ዜና ፍኖተ

መስከረም 5 ቀን 2009 ዓ.ም (15 September 2016)- ርዕሰ ዜና:  በኮንሶ ሕዝብ ላይ የሚደረገው አፈናና በደል ቀጥሏል  – የወያኔ አገዛዝ በየትምህርት ቤቱ የሚያደርገውን ስብሰባ ቀጥሏል – የኮሎኔል ደመቀ ጉዳይ ለመስከረም 9 ተቀጠረ፤ በጎንደር አፈናው ቀጥሏል – በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት በአንዳንድ አካባቢዎች ከባድ ዝናም ይጥላል ተባለ – የካናዳ መንግስት በወያኔ ላይ ቁርጥ አቋም እንዲወስድ ተጠየቀ::

ዝርዝር ዜና

#የኮንሶ ሕዝብ በወያኔ አግአዚ ጦር ከፍተኛ ጭፍጨፋ የተካሄደበት መሆኑን መዘገባችን የሚታወስ ሲህን አፈናውና እስራቱ በዛሬውም ቀን ተጠናክሮ መቀጠሉ እየተነገረ ነው። በርካታ የአካባቢው ነዋሪዎች በወያኔ የጸጥታ ኃይሎች እየታደኑ በቁጥጥር ስር የዋሉ ሲሆን ወደ ቦረና ከተሰደዱት 400 ቤተሰቦች በተጨማሪ ሌሎች ቁጥራቸው ያልታወቀ ዜጎች ቤት ንብረታቸውን እየለቀቁ በተለያዩ አቅጣጫዎች የተሰደዱ መሆናቸውን ተሰምቷል።

#የወያኔ አገዛዝ በመላው ሀገሪቱ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ከሰኞ መስከረም 4 ቀን 2009 ዓ.ም አንስቶ እስከ መስከረም 11 ቀን 2009 ዓ.ም. ድረስ የሚቆይ ስብሰባ እንዳቀደ መዘገባችን ይታወቃል። ስብሰባው በትናንትናው ቀን የተጀመረ ሲሆን ትኩረቱ እየተጋጋለ በመሄድ ላይ ያለውን በጎንደር፣ በወለጋ፣ በአርሲ፣ በሐረር፣ በጎጃም፣ በኮንሶ፣ ወዘተ፣ የሕዝብ ተቃውሞ አጠቃላይ የሆነ ሕዝባዊ ድጋፍ ለማሳጣት የታለመ መሆኑ ታውቋል፡፡ የወያኔ ባለስልጣኖች በተለየያዩ ጊዜያት የተወጠሩባቸውን ሕዝባዊ ተቀቃውሞዎች ለማሽመድመድ አድማጭና ሰሚ አልባ በሆኑ ውይይቶች ሕዝብን ሲያሰለቹና ሲያታክቱ መቆየታችው የሚታወቅ ሲሆን የስብሰባው ዓላማ የተሰብሳቢውን ስሜት የሚነኩ ሀሳቦች እንዲንሸራሽሩ በማድረግና ተሰብሳቢው በስሜት እንዲናገር በመገፋፋት የተቃዋሚነት ሰሜት አላቸው የሚሏቸውን ለማወቅና እየመነጠሩ ለማውጣት እንደነበርና ቀደብ ብሎ ከነበረው ተመክሮ መገንዘብ ተችሏል። ከስብሰባዎቹ በኋላ በርካታ ሰዎች ከሥራ ገበታቸው እንዲፈናቀሉ ተደርገዋል፣ ከሚሠሩበት አካባቢ ተባረዋል፣ በሥራ ላይ ካላቸው ደረጃ ዝቅ እንዲሉ ተደርጓል፡፡ ቀደም ብለው በነበሩ ስብሰባዎች የተሰብሳቢዎችን ቀልብ ለመግዛት ሲከፈል የነበረው አበል በዘንድሮው ስብሰባ ላይ እንደማይከፈል በመነገሩ ስብሰባው ገና ከጅምሩ በተቃውሞ መናጡ ታውቋል፡፡ በአዲስ አበባ በሚገኙ የግል፣ የኮሚኒቲና የሚሽን ትምህርት ቤቶች ሰብሰባው በተጀመረ በሁለተኛው ቀን በአበል ሰበብ ከዘጠና ከመቶ በላይ የሚሆኑ የስብሰባ አዳራሾች ወና መሆናቸውን ለማወቅ ችለናል፡፡ የወያኔ ሹሞች በአንድ ቀን በአበል ስም እሰከ አራት ሺ ብር እንደሚከፈላቸው የሚታወቅ ሲሆን አሁን ገንዘብ አጥሮናል ቢልም መምህራኑ በወሰዱት ቆራጥ ርምጃ መደናገጡ ታውቋል፡፡

የወልቃይት የማንነት ጥያቄ ኮሚቴ አባልና በወያኔ ኃይሎች የጸጥታ ኃይሎች ታስረው የሚገኙት ኮሎኔል ደመቀ ዘውዴ መስከረም አራት ቀን ጉዳያቸው በፍርድ ቤት ይታያል ተብሎ መወሰኑ የሚታወስ ሲሆን በትናንትናው ቀን ጉዳያቸው አለመታየቱና ፍርድ ቤቱ እንደገና ለመስከረም 9 ቀን ቀጠሮ የሰጠ መሆኑ ታውቋል። የኮሎኔሉን ጉዳይ ለመከታተል በርካታ ሕዝብ በፍርድ ቤቱ አካባቢ ተሰባስቦ የነበረ ሲሆን ቁጥሩ ቀላል ያልሆነ የወያኔ አገዛዝ የጸጥታ ኅያል አባላትም በስፍራው እንደነበር ያገኘነው ዜና ይገልጻል። የወያኔ አጋዚ ጦር በጎንደር ወጣቱን በሌሊት አፍኖ መውሰዱን አንደቀጠለ መሆኑ ሲታወቅ ወጣቱም ከአፈናው ለማምለጥ ቦታ እየቀየረ መሆኑ ይነገራል። በደባርቅ ወያኔ ነዋሪውን ትጥቅ ለማስፈታት ቤት ለቤት አሰሳ እያካሄደ መሆኑንና ወጣቱን ማፈንና ህዝብ ማዋከቡን አንደቀጠለ መሆኑን ከቦታ የሚደርሱን መረጃዎች ይገልጻሉ። በርካታ ወገኖችም ወያኔን በማናችውም መንገድ ለመታገል ወደ ገጠር እየገቡ መሆናቸው ይወራል።

በተያያዘ ዜና በቅሊንጦ እስር ቤት ከተነሳው እሳት ጋር ተያይዞ በወያኔ የጸጥታ ኃይሎች ከተገደሉት ሰዎች መካከል አንደኛው የወልቃይት የማንነት ጥያቄ ትደግፋለህ ተብለው ተይዘው የነበሩት አቶ ይላቅ አቸናፊ የሚባሉ መሆናቸውን ለማወቅ ተችሏል። የወያኔ አገዛዝ አስከሬናቸውን ለቤተሰቦቻቸው በማስረከቡ ረቡዕ መስከርም 5 ቀን 2008 ዓ.ም. ስርአተ ቀብራቸው የተካሄደ መሆኑን የተገኘው መረጃ ይገልጻል።

በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት በአንዳንድ የኢትዮጵያ ግዛቶች ከባድና ከወትሮው ለየት ያለ መጠን ያለው ዝናም ሊዘንም እንደሚችል በአየር ምርመራ አዋቂዎች የተተነበየ ሲሆን የዝናሙ መጠን የጎርፍ አደጋ ሊያስከትል የሚችል ከመሆኑም በላይ በአንዳንድ ቦታዎች የደረሱ ሰብሎችን ያበላሻል የሚል ስጋት ፈጥሯል።

የካናዳ መንግስት ከወያኔ አገዛዝ ጋር ያለውን ግንኙነት እንዲመረምርና ቁርጠኛ አቋም እንዲወስድ እየተጠየቀ ነው። በአገሪቱ ዋና ዋና ጋዜጠኞች ላይ በመጻፍም ሆነ በምክር ቤትና በሌሎች ቦታዎች ሆነ አመች መድረኮችን በመጠቀም ታዋቂ የአገሪቱ ዜጎች የካናዳ መንግስት የወያኔ አገዛዝ በሰላማዊ መንገድ ተቃውሞ በሚያሰሙ ዜጎች ላይ እያካሄደ ያለውን ጭፍጨፋ በይፋ እንዲያወዝና የተካሄዱትን ወንጀሎች የሚመረምር ነጻና በዓለም አቀፍ ደረጃ የተቋቋመ ገለልተኛ አካል ወደ አገር ውስጥ እንዲገባ ተገቢውን ተጽእኖ እንዲያደርግ ጠየቀዋል። ጥያቄውም ተግባራዊ እንዲሆን የካናዳ መንግስት ለወያኔ አገዛዝ የሚሰጠው እርዳታ ብድር ላይ ማዕቀብ በመጣል ተጽአኖ እንዲያደርጉም አሳስበዋል።

To Read:
To Listen PART 1:
To Listen PART 2: