የወያኔ ድርጅቶች የበጀት ወጭ እንዳይመረመሩና ዘገባ እንዳይጠየቁ አመለከቱ

የፍኖተ ዴሞክራሲ ዜና – በኢትዮጵያ በተከሰቱ ልዩ ልዩ ችግሮች ምክንያት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተማሪዎች ከትምህርት ውጭ ሆኑ – የወያኔ የኢንዱስትሪ ፓርክ ሰራተኞች ጉልበታቸው እየተበዘበዘ መሆኑን ተናገሩ – የወያኔ የመንግስት ድርጅቶች ላደረጉት የበጀት ወጭ እንዳይመረመሩና ዘገባ እንዳይጠየቁ አመለከቱ።

በኢትዮጵያ ውስጥ በተከሰተው ድርቅና ረሃብ እንዲሁም በተለያዩ ቦታዎች ተቀጣጥሎ በነበረው ሕዝባዊ አመጽ የተነሳ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተማሪዎች ከትምህርት ውጭ መሆናቸው ታወቀ። በወያኔው የትምህርት ሚኒስቴር መረጃ መሰረት በ ታኅሣሥ 2008 የትምህርት ማስተማር ሂደት የተስተጓለባቸው ተማሪዎችና አስተማሪዎች ቁጥር 2.1 ሚሊዮን የነበረ ሲሆን በሰኔ 2008 ደግሞ ይኸው ቁጥር ወደ 4 ሚሊዮን ከፍ ብሎ እንደነበር ተነግሯል። በታኅሳስ 2009 ይኸው ቁጥር ወደ 3 ሚሊዮን ዝቅ ያለ ቢሆንም ይህም ቢሆን ከፍተኛ መሆኑ አጠራጣሪ አይደለም ተብሏል። በአንዳንድ አካባቢዎች የጸጥታው ሁኔታ ለተማሪዎች የትምህርት መስተጓጎል እንደምክንያት ሲጠቀስ ድርቅ ባጠቃቸው አካባቢዎች ደግሞ የውሃ እጥረትና የምግብ አለመኖር ዋና ምክንያቶች መሆናቸውንየዩኒሲኤፍ ባለሙያዎች ይናገራሉ። በተሰበሰበው መረጃ መሰረት በድርቁ አካባቢዎች 76 ከመቶ የሚሆኑት ተማሪዎች ውሃ የማያገኙ መሆናቸው ሲታወቅ 46 ከመቶ የሚሆኑት ትምህርት ቤቶች ደግሞ የተሟላ የመጸዳጃ አገልግሎት የሌላችው መሆኑ ታውቋል። ወደ 2 ሚሊዮን የሚሆኑ ተማሪዎች ህይወታቸው በእርዳታ ምግብ ላይ የቆየ ሲሆን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተማሪዎች ወላጆች ለልጆቻቸው የትምህርት መሳሪያ ለመግዛት አቅም የሌላችው መሆኑም ተነግሯል።

የወያኔ አገዛዝ የኢንዱስትሪ ፓርክ በሚል በየቦታው ያቋቋማቸው ተቋሞች የሰራተኛ ጉልበት መበዝበዣ መሆናቸውን ሰራተኞቹ በምሬት እየተናገሩ ይገኛሉ። ሠራተኞቹ ለተለያዩ የዜና ምንጮች በገለጹት መሰረት የሚከፈላቸው ደሞዝ በጣም አነስተኛ በመሆኑ ለኑሮ የማይበቃቸው መሆኑን ገልጸዋል። በዚህ ተቋም ውስጥ በመስራታቸው የስራ ተመክሮ ቢያገኙም ለረጅም ሰዓታት እየሰሩ መሆናቸውንና የሚከፈላቸው ገንዘብ ከቀለባቸው ተርፎ ለቤት ኪራይና ለትራንስፖርት በቂ እንዳልሆነ ገልጸዋል። ከህንድና ከሌሎች አገሮች ኩባንያዎቻቸውን ነቅለው ወደ እነዚህ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ያመጡት ባለሀብቶች ለሰራተኞች አነስተኛ ደሞዝ በመክፈልና ዋጋቸው ዝቅ ያሉ እቃዎችን በማመረትና በመሸጥ በርካታ ትርፍ ለማካበት በመሆኑ ይህ ሁኔታ የሚጠበቅ ነው ያሉ ክፍሎች ሰራተኞች ተገቢ ክፍያ እንዲያገኙ መታገል እንዳለባቸውና ሌላውም ህብረተሰብ መተባበር እንዳለበት ያሳስባሉ።

የወያኔ አገልጋይ የሆኑ በርካታ የመንግስት ድርጅቶች የወጭ ዘገባ ለማቅረብ ፍላጎት እንደሌላቸው ታወቀ። ባቀረቡትና በጸደቀላችው በጀት መሰረት ከገንዘብ ሚኒስቴር በየወሩ ገንዘብ የሚወስዱ ድርጅቶች የወጭ ሪፖርት ለማቅረብ ፈቃደኛ ካለመሆናቸውም ሌላ ሪፕርት ለማቅረብም ሆነ ኦዲት ለመደረግ እንዳይገደዱ ማመልከቻ ያቀረቡ መሆኑ ተነግሯል። የምንሰራው ስራ ሚስጥራዊነትን ስለሚያጋልጥ ዘገባ ማቅረብ አይገባንም በማለት ደብዳቤ ከጻፉ ድርጅቶች መካከል የመከላከያ፤ የውጭ ጉዳይ፣ የብሔራዊ ጸጥታ ክፍል፤ እና የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የሚገኙበት ሲሆን ሁሉም የወያኔ ቡድን የአፈናና የጭቆና መሳሪያዎች እንዲሁም የወያኔ ቡድን ጥቅም አስጠባቂዎች ከመሆናቸው ሌላ በሙስና የተጨማለቁ መሆናችው ይታወቃል።

ከፍኖተ ዴሞክራሲ የኢትዮጵያ አንድነት ድምጽ ዝርዝር ዜና ያዳምጡ