የወያኔ አሻንጉሊት ፍርድ ቤት ውሳኔ፣ በጎንደር የእንሰሳት ኮሌጅ ተማሪዎች ከትምህርት ታገዱ፣ የግብጽና የኢሳያስ ወዳጅነትና የወያኔ ማስፈራሪያነት

ፍኖተ ዴሞክራሲ የኢትዮጵያ አንድነት ድምጽ (ኅዳር 23 ቀን 2009 ዓ.ም.) – የወያኔ ፍርድ ቤት ዳንኤል ሽበሽና አብርሃ ደስታ የከሰሱበትን ጉዳይ ለመከራከር እንዲታሰሩ ሲወስን እነ ሃብታሙ አያሌውን በነጻ ለቋቸዋል – በጎንደር ታስረው የነበሩ የእንስሳት ሳይንስ ኮሌጅ ተማሪዎች ለአንድ ዓመት ከትምህርት ገበታ ታገዱ – የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እድገት እየቀነሰ ነው – ግብጽ ኢሳያሳን የጋበዘችው የማስፈራሪያ መልእከት ለወያኔ አገዛዝ ለማስተላለፍ ነው ተባለ።

በአዲስ አበባ የሚገኘው የጠቅላይ ፍርድ ቤት ትናንት በዋለው ችሎት አቶ ዳንኤል ሺበሺና አቶ አብርሃ ደስታ “ህግን ለመጣስ ተቃርበዋል” የሚል ክስ ተመስርቶባችው ጉዳያቸውን እስር ቤት ሆነው እንዲከራከሩ አዟል። ከጥቂት ቀናት በፊት ዳንዔል ሺበሺ በኮማንድ ፖስቱ በቁጥጥር ስር መዋሉ የሚታወቅ ሲሆን አብርሃ ደስታ ከመቀሌ ተይዞ ወደ አዲስ አበባ እንደሚመጣ ይጠበቃል። ሁለቱም የቀረበባችው ክስ ለተቃዋሚ ቴሌቪዥን ጣቢያ ቃል ምልልስ ሰጥታችኋል የሚል ነው።

በተያያዘ ዜና የአንድነት ፓርቲ አባል የነበረው አቶ ሃብታሙ አያሌው እንዲሁም አቶ የሺዋሽ አሰፋ እና አቶ አብራሃም ሰለሞን በክሳቸው ላይ የቀረቡት ማስረጃዎች በቂ አይደሉም በሚል ፍርድ ቤቱ በነጻ ለቋቸዋል። ሃብታሙ አያሌው በሰኔ 2007 ዓ.ም. መታሰሩ ሲታወቅ በእስር ቤት በከፍተኛ ህመም ላይ የነበረ መሆኑና ሃኪሞችም ወደ ውጭ ወጥቶ እንዲታከም ድጋፍ የሰጡት መሆኑ አይዘነጋም። በአሁኑ ወቅት ከእስር እንዲፈታ ቢደረግም አገዛዙ ውጭ ውጥቶ እንዲታከም ይፈቅድለታል ወይ የሚለው ጥያቄ በብዙዎች ዘንድ እየተብላላ መሆኑ ይነገራል።

ከወር በፊት ከጎንደር የእንስሳት ሳይንስ ኮሌጅ (ቬትረነሪ ኮሌጅ) በጅምላ ተይዘው ታሰረው የነበሩ 104 ተማሪዎች ለአንድ ዓመት ያህል ከትምህርት ገበታችው የተባረሩ መሆናችው ተነገረ። የተለያዩ ጥያቄዎች አቅርበው ተቃውሞ በማሰማታቸው መታሰራቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እድገት እየቀነሰ መሆኑ ተነገረ። በዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ግምት በዚህ ዓመት የኢኮኖሚው እድገት 4.5 ከመቶ እንደሆነ ተገምቷል ቢባልም እድገቱ ከዚህ በታች ሊያሽቆለቁል እንደሚችል ብዙዎቹ ይናገራሉ። የውጭ ባለሃብቶች አዳዲስ ሥራዎችን ለመጀመር እያቅማሙ ባሉበትና የውጭ ምንዛሬ እጥረት በከፍተኛ ደረጃ በተከሰተበት ሁኔታ የድርቅ መስፋፋትና የምርት መቀነሱ ተጨምሮበት የኢኮኖሚው እድገት በከፍተኛ ደረጃ ሊያሽቆለቁል እንደሚችል ተገምቷል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን ተከትሎ የኢንተርኔት አገልግሎት መቋረጥ አገሪቷን በቀን 500 ሺ ዶላር ያህል እያከሰራት መሆኑ በተደጋጋሚ ተነግሯል።

የግብጹ ፕሬዚዳንት የሻዕቢያን ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂን ጋብዘው ማስተናገዳቸው ለወያኔ አገዛዝ መልእክት ለማስተላለፍ ነው የሚል ሀሳብ ዘ ኒው አራብ የተባለው ማዕከሉን እንግሊዝ አገር ያደረገ የድረ ገጽ ጋዜጣ ዘግቧል። በግንኙነቱ ወቅት ሁለቱ መሪዎች በተለያዩ መስኮች በሁለት አገሮች መካከል ስለሚኖሩ ግንኙነቶች ተነጋገሩ ይባል እንጅ የስብሰባው ዋና ዓላማ የወያኔ አገዛዝ ላይ ተጽእኖ አሳድሮ እንዲለሳለስ ለማድረግ ነው ብሏል። የወያኔ አገዛዝ በግድቡ ስራ ላይ ቢገፋበት ከዚህ በፊት ግብጽ ኢትዮጵያን ለማጥቃት በይፋ የተነገረ እቅድ የሌላት መሆኑን ጋዜጣው ጠቁሞ የአሁኑ የግብጽና የሻዕቢያ ግንኙነት በሻዕቢያ በኩል ጥቃት ለመሰንዘር እቅድ እንዳላት ያሳይል ብሏል።

ከፍኖተ ዴሞክራሲ ዝርዝር ዜና ያዳምጡ