የኢትዮጵያ ወጣት አሁንም ታሪክ ሠሪ ነው!

የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብታዊ ፓርቲ ወጣት ክንፍ ድርጅተ (ኢሕአፓ ወክንድ) Ethiopian Peoples Revolutionary Party Youth League (EPRP YL) –  ወያኔ ለ27 ዓመት ከወራሪ ሃይል ባልተለየ ሁኔታ አገረንና ሕዝብን ሲያደባይና በአራቱም ማዕዘን የኢትዮጵያን ጠላቶች ተደግፎ ሕዝቧን ሊያጨራርስና አገሪቱንም ከፖለቲካ መልካ ምድር ሊፍቅ ያላሴረውና ያልፈፀመው ወንጀል ከቶ አይገኝም። ሆኖም ታሪካዊው የኢትዮጵያ ሕዝብ ይህን የወያኔ ወጥመድ ሰባብሮ አንድነቱንና ኢትዮጵያዊ ማንነቱን ዓለምን ባስደመመ ጠላቶቹን ባስደነገጠ ሁኔታ ይፋ አድርጓል።

በመሆኑም ዛሬም ወላድ በድባብ ትሂድ እንዲሉ የኢትዮጵያ ወጣት ለሀገሩ ሉዓላዊነትና ለወገኑ ስርየት ሲል ግንባሩን ለጥይት አካሉን ለጅራፍ አሳልፎ በመስጠት እያደረገ ያለው ትግል ወያኔን እንደ ቋያ እሳት እየለበለበ ወደ መቃብሩ ሳያወርድ የሚያቆመው የአጋዚ ወታደራዊ ሽብርና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አይኖርም። የውዳቂው ወታደራዊ አገዛዝ ሥርዓት አዳማቂ የሆኑ ክፍሎች የነዚያን (የ60ዎቹን) ብርቅዬ፤ ብሩህና ጀግና ትውልድ የትግል አርዓያነትና መስዋዕትነት ለማጣጣል ቀድመው የወደቁ መሪዎቻቸውን አስጨረሱ በሚል ሲከሱ ኖረዋል ፤ አሁንስ ወጣቱና መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የትግሉ ባለቤት ሆኖ እየከፈለ ያለውን መስዋዕትነት በማን ላይ ያላክኩ ይሆን?

እነሆ ዛሬ ወጣቱ ትውልድ ልክ እንዳለፉት ጀግኖች ወንድም እህቶቹ ያለመስዋዕትነት ትግል ያለትግል ነጻነት እንደማይገኝ ዘመን ያላስተማራቸውን ሃሳዊያን የሸፍጥ ክንብንባቸውን አውልቆ እርቃናቸውን አውጥቷቸዋል። ሕዝባዊ አመጹ ከጎንደር እስክ አምቦ፣ ከወልድያ እስከ ዓለማያ፣ ከደብረታቦር አስከ ሸዋ ሮቢት፣ ከሐረር እስከ ሻሸመኔ፣ ከባህርዳር እስከ ጅማ፣ ከለቀምት እስከ ደብረዘይት፣ ከድሬዳዋ እስከ ሱሉልታ እና ብዙ ሌሎች የኢትዮጵያ ከተሞችን ከማጥለቅለቁም በላይ ሕዝባዊ አመጹ እያደር እየሰፋና እየጎመራ የሕዝብ ትግል አቸናፊነቱን እያረጋገጠ በመሄድ ላይ ይገኛል። የህዝቡ ትግል አረመኔውን የወያኔ አገዛዝ ፤ብርክ አስይዞ፤ የሚይዘውንና የሚጥለውን አሳጥቶታል።

ታሪክ ዝም ብሎ አልተደገመም። ታድሷል እንጂ። በትግል ያለፉትን ወጣት ጀግኖች ሰንደቅ አንስቶ ፋሽስቶችን ተጋፍጦ ክቡር መስዋዕትነትን የተቀበሉትን የብዙ ሺ ወጣቶች ሞት አይፈሬ ወኔ ተላብሶ አምባገነኖችን በትግሉ በደሙ አጋልጧል። ዛሬም የወያኔን ቀፎነት ለዓለም ሁሉ እርቃኑን አውጥቶ አሳይቷል። ታሪክ ዳግም እየታደስ ነው። የትውልድን ወኔ ትውልድ አየተረከበ ነው። ያ መሬት ላራሹ! ትምሀርት ለሁሉም! ዳቦ ለተራበው! የሀይማኖት እኩልንተ ይከበር፤ የህግ የበላይነትና ይስፈን! የዲሞክራሲ መብቶች ይከበሩ! እያለ በከተማው በገጠሩ ድምጹን ያሰማ የነበረው ትውልድ፤ የሀገር ክብር ይጠበቅ!፤ ፋሽስታዊው መንግሥት ይውረድ!፤ የሕዝብ ሉዓላዊንት ይረጋገጥ! እያለ የተሰዋው ትውልድ ተኪ አፍርቷል።

ለሰላማዊ የሕዝብ ተቃውሞ አምባገነኖች የሚሰጡት ምላሽ ጥይት፤ ጭፍጨፋ መሆኑ ትናንትም ታይቷል ዛሬም በወያኔ ተደግሟል። በንጽሃን ወጣቶች የደም ጎርፍ የታጠበው ወያኔ በሕዝብ ትግል መወገዱ አይቅሬ ነው። ለኢትዮጵያ አንድነት መቆም፣ ለህዝብ እኩልነት መታገልና መሰዋዕት መሆን ቅዱስ ተልዕኮና አርበኝነት እንጂ፤ ጠባቦችና አገር አጥፊዎች እንደሚሉት ትምክህተኘንት አይደለም። በአንፃሩ ከፋፋይነት፤ ገንጣይነት፤ ፀረ-ኢትዮጵያዊነት ግን አፀያፊ ክህደትና ወንጀል መሆኑን በሚገባ እናውቃለን፤ ስለሆነም የተቀጣጠለውን ህዝባዊ ትግል በደማችን እየዋጀን ከሀዝቡ ጎን በመሆን እናስቀጥላለን ።
የኢሕፓ ወጣት ክንፍ ድርጅት (ኢወክንድ) ዓባላት የቀደምት የትግል ጓዶቻቸውን ፋና ይዘው ሕዝባዊ ትግሉን ለማፋፋም በውጪ አስፈላጊውን ድጋፍ በመስጠት በአገር ውስጥም ታግሎ በማታገልና አቅጣጫ በማስያዝ እየታገሉ እንደሚገኙ መግለጽ እንወዳለን። በዚህ አጋጣሚም ድርጅታችን የኢትዮጵያ ወጣቶችን ጀግንነትና ቁርጠኝነት ለሃገርና ለወገን ስርየት እየከፈሉት ላሉት መስዋዕትነት አድናቆቱንና የትግል አጋርነቱን ሲገልፅ በከፍተኛ ደስታና ወገናዊ ኩራት ነው።

ፀረ-ወያኔው ትግላችን በጋራ ይፋፋም!
እናቸንፋለን!

pdf_print