።  ወያኔ ለስልጣን ሲበቃም ሽግግር የተባለ ከወያኔ የበላይነት ሂደት  አላላፈም–በአሜሪካ ድጋፍ።  የወያኔ የበላይነት ሰፈነ፤ የኤርትራም ግንጠላ ተከናወነ ጸደቀ፤ ለወያኔ አጋር የሆኑትም ሳይውል ሳያድር በአብዛኛው ተመነጠሩ።  ዛሬም የሽግግር ጉዳይ በሁሉም አፍ ላይ ያለ ሆኗል።  በአብዛኛው ያለፈውን ስህተት ዳግም ሊያመጣ ይመስላል።

ሁለት ግልጽ አማራጮች አሉ።

1ኛ/ ወያኔን በበላይነት አቅፎ እንዲቀጥል ማጀብ።  እነ በረከት፣ ስብሓት ቢወገዱም፣ የወያኔን የበላይነት መቀጠል የሚለውን አሜሪካንና እነ ጻድቃን ብቻ ሳይሆኑ እነ ሌንጬዎችም ደጋፊ ናቸው።  በአጭሩ የ25  አመቱን ውዳቂና ሀገር አፍራሽ ሁኔታ ዕድሜ ሰጥቶ፣ ኢትዮጵያን መጉዳት ማለት ነው። ከወያኔ ወደ ወያኔ መሸጋገር።

2ኛ/ ወያኔን ባያቅፍም ጥቂቶችን ያቀፈ ሽግግር ለማምጣት መጣር።

ሽግግር ካልን ለኢትዮጵያ ህዝብ የሚጠቅም ሽግግር በቅድሚያ:

ሀ/ጸረ ወያኔ መሆን አለበት፤
ለ/ ኢትዮጵያዊ ድርጅቶችን ያቀፈ መሆን አለበት፤
ሐ/ ሁሉን አቀፍና ሰፊ መሆን አለበት።

አንድ ወይም ሁለት ሆኖ የሽግግር ቻርተር አርቅቀናል፤ ህብረት መስርተናልና፣ የፈለገ ይደባለቀን ጥሪ ትግልን የሚጎዳ ነው። ያውም ከኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ጎን እንደሌላ ሀገር ይሁን ድርጅት ባንዲራ እየተውለበለበ።  በዚህ መንገድ የተሰማሩ እንዳሉ ከወዲሁ እያየን ነው። ለሁለት መክረውና አሲረው፤ ስምምነት አውጥተው ብቅ ሲሉ አጨብጭቦ የሚቀበላቸው ሊኖር አይችልም–ትላንት ህዝባችን በቅኝ እየተገዛ ነው የሚሉ የአንድ ሰው ቡድኖች ካልሆኑ በቀር።  ዝንብ ቢሰባሰብ መሶብ አይከፍትም ነውናም፣ ሚዛንና ህልውና የሌላቸው የምትሃት ቡድኖችን አቀፍን ማለቱ የሚኖረው ጠቀሚታና አንደምታ አይኖረውም።  መነገር ያለበት ሀቅ ይህ ነው።  ልማደኛ ግንባር መስራቾቾና የድርጅት ፌንጣዎች በአሁኑ ጊዜ በዝተዋል።  እዚህ እዚያ የሚዘሉ፤ ጽናት ያጡ።  ትላንት መስርተውት አልሰራ ያለውን ግንባር በአዲስ ስም ዛሬም ነፍስ ሊዘሩበት ይጥራሉ።  ዋናው ግብ  በአለቆቻቸው የተጠሉትን ማራቅ ነው።  ይህ የማራቅ ዘመቻ ደግሞ በአማራው ህዝብና በኢሕአፓ ላይ ያነጣጠረ ነው።  መሰረታዊ የሆነውን የሕዝብ ትብብርና መተቃቀፍ ለማፍረስም ይህን እውን ያደርግልናል የሚሉትን ሽግግር ቦታ ሊሰጡ በመጣር ላይ ናቸው።  ዳግም ሽግግር ሲሉ ሽግግር ስንል በሚል  ካልነው በላይ ጊዜ አናጠፋም፤ጉንጭ አናለፋም።  አወቀውና ነቅተው የሚያደርጉት ነውና ሕዝብን ይዘን የምንቃውመው ነው።  ኢትዮጵያን እናፈርሳለን የሚሉትን ለቀጠራቸው ወያኔ ጸረ ህዝብ ክስ ማጠየቂያ የሚሰጡት ሆነ አማራውን በወያኔ ክልል ሊሸነሽኑና ከሕዝብ ሊያጋጩ ሊነጥሉ የሚሞክሩትንም ነቅተንባቸዋልና የቀረን አምርረን ታግለን ከወያኔ ጋር ማስወገድ ብቻ ነው።   በዝምታና በቸልታ አናልፋቸውም።  ከኢትዮጵያ ሌላ ሀገር የለንምና  በሀገር ቀልድ የለም እንላለን።

በአሁኑ ወቅት ትግል በወረቀትና በመግለጫ ሳይሆን በትግሉ ሜዳ ላይ ነው። አውድማው ለሁሉም የሚታይ ነው። የሚፈሰው ደም፤ ግብረ ስየል የሚቀበለውና ታፍሶ የሚታገተው ወገን ብዛት ጠቋሚ ነው።  ያደቆነ ውሸት ሊያቀስ ሲዳዳ የሚመለከታቸው መታቀብ ቢችሉ፣ ቀና ሸጋ በነበር እንላለን።   የሕዝብን ትግል ቀምቶ የእኛው ነው ማለቱም አይጠቅምም ብለን ስንመክር ብንቆይም አሁን ደግሞ ጭራሽኑ ወያኔን በክልሉ ገጥመነዋል እየተባለ ነው።  ይህን የሚያምኑ አሁንም መኖራቸው ምጸታችችን ይጠቁመናል–ምንኛ ለማንም አፈ ጮሌ ሰለባ እንደሆንን።  የሚሉት ውሸት ቢሆንም፣ ቢሆን እንኳን ብንልም ፍየል ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ መሆኑ አልቀረም።  የብሄረሰብ ድርጅቶች ነን ሲሉ የቆዩ ቡድኖች በአቅዋማቸውና በስራቸው ሲወገዙ ሕዝባችን ተሰደበ ብለው አፍ ሊያዘጉ ሲጥሩ እናውቃለን።   ማንኛውም በመጥፎ መስመርና ጎዳና ላይ ያለ ድርጅት በዝምታ መታለፍ የለበትም።  በተለየ ስራው የህዝብን ትግልና ሀገርን የሚጎዳ ሆኖ እየታየ።   ነውናም ከመተቸትና ውሸትን ውሸት ከማለት ወደ ኋላ አንልም።   ሲዋሽ ወያኔ አይጎዳም፤ አይደበርም–ውሸት መሆኑ ያውቃልና።  ሕዝብ ግን ይጎዳል፤ መጡልን ሲል ብቻውን ይቀራል፤ ወያኔ ተጠቃ ሲል ሀሰት ሆኖ ተስፋ አስቆራጭ ሆኖ ይገኛልን።  ለዚህም ነው ዛሬ ሕዝብ በራሱ ትግል ተማምኖ በቆራጥነት በመታገል ላይ ያለው።   በዚሁ መቀጠል ነው የሚጠበቀው።  ከዚህም ሆነ ከዚያ ከሕዝብ ጎን ሊታገል ያውም በጠላቶች ታጥቆ የሚመጣ ጦር የለም።  ኢትዮጵያን ሊያፈርሱ የጣሩትም ቢሆኑ በትጥቅ ሊታገሉ አቅቷቸዋል።   ስለዚህ ሕዝብ በራሱ አንድነት፤ በራሱ ቆራጥነት፣ መስዋዕትነት፤ በጀግንነቱና ሀገር ወዳድነቱ ላይ ተማምኖ ትግሉን መቀጠል ማጧጧፍ ይገባዋል።  አንዱ ታላቅ ድላችን ህዛባችን ይህን ተረድቶ፣ በራሱ መተባበሩና ትግሉን መቀጠሉ ማፋፋሙ ነው።

ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ ቀጣይ ትግል!!

pdf_print