የነጋዴዎች ምሬት፣ በታሳሪ ዜጎች ላይ የሚደርሰው በደል፣ የሚመሩትን ድርጅት ለማዳከም ዶ/ር መራራን ዋስ መከልከል፣ በወያኔና በግብጽ መካከል ያለው ግንኙነት መሻከሩ፣ ወያኔ የኃይል ማመንጫ አስመረቅሁ ሲል የኤሌክትሪክ መቆራረጥ ባሰበት …

ፍካሬ  ዜና ከፍኖተ ዴሞክራሲ የኢትዮጵያ አንድነት ድምጽ ሬዲዮ (ታኅሣሥ 23 ቀን 2009 ዓ.ም.) – ነጋዴዎች ያላቸውን ምሬት እየተናገሩ ነው – በተለያዩ ቦታዎች የታሰሩ ዜጎች ከፍተኛ በደል እንደደረሰባቸው ገለጹ – ወያኔ ዶክተር መረራን የዋስ መብት ነፍጎ በእስር እንዲቆዩ ያደረገው ድርጅቱን ለማሽመድመድ መሆኑ ተነገረ – የኢንተርኔት አገልግሎትን በመዝጋቱ የወያኔ አገዛዝ ከፍተኛ ኪሳራ እየደረሰበት ነው – የወያኔ አገዛዝ አገሪቱን እዳ ውስጥ እየዘፈቃት መሆኑ ታወቀ = የግብጽና የወያኔ ግንኙነት እየሻከረ ሄደ – የግቤ የኃይል ማመንጫ ተጀመረ በተባለ ማግስት የኤሌክትሪክ መቆራረጥ ተባባሰ – ያለፈው የፈረንጆቹ ዓመት በኢትዮጵያ የተካሄደው ሕዝባዊ ትግል ብዙ እመርታን አሳይቷል ተባለ – ባለፈው የፈረንጆቹ ዓመት የመብት ረገጣ መስፋፋቱንም የኢትዮጵያ የፖለቲካ እስረኞች አንድነት ኮሚቴ ገለጸ።

ነጋዴዎች ምሬታቸውን እየተናገሩ ነው

ወያኔ የንግዱ ስርዓት እያመሰው በመሆኑ ነጋዴዎች ምሬታቸውን እየገለጹ ይገኛሉ፡፡ የወያኔው መከላከያ ሚኒስቴርና በስሩ የሚገኙ የተለያዩ ተቋማት በንግዱ ላይ መረን የለቀቀና ግልጽ የሆነ የወሮበላ ተግባር ሲፈጽሙ መቆየታቸው ይታወቃል፡፡ በፒያሳ፣ በመርካቶና በሌሎች ቦታዎች ለሚገኙና በትግራይ ተወላጆች ባለንብረትነት ለተመዘገቡ የወርቅ ቤቶች በመከላከያ መኪናዎች ወርቅ እያስጫኑ እንደሚያቀርቡ ይታወቃል፡፡ ከውስጥ በአንጠረኛነት ከሚሰሩት ዜጎች ማወቅ እንደተቻለው የሚያቀርቡት ወርቅ ሁለት ዐይነት ሲሆን አንደኛው ከአረብ አገሮች ካለቀረጥና እንዲሁም ካለ ምንም የግብር ክፍያ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ የወርቅ ጌጣጌጦች ሲሆኑ ሌላው ደግሞ በአገር ውስጥ ወርቅ ከሚወጣባቸው የተለያዩ አካባቢዎች በተለያየ ሁኔታ የተገኙ ወርቆች ናቸው። ከዚህ በተጨማሪም እነዚህ የወያኔ መከላከያ ተቋማት የተለያዩ ኤክትሮኒክስ እቃዎችን፣ ቴሌቪዥን፣ አልባሳት፣ የሞባይል ቀፎዎችንና ተዛማጅ እቃዎችን፣ መኪናዎችንና መላዋወጫዎችን፣ ብትን ጨርቃ ጨርቆችን፣ የቤትና የቢሮ እቃዎችን፣ የህክምና መገልገያ ቁሳቁሶችን፣ መድሀኒቶችን፣ የህትመት ቁቁሶችን፣ የመኪና ጎማዎችንና ባትሪዎችን፣ ወዘተ. ከቀረጥ ነፃ በሆነ ዋጋ ከውጭ የሚያስገቡ ሲሆን የጉምሩክ የመጋዘን ኪራይ እንኳ ሳይከፍሉ ቀረጥ ከፍለው ከሚያስገቡ ነጋዴዎች ከሚሸጡበት ሃምሳ ከመቶ በታች በሆነ ዋጋ በመሸጥ ገበያን እያወኩና እየረበሹ ከመሆናቸውም በላይ ህጋዊ ነጋዴዎችን እየገፉ ከሥራ ውጪ በማድረጋቸው ነጋዴዎች ምሬታቸውን እየገለጹ መሆናውን ተገንዝበናል፡፡

በተለያዩ ቦታዎች የታሰሩ ዜጎች ከፍተኛ በደል እንደደረሰባቸው ገለጹ

ባሳለፍነው ሳምንት የወያኔ አገዛዝ በገፍ እና በግፍ የታሰሩ እስረኞችን የስብከት ትምህርት ሰጥቶና ደጋፊዎቹ እንዲሆኑ ጥረት አድርጎ መፍታቱን የገለጸ ሲሆን ውጤቱ ግን የዚህ ተቃራኒ መሆኑ ታወቀ፡፡ ከዚህ ቀደም እንደገለጽነው ወያኔ በተለያዩ እስር ቤቶች እና የወታደር ማሰልጠኛ ቅጥሮች ውስጥ በእስረኞች ላይ ሰቆቃ መፈጽሙን ከእስር የተለቀቁት በአንደበታቸው ማረጋገጣቸው ታውቋል፡፡ እስረኞቹ ለአንዳንድ ዜና ምንጮች በሰጡት መረጃና በተለይም ከጀርመን ሬድዮ የአማርኛው ዝግጅት ክፍል ጋር ባደረጉት ቃለ-ምልልስ በረሀብ መገረፋቸውና፣ ባዶ ሲሚንቶ ወለል ላይ እንዲተኙ መደረጋቸውን፣ በባዶ እግራቸው በአሾህና በጠጠር ላይ እንዲሄዱ መደረጋቸውን፣ በጉልበታቸው ተንበርክከው እንዲሄዱ መደረጋቸውንና እርቃናቸውን ሆነው በደረታቸው እንዲሳቡ መደረጋቸው እልህ በተሞላው ቅሬታ መግለጻቸው ታውቋል፡፡ ማንነታቸውንና ሰብእናቸውን የሚነኩ ስድቦችና ዘለፋዎች ይሰነዘርባቸው እንደነበር በቅሬታ አብራርተዋል፡፡ ከሁሉም እስረኞች መንፈስ መረዳት የተቻለው የጀመሩትን ትግል ይበልጥ አፋፍመው ከመቀጠል ወደ ኋላ እንደማይሉ ነው፡፡

ወያኔ ዶክተር መረራን የዋስ መብት ነፍጎ በእስር እንዲቆዩ ያደረገው ድርጅቱን ለማሽመድመድ መሆኑ ተነገረ

ወያኔ በግፍ ያሰራቸው ዶ/ር መራራ ጉዲና በዋስ የመፈታት መብታቸው ተረግጦ በእስር እንዲቆዩ ተወስኗል፡፡ ወያኔ የተቃዋሚ ድርጅቶችን እንደልቡ ለመጋለብ ሲያቅድ መቆየቱ የሚታወቅ ሲሆን በተለያዩ ጊዜዎች ከመካከላቸው አንጃዎች በመፍጠር ሲከፋፍላቸውና የድርጅቶቹ ጥንካሬ እንዲፍረከረክ ለማድረግ ደባ ሲሸረብ የኖረ መሆኑ ይታወቃል። ቀድሞ በዶ/ር መረራ ጉዲና ይመራ የነበረውን ኦብኮ የተሰኘ ድርጅት በተለያዩ ጊዜያት ከውስጡ በወጡ አንጃዎች እንዲበጠበጥ አድርጓል፡፡ የድርጅቱን ቢሮ እያሰበረ የድርጅቱን ንብረቶች አዘርፏል፡፡ የዚህ ድርጅት አመራሮች ኦሮሞ በመሆናቸው ብቻ በፈጠራ በኦነግ አባልነት እየከሰሰ ዘብጥያ ያወርዳል፡፡ እቶ በቀለ ገርባና ጓደኞቻቸው ተጨባጭ ማስረጃዎች ናቸው፡፡ ብዙዎች እንደሚሉት በኦነግ አባልነትና ገደጋፊነት መታሰር ከተገባ መታሰር ያለባቸው የራሱ የወያኔው ኦህዴድ የሚባለው በኦሮሞ ሕዝብ ላይ እራሱን ያነገሰው ድርጅት መሪዎች ነበር፡፡ ይህ የወያኔ በገንዘብ ጥቅም ድርጅቶች ውስጥ አንጃ የመፍጠር ሴራ ውጪ በህቡዕ በሚንቀሳቀሱ እንደ ኢሕአፓ የመሰሉ ድርጅቶችም ላይ መከሰቱ አይዘነጋም፡፡

የኢንተርኔት አገልግሎትን በመዝጋቱ የወያኔ አገዛዝ ከፍተኛ ኪሳራ እየደረሰበት ነው ተባለ

ሕዝባዊ ተቃውሞን ለማፈን ወያኔ ኢንተርኔት አገልግሎትን በመዝጋቱ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ የሚባል የኤኮኖሚ ቀውስ እንደደረሰበት ይፋ ሆነ፡፡ ወያኔ በብቸኝነት የስልክ፣ የኢንተርኔት አገልግሎቶችን በብቸኝነት በመያዝ የዜጎችን የእለት ተእለት ግንኙነት እየጠለፈ መሠረታዊ ሰብአዊ ነፃነትን እየረገጠ በመሆኑ በዓለም ዙሪያ በሚገኙ የሰብአዊ መብት ተቆርቋሪ ተቋማት በተለያዩ ጊዜት ውግዘት እየወረደበት መሆኑ አይዘነጋም፡፡ ከዚህ በላይ ወያኔ ከሞባይልና ከኢንተርኔት ግልጋሎት ሊያገኝ ከሚገባው በላይ በስርቆት ተጨማሪ ክፍያ እንደሚወስድ የሚታወቅ ነው፡፡ ይህ መንግስታዊ ሌብነት የሚባለው ነው፡፡ ወያኔ ኢንተርኔትን ማለትም ቫይበርን፣ ዋትስ አፕን፣ ፌስ ቡክን፣ ዩቲዩብን፣ ወዘተ. መዝጋቱ የሚታወቅ ቢሆንም የወያኔን እግድ የሚሰብር ቪፒኤን እና ፒሲፎን ወዘተ. በተሰኙ አፕሊኬሽኖች ሁሉን ወያኔ የዘጋቸውን የሶሻል ሚዲያዎች መጠቀም በመቻሉ በቻይናዎች እርዳታ ሌሎች የኢንተርኔት አገልግሎቶችን ጥርቅም አድርገው የሚዘጉ መሳሪያዎችን ሥራ ላይ ለማዋል እያውጠነጠነ መሆኑን ሰምተናል፡፡ ለሱም መንገድ አይጠፋም የሚሉ በጉዳዩ ላይ የተለቀ እውቀት ያላቸው ወጣቶች በልበ ሙሉነት ያስረዳሉ፡፡ ከኢንተርኔት አገልግሎት ያገኝ የነበረው ገቢ አልፎ ባቋረጠበት ወቅት ከ9 ሚሊዮን ዶላር መክሰሩ በጥናት የተደረሰበት ሲሆን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ካወጀና ሙሉ በሙሉ ካቋረጠ በኋላ በቀን 500 ሺ ዶላር ኪሳራ ውስጥ መግባቱ ይነገራል።

የወያኔ አገዛዝ አገሪቱን እዳ ውስጥ እየዘፈቃት መሆኑ ታወቀ

ወያኔ በአስር አመታት አገሪቱን በአስር እጅ እጥፍ በብድር እዳ እየዘፈቃት መሆኑ የወቅቱ የመነጋገሪያ ርዕስ እንደሆነ ታወቀ:: የወያኔ ቁንጮዎች በአጠቃላይ ለሀገርና ለወገን ደንታ ቢስ ናቸውና አሁን ሀገሪቱን የዘፈቁበት የእዳ ክምር በመጪዎቹ ሃያ ትውልዶች እንኳ ተከፍሎ የማይዘለቅ መሆኑን የመዋዕለ-ንዋይ ጠበብቶች ያስረዳሉ፡፡ ወያኔ ከዋና ዋና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች የተበደረው ገንዘብ መጠን ከ 22 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ እየነጎደ መሆኑን መገንዘብ ተችሏል፡፡ ለዚህ ለተጠቀሰው እዳ በየአመቱ በአነስተኛ ግምት ከሦስት መቶ ሃምሳ ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ መክፈል የግድ ይላል፡፡ ይህ የተቆለለው ብር የተገኘው በትምህርት ማስፋፋት፣ በመንገድ ግንባታ፣ በጤና አጠባበቅ ስርጭት፣ በመጠጥ ውሀ፣ በኤሌክትሪክ ኃይል ምርትና ስርጭት፣ በኢንተርኔትና በሚባይል ስልክ ኔት ወርክ፣ በኤርፖርት ማስፋፊያ፣ በኢንዱስትሪ መንደር ግንባታ፣ በስኳር ፋብሪካዎች ግንባታ፣ በእግር ኳስ ስቴዲየሞች ግንባታ ወዘተ. ስም ሲሆን አብዛኛዎቹ ከስማቸው በስተቀር በሥራ ላይ ተተርጉመው መታየት የተሳናቸውና ብዙዎችም ከአፋዊነት ባለፈ ግልጋሎት የማያሰጡ በመሆናቸው ። በብድር ወጪ የተደረገባቸው የገንዘብ መጠንና አገልግሎታቸው የሰማይና የምድር ያህል ይራራቃሉ፡፡ የቻይና መንገዶች በአብዛኛው ሳመረቁ በመፈርፈር ይጀምራሉ፤ ትምህርት ይስሙላ በመሆኑ የተለያዩ ዲግሪዎች ይዘው የማያነቡና የማይጽፉ ምሩቃን ቁጥር በርክቷል፡፡ በጤና ስም ግድግዳና ጣሪያ ከመሠራቱ ባለፈ የመመርመሪያ መሳሪያና መድሀኒት ባለመኖሩ ወጣት ሀኪሞች እየተማረሩ ለስደት ተዳርገዋል፡፡ በብድር ስም የሚገኘውን ገንዘብ በተለያዩ እርከኖች ላይ የተቀመጡ የወያኔ ቁንጮዎች እየመነተፉ ባለበት ሁኔታ፣ የሀገር እድገት ውስጧን አስርባ ፊቷን እንደምትቀባ ያለች ኮማሪትን የመሰለ ነው በማለት የመዋዕለ ንዋይ ጠበብቶች ይገልጻሉ፡፡

የግብጽና የወያኔ ግንኙነት እየሻከረ ሄደ

ግብፅና ወያኔ እሰጥ አገባቸው እየከረረ መሄዱ እየታየ ነው፡፡ ከዓባይ ግድብ ጋር በተያያዘ ወያኔና ግብፅ ያላቸው ግንኙነት አፋዊ እንደሆነ የሚታወቅ ነው፡፡ በግድቡ ዙሪያ ላይ በየጊዜው መግባባት ላይ መድረሳቸውን ቢገልጹም የወያኔ “በኃይል ይሞክሩን” ከሚለው የጅል ፉከራ፣ በግብፅ በኩል አንዳንድ ወያኔን የሚቃወሙ ድርጅቶችን እያስጠጋች መሆኗ በቅርቡ ገሀድ መውጣቱ በመታወቁ ውጥረቱ ከፍ እያለ መምጣቱን የፖለቲካ አዋቂዎች ያስረዳሉ፡፡ ከአሁን ቀደም ወያኔንና ሻዕቢያን ኢትዮጵያን ለማፈራረስ በመቆማቸው ግብጽ እንደ እንደነ ሶሪያ፣ ኢራቅ፣ ሳዑዲ፣ ሊቢያ፣ የመሳሰሉ ፀረ-ኢትዮጵያ ኃይሎች ሁሉ የበኩሏን ሚና ስትጫወት መቆየቷ ታሪክ የመዘገበው ሀቅ ነው፡፡ ዛሬ ወያኔን ለመጣል ወይም ደግሞ ፅንፈኛ የሆነውን ከኢትዮጵያ የመገንጠል ዓላማ የሚያራምዱ ኃይሎችን መርዳቷ እንደማያስገርም የሚገልጹ ብዙዎች ናቸው፡፡ ከሁሉም በላይ አንድ የኦሮሞ የቴሌቪዥን ጣቢያ ከግብፅ በአረቢኛ ስርጪት እንደሚያስተላልፍ መሰማቱ በርካቶችን እያነጋገረ መሆኑን ተገንዝበናል፡፡ ከወያኔ ሾልከው ከሚወጡ መረጃዎች መገንዘብ የተቻለው ይህ የግብፅን ሁኔታና የሳዑዲና የኳታር ከኤርትራ ጋር ጡት መጣባትን ለመቋቋም በሚል በጅቡቲ የባህር ኃይል ለማቋቋምና አንድ የምድር ጦር ኃይል ለማስፈር መታቀዱ ታውቋል፡፡

የግቤ የኃይል ማመንጫ ተጀመረ በተባለ ማግስት የኤሌክትሪ መቆራረጥ ተባባሰ

ወያኔ የግቤ ሦስት የኃይል ማመንጫ ግድብ ሥራው ተጠናቆ መመረቁን ባስታወቀ በሳምንቱ የኤክትሪክ ኃይል በተደጋጋሚ እየተቆራረጠ መሆኑ ታወቀ፡፡ በመሰረቱ ይህ የግቤ ሦስት ግንባታ በዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ ተቃውሞና ውግዘት ሲቀርብበት የቆየ መሆኑ የሚታወቅ ነው፡፡ በቱርካና ሀይቅ አካባቢና በሁለቱም ሀገራት ማለትም በኬንያና በኢትዮጵያ ድንበር የሚኖሩ ሕዝቦችን ተፈጥሯዊ መብት የሚጎዳ በመሆኑ በኢትዮጵያም በኬንያም የሞኖሩ ሕዝቦች ተቃውሟቸውን አሰምተዋል፤ አሁንም እያሰሙ ነው፡፡ ወያኔ ከዚሁ ጉዳይ ጋር በተያያዘ በርካታ የአካባቢውን ተወላጆች እያሰረ ደብዛቸውን አጥፍቷል፡፡ ይህ ግድብ ሲመረቅ የወያኔ ባለስልጣኖች ለአንድ ደቂቃም ኤሌክትሪክ ሊቋረጥ እንደማይችል በመግለጽ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት ቢቀላምዱም ሰሞኑን በአጠቃላይ በድፍን ሀገሪቱ ኤሌክትሪክ በተደጋጋሚ እየተቆራረጠ መገኘቱ የወያኔን እድገት እርቃኑን ማስቀረቱን ተገንዝበናል፡፡ በየጊዜው ፊዩዝ ይቃጠላል፣ ትራስፎርመር ይፈነዳል፡፡ ለዚህ የሚሰጠው ምላሽ ቻይና ሠራሽ መሆኑ እንደሆነ ቢሆንም ጭራሹን ቻይናዎቹ ከወያኔው መከላከያ ጋር በሽርክና አገር ውስጥ የሚያመርቱትም በየጊዜው እየፈነዳ መሆኑ የወያኔ ግብ ዘረፋ ብቻ መሆኑን ያስገነዝባል በማለት ብዙዎች በቁጭት ይገልጻሉ፡፡

ያለፈው የፈረንጆቹ ዓመት በኢትዮጵያ የተካሄደው ሕዝባዊ ትግል ብዙ እመርታን አሳይቷል ተባለ

የፈረንጆች 2016 ዓ.ም. ሲያልቅና ያለፈውን ስንቃኘው በኢትዮጵያ ዓመቱ የሕዝባዊ ትግል ዓመት ሆኖ ማለፉን በእርግጠናነት ማቅረብ እንችላለን ያሉ ተንታኞች በዚህ ባለፈውው ዓመት ህዝብ ከፍተኛ መስዋዕትነትን ቢከፍልም በቆራጥነት ተነስቶ ለመብቱና ለሀገሩ ለመታገል በመሆኑ የሚከበር ነው ብለዋል። ከሁሉም በላይ ደግሞ ኢትዮፕጵዊው ትግሉን ለማደናቀፍና በጎጥ ክልል ወስኖ ለማክሸፍ የተደረገው ጥረት ከሽፎ ሕዝብ ኢትዮጵያዊነትና ሰንደቅ ዓላማን አንስቶ ትግሉን መቀጠሉ ለወያኔ አስከፊ መርዶ መሆኑን ታዛቢዎች ገልጸዋል። የት ደርሰናል ስንል ወያኔ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጥቶና አፋኞቹን በሰፊው አሰራጭቶ ከ45 ሺ ሰው በላይ ቢያፍስምና ቢያግትም፤ ግብረ ስየል ቢፈጽምም ትግሉ የቆመ ሳይሆን እመርታ አሳይቶ ወደ ትጥቅ ደረጃ መሸጋገሩ እየታየ ያለ ነው። በይዘትም ከጎንደር እስከ ኮንሶ ተስፋፍቷል። በዚህ ትግል ለታሰሩት ድጋፍ መስጠት ዋና ግዳጅ ሆኖ ሳለ በወያኔ ተንኮል፣ተጠምደው የእርስ በርስ ንትርክን የሚያፋፍሙትን ሕዝብ ማውገዙም ተጠቅሷል። ይህን በተመለከተ የወያኔ ሰለባ የሆኑ በውጭ ሀገሮች ነዋሪዎች የሆኑ ትውልደ ኢትዮጵያውያን የወቀሳው ዋና ተጠያቂ መህናቸውም ተጠቅሷል። ወያኔ በቀደዳቸው የጎጥ ቦይ የሚፈሱና ኢትዮጵያዊነትን ለመፈታተን የተነሱት እነሱ ናቸውና የሕዝብ ውገዘት ቢደርስባቸውም ትክክል መሆኑ ታምኖበታል።
ባለፈው የፈረንጆቹ ዓመት የመብት ረገጣ መስፋፋቱንም የኢትዮጵያ የፖለቲካ እስረኞች አንድነት ኮሚቴ (ኢፖእአኮ) ገለጸ

በየተያያዘ ዜናም ብዙ የማደናቀፍና የማፍረስ እርምጃ ቢወሰድበትም ተቋቋሞ እስከ ዛሬ የሚንቀሳቀሰው የኢትዮጵያ የፖለቲካ እስረኞች አንድነት ኮሚቴ ባደረሰን መግለጫ ባለፈው የፈረንጅ 2016 ዓ.ም. በኢትዮጵያ የመብት ረገጣና ወንጀል ተስፋፍቶ እንጂ ቀንሶ አልታየም በሚል ወያኔን ኮንኗል። ባለፈው ዓመት ወያኔ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ በአጠቃላይ በኦሮሞው፤በአማራው፤ በሙስሊሙ፤በኮንሶው ላይ በተልይ የፈጸመው ግፍና ፍጅት የሚወገዝ ነው በሚል ጠቅሶ ወያኔ የተነሳበትን ሕዝባዊ ትግል ለማፈን ከፍጅትና ግፍ ውጪ መንገድ ስላልታየው በህዝብ ላይ እያደረሰ ያለው በደል በጥብቅ መወገዝ አለበትም ሲል አላሳቧል። በወያኔ ማገቻዎች በአሁኑ ጊዜ ወደ ስልሳ ሺ የሚጠጉ የፖለቲካ እስረኞች አሉ ያለው ኮሚቴው የወያኔን ማገቻዎች ጎብኙ ተብለው የተጠየቁ የባዕድ ተቁዋሞች ያሳዪት ቸልተኛነት የሚወገዝም ነው ብሏል። በሕዝብ ላይ የደረሰውና እየደረሰውን ያለውንም የመብት ረገጣ በተመለከተ የባዕድ ተቅዋሞች ሀቁን በማቅረብ ፈንታ አለሳልሰውና ቀናንሰው ማቅረባቸው የሚያጠያይቅ ነውም ከማለቱ ባሻገር ኢትዮጵያዊ ነን ባዮች ተቋሞችም በዚህ መስክ ስምሪታቸው አጠያያቂ ነው በሚል ተችቷል። በኢትዮጵያ የደረሰ ያለውን ግፍና በደል ሁሉም ዜጋ ተግቶ ማጋለጥ አለበት ሲል ኮሚቴው ኢፖእአኮ አሳስቧል።

ዝርዝር ዜና ከፍኖተ ዴሞክራሲ ያዳምጡ