ከአድዋ ድል እስከ 5ቱ ዓመት ጦርነት በወፍ በረር፡ ቀለም እና ብቀላ

ከዓለሙ ተበጀ – ከ1928 እስከ 1933 ባለው ጊዜ ኢትዮጵያ ከጣሊያን ወረራ ጋይል ጋር ያካሄደችው ጦርነት በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው የቀለም ፍትጊያ በግልጽ አፍጥጦ እንዲያይ አድርጓል። ቀድሞውኑም አድዋን ትከትሎ ዋናዎቹ የአውሮፓ መንግስታት የነጭ ሃይል በጥቁር ሕዝብ የደረሰበት ሽንፈት አስቆጭቷቸውና በነሱም ቅኝ ተገዥዎች ላይ የሚያስከትለው መነሳሳት አስግቷቸው ከተሸናፊዋ ጣልያን ጎን ቆመዋል።

ዶ/ር ሹመት ሲሻኝ እንደገለጹት፣ ጣሊያን የጦር ኋይሏንና መሳሪያዎቿን ታግዝባቸው ዘንድ በእንፋሎት የሚሰሩ መርከቦች ብሪታንያ እረድታለች። ከሰላ ላይ በመሃዲሲቶች ተከቦ የነበረውን 2 ሺህ ገደማ የጣሊያን ሃይል ነጻ ለማድረግም ወታደር ልካለች። የዚህም ዓላማ የመሃዲስቶቹን ሃይል ከጣሊያን ግለል በማድረግ ኢትዮጵያን ዳግመኛ የምትወጋበት ፋታ እንድታገኝ ለማድረግ ነበር። የጀርመን ንጉስም በሃገሩ ወደነበረው የጣሊያን ኢምባሲ በመሄድ በአድዋው ሽንፈት የተሰማውን ሃዘን ገልጿል። አንድ የጀርመንን የውጭ ጉዳይ ቢሮ አመለካከት የሚያንፀባርቅ ጋዜጣ “የአውሮፓ ክብር አፍሪካ ውስጥ ውርደት ደርሶበታል። ይህን ክብር ከመንበሩ ለመመለስም ሌላ ዘመቻ መካሄድ አለበት” በማለት ጽፏል። የወቅቱ የአስትሮ – ሀንጋሪያ አጼ ግዛት መንግስትም በደረሰው ሽንፈት መጸጸቱን ጠቅሶ የጣሊያን መንግስት ለ “እናት ሀገር ደህንነት ምንም ስጋት ሳይገባት” የሚያሻውን ያህል ጦር በኢትዮጵያ ላይ ማዝመት እንደምትችል አሳውቋል።

የባቲካኑ “ቅዱሱ” ካቶሊካዊ አባት ሳይቀሩ በጣሊያን ላይ በደረሰው ሽንፈት እጅግ አዝነዋል። በዚህ የተነሳም ለምሳሌ እ. ኤ. አ በመጋቢት 4/ 1896 እለት ሊካሄዱ ይገባቸው የነበሩ ቤተክርስቲያናዊ ስርዓተ ሁነቶች እንዲስተጓጎሉ አዘዋል። ከአጼ ምኒልክ ጋ የተሻለ ወዳጅነት የነበራት ፈረንሳይም ብትሆን የኢትዮጵያ ድል አስደንግጧታል። አንድ የሃገሪቱ ጋዜጣ “ከአረመኔው ዓለም የውጣ ሃይል ባንድ የስለጠነ ሀገር ላይ ባደረሰው ሽንፈት ፈረንሳይ ተጸጽታለች” ብሏል። አጼ ምኒልክ ለፈረንሳዊው የጅቡቲ ገዥ በጻፉት ደብዳቤ ላይ እንደጠቀሱት ከአድዋው ጦርነት በኋላ የአውሮፓ መንግስታት በጣሉት ማእቀብ ፈረንሳይም ተባብራለች። በአጠቃላይ በወቅቱ ካውሮፓዊያኑ መንግስታት ኦርቶዶክሳዊቷ ሩሲያ ብቻ ለኢትዮጵያ ወገናዊነትን አሳይታለች። በሁለቱ ሀገሮች መካከል ያለው ርቀት የዚህን ወገናዊነት ተግባራዊ ጠቀሜታ አሳጣው እንጂ።

ከ40 ዓመት በኋላም ጣሊያን የወታደራዊ ድል ገድል የለሽ ያደረጋትን የአድዋን ቂሙዋን ልትወጣ ፈለገች። እ. ኤ. አ በ1922 ሞሶሎኒና የፋሽስት ፓርቲው ስልጣን ላይ ሲወጡ ደግሞ የመስፋፋት በተለይም ኢትዮጵያን ወሮ ለመያዝ ፍላጎቷ ዳግም አገረሸባት እና በ1928 ወረራ አካሄደች።

ከአንደኛው የዓለም ጦርንት በሁዋላ የመንግስታትን ትብብር ለማጠናከርና ሌላ መስል ጦርነትን ለማስቀረት እንዲረዳ ታስቦ የተቋቋመውው የመንግስታቱ ማህበር አባላት ውስጥ ፈርጠም ያለ ጡንቻ የነበራቸው ብሪታንያና ፈረንሳይ ደግሞ ሞሶሎኒ ከሂትለር ጋር እንዳያብር የነበራቸው ፍርሃት ኢትየጵያን በተመለከተ በሚቀይሱት ፖሊሲ ላይ ተጸኖ አሳድሯል። ስለዚህም ሁለቱ ዋነኛ የምእራብ አውሮፓ “ዴሞክራሲያዊ” መንግስታት ጣሊያንን ላለማስቀየም ወሰኑ። ቅድሚያ የሰጡትም ከኢትዮጵያ ይልቅ አውሮፓ ነክ ለሆነው የራሳቸው ደህንነት ነው።

በአጠቃላይ የብሪታንያ መንግስት ከፈረንሳይ ጋር በማበር ይህንን መሰል ጣሊያንን አባባይ ፖሊሲ ቢያራምድም የህዝቡ አቋም ባመዛኙ አፍቃሪ..ኢትዮጵያ ነበር ማለት ይቻላል። ይህ ግን መንግስታዊ ያልሆኑ አንዳንድ አካላት ወይም ግለሰቦች የጣሊያንን ወረረራ የሚደግፍ እንቅስቃሴ አላደረጉም ማለት እንዳልሆነ ሊታወስ ይገባል። ለምሳሌ በውቅቱ የኦብዘርቨር እትም አዘጋጅ ጀ. ኤል ጋርቪን “አብስኒያዊያን በነጭ ዘር ላይ ድልን ተቀዳጅተው ቢሆን ኖሮ በጨለማው አህጉርና በሌሎችም አህጉራት መፍትሄ የማይገኝለት ችግር” ይፈጠራል ባይ ነበሩ። የዚሁ አመለካከት ዋና አቀንቃኝ ዘ አርል ኦፍ ማንሰፊልድ “ጣልያን ብትሸነፍ በቀለም ህዝቦች መሃል ረብሻና አመጽን ለማነሳሳት ለሚጥሩት ታላቅ ማበረታቻ ይሆናል፣ በምስራቅ አፍሪካ ይዞታችንም ላይ ከፍተኛ ጥፋት ያስከትላል” በማለት አስጠንቅቀዋል።

የቫቲካኑ ጳጳስ የነበሩት ፒዮስ 11ኛም ያሳሰባቸው የነበረው የኢትዮጵያ መወረር ሳይሆን ወረራው ባይሳካ የሚያስከትለው ውጤት ነበር። በወቅቱም የፈረንሳዩን አምባሳደር ተቀብለው ሲያነጋግሩ እንዲህ ነበር ያሉት፣

“ይህ ጠብ እጅግ እረፍት ነስቶኛል። ኢትዮጵያ እንዲያውም በጠቅላላው ጥቁር አፍሪካ ውስጥ ባሉን ካቶሊካዊ ፍላጎቶቻችን ላይ የሚያስከትለው ጉዳት ካሁኑ ታውቆኛል። ኢትዮጵያ ውስጥ ካቶሊክ ሚሲዮናዊያን ሰላይ ተብለው እየተወነጀሉ ነው። ሁኔታው ኔግሮዎችን በነጮች ላይ ለማነሳሳት ጥቁሮች እየተጠቀሙበት ነው። የጣሊያን መሸነፍ በአፍሪካ የአውሮፓ ቅኝ ግዛቶቻችንን እጣ ፈንታ የሚወስን ይሆናል።”

አሜሪካ ያራመደችው ፖሊሲም ቢሆን ጣሊያንን የሚጠቅም ቢያንስ የማይጎዱ እርምጃዎችን ያካተተ ነው። ሃምሌ ነሃሴ 1927 ላይ ብቻ ውርክቡን በተመለከተ የአሜሪካ መንግስት ሶስት እርምጃዎችን ወስዱዋል። አንደኛው የሃገሪቱ ፕሬዚዴንት ሮዝቤልት ለሞሶሎኒ የላኩት መልእክት ሲሆን፣ ሁለተኛው ነሃሴ መጀመሪያ ላይ ህግ ሆኖ የተደነገገው የመጀመሪያው የገለልተኛነት አቋም ነው። ሶስተኛው ደግሞ የአሚሪካ መንግስት “የሪኬት ውል” (ሪኬት ኮንሰሽን) የተባለው እቅድ ኢትዮጵያ ውስጥ ተግባራዊ እንዳይሆን ያደረገው ግፊት/ጫና ነበር። አውሮፓ ውስጥ አሜሪካ የወሰድችው የገለልተኛነት አቋም ጣሊያን ላይ በሚጣል ማእቀብ ለመተባበር ፈቃደኛነቱ እንደለሌላት አመላካች ተደርጎ ተወሰደ።

የኢትዮጵያ ደጋፊዎችን ስንመለከት ደግሞ፣ ቀድሞም የአድዋ ድል ለጥቁር ህዝቦች ታላቅ የምሥራች ነበር። ከበፊቱም ባርነት በህግ ሳይታገድ እንዲቆይ የሚሟገቱ ወገኖች ከጥቁር ህዝብ ጋር የተያያዘ ማንኛውንም የሰብዓዊነትና የስልጣኔ ዋቢ አሻራ ዋጋ ለማሳጣት በሚጥሩበት በዚያን ወቅት በመዳፋቸው ስር ላሉት ጥቁሮች ከኔነት መጽናኛ ምርኩዛቸው አንዱ ስለኢትዮጵያ የሚሰሙት ታላቅ አፈ ታሪክ ነበር። የምዕራቡን የባርነት ሥርዓት ለማቆየት ግብ ታሪክን የሚያጣምሙ የኃይማኖት፣ የፍልስፍናና የሳይንስ ሰባኪዎች በበዙበት በዚያ በ19ኛው ከፍለ ዘመን፣ ጥቁር ሰባኪዎች በቀላሉ በእጃቸው ሊገባ ከቻለው አስረጂ ምንጭ ከመጽሀፍ ቅዱስ ውስጥ ስለአፍሪካዊያኑ ስለኢትዮጵያ እና ግብፅ ስልጣኔና ገናና ታሪክ አነበቡ።

መዝሙረ ዳዊት 67፡31 ላይ “መኳንንት ከግብፅ ይወጣሉ፣ ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሄር ተዘረጋለች”፣ መጽሀፈ ኤርምያስ 13፡23 ላይ ደግም “በውኑ ኢትዮጵያዊ መልኩን፣ ወይስ ነብር ዥንጉርጉርነቱን ይለውጥ ዘንድ ይችላልን?” የሚሉትን መሰል አባባሎች በጥልቀት እየተረጎሙ ሰበኩ። ኢየሱስ በተሰቀለበት ዕለት መስቀል ተሸክሞ የረዳውን የሰመዖንን አፍሪካዊነት፣ በሀዋርያት ስራ ውስጥ የተገለጸው አማኝ ሞገስ ያለው ኢትዮጵያዊ ባለሥልጣን መሆኑን አስተማሩ። ጥቁር ዘርን በተመለከተ የነኝህ የነኝህ ዋቢዎች መጽሀፍ ቅዱስ ውስጥ መኖራቸው ሁዋላ ላይ በእንግሊዝኛው “ኢትዮጵያኒዝም ተብሎ ለተሰየመውና በዚያ ባርነት በተንሰራፋበት ጨለማ ወቅት ጥቁሮች በሃይማኖታቸው እንዲጸኑ፣ በሰበዓዊነታቸው እንዲያምኑ ላገዘው አፍቃሪ ኢትዮጵያ ተራማጅ እንቅስቃሴ ዋና ምንጭ ሳይሆን አልቀረም።

አፍቃሪ ኢትዮጵያዊነት ከደቡብ አፍሪካ አንስቶ እስከ ካሪቢያን፣ አልፎም እስከ ደቡብ አሜሪካ ድረስ በመዝለቅ አንዱ የጥቁሮች ኃይማኖታዊ አላባ ወይም በፈረንጅኛው ኤለመንት ሆኖ ቆይቷል። በመጽሀፍ ቅዱስ ውስጥ ያሉ ሰብዕናዎችንና ክስተቶችን በአፍሪካዊነት መነጸር የሚያይ ማህበራዊ፣ ኃይማኖታዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ነው። በወቅቱ ተንሰራፍቶ የነበረውን የክርስትና ሰበካም የጥቁሮችን የበታችነት አስፍኖ ለማቆየት ዓላማ እውነታው የተጣመመበት ትምህርት እንደሆነም አድርጎ ይቆጥረው ነበር። እንደ የልቪናግተን አባባል “ኢትዮጵያኒዝም የጥቁሮችን መገበር ተገቢነት ለማስረገጥ በአስረጂነት ከሚቀርቡት የመጽሀፍ ቅዱስ የሃም ልጆች እና የኖህ እርግማን አፈ ታሪኮች በተቃራኒ የቆመ ዕይታ ነበር ማለት ይቻላል። ባጠቃላይ ሊዮናርድ ባረት:

“ኢትዮጵያዊን የመጀመሪያዎቹ የሰው ልጆች ነን ብለው ያምናሉ። ለዚህም ማስረጃቸውን ይጠቅሳሉ። በተጨማሪም አምልኮዎችን፣ ክብረ በዓላትን፣ ቅዱስ የሰበካ ጉባኤዎችን፣ መስዋዕት ማቅረብን ባጭሩ ሰለአማልክት ክብር የሚከወኑ ሁሉንም ድርጊቶች የጀመርን ነን ይላሉ። ስለዚህ ከሰው ልጆች ሁሉ የበለጡ ሃይማኖተኞች፣ የሚያቀርቡትም መስዋዕት ከሁሉም በላይ አማልክትን የሚያስደስት ነው ብለው ያምናሉ። ከሃይማኖተኛነታቸው የተነሳም በማንም ባዕድ አገዛዝ ስር እንዳይወድቁ ማድረግን በመሳሰሉት ጸጋዎች አማልክት እንደባረኳቸው ያስረዳሉ። ምንጊዜም በመካከላቸው ላለው ህብረት ምስጋና ይግባውና ሁልጊዜም ነፃነታቸውን እንዳስከበሩ ይኖራሉ።”

በማለት የጠቀሱት፣ የሲሲሊው ጸሀፊ የዲዮደሩስ አባባል ስለ ኢትዮጵያና ህዝቧ የነበረውን ጥንታዊ ግንዛቤ ባጭሩ ሳያስቀምጠው አይቀርም።

ይህን መሰሉ ግንዛቤ የወለደው የኢትዮጵያኒዝም እሳቤም በማርቆስ ጋርቬይ ጊዜ ከርዕዮተ ዓለምነት አልፎ በተግባር የሚገለጽ እንቅስቃሴ ሆኗል። በእሳቸው እንቅስቃሴ የሚታመንበት አምላክ የኢትዮጵያ አምላክ ነው። እ: ኤ፡ አ በ1920 ኒዮርክ ውስጥ ዓለም አቀፍ የጥቁር ዘር ዕድገት ማህበር /ዘ ዩንቨርሳል ኔግሮ ኢምፕሮቭመንት አሶሲዬሽን/ ጉባኤ የዓለም ጥቁር መብቶች አዋጅን /ድክላሬሽን ኦፍ ዘ ራይትስ ኦፍ ዘ ኔግሮ ፒዩፕልስ ኦፍ ዘ ወርልድ/ ባጸደቀበት ወቅት ያወጣውና ሁሉን አቀፍ የኢትዮጵያ ህዝብ መዝሙር በማለት የሰየመው መዝሙር ስንኞች ወደ አማርኛ ሲመለሱ እንዲህ ይላሉ:

ኢትዮጵያ የአባቶቻችን ምድር፣
አማልክት ሊጎበኙሽ፣ የሚመርጡሽ በፍቅር፣
በሌሊት ድንገት ሲመጣ፣
ማዕበል የተቀላቀለበት ደመና፣
ጦራችን ገንፍሎ ወጣ፣
ድል ማድረግ አለብን በውጊያው፣
ጎራዴዎች ሲያበለጨለጩ፣
ሲመዘዙ ካፎቴያቸው፣
ድል ለኛ ሞገስ ነው፣
በቀይ፣ በጥቁርና ባረንጓዴው ለምንመራው፣

_ አዝማች _

ገስግሱ፣
ወደ ድል ገስግሱ፣
አፍሪካን ነፃነት አልብሱ፣
ጠላትን ለመግጠም ተነሱ፣
ከቀዩ፣ ከጥቁሩና ካረንጓዴው ሃይል ጋር ገስግሱ፣
ኢትዮጵያ ጠላቶችሽ ወድቀው፣
ተፍረከረኩ፣
በሃይል ተመተው፣
በጉልበታቸው ተንበረከኩ፣
ልጆችሽ በጋለ ፍቅር፣
ተናገሩ፣
ርቀት ካላቸው ባህር፣
ማዶዎች መሰከሩ፣
ዬሆ! ታላቁ እኛን ሰምቶናል፣
ለቅሶአችንን፣ እንባችንን አይቶልናል፣
በፍቅሩ መንፈስ አንቀሳቅሶናል፣
በመጭዎቹ ዓመታት፣
አንድ ላይ ያሰባስበናል።

ማርቆስ ጋርቬይም በጽሁፋቸው ውስጥ “እኛ ጥቁሮች አንድ ዓይነት አርአያ አግኝተናል። ምንም እንኳ የእኛ አምላክ ቀለም የሌለው ቢሆንም ሰው የሚያየው በራሱ መነፀር ነው። ነጮች አምላካቸውን የሚያዩት በነጭ መነፀር ነውና እኛም በኢትዮጵያ መነፀር እያየን እናመልካዋለን” ብለዋል። በአፂ ምኒልክ መሪነት የኢትዮጵያ ሃይል በጣሊያን ወራሪ ላይ በአድዋ የተቀዳጀው ድልም ድልድይ ሆኖ የጥንታዊቷን ኢትዮጵያ የታላቅነት ክብር ከዘመናዊ ዓለም ጋር አገናኘው። የዓለምንም ቀልብ ሳበ። የአውሮፓ መንግሥታት ዲፕሎማቶቻቸውን ወደ አዲስ አበባ እንዲልኩ፣ ከኢትዮጵያ ጋር 19 ድንበርን የሚመለከቱ ስምምነቶችን እንዲፈራረሙ አደረጋቸው።

ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ለነበሩት የአፍቃሪ ኢትዮጵያዊነት እንቅስቃሴ መሪዎችም የአድዋው ድል የሞራል እርሾ ሆኗቸዋል። ከእንቅስቃሴው ግንባር ቀደም መሪዎች አንዱ ጀምስ ድዋኔ ግብጽና ሱዳን ውስጥ ያሉትን ክርስቲያን አፍሪካዊያን ሁኔታ ትኩረት ሰጥተው መፍትሄ ይፈልጉለት ዘንድ ለምኒልክ ደብዳቤ የፃፉት የአድዋውን ድል ተከትሎ ነበር። ለዚህም ጉዳይ የሚውል ገንዘብ ለማሰባሰብ ሞክረዋል። የነፃዋ ኢትዮጵያ ተምሳሌትነት በዙሉ እና በሌሎቹ የደቡብ አፍሪካ ክፍሎች ውስጥ ጠንክሮ ሠርጾ ነበር።

እ፡ኤ፡አ፡ በ1930ዎቹ ከጀማይካ፣ ምዕራብ ኪንግስተን ደሳሳ ጎጆዎች ሲፈልቅ የአልባሌ ሰዎች ስብስብ ከመባል አልፎ፣ በተጀመረበት ሀገር ህዝብ ውስጥ የማይነቃነቅ መሰረት የጣለ ብቻ ሳይሆን ከካሪቢያን ወጥቶ በሰሜን አሜሪካ፣ በብሪትሽ አይልስ፣ በአፍሪካ ውስጥ መስፋፋት የቻለው የራስ ተፈሪያዊያን እንቅስቃሴ አመጣጥም ውልዴቱ ከዚህ የኢትዮጵያና የጥቁሮች ህዝባዊ እንቅስቃሴ ትስስር ጋር የተያያዘ ነው። በሌላ አባባል የአፄ ኃይለሥላሴ መንገስ ወይም የእሳቸው የጀማይካ ጉዞና የዝናብ መዝነብ ያመጣው ድንገቴ ክስተት አይደለም ለማለት ነው።

ከሃይማኖቱ ውጭም በአርነት ትግሉ መስክ በቅኝ ግዛት ሥር ለነበሩት እህት የአፍሪካ ሀገሮች ታጋዮችም ኢትዮጵያ ፋና ወጊ መብራታቸውና የራዕይ ምንጫቸው ነበረች። ለዚህም ነው የናይጀሪያ ድኀረ ነፃነት የመጀመሪታ ፕሬዚዴንት የነበሩት ዶክተር አዚኪዊ:

“ኢትዮጵያ ጥቁር ራሱን በራሱ የሚያስተዳድርባት የመጨረሻው ሀገር ነች። በዚህ ክፍለ አህጉር ላይ የአፍሪካ ቀደም አባቶች የመሰረቱት መንግሥት የታሪክ ዋቢ ነች። ኢትዮጵያ ከዘመን ወደ ዘመን እየተሸጋገረች ህልውናዋን ጠብቃ መኖሯ የሚደነቅና መደነቅም ያለበት ነው።”

በማለት ተናግረው የነበረው። ከአድዋው ድል አርባ ዓመት በሁዋላ ጣሊያን ቂሟን ልትወጣ የመላው ጥቁር ህዝብ ዕንቁ በሆነችው ኢትዮጵያ ላይ ወረራ ስታካሂድ በግልጽም ይሁን በተዘዋዋሪ የአውሮፓና የአሜሪካ መንግሥታት ከእሷ ጎን ቆመዋል። በተቃራኒው ግን በአፍሪካም ይሁን በተቀረው ዓለም የተቀጣጠለውን አፍቃሪ አፍሪካዊነት የትግል ስሜት አነስቷል። እልህ አጭሯል። በአጠቃላይ መላው ጥቁር ህዝብ፣ በቁጥር አነስተኛ ቢሆኑም ለፍትህ የታመኑ አውሮፓዊያን ነጮችም ለኢትዮጵያ ያላቸውን ወገናዊነት አጠናክሯል። የነኝህም ጥረት በውጭ የነበረውን ህዝባዊ ድጋፍ ወደ ኢትዮጵያ ያደላ እንዲሆን አድርጎታል።

ባህላዊ እሴቶቻቸውን ያልጣሉ የአፍሪካ ምሁራን ተሰባስበው ከነበሩባቸው የአህጉሩ ከተሞች፣ ከካርቢያን ደሴቶች፣ ከጥቁር አሜሪካዊያን በኩል ወረራው ያጫረው የመጠቃት ስሜት ተስተውሏል። የዚህች ብቸኛ ነፃ ጥቁር ሃገር በድጋሚ በጣሊያን መወረር፣ በጥቁር ምሁራን ዘንድ እልህ አጫረ፣ ድጋፍም ለኢትዮጵያ አስገኘ። አፍቃሪ ኢትዮጵያ ጸሀፊዎችም ብዕራቸውን አነሱ። ኩባዊ ገጣሚ ኒኮላስ ጉዮሊን በሞሶሎኒ ላይ:

ምኑ የባህር ወንበደ ሰይጣን ነው!
ይህ ሞሶሎኒ!
ከዚያ ባልጩት መሳይ የፊት ትይታው!
እና ከነኛ ስግብግብ ጥፍሮቹ ጋር!

በማለት የገለጹት የእልህ ስሜት በብዙ የሀገራቸው ዜጎች ልቦና ውስጥ ይንበለበል ነበር።

ከአድዋ ድል 40 ዓመት በሁዋላ፣ ጠላት የብቀላ ወረራ ሲያካሂድ፣ የኢትዮጵያ ወዳጆች እና ኢትዮጵያዊያን የጥበብ አርበኞች ለምሳሌ ዮፍታሄ ንጉሴ “አጥንቱን ልልቀመው” እያሉ በብዕራቸው ጥላትን ሲዋጉ፣ ወራሪው ደግሞ ከአድዋ ሽንፈቱ አርባ ዓመት በሁዋላ ቂሙን ለመወጣት በአደረገው ጦርነት ያገኘውን ድል እንዲህ እያለ አሞግሶ ነበር – አድዋ በሚል ርዕስ በኒኖ ራስተሊ ተጽፈው፣ ዲኖ ኦሊቪሪ በሙዚቃ በተቀናበሩት ስንኞች፡

አሸነፈ ተመመ፣ ሄደ በርምጃ ጦሩ፣
ድልን ካድማስ አድማስ፣ እያስተጋባ አየሩ፣
በሚሊዮን የሚቆጠሩ፣
ጥፍሮች በምርኮ ተንጰረጰሩ፣
ባደባባይ በአካል ታዩ፣ መሠከሩ፣
አልቻሉም ሊያመልጡ፣ ሊሰወሩ፣
ቦታውን ጣሊያኖቹ፣
በ እጃቸው አስገቡ፣ ተቆጣጣሩ፣ ወንዶቹ፣
በፊታቸው ፈገግታ እያስነበቡ፣
በስሜት እየዘመሩ!
አድዋ ነፃ ወጣች፣
በ እጃችን ተመልሳ ገባች፣
በአድዋ ድል ተመዘገበች፣
ተወለዱ ዳግም ጀግኖች፣
ለድል ገሥግሱ፣ ገሥግሱ …
መላው ዓለም አወቀ፣
የአድዋ የበቀል ፍሬያችንን አደነቀ፣
የ እኛም ነፍስ በደስታ ጩኸት ፈነደቀ፣
አታሞው ተሰማ አስተጋብቶ፣
የምድሩን ጩኸት ተክቶ፣
የደስታ እምባና ልባዊ ምኞት ፈንቅሎ።
ይህ መሬት፣
አንድ ዕለት፣
አፈረ የሆኑበት፣
ሠማዕታት ከሥሩ አሉበት፣
ጥላዎች
የደም ቀለም አሻራዎች፣
በልህ ይቃጠሉ የነበሩ፣
በደስታ እየዘመሩ።

አድዋ ነፃ ወጣች፣
በ እጃችን ተመልሳ ገባች፣
በ አድዋ ድል ተመዘገበች፣
ተወለዱ ዳግም ጀግኖች፣
ለድል ገሥግሱ፣ ገሥግሱ …
መላው ዓለም አወቀ፣
የ አድዋ የበቀል ፍሬያችንን አደነቀ፣
የ እኛም ነፍስ፣ በደስታ ጩኸት ፈነደቀ።

ያን ጊዜስ እንደዚህ ቢሉም በአባት እናቶቻችን ተጋድሎ አድዋ ተመልሳ ከሕጋዊው ባለቤቷ ከኢትዮጵያ ሕዝብ እጅ ካምስት ዓመት በሁዋላ ገብታለች። ዛሬስ? የታሪክ ምፀቱ፣ ከአድዋ በበቀሉ፣ ካርባ ዓመት በሁዋላ ጣሊያን ቂሟን ለመወጣት ስትመጣ ባንዳ ሆነው ባገለገሉ ሰዎች ልጆች እና የልጅ ልጆች በሆኑ የራሳችን ሰዎች የአድዋ ድል ሲንኳሰስ፣ ሲያሻቸውም በደም የተገነባው የጋራ ታሪክነቱ ሲካድ፣ በዚያ ከአራቱም ማዕዘናት የሀገራችን ክፍሎች የተሰባሰቡ ኢትዮጵያዊያን በአንድነትና በወኔ ቆመው ጠላትን እየተፋለሙ በወደቁበት የአድዋ አፈር ላይ የቋንቋ መስመር ዘርግተው እየመተሩ ብሄር ብሄረሰቦች ወካይ የሚሏቸውን ቤቶች ሲሰሩ ምን ይሰማን ይሆን? ደም የተቃቡን ባዕዳንስ ምን ይሰማቸው ይሆን? ኢትዮጵያ እስካለች ነው ኢትዮጵያዊያን በጋራ ተሰባስበን አድዋን በጋራነቱ ልናከብረው የምንችለው። ታሪክ ላንድ ማህበረሰብ ምርኩዙ ነው። ምርኩዛችንን በዝምታ አሳልፎ መስጠቱ ያለውን አደጋ ተገንዝበን የአድዋ ድልን ማሰብ ብቻ ሳይሆን፣ ክብሩን ማስከበርም ግዴታችን ይመስለኛል። ዝነኛው ገጣሚና ጠሀፊ ተውኔት ዮፍታሄ ንጉሴ በሁለተኛው የጣሊያን ወረራ ወቅት በፃፉት “አጥንቱን ልልቀመው” ግጥማቸው ውስጥ:

አጥንቱን ልልቀመው _ መቃብር ቆፍሬ፣
ጎበናን ከሸዋ _ አሉላን ከትግሬ፣
ስመኝ አድሪያለሁ _ ትላንትና ዛሬ፣
አሉላን ለጥይት _ ጎበናን ለጭሬ::
ተሰበሰቡና _ ተማማሉ ማላ፣
አሉላ ተትግሬ _ ጎበና ተጋላ::
ጎበና ሴት ልጁን _ ሊያስተምር ፈረስ፣
አሉላ ሴት ልጁን _ ጥይት ሊያስተኩስ::
አገሬ ተባብራ _ ካልፈጠረች እርካብ፣
ነገራችን ሁሉ _ የእንቧይ ካብ የእንቧይ ካብ::
ትምህርት እንዲስፋፋ _ ጉልበት እንዲጠና፣
አራቱ ጉባዔ _ ይነሱልንና፣
መኮንን ደረሶ _ አሉላ ጎበና፣
አገራችን ትማር _ አሁን እንደገና፣
ጎበና ተፈረስህ _ ጋር ተነሳ እንደገና::

እንዳሉት አሁንም የሀገራችን ህልውና አደጋ ላይ ወድቆ ጥሪውን እያስተላለፈልን ነው። የክተት ጥሪውን።