በዲሲና አካባቢው ካሉ የኢሕአፓ አባላትና ደጋፊዎች የተሰጠ መግለጫ

የተከፋፈለ መጠቃቱ አይቀሬ ነዉ _

(ጥቅምት 2008 ዓ.ም.) እንደሚታወቀዉ ድርጅታችን ኢሕአፓ የታገለለትና ብዙ ዋጋ የከፈለለት አሁንም የሚታገልለትና የሚከፍለልት ኢትዮጵያዊዉ በዉጪም በዉስጥም አንድነቱን ጠብቆ አንዲኖር ነዉ።

ትላንትም ሆነ ዛሬ፣ ነገም ሆነ ወደፊትም ድርጅታችን ኢሕአፓ በሃይማኖት ዉስጥ ጣልቃ አልገባም፤ አይገባምም። ለዚህም ነዉ በተለይ ባለፉት 24 ዓመታት በስልጣን ላይ የተቆናጠጠዉ የወያኔ ዘረኛ አገዛዝ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክህነት ሆነ በኢትዮጵያ እስልምና ሃይማኖት ዉስጥ ፈርፍሮ ገብቶ በቅድሚያ በሲኖዶሱ አሁን ደግሞ በመጅሊሱ ላይ ሲያካሄድ የቆየውን የመጠቅለል ተግባር በፅኑ የምንቃወመዉ።

አንደሚታወቅዉ በህዝብ የተቋቋሙና የሕዝብ ንብረት የሆኑ ተቋሟትን አብያተ ክርስትያናትን ጨምሮ ወያኔ በቁጥጥር ለማስገባት የሚያደርገዉን እንቅስቃሴ ህብረተሰቡ ጠንቅቆ አንዲጠብቅ ስናስጠነቅቅ ባጅተናል። እነሆ በዋሽንግተን ዲሲ ቀዳሚ በተክርሲቲያን አንዱ በሆነችዉ በደብረሰላም ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን ሠሞኑን እየታዩ ያሉት አስደንጋጭና አሳዛኘ ድርጊቶች እንደ አንድ ሃላፊነት እንዳለዉ ሃገራዊ ድርጅት በጥሞና እየከታተልነዉ እንገኛለን።

ከመጀመሪያዉ በዉይይትና በህግ ደንብ መሠረት ሊፈቱ የሚችሉ ቀላል ጉዳዮች ተለጥጠዉ እዚህ በመድረሳቸዉ የተሰማንን ሀዘኔታ እየገለጥን፣ ከዋናዉ ጉዳይ አዉጥተዉ በየዋህነት በተታለሉ ሆነ በፀረኢሕአፓነት ባሉ ግለሰቦች የሚናፈሰዉን አሉባልታ በከፍተኛ ደረጃ እናወግዛለን። ከነገረቀደም ኢሕአፓ ማለት ከሠማይ የተንጠባጠበ ምትሃታዊ ሃይል ሣይሆን ኢትዮጵያዊ ልጆች ያቋቋሙት ዘርና ሃይማኖት ሣይለያቸዉ ለሀገር የሚታገሉበት ድርጅት መሆኑ መታወቅ አለበት። አባላቱ ከተለያየ ዘር የተሠበሠቡ አንደመሆኑ መጠን የተለያየ ሃይማኖት አማኞችም ናቸዉና አንደየ እምነታቸዉ፤ አምነታቸዉን ጠብቀዉ ባሻቸዉ ቤተ እምነት የመሄድ ና የመሣተፍ መብታቸዉ የተጠበቀ መሆኑን አስረግጠን ለማሳወቅ እንወዳለን።

ወደ ቁም ነገሩ ስንመለስ ሠሞኑን የተካሄደዉና እየተካሄደ ባለዉ በቅድስት ማርያም ችግር ዉስጥ ኢሕአፓ አለበት የሚባለው ወሬ መሰረተ ቢስ መሆኑን በአጽንኦት እየገለጽን እንደሚወራዉ አንድም የኢሕአፓ አባል የሆኑ ግለሰብ በቦርዱ ዉስጥ በአባልነት የሌለበት መሆኑን ግልጽ ማድረግ እንወዳለን። ቢኖር ኖሮ አለ ለማለት የምናፍርበት ወይም የምንፈራው ምድረዊ ሃይል የለም።

መግለጫችንንም ስንቋጭ ፣ የቤተክርስትያኗ ችግር ሊፈታ የሚችለዉ በዉይይትና በአባላቱ የተሳትፎ ዉሳኔ፤ እንዲሁም በዕርቅ ነዉ ብለን ሃሣባችንን ለመስጠት ወደኋላ አንለም። ከላይ ለመግለፅ እንደሞከርነዉ የተከፋፈለ መጠቃቱ አይቀሬ ነዉና ወያኔ የተባለ ተምች በግርግር ገብቶ ቅራኔ አባብሦ ቤተ ክርሲቲያኗንም ሆነ ሌላ ኢትዮጵያዊ ተቋማትን እንዳይወር አጥብቀን እንደምንከላከልና ምዕመናኑንም ይህን ተገንዝቦ በስነስርዓት ያሻዉን የመወሰን መብቱ የተጠበቀ ነዉ እንላለን።

በመጨረሻም በፀረ ኢትዮጵያዉ ወያኔ ና በኢሕአፓ መካከል ያለዉ የማይታረቅ ቅራኔ ሥለሆነ በኢሕአፓ በማይመለከተው የሚቀርብበት ክስ አንዱ፣ በራሱ በወያኔ ሌላዉ ደግሞ ኢሕአፓን ማጥፋት ማለት ወጣቱን በጅምላ ጨፍጭፎ ሬሣ መራመድ ነዉ ሲሉ በነበሩ የመንግስቱ ሃ/ማርያም አንጋሽና አንጋች ካድሬዎችና አብዮት ጠባቂዎች ሲሆን ዛሬ ያለንሰሃም ቢሆን (የቤ/ክርሲቲያኗ አባል መሆን ወይም መጠምጠም መብታችዉ ቢሆንም) የራሳቸዉን ቁርሾ ለመወጣት በኢሕአፓ ላይ የሚያደርጉትን ዘመቻ ህብረተሰቡ እንዳይቀበለዉ በትህትና እንገልፃለን