ዋናው ትኩረት በወያኔ ላይ ቢሆን ይመረጣል

የፍኖተ  ዴሞክራሲ  የኢትዮጵያ አንድነት ድምፅ ሬዲዮ  ሀተታ:

በአሁኑ ወቅት በፖለቲካው መድረክ ግርግር መፈጠሩ ለሁሉም ገሃድ ነው። የሚያሳዝነው ግን ያለው ሁኔታ የማይፈለገውን ንትርክ በተቃዋሚው ጎራ መፍጠሩ ነው። በወያኔ ላይ በቀጣይነት መያዝ ያለበት ትኩረት ተረስቶ ትኩረት ወደ ሌላ ሆኗልና ወገን ትኩረት ወያኔ ላይ ይሁን ማለቱ ወቅታዊ ሆኖ ይገኛል።

ትኩረት በወያኔ ላይ ስንል ሌሎች ጠላቶችን እንርሳ ማለት አይደለም። በሀገር ውስጥም ሆነ በአካባቢው፤በዓለም አቀፍ ደረጃም የኢትዮጵያ ጠላቶች ብዙ ናቸው። ማን አደጋ ሆኖ ህልውናዋን እያሰጋ ነው ለሚለው መልስ መስጠት ያስፈልጋል። ሳውዲ አትወደንም፤ ግብጽም አትተኛንልም፤ አሜሪካም ደግ አታስብንልም ወዘተ — ሁሉም ትክክለኛ ስጋቶች ናቸው። በጠላት መሀል የከፋውን ነጥሎ ትኩረት መስጠቱ ግን ከመባከንና ጠላት ከማብዛትም ያድናል። ትኩረታችን በወያኔ ላይ ለሆነ ግን ለመለስተኛ ክስተቶችና አከራካሪ ሁኔታዎች አላስፈላጊ ክብደትና ቦታ አንሰጣቸውም። በተለይም በተቃዋሚው ጎራ፤ የሕዝብ ወገን በሚባለው ሰፈር ልዩነትን ፈጣሪና አስፋፊ ከሆኑ ሊያሳስቡን ይገባል። ትኩረታችን በወያኔ ላይ ከሆነ ዕይታችን ከዚህ የሚነሳ ይሆናል። በመሆኑም በቀላሉ ለወያኔ ከፋፋይ ድርጊት ሰለባ አንሆንም። ወያኔ ተመሳሳይ ቀዳዳ ሲያገኝ ዋሻ ይቆፍራል፤ ሰርጎ ገቦቹን በየአቅጣጫው አሰማርቶና ተቃራኒ አቅዋሞችን ደግፎ በመጮህ በማስጮህ ልዩነትን ያሰፋል፤ ያካርራል። ወያኔነታቸውን ደብቀው ህዝብን የሚያፋጁትን መሰሪዎች ማየቱ በቂ ነው።

የትኩረታችን ዋናው ኢላማ ወያኔ ከሆነ በዚህ በዚያ ሊፈጠሩ የሚችሉ መለስተኛ ቅራኔዎች አቅጣጫና ትኩረት አያስቀይሩንም። ሊያስቀይሩን አይገባም ማለት ነው። የሕዝብን ቁጣና ክንድ አስተባብሮ ዋናውን ጠላት መደቆስ ማጥቃት ይገባልና ማን ዋና ጠላት የሚለውን ጠንቅቆ ማወቅ የግድ ይሆናል። ለምሳሌ አንዳንዶች–በተለይም ትላንት የሕዝብ ደም አፍሳሾችና ቅጥረኛ ምሁሮች– ጥቃታቸው በኢሕአፓ ላይ ያተኮረ ነው። ወያኔን በተመለከተ የሚያደርጉት ጎጂ ቅስቀሳም ሆነ ተግባራዊ ስምሪት የለም:: ድርጅቱን ለማጥቃት ግን የገለሙና ሃሰት የሆኑ ክሶችን እየጎለጎሉ ትውልድን ሊያደናግሩ–በዚህም አወቁትም አላወቁትም ወያኔን ሊጠቅሙ–ይራወጣሉ። ድርጅቱ በዕይታው ያስገባቸውና ለትግሉም ለህልውናውም ጠንቅ የሆኑ ቢኖሩም ዋናው ትኩረት አሁንም በወያኔ ላይ በመሆኑ አላስፈላጊ ንትርኮችንና እርምጃዎችን ሊያስተናግድ ፍቃደኛ ሆኖ አልተገኘም። ሀላፊነትን ማጉደል ወይም ግዳጅን መሸሽ ሳይሆን አላስፈላጊ ጦርነትን ላለመዋጋት ነው።

በወቅቱ ባለ ስሌት ግልጽ ሆኖ የሚታየው ዋናው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጠላት ወያኔና ዘረኛ አገዛዙ መሆኑ ነው። ይህን የሕዝብ ጠላት የሚረዱና የሚያግዙ ያሉ ቢሆንም እነሱን የምናጠቃቸው ዋናውን ጠላት ወያኔን በማጥቃት ነው። ወያኔን ለማጥቃት ደግሞ ሙሉ ትኩረትን ይጠይቃል። በሁሉም መንገድና በሁሉም መስክ ጥቃት ለመሰንዘር ሲሞከር ያዝ ለቀቅን መተው፤ ማስወገድን መጠየቁ አልቀረም። ለምሳሌ ጦሩ ሚናው ሀገራዊ ሳይሆን ለወያኔ ነውና በተቻለ መጠን ሁሉ ይህን ለመቀየር በሁሉም መንገድ መሰማራትን የግድ ይላል። ማዕቀብ የወያኔን ኤኮኖሚያዊ አቅም የሚያደቅ ነውና ይደረግ ሲባልም ግለኝነትን ወይም የተዛባ ሀገር ወዳድነትን ማጠየቂያ አድርጎ ከዚህ ሀገራዊ ግዳጅ መሸሽ አይገባም። ለምሳሌ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሀገርን የሚጠቅም ሳይሆን የወያኔ አየር መንገድ መባል ያለበት ነው። አየር መንገዱ 85 በመቶ በትግራይ ተወላጆች እንዲሞላ መደረጉ ብቻ ሳይሆን አስተዳዳሪውም ቦርድ በወያኔ ቁጥጥር ስር ነው። ገቢውም ወደ ኢትዮጵያ ባንክ ሳይሆን ወደ ወያኔ ኪስ የሚገባ መሆኑን መረጃን አስደግፈው ያጋለጡት አሉ። በዚህና በውጭ ሀገር ያሉ ዜጎች ወይም ትውልደ ኢትዮጵያዎች በሚልኩት ገንዘብ (ወደ 3 ቢሊዮን ዶላር በዓመት) ወያኔ ራሱን ያስታጥቃል፤ ያደረጃል፤ያፈረጥማል። አልፎም በቢሊዮን የሚቆጠር የሀገሪቷን ንዋይም ይሰርቃል። ትግራይ እንድትለማ መላ ኢትዮጵያ ትድማ እምነቱን በስራ ያውላል።

ለዚህም ነው ዛሬ ከ24 ዓመት የስቃይ ተመክሮ በኋላ ሀገር አጥፊውን ወያኔን ያከበሩ መስሏቸው ህወሃት-ኢሕአዴግ ብለው እየጠሩ ለሽግግር ውይይት የሚጋብዙ ክፍሎች ስህተታቸው ከመለስተኛ መደናገር በላይ ሆኖ የሚገኘው። የሕዝብን ትግል የሚጎዳ ነው፤ ወያኔ ጠላት መሆኑን የማያምንና ወያኔን እንደ ወዳጅ፤ እንደ የሕዝባዊ ውይይት ተካፋይ አድርጎ የሚወስድ ነው። ወያኔ ትኩረታችንን የሚሻ ዋና ጠላት ነው የሚለውንም ይቃረናል። ይህን ዓይነት የአድርባይና አፍቅሮ ወያኔ ስሜት አንጸባራቂ አቅዋምን የሚገፉት ክፍሎች ትኩረታቸው ሌሎች ድርጅቶችን ማጥቃት ቢሆን የሚያስገርም አይደለም። ኢሕ አፓና መሪዎቹ ላይ ሲዘንብ የቆየውን የስም ማጥፋት ዘመቻና ጥቃት ምሳሌ አድርጎ ማቅረብ ይቻላል። አንዳንድ ድርጅቶች ራሳችውን ወያኔን ተቃዋሚ ብለው ቢሰይሙም ዋና ተልዕኮአቸው ወይ ትኩረታቸው ወጣቱን አደናግሮና አሳስቶ ከትግል ማራቅ መሆኑን መረዳት አላቃተንም:፡ ይህ ሁሉ ችግርና ዕንቅፋት ከፊታችን ቢደቀንም ትኩረታችን ከዋናው ጠላት ላይ እንዲነሳ ማድረግ የለበትም። በመሆኑም ሂደቱ በጣም አስቸጋሪ ቢሆንም ጸረ ወያኔ ሕብረትን በየፈርጁ መፈለግ አማራጭ የለሽ ስምሪት ነው ። አንድም ሰፊውን ሕዝብ በአንድነት በጸረ ወያኔነት እንዲነሳ መታገል ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ሀቀኛ ሀገር ወዳድ ድርጅቶችም ህብረት እንዲኖራችው መጣር ማለት ነው። ሁሉም ህብረት ህብረት ያለ ድርጅት በእውነትም ህብረትን ይፈልጋል ማለትም አይደለም። እኔ የበላይ እኔ አዛዥ ስሜቶችም አልጠፉም፡፡ ተጠያቂነታቸው ለሕዝብ ሳይሆን ለባዕድ የሆን ቡድኖች ደግሞ ፈቃድ ካላገኙ አይንቀሳቀሱም። የኢትዮጵያ ጠላትች በበኩላቸው የሀገር ወዳዶችን ህብረት መቸም አይፈልጉትም።

በዚህ አቢይ ጉዳይ ላይ ተገቢው ግንዛቤ ከሰፈነ ውጤቱ ያማረ ይሆናል። የሀገራችንን ከወያኔ መላቀቅ እንፈልጋለን የሚሉ ዜጎችም በድርጅቶች መሀል ገደል ከመፍጠርና ከማስፋት ይልቅ የህብረት ጠሪዎችና ደጋፊዎች ከሆኑ በድርጅቶቹ ላይ ተጽ ዕኖ ይኖራቸዋል። ወደ ፖለቲካው ዓለም ገብቶ በጸረ ወያኔው ትግል መሳተፍ ቀዳሚ ይሆናል ማለት ነው። በሀገር ጉዳይ የሩቅ ተመልካች ከተኮነ የትችትም መብት ሊገኝ አይችልም። ያላወቀ አይናገር፤ ያልተሳተፈ አይተች ተብሏል። ማን ያውራ የነበረ የሚለው ዓይነት ነው። የኢትዮጵያ ሀገራችን ህልውናና ሁኔታ ይመለከተናል የምንል ሁሉ በጸረ ወያኔው ትግል የአቅማችንን አስተዋጾ ማድረግ ይጠበቅብናል ማለት ነው። ይህ ወያኔ ላይ ያተኮረ ርብርቦሽ የህዝብን ክንድ ያጠነክራል፤ ወያኔን ይጎዳል። ወጣም ወረደም ግን ወያኔን ከፋፍሎና አጥቅቶ መጣል ይገባል እንጂ ከዚህ ሁሉ ዓመት በኋላ፤ ወያኔ ጸረ ህዝብነቱን ካስረገጠ በኋላ ወያኔን እንደ ወዳጅ ወይም አጋር ሀይል አይቶ ከወያኔ ጋር እንደራደር ጥሪ ወያኔነት ነው። መጬው ሽግግር ጸረ ወያኔ እንጂ ወያኔን እንደ አገዛዝ የሚያቅፍ አይሆንም። በተቻለ መጠን ወያኔን መከፋፈልና መሰነጣጠቅ ቢፈለግም፤ ቢገባም ወያኔን እንደ አገዛዝ፤ ቆሻሻውን ሳያጥብ ሳያራግፍ ለማቀፍ መነሳት ወይም መጥራት ትግልን ለማግማማትና ለመጉዳት መጣር ይሆናል።

ይህን ሁሉ በማጤን ትኩረታችንና ጥቃታችን በጸረ ወያኔ ድርጅቶች ላይ ሳይሆን በወያኔ ላይ መሆን አለበት ማለቱን እንደግመዋለን። ቀናው መንገድ ይህ ነውና ። በመሃል ሰርገው ገብተው ለወያኔ የሚያገለግሉትንም መንቀሳቀሻ ያሳጣቸዋል። የባዕድ ቅጥረኞችንም ዕድል አይሰጣቸውም። በ ሀቀኛ ሀገር ወዳድ ድርጅቶች ዙሪያ ሕዝብ የብረት ግድግዳ ከሆነ ትግሉ የሚሰምርበት ሁኔታ ይፈጠራል፤ይጠናከራል። ወያኔም ይጎዳል፤ ይጠቃል። በቆራጥነት መራራውን ፍልሚያ እየጀመርን በዚያው መደናቀፉ ያቆማልም ማለት ነው። ወያኔ በበኩሉ የሕዝብ ትኩረት በላዩ ላይ እንደይሆን ጉዳይ በጉዳይ፤ ትኩስ ዜና፤ አዲስ ጥቃት ወዘተ እየቀፈቀፈ የህዝብን ዕይታ ትኩረት ወደሌላ አቅጣጫ ይጐትታል። ሕዝብ ሊነሳሳ ነው? ህዳሴ የሚባል ግድብን ድቅን! ድምጽ ተነጠቀ ህዝቡ? የታሰሩት መሪዎች ጉዳይ ትኩረት ይሰጠው ይላል። ሙስሊም ዜጎች ለመብታቸው ሲታገሉ ክርስቲያኖችን የሚያስፈራራ ቅስቀሳውን ያጦፋል። ለዚህ ሁሉ ሰለባ መሆን መቆም አለበት። ዋናውን ትኩረት ከወያኔ ለሰኮንድም አለማንሳት ያስፈልጋል። ሻዕቢያ ኢትዮጵያን በአያሌው የጎዳና ደጉን የማይመኝላት ሀይል መሆኑ እንዳለ ሆኖ ዋናው ጠላታችን ወያኔ ነው። ከዝንጀሮ ቆንጆ ወያኔ ግን አስቀያሚ ነው ሲል አንድ ኢትዮጵያዊ እንዳስቀመጠው ነው። ትኩረታች ማን ላይና ወደየት እንዲሆን ወያኔ ሊወስንልን የምንተወው አይደለም። ቅጥረኛ ቡድኖቹም ይህ መብት የላቸውም።

የትግል ትኩረታችን በወያኔ ላይ ይሁን !

የወያኔን አገዛዝ ለማስወገድ በጋራ እንነሳ !!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *