እምቢታው ቀጥሏል፣ የወያኔ ባለሥልጣናት ሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃ፣ የነዳጅ እጥረት . . .

ፍካሬ ዜና ታህሣሥ 22 ቀን 2010 ዓ.ም. (31 December 2017) – በተለያዩ አካባቢዎች ወያኔ ሕዝብ መጨፍጨፉ ተነገረ – የጎዳና ኗሪዎች ሞት እየጨመረ መሄዱ ታወቀ – የወያኔ ክፍፍል ወደ እርስ በእርስ መጠፋፋት እየተሸጋገር ነው ተባለ – ኮሌራ በተለያዩ አካባቢዎች መከሰቱ ተሰማ – በየዩኒቨርሲቲዎች የተቀጣጠለው የተማሪዎች አመጽ ተጠናክሮ ቀጠለ – የወያኔ ፓርላማ ላነሳው ጥያቄ ምላሹ በዝግ ስብሰባ መሆኑ እያነጋገረ ነው – ወያኔ ካድሬዎቹን በሀሰት የትምህርት ማስረጃ በኃላፊነት ማስቀመጡ ችግር ያስከተለ መሆኑ ታወቀ – የነዳጅ እጥረት በሰፊው መከሰቱ እየታየ ነው – የሀኪሞች ስደት በአስደንጋጭ ሁነታ እየጨመረ ነው ተባለ፡፡

በተለያዩ አካባቢዎች ወያኔ ሕዝብ መጨፍጨፉ ተነገረ

በተለያዩ አካባቢዎች የተጀመረው ፀረ-ወያኔ አመጽ በዚህ ባሳለፍነው ሳምንትም መቀጠሉ ተሰምቷል፡፡ በሻምቡ ከፍንጫ ስኳር ፋብሪካ በካሚዮኖች ተጭኖ እየተጓጓዘ የነበረውን መንገድ በመዝጋት ቅድሚያ ለአካባቢው ሕዝብ ሊታደል እንደሚገባው በመግለጽ የካዮኖቹን ጉዞ በመግታት የአካባቢው ሕዝብ ወያኔን መቃወሙ ታውቋል፡፡ ይህን የሕዝብ አመጽ ለመበተን ወያኔ አረመኔው አጋዚ የተባለው ጦሩን በሕዝቡ ላይ አዝምቶ ወደ አራት ሰዎችን የገደለ ሲሆን ከነዚህ ውስጥም አንዱ በጫማ ማጽዳት ይተዳደር የነበረና በወቅቱ እሚያጸዳበት ስፍራ ጫማ እየጠገነ እንደነበር ከስፍራው ከደረሰን መረዳት ተችሏል፡፡ ለጊዜው ቁጥራው በውል ያልታወቀ በጽኑ መቁሰላቸውን ተረድተናል፡፡ ወያኔ ለተከሰተው ሕዝባዊ አመጽ ተከሳሹ እራሱ መሆኑን ቢቀበልም ደም ማፍሰሱን በመቀጠሉ ወያኔ የሚያነባው የአዞ እምባ እንደሆነ የታወቀ መሆኑን ብዙዎች ይናገራሉ፡፡ ከዚሁ ጋር በተያዘ በባኮ፣ በቄለም፣ በኑኑ ቁምቢ ከዩኒቨርሲቲዎች ቅጥር የወታደር ኃይል ይውጣ፣ ፖለቲካ እስረኞቹ እነ ዶ/ር መረራ፣ አቶ በቀለ ገርባና ባልደረቦቻቸው በአስቸኳይ ይፈቱ፣ ወዘተ. የሚሉ ጥያቄዎች ያንጸባረቁ ሰልፎች መካሄደቸው ተሰምቷል፡፡

የጎዳና ኗሪዎች ሞት እየጨመረ መሄዱ ታወቀ

እንደሚታወቀው ዛሬ በየከተሞች በጎዳና ከሃያ እስከ መቶ ሺ የሚቆጠር ሕዝብ እየኖረ ነው፡፡ ወያኔ የዜግነትና የሰብአዊ መብቶቻቸውን በመርገጥ መጠለያ፣ የእለት ምግብና መሰረታዊ ህክምና የማግኘት መብቶቻቸውን እረግጦ በህይወት እያሉ ከመቃብር በታች በሆነ ህይወት እንዲሰቃዩ አድርጓቸዋል፡፡ ከህዳር ወር አንስቶ የአየር ንብረቱ ቅዝቃዜ እየጨመረ በመሄዱ በየቀኑ በአዲስ አበባ በተለያዩ አቅጣጫዎች በጎዳና ከሚኖሩት ውስጥ በቁርና በጠኔ ከአስር እስከ አስራ አምስት ሰዎች እንደሚሞቱ የደረሰን መረጃ ይጠቁማል፡፡ ለዚህ አደጋ ወያኔ ምንም ዓይነት የመታደግ እርምጃ እየወሰደ አለመሆኑ እነዚህን የጎዳና ኗሪዎች ክፉኛ እንዳሳዘናቸው መረዳት ተችሏል፡፡

የወያኔ ክፍፍል ወደ እርስ በእርስ መጠፋፋት እየተሸጋገር ነው ተባለ

ወያኔ በየጊዜው የክፍፍል አደጋ በተከሰተበት ወቅቶች ሁሉ የኃይል እርምጃ በመውሰድ በጭካኔ በስለትና በጥይት ገድሏል፤ እያሰረ አሰቃይቷል፤ አፍኖ ከነህይወታቸው ቀብሯል፡፡ ከዚህ ሁሉ ፋሽስታዊ ድርጊት ጀርባ በመሆን የጭፍጨፋዎቹና፣የግድያዎቹና የእስራቶቹ በሀንዲስ ስብሀት የሚባለው አረመኔ መሆኑ የሚታወቅ ነው፡፡ አሁን በተከሰተው የወያኔ-ህወሀት መከፋፈል ለጊዜውም ቢሆን የበላይነቱን የያዘው የስብሀትና የደብረ-ጽዮን ቡድን እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ይህ ቡድን የተመታው የዓባይ ወልዱና የአዜብ ቡድን ሊያንሰራራ ይችላል የሚል ስጋት አለውና ከፍተኛና ነባር የህወሀት-ወያኔ ካድሬዎችን እያፈነ በድብቅ እስር ቤቶች እያሰቃየ መሆኑ እየተሰማ ነው፡፡ የዛሬ አስራ አምስት ቀን አካባቢ ከአሁን ቀደም በሳዑዲ የሚገኘው የወያኔ ኤምባሲ ከፍተኛ ኃላፊ እንደነበር የሚነገርለት ሀዲሽ የተባለ ነባር የወያኔ ካድሬ ድምጽ በሌለው መሳሪያ መገደሉ ታውቋል፡፡ አንዳንዶች እንደሚሉት ሰውየው ቢሮው በተቀመጠበት የተገደለው በጨረር እንደሆነ ከሀኪሞች የተገኘው መረጃ መረዳት ቢቻልም፣ እንዲታፈን ማስፈራሪያ በመተላለፉ የሰውየው የግድያ ሁኔታ እየተነገረ የሚገኘው በሹክሹክታ መሆኑን መገንዘብ ተችሏል፡፡ ሟቹን ከሳዑዲ ኤምባሲ በማንሳት የወያኔ ንብረት በሆነው በሱር ኩንስትራክሽን ኩባንያ የፋይናንስ ኃላፊ መደረጉ የሚታወስ ሲሆን ሰውየው በዘረፈው ገንዘብ ቦሌ መንገድ ሜጋ በተሰኘው፣ የወያኔ ህንፃ አጠገብ ግዙፍ ሰማይ ጠቀስ ፎቅ በቅርቡ ማስረቁንም ለማወቅ ተችሏል፡፡

ኮሌራ በተለያዩ አካባቢዎች መከሰቱ ተሰማ

ወያኔ ሀቁን ለመደበቅ በየጊዜው አጣዳፊ ተውከትና ተቅማጥ እያለ የሚገልጸው ኮሌራን እንደሆነ በስፋትና በሀኪሞች ማስረጃነት እየተጋለጠ እንደሆነ መዘገቡ የሚታወስ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት በበርካታ የሀገሪቱ አካባቢዎች መከሰቱ የታወቀ ሲሆን በአስደንጋጭ ሁኔታ በአፋር፣ በጎንደር፣ በጎጃም፣ በወሎ፣ በትግራይ እየተስፋፋ መሆኑንና በወያኔ በኩል እዚህ ግባ የሚባል የህክምና ዘመቻ እየተደረገ አለመሆኑን ህፃና አድን የተባለው ዓለም አቀፍ ድርጅት ማጋለጡን መረዳት ተችሏል፡፡

በየዩኒቨርሲቲዎች የተቀጣጠለው የተማሪዎች አመጽ ተጠናክሮ ቀጠለ

ዘንድሮ በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ተማሪዎች የምረቃ ማረጋገጫ ፈተናን በመቃወም፣ በአዲግራት ዩኒቨርሲቲ አንድ ከወሎ የሄደ ተማሪን ግድያ በመቃወም ፣ በኦሮሞዎች ወያኔ እየፈጸመ ያለውን የጅምላ ማፈናቀል፣ አፈና፣ ግድያ፣ የቤቶችና የመንደሮች በእሳት ውድመት በመቃወም፣ ወዘተ. እየተደረጉ ያሉ የተማሪዎች አመጾች በዚህ ሳምንትም ተቀጣጥለው መቀጠላቸውን መረዳት ተችሏል፡፡ በአምቦ፣ በወለጋ፣ በድሬ ዳዋ፣ በሀሮማያ፣ በአዳማ፣ በመቱ፣ ወዘተ. ዩኒቨርሲቲዎች እስካሁን ትምህርት አለመጀመሩን ከየስፍራው ከደረሱን መረጃዎች መገንዘብ ተችሏል፡፡ በአሁኑ ወቅት ወያኔ በሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች የአረመኔው አጋዚ ጦሩንና የጨካኙ የፌደራል ፖሊስን በማስፈሩ የትምህርት ተቋማቱ ወደ ጦር ሰፈርነት በመቀየራቸው ተማሪዎች ወታደሮች ከግቢያቸው ለቀው እስካልወጡ ድረስ ወደ ትምህርት ገበታቸው እንደማይመለሱ ውሳኔ ላይ መድረሳቸውን ተያይዞ ከደረሰን መረጃ ተረድተናል፡፡

የወያኔ ፓርላማ ላነሳው ጥያቄ ምላሹ በዝግ ስብሰባ መሆኑ እያነጋገረ ነው

የወያኔ ፓርላማ በየጊዜው በሐረርጌ በኦሮሞዎች ላይ እየተፈጸመ ያለው ጭፍጨፋን በተመለከተ የወያኔ ቡችላ ጠቅላይ ሚንስትር ፓርላማ ቀርቦ ማራሪያ እንዲሰጥ ለተጠየቀው ሰውየው በወያኔ-ህወሀት በኩል እምነት በማጣቱና ሁኔታው ሸፋፍኖ ለማስረዳት ብቃቱ አናሳ ነው በሚል ከእሱ ጋር የአማራ፤ የኦሮሞ፣ የትግራይ ሹሞች እንዲገኙ መደረጉ ሰሞኑን ብዙዎችን ሲያነጋግር መክረሙን መገንዘብ ተችሏል፡፡ ይህ ሁኔታ ከአሁኑ ሰውየውን እንደ አሮጌ ቁና ለመወርወር መታቀዱን የሚያሳይ ሲሆን በምትኩ ለረጅም ጊዜ ሲወራለት የነበረውን በጠባብነቱና በጫካኝነቱ የሚታወቀው ደብረ-ጽዮን የተሰኘውን የህወሀት ካድሬ ለማድረግ እንደታቀደ ፍንጭ እየታየ ነው የሚሉ በርካቶች ናቸው፡፡

ወያኔ ካድሬዎቹን በሀሰት የትምህርት ማስረጃ በኃላፊነት ማስቀመጡ ችግር ያስከተለ መሆኑ ታወቀ

አብዛኛዎቹ የወያኔ ሹሞችና ካድሬዎች ከሀገር ውስጥ እና ከውጭ ሀገር በገንዘብ በተገዙ የትምህርት ማስረጃዎች ባለቤቶች እንደሆኑ የሚታወቅ ሲሆን ከሀገር ውስጥ የተገኙ የትምህርት ማስረጃዎች በትእዛዝና በገንዘብ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የተገኙ መሆናቸው ታውቋል፡፡ እነዚህ የትምህርት ማስረጃዎች ከመጀመሪያ ዲግሪ እሰከ ዶክትሬት የሚደርሱ መሆናቸውንም ከተሰበሰበው መረጃ መገንዘብ ተችሏል፡፡ ከወያኔ ሚኒስትሮች ጥቂት የማይባሉ በሀሰተኛ የትምህርት መረጃ ለሹመት መብቃታቸው ይነገራል፡፡ በአዲስ አበባ እራሳቸውን ለሚያጋልጡ ምህረት እንደሚደረግ በወጣው ማስታወቂያ መሰረት ከመቶ በላይ የሚሆኑ የወያኔ ካድሬዎች እራሳቸውን ማጋለጣቸው እየተነገረ ሲሆን ሌሎችም የተሰጠውን እድል ተጠቅመው እራሳቸውን እንዲያጋልጡ እስከ እዚህ ወር በጨረሻ ቀነ ገደብ እንደ ተሰጣቸው መገንዘብ የተቻለ ሲሆን የተፈጸመው ወንጀል ከይቅርታ በላይ ነውና ይቅርታ ሰጥቻለሁ የሚለው ክፍልም ከአጥፊዎቹ ጋር አግባብ ያለው ሀጋዊ እርምጃ ሊወሰድባቸው እንደሚገባ አስተያየታቸውን እየሰነዘሩ መሆናቸውን ተገንዝበናል፡፡

የነዳጅ እጥረት በሰፊው መከሰቱ እየታየ ነው

ከሀሙስ አንስቶ በአዲስ አበባ በበርካታ ነዳጅ ማደያዎች ነዳጅ እንደሌለ ነዳጅ ፍለጋ በተለያዩ የከተማዋ አቅጣጫዎች ከተንቀሳቀሱ ሾፌሮች መረዳት ተችሏል፡፡ በአሁኑ ወቅት ወያኔ ለነዳጅ ማስገቢያ የሚሆን የውጪ ምንዛሪ ስለ ሌለው የተለያዩ ነዳጆችንና ቅባቶችን ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባት ከወያኔ ጋር ውል የፈጸሙ ኩባንያዎች ወያኔ ሂሳባቸውን በወቅቱ እንዲከፍላቸው ከወያኔ ጋር ሙግት ውስጥ መግባታቸው የሚታወቅ ነው ተብሏል፡፡ አንድም በየወሩ መጨረሻ ወያኔ የሚያደርገውን የነዳጅ ዋጋ ማሻሻያ ለማድረግ ከወዲሁ የተደረገ ዝግጅት ሊሆን እንደሚችልም ጥርጣያቸውን የሚሰነዝሩም እንዳሉ ተገንዝበናል፡፡

የሀኪሞች ስደት በአስደንጋጭ ሁነታ እየጨመረ ነው ተባለ

የህክምና ባለሙያዎች ፍልሰት ከአመት አመት እየጨመረ እንደሆነና በወያኔ በኩል ችግሩን ለመፍታት የተደረገ ሌላው ቀርቶ፣ ሙከራ እንኳ አለመኖሩ እያነጋገረ ነው፡፡ ለሀኪሞች የሚከፈለው የወር ደሞዝ ስድስት ሺ ብር በመሆኑና እንደገና ወደ ትምህርት ቤት ተመልሰው የተወሰነ የህክምና ዘርፍ ለማጥናት እንደ ተመደቡበት አካባቢ ከሁለት እስከ አራት አመታት ለመጠበቅ ይገደዳሉ፡፡ ከዚህ ጋርም በተያያዘ በሄዱባቸው አካባቢዎች የወያኔ ዘረኛና ጠባብ የፖለቲካ ድባብ ስለሚጫናቸውና የወኔ አባል እንዲሆኑ ግዴታ ስለሚጣልባቸው የሚወዱት ሀገራቸውንና ወገናቸውን እየጣሉ ህሊናቸው ለማይፈቅደው ለስደት ዓለም መዳረጋቸው ታውቋል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ በአነስተኛ ግምት ዘጠና ከመቶው የሚሆኑ ሆስፒታሎች ለህይወት እጅግ አስፈላጊ የሆኑ በሽታ መመርመሪያ መሳሪያዎች የሌላቸው ከመሆኑም በላይ መደሀኒትም የለም፡፡ ከበሽታቸው በቀላሉ ሊፈወሱ የሚችሉ ህፃናት፣ እናቶች፣ አረጋውያን፣ ጎልማሶች በሀኪሞቹ እጅ ላይ ሆነው ህይወታቸው ሲያልፍ ማየት በእጅጉ የሚረብሽ በመሆኑ ሀገራቸውን እየጣሉ በገፍ እየተሰደዱ መሆናቸው የወያኔ የዘር ፖለቲካ አንዱ አሳዛኝ ገጽታ ነው ተብሏል፡፡

ለዝርዝር ዜና ፍኖተ ዴሞክራሲ የኢትዮጵያ አንድነት ድምጽ ሬዲዮን ያዳምጡ