የጎንደር ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች በአግአዚ ታፈሱ፣ በክፍለሀገሩ የተለያዩ ስፍራዎች ጦርነት አለ፣ የታገቱት 20 አውሮፕላኖች ተለቀቁ፣ የወያኔና የቻይና ወታደራዊ ፍቅር፣ ከየመን ወደጂቡቲ የተፈናቀሉት ስደተኞች

ፍኖተ ዴሞክራሲ የኢትዮጵያ አንድነት ድምጽ ሬዲዮ (ኅዳር 16 ቀን 2009 ዓ.ም.) – በጎንደር ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች በአግአዚ ጦር ታፍሰው ታሰሩ፤ በተለያዩ የጎንደር ክፍሎች ጦርነት መኖሩ ተሰማ #በጋምቤላ ታግተው የነበሩ የትናንሽ አውሮፕላን አብራሪዎች ተለቀው ወደ ደቡባዊ አፍሪካ ተጓዙ – ቻይናና የወያኔ አገዛዝ በወታደራዊ ጉዳዮች ጠንካራ ግንኙነት ለማድረግ ተስማሙ – ከየመን ተፈናቅለው ወደ ጂቡቲ የተዛወሩ ስደተኞች ያለውዴታቸው ለወያኔ ሊሰጡ ነው ተባለ።

በጎንደር ዩኒቨርስቲ የእንስሳት ሳይንስ ፋርማሲ ኮሌጅ የሶስተኛ ና የአራተኛ ዓመት ተማሪዎች ትምህርት በማቆማቸው ምክንያት ተወስደው የታሰሩ መሆናችው ታውቋል። ለተማሪዎቹ ተቃውሞ ምክንያት የሆኑት ጉዳዮች የተለያዩ ሲሆኑ ብቁ አስተማሪዎች ያልተመደበላቸው መሆኑ ከምክንያቶች ውስጥ አንደኛው መሆኑ ታውቋል። በተያያዘ ዜና በጎንደር ሳንጃ ከተማ አካባቢ በጎበዝ አለቃ የሚመራ ሕዝባዊ ጦር በወያኔ አግአዚ ጦር ላይ ጥቃት ፈጽሞ ጉዳት ማድረሱንና እንዲሁም በቋራም ሕዝባዊ ጦሮች እየተንቀሳቀሱ መሆናቸው ይወራል።

በጋምቤላ ታግተው የነበሩና ቪንቴጅ ኤር ራለይ በሚል ስም የሚታወቁ የትናንሽ ሲቪል አውሮፕላኖች አብራሪዎች ተለቀው ጉዟቸውን ወደ ደቡብ አፍሪካ የቀጠሉ መሆናቸውን የዜና ምንጮች ገልጸዋል። የወያኔ አገዛዝ ሰዎችን ያገተበት ምክንያት የአየር ወሰንን አለፈቃድ በመጣሳቸው መሆኑን ጠቅሶ ከማክሰኞ ኅዳር 13 ቀን ጀምሮ ከጋምቤላ አውሮፕላን ማረፊያ እንዳይወጡ ያደረገ መሆኑን ገልጿል። ሰዎችን ለማስፈታት በርካታ የምዕራብ አገሮች ዲፕሎማቶች ከፍተኛ ጥረት ማድረጋቸው ይታወሳል።

ቻይናና የወያኔን አገዛዝ በወታደራዊ መስክ ያላቸውን ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር እርምጃ የተወሰደ መሆኑን ቻይና ዴይሊ የተባለው ጋዜጣ በሐሙስ ኅዳር 15 ቀን ዕትሙ ገልጿል፡፤ በቅርቡ የቻይናው የሚሊቴሪ ኮሚሽን ምክትል መሪ በኢትዮጵያ ያደረጉት ጉብኝት ፍሬያማ መሆኑን ጋዜጣው ጠቅሶ በወታደራዊ ስልጠና በህክምና፤ በሰላም አስከባሪ ኃይል ትብብር ወዘተ… በይበልጥ ለመተባበር ከወያኔ ጋር ስምምንት ላይ መደረሱን አብራርቷል። ሕዝባዊ አመጽን በማፈንና በመቆጣጠር በኩል አምባገነኑ የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ ያለውን ተመክሮ ከማስተላለፍ አልፎ በተግባር አብሮ ለመንቀሳቀስ እቅድ ሳይኖረው አይቀርም የሚል ግምት ተፈጥሯል።

የእርስ በርሱ ጦርነት በፈጠረው ችግር ምክንያት ከየመን ወደ ጁቢቱ ተዛውረው የነበሩ ቁጥራቸው በመቶ የሚቆጠር ኢትዮጵያውያን ወደ ኢትዮጵያ በግዴታ እንዲመለሱ የታቀደ መሆኑን አንዳንድ ምንጮች ገልጸዋል። በግዴታ ወደ ኢትዮጵያ የሚመለሱ ከሆነ በወያኔ አገዛዝ ቢያንስ የእስራት እርምጃ ሊወሰድባቸው እንደሚችል ከፍተኛ ስጋት አለ። ስደተኞችን ባሉበት ለማቆየት ጉዳዩን ለሰብአዊ መብትና ለዓለም አቀፍ ድርጅቶች ከማሳወቅ ጀምሮ ማናቸውንም ጥረቶችን እንዲደርጉ ለኢትዮጵያውያን ጥሪ ቀርቧል።

ፍኖተ ዴሞክራሲ የኢትዮጵያ አንድነት ድምጽ ሬዲዮን ያዳምጡ

ክፍል አንድ

ክፍል ሁለት

To Listen PART 1: http://www.finote.org/TodayPart1.mp3

To Listen PART 2: http://www.finote.org/TodayPart2.mp3