ወቅታዊ ዜና ከፍኖተ ዴሞክራሲ ሬዲዮ

ነሐሴ 28 ቀን 2008 ዓም. ዜና (September 03, 2016 News):

በቅሊንጦ የሚገኘው እስር ቤት ዛሬ ጠዋት የተቃጠለ መሆኑ ታውቋል። ከእሳቱ በፊት የተኩስ ድምጽ ይሰማ እንደነበር የዓይን እማኞች ሲናገሩ የእሳቱ መነሻ ምን እንደሆነና የደረሰው ጉዳት እስካሁን ድረስ በትክክል አለመታወቁም ተነግሯል። በርከት ያሉ እስረኞች የተገደሉ መሆናቸው በአካባቢው የነበሩ ዜጎች ገልጸዋል። የቅሊንጦ እስር ቤት እነ አቶ በቀለ ገርባ ዮናታን ተስፋይን ጨምሮ በርካታ የፖሊቲካ ድርጅቶች መሪዎች እንዲሁም የሙስሊም መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላትንና ሌሎችም ታዋቂ ሰዎች የታሰሩበት መሆኑም ይታወቃል። ቀደም ብሎ በጎንደር በደብረታቦርና በአምቦ በተመሳሳይ ደረጃ እስርቤቶች የታቃጠሉ መሆናቸው እንዲሁም በእሳቱ ሰበብ የወያኔ ወታደሮች የሚፈልጋቸውን እስረኞ መግደላቸው የሚታወቅ ሲሆን በተመሳሳይ በዚህም እስር ቤት በርካታ እስረኞች በወያኔ የጸጥታ ኃይሎች ሳይገደሉ አይቀሩም የሚል ስጋት አለ።
ትናንት አርብ ነሐሴ 27 ቀን 2008 በጎንደር የወያኔ ባለስልጣኖች በተለያዩ ቦታዎች ስብሰባ ያካሄዱ ሲሆን በውይይቱ ወቅት ሕዝቡ ያለበትን ብሶት በመግለጽ አገዛዙን ሲያወግዝ መዋሉ ታውቋል። በርካታ ዜጎች የሃይማኖት አባቶችን ጨምሮች ባለፉት 25 ዓመታት ሕዝቡ በአገዛዙ የደረሰበትን ግፍ በዝርዝር የተናገሩ ሲሆን ለማነጋገር የመጡትን የወያኔ አለቅላቂ ሹሞች ከሕዝብ ጋር እንዲቆሙ መክረዋል። በመጨረሻም የወያኔ አግአዚ ጦር ከጎንደር ክፍለሀገር ለቅቆ እንዲወጣ፤ የታሰሩት እስረኞች እንዲፈቱና የወልቃይት ህዝብ የማንነት ጥያቄ እንዲረጋገጥ የሚሉና ሌሎችም ጥያቄዎች ጠይቀው ጥያቄዎቹ ሰሚ ካላገኙ ሕዝባዊ ትግሉ እንደሚቀጥል አስገንዝበው ሸኝተዋችዋል።

#የወያኔ አገዛዝ ታማኝ የሆነውን የአግአዚ ጦርና እንዲሁም የፌዴራል አና የአካባቢ ፖሊሶችን በማሰማራት በየቦታው ወጣቶችን ከየቤታቸው እያፈነ በመያዝ ላይ መሆኑን ከየአቅጣጫው የሚደርሱ ዜናዎች ይጠቁማሉ። በደሴ ከተማ በርካታ ወጣቶች መያዛቸው የአካባቢዎች ከሰጡት ዘገባ ለማወቅ ሲቻል በቻግኔም እንዲሁም በጎጃም በተላያዩ ከተሞች ባለፉት ቀናት ሰላማዊ ስልፍ ወጥታችኋል በሚል ምክንያት ዜጎች እየታየዙ መታሰራቸው ተነግሯል።

የወያኔ አረመኔያዊ አገዛዝ በሕዝቡ ላይ እያካሄደ ያለውን ጭፍጨፋ የተወሰኑ የምዕራብ ብዙሃን መገናኚዎች እና የሰብአዊ መብት ድርጅቶች በተወሰነ ደረጃ ቢያጋልጡትም አብዛኞቹ መንግስታት አይኔን ግምባር ያድርገው በማለት ዝምታን መርጠው እንደነብር ተስተውሏል። የአሜሪካው ምክር ቤት ንኡስ ኮሚቴዎች በጉዳዩ መግለጫዎችን ሰምተው ለመወሰን ያቀዱ ሲሆን የካናዳ የመንግስት አስተዳድርና ምክር ቤትም ለወያኔ የሚሰጠውን እርዳታ እንዲያቆምና ሌሎች እርምጃዎችን እንዲወስድ ተጽእኖ እየተደረገበት ነው። ለዜጎች ሰብአዊ መብት በመቆም ደረጃ ብዙም የማይታማው የአፍሪካ ህብረትም ሁሉም ወገን ትእግስት ያድርግ የሚል ለስላሳ መግለጫ ፈራ ተባ እያለ ለይስሙላ መግለጫ ማውጣቱ ታውቋል።

ዝርዝር ዜና ለማንበብ ይህን ይጫኑ፣

ወይም ቀጥሎ  ያለውን በመጫን ያዳምጡ:

 

ክፍል 1:http://www.finote.org/TodayPart1.mp3

ክፍል 2: http://www.finote.org/TodayPart1.mp3