ወያኔ እስረኞች እለቃለሁ ቢልም ብዛት ያላቸውን ዜጎች እያሰረ ነው፣ የአሜሪካው ባለሥልጣን ረብ የለሽ ጉብኝት፣ ዳግም ድርቅና የምግብ እጥረት፣ ኬንያዊው በወያኔ እስር ቤት ሞተ

ፍኖተ ዴሞክራሲ የኢትዮጵያ አንድነት ድምጽ ሬዲዮ (ታኅሣሥ 08 ቀን 2009 ዓ.ም.) – የወያኔ ኮማንድ ፖስት የተወሰኑ እስረኞችን እንደሚለቅ ተናገረ በሁለተኛ ዙር ተጨማሪ ዜጎች ማሰሩን ገለጸ የአሜሪካው ረዳት ሰክሬተሪ የረባ ስራ አላደረጉም ተባለ – የተመድ የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ በደቡብና ደቡብ ምስራቅ በድርቅ ምክንያት የምግብ እጥረት ይኖራል በማለት ገለጸ – በቅሊንጦ እስር ቤት የነበረው ኬኒያዊ በሜኔንጃይትስ በሽታ ሞተ።

የወያኔ ኮማንድ ፖስት በመጀመሪያው ዙር በቁጥጥር ስር ውለው ትምህርት ተሰጥቷቸዋል ካላቸው ውስጥ 9800 የሚሆኑትን በሚቀጥለው ዕሮብ እንደሚለቅ እንዲሁም 2500 የሚሆኑ ዜጎችን ደግሞ ፍርድ ቤት እንደሚያቀርብ ገልጿል። በሁለተኛ ዙር 12500 ሰዎች መያዛቸው ገልጾ ስንቀሌ አዲስ ባሰራው አዲስ ጣቢያ እንደሚታጎሩም ተናግሯል ። የወያኔ ባለስልጣኖች እስካሁን በተደጋጋሚ ከዚህ በፊት 11 600 ሰዎች ብቻ መታሰራቸው መግለጹና ይህንንም የውጭ መገናኚያ ብዙሃን ተቋሞች ሲያስተጋቡ መቆየታቸው የሚታወቅ ሲሆን አሁን በሌላ መግለጫ በሁለተኛ ዙር ተይዘዋል ያለው ቁጥር ከቀደሞው ጋር ሲደመር ከ24 ሺ በላይ መሆኑ ተጋልጧል። እስካሁን የተያዙት ሰዎች ትክክለኛ ቁጥር ከ40 ሺ እስከ ስድሳ ሺ መሆኑን በርካታ ዜጎች የሚገምቱ ሲሆን የወያኔ አገዛዝ ይፋ ማድረገና አለማድረጉ ወደፊት ይታያልም ይላሉ።

ባለፈው ታኅሣሥ 6 የአሜሪካው ረዳት ስክሬተሪ ወደ አዲስ አበባ ሄደው ስለ ሰብአዊ መብት ጉዳይ ከወያኔ አገዛዝ ባለስልጣኖች ጋር ይነጋገራሉ ቢባልም ከሰባት ዓመት በፊት በተቋቋመው የሁለቱ አገሮች የጋራ ጉዳይ ኮሚቴ ስብሰባ ላይ መገኘታቸው ከመገለጹ በስተቀር ፋይዳ ያለው ስራ አለመሰራቱ እየተነገረ ነው። የወያኔ አገዛዝ እና የአሜሪካ ኤምባሲ ሰራተኞች የሚገኙበት ኮሚቴ ስለ ምርጫ መሻሻል፤ ስለ ህገ መንግስት መብቶች ውይይትና ድርድር ስለማድረግ ወዘተ…. መወያየቱ የተነገረ ሲሆን ረዳት ሰክረተሪው በዚህ ስበስባ ላይ ተገኙ ከመባሉ በስተቀር ከወትሮው የተለየ ክንውን አለመደረጉን ብዙዎች ይናገራሉ።

ሪሊፍ ዌብ (Relief Web) የተባለው የተመድ የሰብአዊ ጉዳዮች አስተባባሪ ቢሮ ድረ ገጽ ሐሙስ ታኅሣሥ 7 ቀን ይፋ ባደረገው ዘገባ ካለፈው ዓመት ጥር ወር እስከ መስከረም ወር ድረስ በከፍተኛ የምግብ እጥረት የተጠቁ 24480 የሚሆኑ ህጻናት አስፈላጊው እንክብካቤ የተደረገላቸው መሆኑን ገልጿል። በተያዘው ዓመት 9.7 ሚሊዮን የድርቅ ተጠቂዎች ሲረዱ መቆየታቸውንና 3.95 ሚሊዮን የሚሆኑ ዜጎች ደግሞ ንጹህ የመጠጥ ውሃ ያልነበራቸው መሆኑን ዘግቧል። በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ ውስጥ 783 340 ስደተኞች መኖራቸውንም ተገልጿል። በተመድ ውስጥ ዪኒሲኤፍ የተባለው ተቋም 124 ሚሊዮን ዶላር ለሰብአዊ ርዳታ 115 ሚሊዮን ዶላር ለድርቅ እንዲሆም 8፣5 ሚሊዮን ለስደተኞች ጉዳይ እንደሚያስፈልገው ገልጿል። ከመጭው ታኅሳስ ወር በኋላ ያለውን ሁኔታ አስመልክቶ የወያኔ አገዛዝ የመኸሩ ምርት አጥጋቢ ሊሆን ይችላል የሚል መግለጫ መስጠቱን ጠቅሶ በደቡብ እና በደቡብ ምስራቅ አካባቢዎች እስካሁን ያለው አነስተኛ የዝናም ሁኔታ ከፍተኛ ድርቅ ሊያስከትል እንደሚችል ጠቋሚ ነው ብሏል። በሶማሊያ ክልል ከዘጠኙ ወረዳዎች ውስጥ ሰባቱ እንዲሁም በቦረናና በጉጂ የዝናሙ ሁኔታ አነስተኛ በመሆኑ የውሃ እጥረትን ሊያስከትል እና በሰውና በእንስሳት ላይ ጉዳት ሊያመጣ ይችላል ብሏል።

በጥር 2007 ዓ.ም. በጅጅጋ ከተማ የሳተላይት አገልግሎት አለፈቃድ ሲያስገቡ ነበር ተብለው ከተወነጀሉትና በቅሊንጦ እስር ቤት ከነበሩት ሁለት የኬኒያ ተወላጆች መካከል አንደኛ በቅርቡ በሜኔጃይትስ በሽታ ሞቶ አስከሬኑ ወደኬኒያ የተላከ መሆኑ ተነግሯል። በስራው መሀንዲስ የሆነው ሟቹ የኬኒያ ተወላጅ ዛጋዮ ሙሪይኪ ቢ ዔስ ዔስ ሊትድ (BSS Ltd) ለሚባለው ኩባንያ ተቀጥሮ የሳተላይት አገልግልት ሲተከል እንደነበር ይታወቃል። የወያኔ አገዛዝ ግለሰቡን ሌላ የስራ ባልደረባውን ፈቃድ የላቸውም በማለት በቁጥጥር ስር ማዋሉ ይታወቃል። ማቹ በእስር ቤት ባልታወቀ ሁኔታ መሞቱ በኬኒያ ውስጥ ከፍተኛ ውዝግብ ማስከተሉ እየተነገረ ነው።

ከፍኖተ ዴሞክራሲ የኢትዮጵያ አንድነት ድምጽ ሬዲዮ ዝርዝር ዜና