ፓኪስታን ከኢትዮጵያ ቦለቄ እንዳይገባ መከልከሏ፣ የወያኔና የሱዳን የጦር አለቆች ምክክር

ፍካሬ ዜና (መጋቢት 24 ቀን 2009 ዓ.ም.)  – የወያኔ አገዛዝ ሀገሪቱ በወታደራዊ አዋጅ ስር እንድትቆይ በድጋሚ ማወጁ አነጋጋሪ መሆኑ ታወቀ – ፓኪስታን ከኢትዮጵያ የምታስመጣው ቦለቄ ወደ አገሯ እንዳይገባ ከለከለች – የወያኔና የሱዳን የጦር አለቆች ምክክር ማድረጋቸው ታወቀ – የአልሸባብ መጠናከር የሰላም አስከባሪ ኃይሉን ሚና ጥያቄ ውስጥ አሰገባ ተባለ – በርሀብ እየተሰቃዩ የሚገኙ ወገኖች ቁጥር እየጨመረ መሆኑ ድንጋጤ ፈጥሯል።

የወያኔ አገዛዝ ሀገሪቱ በወታደራዊ አዋጅ ስር እንድትቆይ በድጋሚ ማወጁ አነጋጋሪ መሆኑ ታወቀ

ባሳለፍነው ሳምንት መገባደጃ ላይ ወያኔ ለስድስት ወራት በይፋ ያወጀውን ወታደራዊ እስቸኳይ አዋጅ በአራት ወራት ማራዘሙን አውጇል፡፡ አብዛኛው ሕዝብ ጠብቆት የነበረው ምናልባት አዋጁ ተነስቷል ቢባል እንኳ ወያኔ አፍኖ ማሰሩን፣ በአልሞ ተኳሾች ንፁሀን ዜጎችን መግደሉን፣ ካለ ፍርድ ቤት ትእዛዝ መኖሪያ ቤቶችን መፈተሹን፣ ወዘተ. መቀጠሉ የማይቀር ነው የሚል ነበር። በተለያዩ መድረኮች ተነስቶ የነበረውን ሕዝባዊ ተቃውሞ ማቆም መቻሉንና ለወደፊትም እንዳይከሰት ማድረጉን እየለፈፈ ባለበት ይህ የአስቸኳይ ወታደራዊ አዋጅ መራዘሙ የወያኔን ቀላማጅነት ማጋለጡን በርካቶች ያስረዳሉ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በተለያዩ አካባቢዎች ሕዝቡ ወያኔን ለማስወገድ የሚያደርገውን ትግል ወደ ሙሉ ህቡዕነት በመለወጡ ወያኔ አነፍናፊዎቹ ሊደርሱበት ባለመቻላቸው በተለያየ እርከን ላይ የሚገኙት የወያኔ ሹሞች በስጋት እየራዱ መሆናቸውን ማወቅ ተችሏል፡፡ የፖለቲካ ተንታኞች እንደሚሉት ይህ የተጀመረው ሕዝባዊ ተቃውሞ ወያኔን ካላስወገደ እንደማይቆም የሚታወቅ ሲሆን ይህ የወያኔ የአፈና አስቸኳይ አዋጅም እስከ ወያኔ እለተ-ሞት ድረስ ሊዘልቅ እንደሚችል የጠነከረ ግምታቸውን ይሰነዝራሉ፡፡

ፓኪስታን ከኢትዮጵያ የምታስመጣው ቦለቄ ወደ አገሯ እንዳይገባ ከለከለች

የተለያዩ የቅባት እህሎችና ጥራጥሬዎች ከሚገዙትና ከፍተኛ የውጪ ምንዛሪ ከሚያስገኙት ሀገሮች መካከል አንዷ ፓኪስታን መሆኗ የሚታወቅ ነው፡፡ በቅርቡ ከኢትዮጵያ የሚላከው አደንጓሬ በበሽታ የተበከለ በመሆኑ ወደ ሀገሯ እንዳይገባ ማገዷ ታውቋል፡፡ ይህ ሁኔታ ዜሮ ለሆነው ለውጪ ምንዛሪ እጥረት ሌላ ጦስ መሆኑን የምጣኔ ሀብት አዋቂዎች አስተያየታቸውን ይሰነዝራሉ፡፡

የወያኔና የሱዳን የጦር አለቆች ምክክር ማድረጋቸው ታወቀ

ባሳለፍነው ሳምንት ወያኔ ከሱዳን ጋር በካርቱም ምክክር መጀመሩ ቀደም ብለው ሲደረጉ ከነበሩት የተለየ ጉዳይ መኖሩን የፖለቲካ አዋቂዎች አስተያየታቸውን እየሰጡ ነው፡፡ በቅርቡ ግብፅና ሱዳን የጋራ ስብሰባ በማካሄድ የድንበር ንትርካቸውን በድርድር ለመፍታትና የጋራ ወታደራዊ ስምምነት መፈጸማቸውን ተከትሎ ወያኔ ግብፅ በረገጠችበት መሬት ሁሉ በመገኘት እያቀረበ ካለው ተማጽኖ ጋር እንደሚገናኝ የጠነከረ አስተያየታቸውን ይሰነዝራሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በጎንደርና በአካባቢው እየተጠናከረ የመጣውና በሰፊው እየተነገረለት የሚገኘው በጎበዝ አለቆች አማካይነት እየተካሄደ ያለው የመሣሪያ ትግል ለወያኔ ከፍተኛ እራስ ምታት በመሆኑ ከሱዳን ጋር በጋራ በሕዝቡ ላይ ለመዝመት የተሸረበ ሴራ መሆኑን መረዳት እንደሚቻል እነዚሁ የፖለቲካ ተንታኞች ያስረዳሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ወያኔ ሀገሩንና ማንነቱን ለማስከበር የተነሳውን ሕዝብ ለመምታት በየጊዜው ከሚያዘምተው ጦር እያፈነገጡ የሕዝቡን ሠራዊት የሚቀላቀሉት ቁጥር እየጨመረ በመሄዱ ይህን ሁኔታ ከሱዳን ጋር በመሆን በጋራ ለመምታት ያለመ ሴራ መሆኑ ሊታወቅ ይገባዋል የሚሉ ብዙዎች ናቸው፡፡

የአልሸባብ መጠናከር የሰላም አስከባሪ ኃይሉን ሚና ጥያቄ ውስጥ አሰገባ ተባለ

የሶማሌው አሸባሪ ኃይል ይበልጥ መጠናከር በሰላም ማስከበር ስም ሶማሌ ውስጥ በመንቀሳቀስ የሚገኙ የጎረቤት ሀገራትን ሚና ጥያቄ ውስጥ መጨመሩ ተገለጸ፡፡ ወያኔ ከዛሬ አስር አመት በፊት በሶማሌ ውስጥ አልሽባብ የተባለውን አሸባሪ ቡድን ለመዋጋት ከማንኛቸውም ጎረቤት አገር ቀደም ብሎ መግባቱን ለሰላም ማስከበር እንዳልሆነ የሚከራከሩ ወገኖች ወታደሮቹን የላከው ለአሜሪካ ተቀጥሮ መሆኑን አበክረው ያስረዳሉ፡፡ እስከ ዛሬ ድረስ የታየው አልሽባብ ይበልጥ እየተጠናከረና ፀረ-የትግሬ ወራሪ ጦር አቋም በመያዙ የአብዛኛውን የሶማሌ ሕዝብን ድጋፍ መሸመት መቻሉን ብዙዎች ይገልፃሉ፡፡ ሶማሌ የሚገኘው የወያኔ ጦር አዛዦች በአንድ በኩል ከአሜሪካ አልሸባብን ለመዋጋት የአሜሪካን ዶላር ሲከፈላቸው፣ በተፃራሪው ደግሞ እነዚሁ የወያኔ ከፍተኛ መኮንኖች ለአልሸባብ የጦር መሳሪያ እንደሚቸበችቡ በተለያዩ አጋጣሚዎች እየታጋለጠ መሆኑ የሚታወቅ ነው፡፡ ይህንን የወያኔን መሰሪ ዓላማ በቅጡ የሚያውቁት በቅርቡ የተመረጡት የሶማሌ ጠቅላይ ሚንስትር ለወያኔ ጀርባቸውን እየሰጡ መሆናቸው ለወያኔ የአሜሪካ ዶላር ምንጭ የሆነውንና ከይስሙላ ጦርነት የሚገኘውን ገቢ ሳያነጥፈው እንደማይቀር ብዙዎች ይተነብያሉ፡ ፡ በዚህ ባሳለፍነው ሳምንት የትረምፕ መንግስት አልሽባብን በሰው- አልባ ተዋጊ አውሮፕላን ለመደብደብ ያሳለፈው ውሳኔ ከየአቅጣጫው ውግዘት እያደረሰበት መሆኑ የሚታወቅ ነው፡፡ በርሀብ እየማቀቀ፣ በነፍስ ግቢና በነፍስ ውጪ ስቃይ ላይ ባለበት በሰው-አልባ ተዋጊ አውሮፕላን የሚደረግ ጦርነት ሸሽቶ የማያመልጠውን ሕዝብ ለመጨፍጨፍ ካልሆነ በስተቀር ፋይዳው ከንቱ መሆኑን በርካቶች ስጋታቸውን እየገለጹ ነው፡፡

በርሀብ እየተሰቃዩ የሚገኙ ወገኖች ቁጥር እየጨመረ መሆኑ ድንጋጤ ፈጥሯል

ወያኔ በርሀብ ለተጠቁት ወገኖች ምንም ሳያደርግ መቆየቱ የሚታወቅ ሆኖ ሳለ በቂ የምግብ ክምችት እንዳለ በማስመሰል ባዶ ፕሮፓጋንዳ ሲረጭ ከቆየ በኋላ የዓለም አቀፍ ለጋሾች እይታ ወደ ደቡብ ሱዳንና ወደ ሶማሌ ከሆነ በኋላ ጫጫታ ማሰማት ቀጥሏል። በዚህም ምክንያት በርሀብ የተጠቁ ወገኖቻችን ተገቢው እርዳታ ሳይደረግላቸው መቆየታቸው የሚታወቅ ነው፡፡ ለዚህ ጉዳይ ቅርበት ያላቸው ወገኖች እንደሚሉት ወያኔ የእህል ክምችት እንዳለው በተደጋጋሚ ይገልጽ የነበረው ለተባበሩት መንግስታት የምግብ ፕሮግራምና ለሌሎች ለጋሽ ድርጅቶችና ሀገራት በሽያጭ ለማቅረብ የገበያ ቀዳዳ ለማግኘት ከሚል የነበረ ሲሆን ይህም ሣይሳካ እንደቀረ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ይህ በእንዲህ እያለ በርሀብ የተጎዱ ወገኖቻችን ቁጥር በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ በአስደንጋጭ ሁኔታ እየጨመረ በመሆኑ ከፍተኛ የሆነ ቀውስ ሊያስከትል እንደሚችል ብዙዎች ያስረዳሉ፡፡ የበልግ ዝናም ዘግይቶም ቢሆን ይጀምራል የሚል ያንዳንዶች ተስፋ ቢኖርም የማይጨበጥ ሆኗል፡፡ በዚህ ሳቢያ ሙሉ በሙሉ ቦረና፣ ጉጂ፣ ደቡብ ኦሞ፣ ምሥራቅ ሐረርጌ፣ ወይና ደጋና ቆላማ የአርሲና የባሌ አካባቢዎችን፣ ቆላማና ወይና ደጋ ሰሜን ሸዋን፣ ወሎንና አፋርን ወዘተ. ረሃቡ እየወረረ መሆኑን መረዳት ተችሏል፡፡

ዝርዝር ዜና ከፍኖተ ዴሞክራሲ የኢትዮጵያ አንድነት ድምጽ ሬዲዮ  ያዳምጡ