የወያኔ አፈና ቀጥሏል፣ 2 ግብፃዊያን ታሰሩ፣ ሌላም ወቅታዊ ዜና

ከፍኖተ ዴሞክራሲ የኢትዮጵያ አንድነት ድምጽ ሬዲዮ (ጥቅምት 28፣ 2009 ዓ.ም.) – የወያኔ አገዛዝ የሚያካሂደው ግድያና የጅምላ እስራት ቀጥሏል – ሁለት ግብጻውያን ተይዘው መታሰራቸው ታወቀ –  መርካቶ አሜሪካን ግቢ በከፍተኛ ዋጋ በጨረታ የተሸጠው መሬት አነጋጋሪ ሆነ –  በአውስትራሊያ የሚኖሩና አገዛዙን የተቃወሙ የሱማሌ ኢትዮጵያውን ቤተሰቦች በወያኔ ታሰሩ –  እስክንድር ነጋ ይፈታ የሚል ዘመቻ በሂውማን ራይትስ ዎች እየተካሄደው ነው –  የአፍሪካ ህብረት ሊቀ መንበር የኢትዮጵያ ችግሮች በውይይት መፈታት አለበት አሉ –  ሊጋተም ኢንስቲዩት ዜጎቻቸው ብልጽግና ደስታ ካሉባቸው የዓለም አገሮች መካከል ኢትዮጵያን በመጨረሻዎቹ አገሮች ተርታ ላይ መደባት –  በመንግሥታቸው ላይ ተቃውሞ ያደረጉ የደቡብ ሱዳን ተማሪዎች በወያኔ ታስሩ።

የወያኔ አገዛዝ በሕዝብ ላይ በጫነው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሽፋን በየቦታው የሚያካሂደው ግድያና የጅምላ እስራት በሰፊው የቀጠለ መሆኑ በየጊዜው ከተለያዩ አካባቢዎች የሚደርሱት ዜናዎች ይገልጻሉ። ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ በምዕራብ አርሲ የወያኔ አግአዚ ጦር አባላት በሌሊት ድቅድቅ ጨለማ አንድ ቤት ውስጥ ገብተው ሶስት ወንድማማቾችን ገድለው የሄዱ መሆናቸው ከተገኘው መረጃ ለማወቅ ተችሏል። በጎንደርና በጎጃም ክፍለ ሀገሮችም የጅምላ እስራቱና ግድያው በሰፊው እየተካሄደ መሆኑ ይነገራል።

ባሳለፍነው ሳምንት መጀመሪያ ላይ ሁለት ግብፃውያን አዲስ አበባ ውስጥ መታሰራቸውን ለወያኔ አገዛዝ ቅርብ ከሆኑ ምንጮች የተገኘው ዜና ይገልጻል።፡ ሁለቱ ግብፃውያን የታሰሩበት ምክንያት ምን እንደሆነ እስካሁን የተሰጠ ይፋ መግለጫ ባይኖርም ግብጽ ከሕዝባዊ አመጹ ጀርባ አለበት ከሚለው የወያኔ ውንጀላ ጋር ሳይያዝ አይቀርም የሚል ግምት አንዳንድ ወገኖች ይሰነዝራሉ። ከታሰሩት መካከል አንደኛው ጣሀ መንሱር የሚባል ሲሆን የራዲሰን ብሉ ሆቴል ምክትል አስተዳዳሪ መሆኑ ታውቋል፡፡ የሁለተኛው ግብፃዊ ማንነት ግን ይህ ዜና እስከ ተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ ሊታወቅ አልቻለም፡፡ እርምጃው በወያኔ አገዛዝ እና በግብጽ መካከል ያለውን አለመግባባት ሊያሰፋና መቆራቆዙን ሊያጠናክር ይችላል የሚል ግምት አለ።

መርካቶ፣ አሜሪካ ግቢ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ መሬት ለመሸጥ ወያኔ ላቀረበው ጨረታ ለአንድ ካሬ ሜትር መሬት 355‚500 ብር ለመክፈል ፈቃደኛ በመሆን ጋደን ሪል እስቴት የተሰኘ ድርጅት ጨረታውን ማሸነፉ በርካቶችን ማስደንገጡ ታወቀ። የመሬቱ አጠቃላይ ስፋት 1‚380 ካሬ ሜትር ሲሆን ጠቅላላ ክፍያው 491 ሚሊዮን ብር እንደሆነ ታውቋል፡፡ በዚሁ በተጠቀሰው ሰፈር ለሌላ መሬት ለአንድ ካሬ ሜትር ቦታ 311‚500 ብር ያቀረበው አሸናፊ መሆኑ ታውቋል፡፡ ከዚህ ቀደም በርበሬ ተራ በሚባለው አካባቢ ለአንድ ካሬ ሜትር ቦታ 305‚000 ብር ያቀረበው አሸናፊ በመሆኑ በሕዝብ ውግዘት ስለደረሰበት ግዢውን ሳይፈጽም እንደተወው መነገሩ አይዘነጋም፡፡ ይህ አዲስ አበባን በባለገንዘቦችና በእራሱ በወያኔ አባላት የማስወረር ዘመቻ ውሎ አድሮ የሚያስከትለው ጦስ እንዲህ በቀላሉ የሚታይ እንዳልሆነ የከተማ እድገት ባለሙያዎች እየገለጹ ይገኛሉ።

ሂውማን ራይትስ ዎች የተባለው የሰብአዊ መብት ተከራካሪ ድርጅት ሰኞ ጥቅምት 28 ቀን ባወጣው መግለጫ የወያኔ አገዛዝ አውስትራሊያ የሚገኙ የሱማሌ ኢትዮጵያውያን ቤተሰቦችን ከአራት ወራት በላይ አስሮ እያሰቃያቸው መሆኑን በማጋለጥ ባስቸኳይ እንዲፈቱ ጠይቋል። ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር ውስጥ አብዱ መሀሙድ ኦማር የተባለው የወያኔ የሱማሌ ክልል ተብየው ፕሬዚዳንት በአውስትራሊያ ሜልቦርን ከተማ ውስጥ ሊያካሄድ የነበረውን የስብሰባ እቅድ በከተማዋ የሚገኙ ሶማሌ ኢትዮጵያውያን ከፍተኛ ተቃውሞ በማድረጋቸውና እቅዱ እንዲሰረዝ በማስገደዳቸው ለዚህ አጸፋ የወያኔ አገዛዝ የተቃውሞ ሰልፍ አድራጊዎችን ቤተሰቦች ይዞ አብዛኞቹን ለአለፉት አራት ወራት ሲያሰቃይ መቆየቱን ሂውማን ራይስት ዎች ዘርዝሮ ገልጿል። ተቋሙ ባካሄደው ጥናት ቢያንስ 32 ቤተሰቦች የታሰሩ መሆናቸውን ማረጋገጡን ጠቁሞ በመሃል ጥቂት የተፈቱ ቢኖሩም አብዛኞቹ አሁንም በእስር ቤት እየማቀቁ መሆናቸውን ይፋ አድርጓል። ተቋሙ አብዱ መሀሙድ ኦማር ቀደም ብሎ ኢትዮጵያውያንን በመጨፍጨፍ ከፍተኛ ግፍ የፈጸመ ግለሰብ መሆኑን ገልጾ የአውስትራሊያ መንግስት ለወያኔ አገዛዝ ጉዳዩን አንስቶ እንዲጠይቅ ማሳሰቢያ ሰጥቷል።
#በተያያዘ ዜና ሂውማን ራይትስ ዎች የተባለው በዚህ ሳምንት ለጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ የማስፈታት ዘመቻ እንዲደረግ የጠየቀ መሆኑ ታውቋል። ተቋሙ በዓለም በተለያዩ አምባገነን አገዛዝ ታስረው የሚሰቃዩትን ጋዜጠኞች፤ የሕግ አዋቂዎች፤ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ግምባር ቀደም የሚሆኑ የድርጊት ተሳታፊዎች፤ አርቲስቶች፤ የተቃዋሚ የፖሊቲካ ድርጅቶች አባላት ወዘተ…እንዲፈቱ በየሳምንቱ አንዳንድ ሰዎችን እየመረጡ የይፈቱ ዘመቻ እንዲካሄድላቸው ያደርጋል። በዚህ ሳምንት የተመረጠው ኢትዮጵያዊው እስክንድር ነጋ ሲሆን በወያኔ አገዛዝ በግፍ የሃያ ዓመት እስራት ተፈርዶበት በእስርቤት በመሰቃየት ላይ ይገኛል።

ማዕከሉ እንግሊዝ አገር የሆነው ሌጋተም ኢንስቲትዩት የተባለው ተቋም የተለያዩ መመዘኛዎች በመጠቀም በዓለም ላይ የተለያዩ አገሮችን ከመረመረ በኋላ አገሮች ያሉበትን ደረጃ አውጥቶ ይፋ አድርጓል። ተቋሙ አማካይ የነፍስ ወከፍ ገቢና የሙሉ ጊዜ ስራ እድልን እንደመመዘኛ ቢጠቀምም የህብረተሰብ መቻቻልንና የኢንተርኔት አገልግሎት መስፋፋትን በመመዘኛ ውስጥ አካትቷል። ከእነዚህ ሌላ በዋና መመዘኛነት ከተጠቀመባቸው መካከል የኢኮኖሚ እኩልነት፤ የንግድና የስራ መመቻቸት፤ የአስተዳድር መስተካከል፤ የትምህርት ይዞታ፤ የጤና መሟላት፤ የግል ነጻነቶች መጠበቅ፤ የህብረተሰባዊ ካፒታል ሁኔታ እና የአካባቢ መሬትና አየር ሁኔታዎች ናቸው። እነዚህን መመዘኛዎች መሰረት አድርጎ ተቋሙ ደረጃ ከሰጣቸው 149 የዓለም አገሮች መካከል ኢትዮጵያ ወደ መጨረሻዎቹ አገሮች ላይ የተመደበች ስትሆን የምትበልጣቸው 17 አገሮች ብቻ ሆነው ተገኝተዋል። በቂ መረጃዎች ባለመገኘታቸው ምክንያት አንዳንድ አገሮች በምደባው ላይ ያልተካተቱ መሆናቸው ተነግሯል።

የአፍሪካ ህብረት ሊቀ መንበር ድላሚኒ ዙማ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ሕዝባዊ አመጽና የፖለቲካ ቀውስ አስመልክቶ መግለጫ የሰጡ መሆናቸው ታውቋል። ሊቀ መንበሯ በሰጡት መግለጫ የዜጎች መብት እንዲጠበቅ የጠየቁ ሲሆን በተለያዩ ክፍሎች መካከል ውይይት ተካሂዶ ለችግሩ ዘላቂ መፍትሄ መገኘት አለበት ብለዋል።

በአዲስ አበባ በቮኬሽናል ትሬኒንግ ኢንስቲትዩት የሚማሩ 42 የደቡብ ሱዳን ተማሪዎች ከመንግስታቸው የሚላክላቸው ገንዘብ በመቋረጡ ምክንያት በደቡብ ሱዳን ኤምባሲ ውስጥ ሰላማዊ ሰልፍ በማድረጋቸው በወያኔ ፖሊስ ተይዘው ባልታወቁ ስፍራ የታስሩ መሆናችውን ራዲዮ ታማዙጅ የተባለ የደቡብ ሱዳን የራዲዮ ስርጭት ገልጿል። ተማሪዎቹ በየወሩ ለኑሮ የሚሰጣቸው 100 የአሜሪካ ዶላር ላለፉት 14 ወራት ያልተላከላቸው መሆኑን ይናገራሉ።

ለዝርዝር ዜና ያዳምጡ