የታህሳስ 3 ሠማዕታት መታሰቢያ የጋምቤላ ድርጅት የትግል አጋርነት

ታህሳስ 25/2008 (ኦገስት 1/2016):  እኛ ኢትዮጵያውያን የጋምቤላ ልጆች በአለፉት ሀያ አምስት ዓመታት የመከራ ዘመን ከማንም በበለጠ መልኩ ተቀጥቅጠናል፤ ዘራችን ጠፍቷል፤ ድንግል መሬታችን በጉልበተኞች ተወርሷል፤ ለባዕድ ተሰጥቷል።

ዛሬ እኛ አኝዋኮች ያለ አጋር አንገታችንን ደፍተን በሃዘን ላይ እንገኛለን ።ሆኖም እናት ሀገራችንን ኢትዮጵያን ከማንም ባላነስ እናፈቅራታለን። የበደለን አምባገነኑ ዘረኛ የጥቂት ትግሬዎች ቡድን ቢሆንም ታላላቆቹ ነገዶች–የአማራው፤ የኦሮሞው ወዘተ–የሌላው ኢትዮጵያዊንደም የእኛም ደማችን ነው። ቁስሉም ቁስላችን ነው።  በእኛ እምነት የጋምቤላ እንባ የሚደርቀው፤ነጻነቱን የሚጎናጸፈው የሌላውም ኢትዮጵያዊ ጨለማው ሲገፈፍለት የዚያን ጊዜ ነው የእኛም ብርሃን  የሚወጣው።  ይህ የባዕድ ቅጥረኛ የሆነ ስርዓት ተወግዶ ለሁላችንም እኩል የሆነች፤ ሉዓላዊነቷ  የተረጋገጠ ኢትዮጵያ የምትመሰረተው እጅ ለእጅ ተያይዘን በአንድ ስንዘምር፤ ስንታገል፤ ስንወድቅ ስንጥል ብቻ ነው  የሚል የጸና ኢትዮጵያዊ ወኔ የሰነቅን ጋምቤሎች መሆናችንን እናረጋግጣለን።

ባለፉት አራት ዓመታት የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ትግልና መስዋዕትነት እያስታወስን  በዚህ 6 ወርም የኦሮሞ ልጆች ህዝባዊ አመጻና ወያኔ ባልታጠቁ ዜጎች ያወረደውን መዓት ዝንዘክር፤ ዛሬ ደግሞ የጎንደር ምልዓተ ሕዝብ ሆ ብሎ በአንድ ተነስቶ ለ 25 ዓመት የጠፋብንን አንድነትና ኢትዮጵያዊ ወኔ በአረንጓዴ ቢጫ ቀይ ሠንደቅ አጅቦ አደባባይ ሲወጣ ስንመለከት አንገታችን ቀንቷል። በሀዘን ያረረው አንጀታችን በደስታ ርሷል።  ይህን ኢትዮጵያዊ ትግል ላቀጣጠሉ አማራዎች ኢትዮጵያዊ አጋርነታችንን በሙሉ ልብ እንገልጻለን።  ወሳኙ ያልተሸራረፈ ነጻነታችንን የምንጎናጸፈው በተራ እየተነሱ በተራ ላለመታት እንዲሁም ይህን አጥፊ የወያኔ ስርዓት ግብዓተ መሬቱን ለመፈጸም ትግላችንን በህብረትና በተደራጀ መልኩ ለመቀጠል ከማንኛውም በኢትዮጵያ አንድነት ክሚያምንና እኩልነትና ዴሞክራሲን ከሚቀበል ድርጅት ይሁን ስብስብ  ያልተጀመረውን ለመጀመር፤ የተጀመረውን ለማጠናከር በኢትዮጵያ ስም ቃል እንገባለን።

ድል ለሕዝብ!
የታህሣስ 3 ሰማዕታት መታሰቢያ የጋምቤላ ድርጅት