ወያኔ የርሃብተኛውን ቁጥር ደብቋል፣ የባህርዳሩን የቦንብ ፍንዳታም ጭምር

ፍኖተ ሬዲዮ  (ሚያዚያ 24 ቀን 2009 ዓ.ም.) – የወያኔ አገዛዝ የረሃብተኛውንና የተረጅውን ቁጥር ደብቆ ቆይቷል በሚል ተወነጀለ – ባለፈው ቅዳሜ በባህር ዳር ከተማ የፈነዳው ቦምብ የሰው ህይወት ማጥፋቱ የዜና ምንጮች ሲዘግቡ የአገዛዙ ሚዲያዎች በዝምታ አልፈውታል – በወያኔ ምርመራ ጣቢያ እየተሰቃየ የሚገኘው የታወቀው የህክምና ባለሙያ ዶ/ጋሹ ክንዱ ባስቸኳይ እንዲፈታ የአማራ ሃኪሞች ማኅበር ጠየቀ።

የወያኔ አገዛዝ በቅርቡ የረሃብተኛውና የተረጅው ቁጥር ከ5.6. ወደ 7.7 ሚሊዮን ማደጉን በመግለጽ የሰጠው መረጃ ቀደም ብሎ ይፋ ማድረግ ነበረበት በማለት የዋሽንግተን ፖስት ጋዜጣ ሰኞ ሚያዚያ 23 ቀን ባወጣው ዕትሙ ገልጿል። አገዛዙ እውነቱን በወቅቱ ሊገልጽ ያልፈለገው ባስቸኳይ ኢኮኖሚውን እያሳደጉ ነው የሚባለውን ቅዠት ጥላሸት ይቀባል ከሚልማ እንዲሁም ያለበትን የፖለቲካ ውጥረቱን ያባብሰዋል ከሚል ስጋት መሆኑን የሚገልጹ ወገኖች አሉ። በየቦታው ሕዝብ በረሃብና በአልሚ ምግብ እጥረት በሚሰቃይበት ሁኔታ በአዲስ አበባ ሰማይ ጠቀስ ፎቅ መገንባት ወይም እንደ ፒዛ ሃት የሚባሉት የምግብ መሸጫ ቤቶች ስራ ይጀምራሉ ብሎ ማወጅ ትርጉም የለውም የሚሉ ክፍሎች ረሃቡ እየተስፋፋ መሄዱን ገልጸው እርዳታ ሰጭዎችም የረሃብና የድርቅ አካባቢዎች በመስፋፋታቸው ምክንያት የሚሰጡት የእርዳታ መጠን እየቀነሰ መምጣቱን ገልጸዋል። ባለፈው ጥር ወር በኢትዮጵያ ለገባው ድርቅ አንድ ቢሊዮን ዶላር ያስፈልጋል ተብሎ የነበረ ቢሆንም እስካሁን ድረስ የተሰበሰበው የዚህን ግማሽ ብቻ ነው ተብሏል። በአሜሪካው የትራምፕ አስተዳደር ይደርጋል በተባለው የበጀት ቅነሳ ምክንያት በተመድ ስር ያለው የአለም የምግብ ድርጅትም ሆነ የሌሎች የተራድኦ ድርጅቶች በጀት በከፍተኛ ደረጃ ሊቀንስ ስለሚችል ችግሩ እየተባባሰ ይሄዳል የሚል ስጋት አለ። ከዚህ በተጨማሪ በ2008 በድርቅ ተመተው የነበሩ ደጋማ ቦታዎች ሌላ ድርቅ ሊጋረጥባቸው ይችላል የሚል ግምትም እየተሰጠ ነው። በተባበሩት መንግስታት ስር የዓለም የሚትሮሎጂ ድርጅት ባለፈው ሳምንት አርብ ዕለት በባወጣው መግለጫ በዓለም ላይ የደረሰው የአየር ለውጥ ምክንያት በፓሲፊክ ውቅያኖስ ላይ የሚፈጠረው ከፍተኛ ሙቀት ሳቢያ በኢትዮጵያ የሚገኙ የደጋ አካባቢዎች በድርቅ ሊመቱ የሚችሉበት እድል ከ50 እስከ 60 በመቶ ነው ብሏል። ይህም ከፍተኛ ችግር ሊፈጥር ይችላል ተብሏል።

ባለፈው ቅዳሜ በባህር ዳር በፈነዳው ቦምብ ሁለት ሰዎችን ህይወታቸውን ማጣታቸውንና ሌሎች አምስት ሰዎች በአካላቸው ላይ ጉዳት መድረሱን የዜና ምንጮች ገልጸዋል። ቦምቡ የፈነዳው የወያኔ ንብረት የሆነው የዳሽን ቢራ ፋብሪካ ባላገር በሚል ስም አዲስ ያወጣውን የቢራ ለማስመረቅ ባዘጋጀው ኮንሰርት ላይ ሲሆን ቀደም ብሎ የወያኔ አስከፊ አገዛዝ ያስመረራቸው ወገኖች የኮንሰርቱን መደረግ የተቃወሙ መሆኑ ግልጽ ነው። የወያኔው የዜና ማዕከሎች ቢራውን ለማስመረቅ ስለተደረገው ኮንሰርት ብቻ ሲያወሩ ስለፈነዳው ቦምብ እና ስለደረሰው ጉዳት ምንም ሳይተነፍሱ አልፈዋል።

የአማራ ሀኪሞች ማህበር የተባለው ድርጅት በቅርቡ ባወጣው መግለጫ የታወቀው የህክምና ባለሙያ ዶ/ጋሹ ክንዱ ማዕካላዊ ተብሎ በሚጠራው የማሰቃያና የመመርመሪያ ተቋም ውስጥ በከፍተኛ ደረጃና ኢሰብአዊነት በጎደለበት ሁኔታ አካላዊና ስነልቦናዊ ጉዳት እየደረሰበት መሆኑን ገልጿል። ከወራት በፊት ከባህር ከተማ ታፍኖ ወደ ማዕከላዊ የተወሰደው ዶ/ጋሹ ክንዱ ምንም ዓይነት የወንጀል ማስረጃ ያልተገኘበት ከመሆኑ ሌላ ያለምንም ፍርድ ለሶስት ጊዜ ያህል የተቀጠረ መሆኑ ተነግሯል። የሀኪሞቹ ማህበር መግለጫ ዶ/ ጋሹ የህሊና እስረኛ ነው ካለ በኋላ ሁሉም ሀኪሞችና ማህበራት ዶ/ጋሹ ከእስር እንዲፈታና ከስቃዩ እንዲላቀቅ በመታገል ግዴታቸውን መወጣት አለባቸው በማለት ጥሪ አቅርቧል።

ዝርዝር ዜና ከፍኖተ ዴሞክራሲ የኢትዮጵያ አንድነት ድምጽ ሬዲዮ ያዳምጡ