ወቅታዊ ዜና

መስከረም 4 ቀን 2009 ዓ.ም.(ከፍኖተ ዴሞክራሲ የኢትዮጵያ አንድነት ድምጽ ሬዲዮ):

ርዕሰ ዜና: ወያኔ በኮንሶ ሕዝብ ላይ ጭፍጨፋ አካሄደ – አመጽን ለመከላከል ወያኔ ለመምህራንና ለተማሪዎች ሥልጠና ሊሰጥ ነው ወላጆችንም አሳትፋለሁ ይላል – በጎንደር ወጣቶችን በመጠቆም ተግባር ተሰማርተው የነበሩ ከፍተኛ መገለል እየደረሰባቸው ነው – የዩናይትድ ስቴትስ ምክር ቤት አባላት ወያኔን የሚያወግዝ የውሳኔ ረቂቅ አቀረቡ::

ዝርዝር ዜና:

የወያኔ አግአዚ ጦር በኮንሶ ብሔረሰብ ላይ ያካሄደው ጭፍጨፋ ከፍተኛ መሆኑን ከአካባቢው የሚደርሱን ዜናዎች ይጠቁማሉ። ብሔረሰቡ የማንነት ጥያቄ በማንሳቱና ለብቻ ክልል እንዲሰጠው በመጠየቁ ብቻ የወያኔ የጸጥታ ኃይሎች ከፍተኛ ጥቃት ሰንዝረው ከስድስት በላይ በሆኑ ቀበሌዎች ያሉትን የመኖሪያ ቤቶች አቃጥለው ከ60 በላይ የሚሆኑ ዜጎች ገድለውና ከ100 በላይ በሚሆኑት ላይ ከፍተኛ የአካል ጉዳት ያደረሱ መሆኑ ይነገራል። ከ30 በላይ የሚሆኑ ዜጎች መዳረሻቸው ጠፍቷል። 1200 አባላት የሚገኙበት 400 ቤተሰቦችም ተሰደው ቦረና ዞን ውስጥ ገብተዋል ተብሏል። ከ160 የአካባቢው ፖሊሶች 156-ኡ በአግአዚው ጦር መሳሪያ የተነጠቁ ሲሆን የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችና ሌሎች አገልግሎቶች ተዘግተዋል። ሠራተኞች ደሞዝ የተከፈላቸው ከአራት ወራት በፊት መሆኑም ተነገሯል።

የወያኔ አገዛዝ የዘንድሮው የትምህርት ዓመት የሚጀመርበትን ወቅት ለማስረዘም የወሰነ መሆኑና በዚህም የአንደኛ፣ የሁለተኛ ደረጃ እና የዩኒቨርስቲም መምህራንና እንዲሁም ከስምንተኛ ክፍል ጀምሮ እስከ ዩኒቨርስቲ ያሉ ተማሪዎችን ሥልጠና ለመስጠት አቅዷል። በልዩ መድርክም የተማሪዎች ወላጆችን ለማሳተፍ እቅድ አለው ተብሏል። ይህ ፕሮግራም የተዘጋጀው በትምህርት ይዘትና ጥራት ላይ ለመወያየት ነው በማለት የአገዛዙ ባለሥልጣናት ይግለጹ እንጅ ዋናው ዓላማው እየተቀጣጠለ የመጣው ሕዝባዊ አመጽ ወደ ትምህርት ተቋሞች ተዛምቶ የአገዛዙን ውድቀት እንዳያፋጥን በመፍራት ቅስቀሳና ማስፈራሪያ ለመስጠት መሆኑ ታውቋል። ተማሪዎች ትምህርት ቤታቸውን እንደመሰባሰብያ በመውሰድ ግምባር ቀደም ተቃውሞ በማድረግ የሚታወቁ ሲሆን ዘንድሮም በተመሳሳይ መልኩ አመጹ በተማሪዎች አማካይነት ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚችል ተገምቷል። በሥልጠናው ወቅት ተቃውሞን በዝምታ አድማ ለማሳለፍ ስምምነት የተደረገ ሲሆን ትምህርት ቤቶች በሚከፈቱበት ሰዓትም አመጹ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል እየተነገረ ይገኛል።

በጎንደር የተወሰነ ገንዘብ ከወያኔ እየተሰጣቸው ወጣቶችን ከየቤታቸው በመጠቆም ለወያኔ ከፍ ያለ አገልግሎት ሲሰጡ የነበሩ ጠቋሚዎች በአካባቢው ሕዝብ እንደ ባንዳ እና እንደ ከሀዲ እየታዩ በቤተሰቦቻቸው ጭምር ከፍተኛ ተጽእኖ ስለተደረገባቸው አንዳንዶቹ ይቅርታ በመጠየቅ ሕብረተሰቡን ሲቀላቀሉ ሌሎቹ ከተማውን ለቀው እየወጡ መሆናቸውን ከአካባቢው የሚደርሱ ዜናዎች ይጠቁማሉ። በተያያዘ ዜና የወያኔ የመሣሪያ ማስፈታት እቅድ ሕዝቡ በብርቱ እየተቃወመው ያለ መሆኑንና እቅዱ ተግባራዊ ቢደረግ ለመዋደቅ ዝግጁ መሆኑን እየተናገረ ይገኛል።

ማክሰኞ መስከረም 3 ቀን 2009 ዓ.ም. የዩናይትድ ስቴትስ ኮንግሬስ የምክር ቤት አባላት በሆኑት በክሪስ ስሚዝ፤ በኬት ኤሊሰንና በማይክ ኮፍማን አማካይነት ውሳኔ 861 የሚል ርዕስ የተሰጠው አንድ የሕግ ረቂቅ ቀርቧል። የሕጉ ረቂቅ አሁን በኢትዮጵያ ውስጥ በወያኔ አገዛዝ እየተካሄደ ያለው የመብት ረገጣና የፖለቲካ አለመረጋጋት ሁኔታን ይመለከታል። ረቂቅ ውሳኔው በአማራውና በኦሮሞ አካባቢዎች በወያኔ አገዛዝ የተካሄዱትን ጭፍጨፋዎች የሚያወግዝ ሲሆን አገዛዙ ነጻ፤ ገለልተኛ፤ ግልጽና ተዓማኒነት ያለው ምርመራ እንዲያካሂድ እንዲሁም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የራሱን የመርማሪ ቡድን ለማስገባት የጠየቀው ጥያቄ ተግባራዊ እንዲሆን ይጠይቃል። በተጨማሪም ረቂቁ ውሳኔ፤ የአሜሪካ መንግሥትም ለወያኔ አገዛዝ የሚሰጠውን እርዳታ እንዲመረምር ያሳስባል። በውጭ የሚገኙ የስብዓዊ መብት ተከራካሪ ድርጅቶችና የሲቪክ ማህበራት በጋራ ባወጡት መግለጫ ይህንኑ የኮንግሬስ የሕግ ረቂቅ ጥሩ ሀሳብ ነው በማለት ድጋፋቸውን ሰጥተዋል።

To Read:
To Listen PART 1
To Listen PART 2