በጎንደር የህዝባዊ ሃይል አባላት ከወያኔ ጋር እየተፋለሙ ነው፣ በውጭ ምንዛሬ እጥረት ኩባንያዎች ሠራተኛ መቀነስ ጀመሩ፣ የወያኔ በሱማሊያ ውስጥ ምርጫ የማስከበር ፌዝ

ፍኖተ ዴሞክራሲ የኢትዮጵያ አንድነት ድምጽ ሬዲዮ (ኅዳር 19 ቀን 2009 ዓ.ም) – በጎንደር የሕዝባዊ ኃይል አባላት ከወያኔ የጸጥታ ኃይሎች ጋር እየተፋለሙ ነው – በምንዛሬ እጥረትና በሥራዎች መቀዝቀዝ አንዳንድ ኩባንያዎችና የስራ ድርጅቶች ሰራተኛ ማባረር ጀመሩ – የወያኔ ባለስልጣኖች በሱማሌያ የሚካሄደውን ምርጫ ጸጥታ ለማስከበር ጥረት እንደሚያደርጉ ገለጹ።

በምዕራብ ጎንደር በአርማጭሆና በሌሎች ቦታዎች ራስቸውን አደራጅተው ትግላቸውን ያጠናከሩ የታጠቁ ህዝባዊ ኃይሎች ከወያኔ አግአዚ ጦር ጋር በጦርነት እየተፋለሙ መሆናቸው ይነገራል። ባለፉት ጥቂት ቀናት በተከታታይ በተደረጉ ጦርነቶች የወያኔ አገዛዝ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰበት መሆኑ ሲገለጽ ሕዝባዊ ኃይሉ በሰው ኃይልም ሆነ በሞራል እየጠናከሩ መጥተዋል ተብሏል። በተያያዘ ዜና በወገራ አውራጃ የወያኔ አገዛዝ ሕዝቡን ትጥቅ ለማስፈታት ያደረገው ሙከራ ከሕዝቡ ከፍተኛ ተቃውሞ ገጥሞት ጉዳት የደረሰበት መሆኑም ተነግሯል።

በምንዛሬ እጥረትና በስራዎች መቀዝቀዝ ምክንያት አንዳንድ ኩባንያዎችና የስራ ድርጅቶች ሰራተኞች ማባራር የጀመሩ መሆናቸው ሲታወቅ አንዳንዶቹም በቅርቡ ለመዝጋት የሚገደዱ መሆናቸው እየገለጹ ነው ተብሏል። ለአንድ ዓመት ያህል ሲቀጣጠል የቆየው ሕዝባዊ አመጽና ተከትሎ የመጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በአገሪቱ ላይ ከፍተኛ የሆነ የፖለቲካ አለመረጋጋት መፍጥሩ ይታወቃል። ይህ ሁኔታ ተጨማሪ ባለሀብቶች አዳዲስ የስራ መስኮችን እንዳይከፍቱ ያደረጋቸው ከመሆኑም በላይ የገዥው ክፍል አባሎች በሁኔታው በመደናገጥ የዘረፉትን ሀብት በይፋም ሆነ በድብቅ በገፍ ከአገር ውስጥ ሲያወጡ ቆይተዋል። በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ እጥረት በመከሰቱና አዳዲስ የስራ ዘርፎችም እየጠፉ በመምጣታቸው ኩንያዎችና የስራ ተቋሞች ችግር እያጋጣማቸው መሆኑ ይነገራል።

በሶማሊያ የሚካሄደው ምርጫ አስመልክቶ የጸጥታ ሁኔታውን በማስከበር በኩል የሚቻለውን እንደሚያደርግ የወያኔ አገዛዝ የገለጸ መሆኑ ተሰምቷል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የወያኔ አገዛዝ በአገር ውስጥ በተቀጣጠለው ሕዝባዊ አመጽ ምክንያትና እንዲሁም ከአንዳንድ ሕዝባዊ የታጠቁ ኃይሎች የሚደርስበትን ጥቃት የሚመክትበትን ኃይል ለመጨመር በሺ የሚቆጠሩ ወታደሮችን በተከታታይ ከሱማሊያ ማስወጣቱ የሚታወቅ ሲሆን የወያኔ ወታደሮች ተሰማርተው የቆዩባቸው ግዛቶች በሙሉ በአልሸባ ኃይሎች የተያዙ መሆናቸው ተነግሯል። አልሸባብ ዘጠኝ የሚሆኑ ከተሞችን የተቆጣጠረ ከመሆኑም በላይ በታኅሳስ አንድ ቀን ይካሄዳል የተባለውን ምርጫም በከፍተኛ መንገድ እንደሚያደናቅፍ ዝቷል። የምክር ቤቱ ምርጫ 50 ከመቶ የጠናቀቀ ነው ቢባልም ለፕሬዚዳንቱ ቦታ የሚደረገው ምርጫ ለሚቀጥለው ወር አጋማሽ የተላለፈ መሆኑም ይነገራል። የወያኔ ጦር ከሶማሊያ በወጣበትና አልሸባብ ሰፊ አካባቢዎችን በተቆጣጠረበት ሁኔታ በምን ዓይነት መንገድ ወያኔ ሁኔታውን በቁጥጥር ስር ለማድረግ እንደሚችል ግልጽ አይደለም።

ዝርዝር ዜና ከፍኖተ ዴሞክራሲ ያዳምጡ

ክፍል አንድ

ክፍል ሁለት