ከ13 በላይ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላኖች ከአዲስ አበባ ወደ መቀሌ እንዲበሩ ታዘዘ

በመላው ኢትዮጵያ  በተለይም ጎንደር/ባህርዳር እና ወሎ  ውስጥ  የሚካሄደው ህዝባዊ የተቃውሞ እንቅስቃሴ እየተጠናከረ ከመጣ ወዲህ፣ በንግድም ይሁን በግል የየብስ ማጓጓዣ ወደ ትግራይ መጓጓዝ አስቸጋሪ እየሆነ መጥቷል።  በዚህ እና  በተከተለው ፍርሃት ሰበብ ከአዲስ አበባና ከመሃል  ሀገር ወደ መቀሌ በአየር የሚጓዘው  ተጓዥ  ቁጥር ከፍ ብሏል።  ስለሆነም የወያኔ  አባል ለሆነውና የአየር መንገዱ ስራ አስኪያጅ  ለሆነው ለተወልደ  በተሰጠው መመሪያ መሠረት በአሁኑ ጊዜ ከአዲስ አበባ ወደ መቀሌ በቀን ከ13 በላይ በረራ እየተደረገ ነው።

ከዚህ በፊት የመቀሌ አውሮፕላን ማረፊያን በዓለማአቀፍ ደረጃ  ለማሳደግ ተይዞ  የነበረው እቅድ በአስቸኳይ ተግባራዊ እንዲሆን ወያኔ  በወሰነው መሠረት፣  ይህንኑ እውን ለማድረግ ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን  የመቀሌ  ምንጫችን እማኝነቱን ሰጥቶናል።   ከሌሎቹ መሠረተ ልማቶቹ በተጨማሪ፣  የኢትዮጵያ  አየር ኃይል በድሬደዋ  ያደርግ የነበረው  የበረራ  ልምምድ  ወደ መቀሌ እንዲዛወር መደረጉንም እናስታውሳለን።

ከወያኔ ጋር ባላቸው ንክኪ እና  ላለፉት  ሃያ  ሰባት ዓመታት አገዛዙ  በዘራው የማቃቃር ፖሊሲ ምክንያት በተከሰተ  ፈርሃት ሰበብ  ከአዲስ አበባም ሆነ  ከመሃል  ሃገር ወደከተማው ብዙ ሰው እየመጣ ስለሆነ፣   በመቀሌ የቤት እና የቦታ  ዋጋ  ከፍ እያለ መሆኑን  ምንጫችን  ጨምሮ  ገልፆልናል።  ከዚህም ሌላ፣  በአጠቃላይ በሀገሪቱ እየተካሄደ  ያለው የመጓጓዣ፣  የግብይይት እና  የስራ ማቆም  ህዝባዊ እንቅስቃሴ፣  በተለይም የወሎዎቹ ወልዲያ፣ መርሳ፣ ቆብ ሌሎችም ቦታዎች እምቢታ ወደ ትግራይ  ይገባ የነበረውን የሸቀጣ ሸቀጦች እና ሌሎችም  ምርቶች  ፍሰት  ስላስተጓጎለው በትግራይ  የገበያ  ዋጋ  እየናረ  ነው።  የወሎው እንቅስቃሴ  ተጠናክሮ  ከቀጠለ፣ አፋርም ወሎን ተከትሎ ህዝባዊ ትግሉን ካፋፋመ፣ በተለይ  አትክልትና  ፍራፍሬ፣ ቡና፣ በርበሬና የመሳሰሉት  ምርቶች  ከገበያ ላይ ሊጠፉ ይችላሉ የሚል ስጋት መኖሩም  ታውቋል።